አንገት ሲደፋ ምን ፈሰሰ?

ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም

ሰሞኑን አዲስ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶግራፍ በብዛት በያለበት ይታይ ነበር፤ ያዘነ፣ የተከዘና አንገቱን የደፋ መለስ ዜናዊ! እኔን ቀልቤን የሳበው የጠቅላይ ሚኒስትሩን አንገት ሊያስደፋ የቻለው ነገር አይደለም፤ ወይም አበበ ገላው የተናገረው ነገር አይደለም፤ አበበ ገላው የተናገረውን ለመናገር ሙሉ መብት አለው፤ በተባለው ነገር የማይስማማ ሰው በማስረጃም ሆነ ያለማስረጃ የተባለውን ለማስተባበል መሞከር መብቱ ነው፤ የአሜሪካኑን ፕሬዚዳንት፣ ወይም የእንግሊዙን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥማቸው፣ ወይም በጆርጅ ቡሽ ላይ አንዱ ኢራቃዊ እንዳደረገው ጫማውን እያወለቀ ቢወረውርም ምንም የሚያስደንቅ ነገር አይኖርም