ምን? ወይስ እንዴት?

አንዲትን መንደር ኃይለኛ ሞገደኛ ነፋስ እየተነሣ ያስቸግራታል፡፡ የመንደርዋ ካቢኔ ተሰበሰበና ሦስት ባለሞያዎችን መድቦ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጡ ለማድረግ ወሰነ፡፡ በዚህም መሠረት ሦስት ባለሞያዎች ተጠሩና ችግሩ ተነገራቸው፡፡ ከዚያም በችግሩ ላይ አሉን የሚሉትን መፍትሔ እንዲያቀርቡ የአንድ ሳምንት ጊዜ ተሰጣቸው፡፡
ከአንድ ሳምንት በኋላ ካቢኔው ተሰብስቦ ሃሳባቸውን መስማት ጀመረ፡፡ የሦስቱን ሰዎች ሃሳብ ለመስማት ከተቀመጠው ካቢኔ ጋር በጉዳዩ ላይ ላቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው አንድ ሰው እንዲገኙ ተደርገው ነበር፡፡ የመጀመርያው ሰው «ሞገደኛው ነፋስ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሕይወት አስጊ በመሆኑ ነዋሪዎቹን ሌላ ቦታ ማስፈር» እንደሚገባ ሃሳብ አቀረበ፡፡ ሁለተኛው ሰው ደግሞ «ነዋሪዎቹን ወደ ሌላ ቦታ መውሰዱ ከብዙ ማኅበራዊ ነገር ስለሚያፈናቅላቸው እዚያው ባለቡት ሆነው ነገር ግን ሞገደኛው ነፋስ ሲነሣ ሊጠለሉበት የሚችሉበት የመሬት ውስጥ የምሽግ ቤት እንዲሠራ» ሃሳብ ሰጠ፡፡

ሦስተኛው ሰው ደግሞ «ይህ ሞገደኛ ነፋስ ለነዋሪዎቹ የተሰጠ በረከት ነው» አለ፡፡ «ነዋሪዎቹ ነፋሱ በሚቀንስበት የአካባቢው መልክዐ ምድር ላይ ሄደው እንዲሠፍሩ ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህንን ነፋስ መጠቀም አለባቸው፡፡ ይህ ነፋስ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊያመነጭ የሚችል ነው፡፡ በዚህ አካባቢ መተከል ያለባቸው መሣርያዎች አሉ፡፡ ነዋሪዎቹ በአንድ ላይ ገንዘብ አዋጥተው እነዚህን መሣርያዎች ይትከሉ፡፡ በጋራም ለየአካባው የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ ተጠቃሚ ይሁኑ፡፡ ይህ ነፋስ ችግር አይደለም፤ በረከት ነው፡፡» አለ፡፡
የካቢኔው አባላት የትኛውን መቀበል እንዳለባቸው ለመወሰን ስለተቸገሩ እኒያን ተጋባዥ ባለሞያ አማከሯቸው፡፡ እርሳቸውም እንዲህ አሉ «ጉዳዩ ሰዎቻችን ምን አዩ? የሚለው አይደለም፡፡ እንዴት አዩ? የሚለው ነው፡፡ ኃይለኛና ሞገደኛውን ነፋስማ ማንም ያየዋል? ያውቀዋል፤ ይረዳዋል፡፡ ጥበብ እርሱን ማየት አይደለም፤ እንዴት ታየዋለህ? ነው፡፡ ሁለቱ ሰዎች በችግር ዓይን አዩት፤ ሦስተኛው ሰው ግን በበረከት ዓይን አየው፡፡ አሁንም እናንት መወሰን ያለባችሁ በነፋሱ ላይ አይደለም፡፡ በራሳችሁ ላይ ነው» አሏቸው፡፡
«እንዴት በራሳችን ላይ?» አሉ የካቢኔ አባላቱ፡፡
«ውሳኔውኮ ምን እንይ? አይደለም፡፡ እንዴት እንይ? ነው፡፡ ነፋሱን መርገም አድርገን እንየው ወይንስ በረከት? ጥቅም አድርገን እንየው ወይስ ጉዳት? እሴት አድርገን እንየው ወይስ ዕዳ? ነውኮ ጥያቄው፡፡» አሉ ባለሞያው፡፡
ለምሳሌ ለሁላችንም እውነት ተመሳሳይ ነው፡፡ እውነቱንም እናውቀዋለን፤ እንረዳዋለን፡፡ ውስጣችንም ይነግረናል፡፡ ግን አንዳንዶቻችን እውነትን ስንናገርና እውነት የሚያመጣውን ሰማዕትነት ስንቀበል ሌሎቻችን የምናውቀውን እውነት መናገር ለምን ይቸግረናል? ስለ እውነት ያለን ዕውቀት አይደለምኮ? ለእውነት ያለን አመለካከት ነው ልዩነቱ? ለአንዳንዶቹ እውነት ሊሸፍኗት የማይገባ፣ ልትገለጥ ግድ የምትል፤ በመገ ለጧም የምታስከትለውን ዋጋ ሊከፈልላት የሚገባ ነገር ናት፡፡ ለሌሎች ደግሞ እውነት እውነት ብትሆንም አደጋ የምታስከትል ከሆነ ውሸትም ልትሆን ትችላለች፡፡ 
ለመሆኑ ያገቡ ሰዎች ሁሉ በትዳር ላይ ነው እንዴ ልዩነታቸው? በትዳር ላይ ልዩነት ቢኖራቸውማ አይጋቡም ነበር፡፡ ትዳርን በሚያዩበት ዓይን ላይ ነውኮ ልዩነቱ? ሚስትህን በጣም ክፉ አድርገህ ማሰብም ትችላለህ፤ በጣም ደግ አድርገህ ማሰብም ትችላለህ፤ በጣም ቆንጆ አድርገህ ማየት ትችላለህ፤ በጣም አስቀያሚ አድርገህ ማየትም ትችላለህ፤ ትዳርህን ምቹ ማደረግም ትችላለህ፤ ጎርበጥባጣ ማድረግም ትችላለህ፡፡ 
ግን ብዙ ጊዜ ሚስት እርሷ አመለካከቷን ሳትለውጥ ባሏ እንዲለወጥ ትፈልጋለች፤ ባልም እርሱ አመለካከቱን ሳይለውጥ ሚስቱ እንድትለወጥ ይፈልጋል፡፡ የሚገርመው ደግሞ ሁለቱም አመለካከታቸውን ሳይለውጡ ትዳራቸው እንዲለወጥ ይፈልጋሉ፡፡ ችግሩ እዚያ ነው ብለው ስለሚያምኑ፡፡ ችግሩ ግን እዚያ አይደለም እዚህ ነው፡፡ ውጭ አይደለም ውስጥህ ነው፡፡ ከዚያኛው አካል አይደለም ካንተ ነው፡፡ ወዳጄ «ጨለማ በጸጥታ የምንሠራበት ጊዜ ነው» ያሉ ሰዎች መብራት ሠሩ፡፡ በጨለማ ለመሥራት፡፡ «ጨለማ የዕንቅልፍ ጊዜ ነው» ያሉ ሰዎች ይሄው እስካሁን እንደተኙ ናቸው፡፡
«እስኪ በመስኮት በኩል ተመልከቱ» አሉ፡፡ ሁሉም በመስኮት በኩል ተመለከቱ፡፡
«ይኼ በግቢው ውስጥ የተተከለው ዛፍ ይታያችኋል?» ሁሉም ራሱን ነቀነቀ፡፡ 
«ዛፉ ምንድን ነው ለናንተ?» ጠየቁ፡፡
የግቢው ውበት ነው
አየሩን ያቀዘቅዛል
የአፈሩን መሸርሸር ይጠብቃል
የአየር ንብረቱን ምቹ ያደርጋል
ሃሳብ ተሰነዘረ፡፡ 
«በጣም ጥሩ፡፡ ይኼ እንግዲህ በሰው ዓይን ሲታይ ነው፡፡ አንዲትን ዝንጀሮ አምጥተን ስለ ዛፉ ብንጠይቃት ደግሞ ምን የምትል ይመስላችኋል? ለርሷ ዛፉ መኖርያ ነው፡፡ ምግብ ነው፡፡ አያችሁ ዛፉ አልተቀየረም፡፡ የተቀየረው የተመለከትንበት ዓይን ነው፡፡ 
«ችግር እንኳን ችግር የሚሆነው በተመልካቹ ዓይን ነው፡፡ ለአንዳንዶች እሥር ቤት የመከራ፣ የስቃይ፣ ከዓለም የተገለሉበት፣ ራሳቸውን የጣሉበትና ተስፋ የቆረጡበት ቦታ ነው፡፡ ለሌሎች ደግሞ ነጥረው፣ እንደ ብረት ጠንክረው፣ ሌላ ሰው ሆነው የወጡበት ቦታ ነው፡፡ ልዩነቱ እሥር ቤቱ ሳይሆን ለእሥር ቤቱ የነበራቸው አመለካከት ነው፡፡
«ለአንዳንዶች መውደቅ የመነሣት መጀመርያ ሆኗቸዋል፡፡ ለሌሎቹ ደግሞ የመሞት መጀመርያ፡፡ ለአንዳንዶች ከሥራ መባረር የሌላ የላቀ ሥራ መጀመርያ ሆኗቸዋል፤ለሌሎቹ ደግሞ የቦዘኔነት መጀመርያ፡፡ ለአንዳንዶች ከትምህርት ገበታ መሰናበት የምርምር መነሻ ሆኗቸዋል፤ ለሌሎች ደግሞ የውንብድና መጀመርያ፡፡ ስለዚህ ምን ገጠመህ? አይደለም ዋናው ነገር እንዴት ገጠምከው? ነው፡፡ ምን ሆነብህ? አይደለም፤ እንዴት አገኘኸው? ነው፡፡ ምን ደረሰብህ? አይደለም፤ እንዴት ተቀበልከው? ነው፡፡ 
«እያለቀሱ የሚኖሩ አሉ፡፡ እየተደሰቱ የሚሞቱም አሉ፡፡ በክርስትና ታሪክ ብዙ ሰማዕታት እየዘመሩና እየተደሰቱ ነው የሞት ጽዋን የተቀበሉት፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሕይወት እያሉ አንድም ቀን ሳይስቁ፣ እያማረሩና እያለቀሱ የሚኖሩ አሉ፡፡ ልዩነቱ ከምን የመነጨ ይመስላችኋል? ከአመለካከት ነው፡፡ እነዚያ ሞትን የኑሮ መጨረሻ አድርገው አላዩትም፡፡ እነዚያ ሞትን የመሸነፊያ መሣርያ አድርገው አላዩትም፡፡ እነዚያ ሞትን ቅጣት አድርገው አላዩትም፡፡ ለእነርሱ ሞት የሚሸሹት ሳይሆን የሚጋፈጡት ነው፡፡ ለእነርሱ ሞት ከአንድ ዓይነት የኑሮ ቅርጽ ወደ ሌላ ዓይነት የኑሮ ቅርጽ መሸጋገርያ ነው፡፡ ለእነርሱ ሞት ለእውነት የሚከፍሉት ዋጋ ነው፡፡ ለእነርሱ ሞት ለትውልድ የመልካም ሕይወት ድልድይ መሥሪያ ነው፡፡ ለእነርሱ ሞት ከመኖር ለሚበልጥ ዓላማ የሚከፈል ዋጋ ነው፡፡
«ታድያ እየሞቱ መሳቅና መደሰት ካለ፤ ለምንድን ነው እየኖሩ ማልቀስ የሚኖረው፡፡ አንዳንዶች በሞት ሲደሰቱ በኑሮ ለምን እናለቅሳለን? የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ ለምን ሁል ጊዜ ችግሮችን በምሬትና፣ በሰቆቃ፣ በተስፋ መቁረጥና በኀዘን ስሜት ብቻ እንቀበላቸዋለን? ለምን በሽታን የመድኃኒት መፍጠርያ አናደርገውም? ለምን በሥራ ቦታህ ሁል ጊዜ ትማረራለህ? ለምን አካባቢህን አትቀይረውም፡፡ ለምን ያንን አጋጣሚ የጀግንነት መነሻ አታደርገውም? እንዴት ልቀይረው? ብለህ የምታነብበት፣ የምታስብበት፣ የምትወያይበት፣ አማራጭ የምትደረድርበት አጋጣሚ ለምን አታደርገውም? 
«ትልቁ ችግራችን ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ?»
ሁሉም በትኩረት ያዩዋቸው ነበር
«ሰው ሁሉ ዓለምን ስለ መለወጥ ስለሚጨነቅ ነው፡፡»
የግርታ ስሜት ተፈጠረ፡፡ ታድያ ዓለምን መለወጥ አይደል እንዴ ቁልፉ የሚል ዓይነት፡፡
«ዓለምን ለመለወጥ ከተነሣን ምንም አንለውጥም፡፡ መለወጥ ያለባት ዓለም አይደለችም፡፡ እኛ ነን፡፡ የሰው አመለካከት ነው መለወጥ ያለበት፡፡ ሰው ዓለምን የሚያይበት ርእዮት ነው መለወጥ ያለበት፡፡ ያን ጊዜ ዓለምን ስትቀይራት ትታይሃለች፡፡ ራሳቸው ሳይቀየሩ ዓለምን ለመቀየር የተነሡ ሰዎች ናቸው ዓለማችንን ያበላሿት፡፡ ዝም ብለው ዓለምን ለመቀየር የተነሡ ሰዎች ሁሉንም ነገር እንደ ችግር፣ ዕንቅፋት፣ የብልጽግና ጠላት እያደረጉ ያዩታል፡፡ ይህ የአመለካከት ችግር ነው፡፡ በዓለም ላይ ሰው ሊጠቀምበት የማይችል አንዳች ነገር የለም፡፡ መጥፎ ሆኖ የተፈጠረ ምንም ነገር የለም፡፡ አያስፈልግም ይወገድ የሚባል ምንም ፍጥረት የለም፡፡ ያ የኛ የአመለካከት ችግር ነው፡፡ ለዚህ ነው እኛ ነን እንጂ ዓለም አይደለችም መለወጥ ያለባት የሚባለው፡፡
«አንተም አካባቢህን ለመቀየር አይደለም መጀመርያ መነሣት ያለብህ፡፡ ለውጥን ከወዲያ አትጀምረው፡፡ ከጎረቤትህ አትጀምረው፤ ከጠላትህ አትጀምረው፤ ከራስህ ጀምረው፡፡ አንተ ተለወጥ፡፡ አንተ ስትለወጥ አካባቢህም መለወጥ ይጀምራል፡፡ እንደ ጠላት የምታያቸውን መውደድ ትጀምራለህ፤ እንደ ችግር የምታየውን ጥቅሙን ትረዳዋለህ፤ መሰናክል የመሰለህ ነገር ድልድይ ሆኖ ታገኘዋለህ፤ ጨለማ የመሰለህ ነገር በርቶ ታየዋለህ፤ ገደሉ ደልዳላ ሆኖ ይታይሃል፡፡ 
ችግሩ ሥልጣን አይደለም፤ ስለ ሥልጣን ያለው አመለካከት ነው፤ ችግሩ ሀብት አይደለም፣ ስለ ሀብት ያለው አመለካከት ነው፡፡ ችግሩ ዘር አይደለም ስለ ዘር ያለው አመለካከት ነው፡፡ ችግሩ ቀለም አይደለም፣ ስለ ቀለም ያለው አመለካከት ነው፡፡ ችግሩ ዴሞክራሲ አይደለም፣ ስለ ዴሞክራሲ ያለው አመለካከት ነው፤ ችግሩ ፓርቲ አይደለም፣ ስለ ፓርቲ ያለው አመለካከት ነው፡፡ ችግሩ ውበት አይደለም፣ ስለ ውበት ያለው አመለካከት ነው፡፡ ችግሩ የሌላ እምነት መኖር አይደለም፣ ሌላውን እምነት የምታይበት አመለካከት ነው፡፡
«አንዳንድ አካባቢ አላያችሁም፡፡ አካባቢያቸው ተራራማ በመሆኑ ሲያማርሩ ትሰማላችሁ፡፡ አንዳንድ አካባቢ ደግሞ ያመሰግናሉ፡፡ እነዚያ የሚያማረሩት ተራራውን እንደ ዕዳ ስለሚያዩት ችግር ችግሩ ነው የሚታያቸው፣ የሚሰማቸውም፡፡ እነዚያኞቹ ግን በተራራው ላይ መዝናኛ ገንብተው፤ ኬብል ዘርግተው፤ የተራራ መውጫ አዘጋጅተው፤ አካባቢውን አሳምረው የቱሪስት መናኸርያ አድርገውታል፡፡ ታድያ ተራራው ምን አጠፋ? ያጠፋውኮ ሰዎቹ ተራራውን ያዩበት መንገድ ነው፡፡
«እኛምጋ እንደዚህ ነው ወዳጆቼ፡፡ ነፋሱ ምን አጠፋ፡፡ ተውት ይንፈስ፡፡ ለእኛ ግን ነፋሱ ምንድን ነው? ችግር ነው ወይስ በረከት? ዕዳ ነው ወይስ እሴት? ይህንን ብቻ ነው መመለስ ያለብን፡፡ ችግር ነው፣ ዕዳ ነው ካልን ለቅቀን ከሰፈራችን እንሂድ፡፡ በረከት ነው፣ እሴት ነው ካልን ደግሞ እንጠቀምበት፡፡ መወሰን ያለብን በነፋሱ ላይ ሳይሆን በራሳችን አመለካከት ላይ ነው፡፡ 
ሁሉም ራሳቸውን ከላይ ወደ ታች ነቀነቁ፡፡
አሌክሳንድርያ፣ ቨርጂንያ፣ ዩ ኤስ ኤ