ዶ|ር ብርሃኑ ነጋ ዓለም ለአምባገነኖች የነበረው ትእግስት መሙዋጠጡን ገለጹ

ከቱኒዚያ ተነስቶ በተለይም የሰሜን አፍሪቃ ሃገራትን የለበለበው ህዝባዊ ማእበል የበርካታ ሃገራትን በር ማንኳኳት ከጀመረ ወዲህ ዓለማቺን ለአምባገነኖች የነበራት ትእግስት አልቆ እንጥፍጣፊ ብቻ እንደቀራት የግንቦት ሰባት የፍትህ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶ ር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ፣ ፣ ዶ ር ብርሃኑ ነጋ ይህን የተናገሩት ባለፈው ቅዳሜና እሁድ መጋቢት 2 እና 3 ቀን 2003 ዓም በስቶክሆለም ስዊድንና በኦስሎ ኖርዎይ ተገኝተው ከኢትዮጵያዊያን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ባደረጉበት ውይይት ወቅት መሆኑን ዘጋቢያችን ከኦስሎ ባስተላለፈልን ሪፖርት ለማወቅ ተችሎአል።

ዶ|ር ብርሃኑ በሁለቱም አገራት ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋር በያንዳንዱ ከአራት ሰአት በላይ የፈጀ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ለውይይት መነሻ ያቀረቡት ጽሁፍም በቃ ገየ የሚል እንደሆነ ተያይዞ የደረሰን ዘገባ ገልጿል።  ዶ|ር ብርሃኑ ይህን ርእስ ለውይይት መንሻ እንዲሆን የፈለጉበት ዋና ምክንያት ባሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ውስጥ ሆን ተብሎ ማህበረሰባችንን ለመከፋፈል የሚፈለገውን ነገር አንድ ሆነን በአንድ ቃል መነሳት እንደምንችል ለማሳየት እንደሆነ ለተሰብሳቢዎቹ ገልጸዋል።

ዛሬ ስለ ኢትዮጵያ አበሳ ማውራት ራሱን የቻለ ስራና ጊዜንም የሚወስድ ነው ያሉት ዶ|ር ብርሃኑ በሰሜን አፍሪቃ የታየው ክስተት እኛንም እንደሚነካና ያለንበት ወቅትም የአብዮት እንደሆነ ገልጸው ከኢትዮጵያዊያኑ ጋር ለመወያየት ያነሱት ነጥብ ቀደም ብሎ በዳላስና በሂዩስተን የቀረበ ሃሳብ ቀጣይ ክፍል እንደሆነ ገልፀዋል።  ዶ|ር ብርሃኑ ቀደም ብሎ በዳላስና በሂዩስተን ኢትዮጵያዊያን ከሰሜን አፍሪቃው አብዮት ልንማራቸው ስለሚገቡ ሶስት ነገሮች በሚል ርእስ ባደረጉት ንግግር የነጻነትና ዴሞክራሲ ፍላጎቶች የሰው ልጆች ሁሉ የሚፈልጓቸው እሴቶች መሆናቸው መረጋገጡን፣  የሰሜን አፍሪቃ አብዮቶች አፍሪቃዊያን በራሳቸው ያላቸውን መተማመን አጉልቶ ያወጣና አፍሪቃዊያንም የስ ዊ ካን ያሉበት እንደነበር እንዲሁም  ወቅቱ አፍሪቃዊያን የራሳቸውን እድል በራሳቸው ለመወሰን የተነሱበት አጋጣሚ በመሆኑ ነጻነት ወይም ሞት ብለው ፊት ለፊት መጋፈጣቸውን መግለጻቸውን አውስተዋል።

ዶ|ር ብርሃኑ በዚህ የአውሮፓ ጉዞአቸው ያተኮሩበት የውይይት ሃሳብ የአምባገነኖችን ባህሪ አስመልክቶ ማወቅ ስለሚገባን ነገርና ለዚህም ልንወስደው ስለሚገባ ልምድ የሚዳስስ እንደነበረ ሮፖርተራችን ከላከልን ዘገባ ለማወቅ ተችሎአል።  የአምባገነኖች ባህሪያት  በአብዛኛው የሚመሳሰል ቢሆንም አንድ አይነት እንዳልሆኑ ታይቷል ያሉት ዶር ብርሃኑ ቤን አሊ ህዝቡና ወታደሩ እንደከዳው ሲያውቅ በጊዜ በመሸሹና ቢያንስ እንደሌሎቹ  አጥፍቶ መጥፋትን ከሚያስቡ አምባገነኖች አንጻር ሲታይ መልካም ሊባል እንደሚችል፣  ሆስኒ ሙባረክ ከቤን አሊ በባሰ መልኩ ስልጣኔን ከለቀቅሁ ግብጽ ርስ በርስ ትጋጫለች የሚል አምባገነን ስለነበር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከስልጣን አልወርድም ብሎ በመቆየቱ ጥፋት መድረሱን፣ ቅሌቱ ግን ከቤን አሊ የባሰ እንደነበር ፣  የየመኑ አሊ አብደላህ በባሰ መልኩ የሲቪል ጦርነት እንዲነሳ የሚችለውን እያደረገ በመሆኑ ይህም የጥፋቱን መጠን ከፍተኛ እንደሚያደርገው፣ እንዲሁም ጋዳፊ እኔን ያልወደደ ሊቢያዊ አይደለም ብሎ እስከማመን በመድረሱ ከሁሉም የከፋ አምባገነን እንደሆነ ገልጸዋል፣ ፣

ስለ አምባገነኖች የአእምሮ በሽተኛነት ከጋዳፊ የበለጠ ገላጭ ነገር የለም ያሉት ዶ|ር ብርሃኑ ፣ የጋዳፊ መጨረሻ እስካሁን ከታዩት አምባገነኖች የከፋ እንደሚሆን በዚህም ምክኒያት የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከነጻነት ናፋቂው ህዝብ ጋር መቆም ግድ እንደሆነበትና ፣ ዓለማችንም  እንዲህ እንዳሁኑ በአምባገነኖች ላይ ሲተባበር ታይቶ እንደማይታወቅ ገልጸዋል፣ ፣ አያይዘውም አብዮቱ በዓለም ህዝብ ላይ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ፣ አብዮቱ አድማሱን እያሰፋ መሆኑን ፣ በዚህም ምክንያት በተለይ ቻይናዊያን በሃገራቸው አመጽ እንዳይነሳ በሚል በሙሉ ሃይላቸው እየሰሩ መሆኑን ፣ የደቡብ ኮሪያ ወጣቶች ለሰሜኖቹ ወንድሞቻቸው ስለሰሜን አፍሪቃው አብዮት የሚገልጹ ጽሁፎችን በፊኛ (ባሉን) እየጻፉ መላካቸውን ፣ በአንዳንድ የአፍሪቅ ሃገራት አካባቢ ማስፈራሪያ እስከመሆን መድረሱን፣ በዚህም ምክንያት ዓለም ለአምባገነኖች የነበረው ትእግስት አልቆ እንጥፍጣፊው ብቻ የቀረ መሆኑን በስፋት ገልጸዋል።

ዶ|ር ብርሃኑ ነጋ በንግግራቸው መጨረሻ ኢትዮጵያዊያን ከሰሜን አፍሪቃው አብዮት ምን ትምህርት መቅሰም እንደሚኖርብን በስፋት የዘረዘሩ ሲሆን በሁለቱም አገሮች በተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ ቁጥሩ ከምንጊዜውም በላይ የሆነ ኢትዮፕያዊ መገኘቱን ለማወቅ ተችሎአል።