ሦስቱ ማጣርያዎች
አንድ ወዳጄ እንዲህ የሚል የዕውቁን የግሪክ ፈላስፋ የሶቅራጥስን አባባል ላከልኝ፡፡
ሶቅራጥስ አንድ ጓደኛ ነበረው አሉ፡፡ አንድ ቀን ይኼ ጓደኛው መጣና «ሶቅራጥስ እገሌ ስለሚባል አንድ ወዳጅህ የሰማሁትን ነገር ታውቃለህ?» አለው፡፡ ሶቅራጥስም ዝም ብሎ ተወው፡፡ ሰውዬው ግን በሰማው ነገር ሳይደነቅ አልቀረምና እየደጋገመ «በጣም የሚገርምኮ ነው፡፡ እንዲህ ይሆናል ብዬ የማልገምተው ነገር ነው» ይለው ነበር፡፡ በነገሩ የተሰላቸው ሶቅራጥስም
«በጣም ጥሩ፡፡ የሰማኸውን ነገር ትነግረኛለህ፡፡ መጀመርያ ግን ሦስት ጥያቄዎችን መመለስ አለብህ፡፡ የምትነግረኝ ነገር የእነዚህን የሦስት ጥያቄዎች መልሶች የሚያሟላ ከሆነ ብቻ እሰማሃለሁ» አለው፡፡
ሰውዬውም በዚያው ሃሳብ ተስማማ፡፡
«የመጀመርያው ጥያቄዬ የእውነታ ጥያቄ ነው» አለው፡፡
«ቀጥል» አለ ሰውዬው
«ለመሆኑ አሁን ለእኔ የምትነግረኝ ነገር መቶ በመቶ እውነት መሆኑን ርግጠኛ ነህ?» አለው፡፡ ሰውዬው ጥቂት አሰበና «መቶ በመቶ እውነት መሆኑን አላረጋገጥኩም፡፡ ነገር ግን የሰማሁት ነገር» ብሎ ሊቀጥል ሲል ሶቅራጥስ አቋረጠውና
«ስለዚህ ያነሣኸው ነገር እውነት ይሁን ውሸት ርግጠኛ አይደለህም ማለት ነው፡፡ መልካም አሁን ወደ ሁለተኛው ጥያቄ እንለፍ፡፡ ሁለተኛው ጥያቄ የመልካምነት ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ስለ ወዳጄ ልትነግረኝ የተዘጋጀኸው ነገር መልካም ነገር ነው?» አለው፡፡
ሰውዬውም «መልካምማ አይደለም፤ እንዲያውም በተቃራኒው ነው» ሲል መለሰለት፡፡ ሶቅራጥስም «ስለ ወዳጄ የምትነግረኝ ነገር እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ ደግሞም መልካም ያልሆነ ነገር ነው፡፡ ይገርማል፡፡ አሁን ሦስተኛው ጥያቄ ይቀርሃል፡፡ ሦስተኛው ጥያቄ የጠቀሜታ ጥያቄ ነው፡፡ ለመሆኑ ስለ ወዳጄ የምትነግረኝ ነገር ለእኔ ምን የሚጠቅም ነገር አለው?» አለና ጠየቀው፡፡
ሰውዬውም «ላንተ የሚጠቅምህ ነገር የለውም፡፡ ግን ብትሰማው መልካም ነው ብዬ ነው» አለው፡፡
«በጣም ጥሩ» አለ ሶቅራጥስ፡፡ «አሁን ስለ ወዳጄ የምትነግረኝ ነገር እውነትነቱ ያልተረጋገጠ፣ መልካም ያልሆነና ለእኔም ምንም የማይጠቅመኝ ነገር ነው ማለት ነው፡፡ ታድያ ለምን ይህንን ነገር እሰማሃለሁ?» አለና መለሰለት፡፡
እኛን ስለሚወዱንም ሆነ ስለሚጠሉን፡፡ ስለሚያከብሩንም ሆነ ስለሚንቁን፡ ስለምናውቃቸውም ሆነ ስለማናውቃቸው ሰዎች በየጨዋታችን መካከል ይነሣል፡፡ «አንተ እገሌን ታውቀዋለህ? ያ እንኳን እንዲህና እንዲያ ያደረገው፣ ወንድሙ እንደዚህ እኅቱ እንኳን እንዲህ የሆነችው፡፡ በቀደም ዕለት እንኳን እንዲህ ቦታ ያየነው፤ ባለፈው እንኳን እገሌ የነገረን፤ ያ እዚያ መሥሪያ ቤት ያገኘነው» እየተባለ ይነገራል፤ ይተነተናል፡፡ ከቻልን «እ ዐወቅኩት» ብለን እናረጋግጣለን፡፡ ካልቻልንም «እሺ ግዴለም እስኪ ንገረኝ» ብለን ወሬውን እናስኬደዋለን፡፡
ከዚያስ? ከዚያ በኋላማ ሰውዬው እንደ ቄራ ሥጋ ይበለታል፤ እንደ ትንታኔ ዜና ይወራረዳል፤ እንደ ጠቅላላ ሕክምና ሙሉ ምርመራ ይሠራለታል፤ አንዳንዴም ይወገዛል፡፡ ይፈረድበታል፡፡ ይታማል፡፡ ይቦጨቃል፡፡
ደግሞም ስለ ሰው መመርመር፣ ማጣራት፣ መረጃ መሰብሰብ ደስ የሚላቸው፡፡ የዕውቀታቸውን ጣራ ባወቋቸው ሰዎች መጠን የሚለኩም አሉ፡፡ ሰውዬው የማያውቀውን ዝምድና የሚያውቁለት፣ ሰውዬውም የረሳውን አጋጣሚ የሚያስታውሱለት፣ ሰውዬው የተወውንም የሚያነሡለት «የወሬ ዳታ ቤዝ» ያላቸው አሉላችሁ፡፡ «እገሌን እርሱንማ ዐውቅልሃለሁ፤ እገሊትን የርሷን ነገር ለእኔ ተውት፤ እንዲህ ያለችው ናት አይደል? እዚህ የምትሠራው፣ እዚያ የምትኖረው፣ እንዲህ የምትበላው፣ እንዲያ የምትጠጣው» እያሉ የጫማ ቁጥር ሳይቀር የሚተነትኑ ሞልተውላችኋል፡፡
እያንዳንዱ ሰው መቅደስ ነው፡፡ መቅደስ ሦስት ዓይነት ክፍሎች ነበሯት፡፡ የመጀመርያው የውጩ ክፍል ነው፡፡ አደባባዩ፣ የሚያምነውም የማያምነውም የሚገባበት፡፡ ሁለተኛው ቤተ መቅደሱ ነው፡፡ ያመኑ ለአገልግሎት ብቻ የሚገቡበት፡፡ ሦስተኛው ክፍል ግን ካህናቱና ፈጣሪያቸው የሚገቡበት ነው፡፡ የሰውም ሕይወት እንዲሁ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው ሊገባበት የሚችለው ክፍል አለው፡፡ የሚታየው፣ የሚገለጠው፣ የሚነበበው ሕይወቱ እንዲህ ያለ ነው፡፡ እንደገናም የተወሰኑ ቤተሰቦቹ፣ ወዳጆቹ፣ ዘመዶቹ፣ ብቻ የሚገቡበት ክፍልም አለው፡፡ ደግሞም ማንም የማይገባበት ክፍልም አለው፡፡ እርሱ እና ፈጣሪው ብቻ የሚገቡበት፡፡
እዚያ የሰው ቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እርሱም የፈለገውን ሁሉ ማስገባት የለበትም፤ ሌላውም እየዘለለ መግባት የለበትም፡፡ በሩ ተከፍቶ ቢያገኘው እንኳን መግባት ክልክል መሆኑን ግን መረዳት አለበት፡፡ አንዳንዴ ግን እኛም ወደ ሰዎች መቅደስ እንገባለን፤ ሰዎችም ወደ ለእኛ መቅደስ እንዲገቡ እናደርጋለን፡፡
እንዲህ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን እንደ ሊቅ እንዲቆጥሩ፣ እንኳን የተከፈተ መቅደስ አግኝተው በተዘጋውም እየሰበሩ እንዲገቡ፣ የሰውን ውሳጤ ማወቅ ሱሳቸው እንዲሆን፣ ያወቁትንም ሁሉ በያገኙበት እንዲዘረግፉ፣ ዘርግፈውም ለዘርጋፊ እንዲሰጡ የምንተባበራቸውም እኛ ነን፡፡ ሰሚና አድናቂ ካላገኘ ማንም አይናገርም፡፡
አንዳንዶቻችን እንዲያውም «ወዳጅህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ» የሚለውን ሁሉ ረስተን የምናውቃቸውም ሆነ የማናውቃቸው ሰዎች ሲበለቱ ነገሩን እየጠላነው፣ ሰውዬውንም እየታዘብነው እንኳን ዝም ብለን እንሰማቸዋለን፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች ሰሚ ከማግኘታቸውና አድናቂም ከመፍጠራቸው የተነሳ ከዋናው ሂሳብ ይልቅ ቫቱን እያበዘዙ፣ የፈለጉትንም እየጨማመሩ ወደማውራት ደረጃ ተሸጋግረዋል፡፡
አንድ ያልተረዳነው ነገር ቢኖር ዛሬ እኛ የሌሎችን ጉዳይ ያለ ሰዎቹ ፈቃድ እንደ ሰማነው ሁሉ የእኛም ጉዳይ ሌላ ቦታ ይዘረዘራል፡፡ እኛ ወደ ሌሎች መቅደሶች የሚገቡትን ‘ሃይ’ ሳንል እንደተውናቸው ሁሉ ወደ እኛም መቅደስ ሲገባ ‘ሃይ’ የሚል አይኖርም፡፡ አንዳንዴ ስለምንጠላቸው ሰዎች መጥፎ ዕድልና ውድቀት የሚነግሩንን ሰዎች «ይበለው፣ ተወው» እያልን እኛ የምንተዋቸውን ያህል እዚያኛውም መንደር ሄደው ይህንኑ ዕድል ሊያገኙ እንደሚችሉ መርሳት የለብንም፡፡
ለዚህ ነው ሶቅራጥስ ሦስቱን ጥያቄዎች የጠየቀው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ደግሞ የሶቅራጥስ ብቻ ሳይሆኑ የእኛም ጥያቄዎች መሆን አለባቸው፡፡
ሰዎች የሌሎችን ሰዎች ጉዳይ ይዘው እኛ ጋር ሲመጡ እንደ ሶቅራጥስ ሁሉ ነገሩ እውነት ነው ወይ? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ የምናምነው ሰው ሊያወራው ይችል ይሆናል፤ ትልቅ የምንለው ሰው ያወራው ይሆናል፤ ልንናገረው የማንችል ሰው ያወራው ይሆናል፤ እጅግ በጣም የሚቀርበን ሰው ያወራው ይሆናል፤ ግን የእውነታ ጥያቄ መጠየቅ አለበት፡፡ ምን ማረጋገጫ አለ? ዜናው የተገኘበት ምንጭ ታማኝ ነወይ? እየተባለ መጠየቅ አለበት፡፡ የሚታመን ሰው ሁሉ የሚታመን ወሬ አያወራም፡፡
ስለ ሰው እንዲሁ የሰሙትን ሁሉ የሚያወሩ ሰዎች ሦስት ዓይነት ዐመል አለባቸው፡፡ የቀዳዳ ወንፊትነት፣ የግልብነትና ለእውነት አይጨነቄነት፡፡ አንድ ሰው የሰማውን ነገር ሁሉ የሚያምን፤ ከማመንም አልፎ እንደመጣለት የሚያስተላልፍ ከሆነ አእምሮው ውስጥ ያለው የነገር ማጣርያው ወንፊት ተቀድዶበታል ማለት ነው፡፡ የወንፊቱ መቀደድ ብቻም ሳይሆን ግልብነትንም ይጨምራል፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በቀላሉ ለማመንም በቀላሉ ለመካድም የሚችሉ፣ ማንም እንደፈለገ ሊቀይራቸው የሚችሉ፣ ስለ አንድ ነገር ጥቂት እንኳን ለማሰብ ዐቅም የሌላቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ለእውነት የማይጨነቁ መሆናቸው ነው፡፡ የሚያወራው ሰው «ምስኪን» መሆኑን፣ የሚወራው ወሬ አስደሳች መሆኑ፣ ለማውራት የሚመች መሆኑን፣ የሰው ቀልብ የሚስብ መሆኑን፣ እነርሱም ሊቀበሉት ቀላል መሆኑን እንጂ እውነት መሆኑን ለማረጋገጥ አንዲት ጋት ጭንቀት የላቸውም፡፡
ሁለተኛው ጥያቄ የመልካምነት ጥያቄ ነው፡፡ የምንሰማው ነገር የሰውን ውድቀት፣ ገመና፣ ጉድ፣ ከሆነ ምን ያደርግልናል? ስለ ሰው ክፉ መስማት ሰይጣንን ካልሆነ በቀር የትኛዋን ነፍስ ያስደስታታል? በርግጥ በዓለም ላይ ተወለደ ከሚለው ሞተ፣ ተጋቡ ከሚለው ይልቅ ተፋቱ፣ ተስማሙ ከሚለው ይልቅ ተለያዩ፣ ተፋቀሩ ከሚለው ይልቅ ጦር ተማዘዙ፣ መጡ ከሚለው ይልቅ ከዱ፣ አመኑ ከሚለው ይልቅ ካዱ፣ የሚለው ወሬ የሰዎችን ጆሮ የመግዛት ኃይል አለው፡፡
በየዜና ማሠራጫዎችም ከመልካም ዜናዎች ይልቅ የአደጋ፣ የጦርነት፣ የጠብ፣ የሽኩቻ፣ የቅሌት፣ የዝርፊያ ዜናዎች የአድማጮችንና የተመልካቾችን ቀልብ በመሳብ ተወዳዳሪ እንደሌላቸው ይነገራል፡፡
ለእኛ ግን ስለ ሰዎች ክፉ ክፉውን መስማት ምን ያደርግልናል? እዚያ የምናየው ክፉ ወይንም መልካም ነገር እኛም ላይ ያለ ነው፡፡ ያ ሰው እጅግ የምንጠላውና ክፉውን ለመስማት የምንጓጓለት ሰው እንኳን ቢሆን የእርሱን ክፉ መስማታችን የእኛን ለክፋት የተጠማ ሰይጣናዊ ጠባይ እንጂ የሰውዬውን ክፉነት አያሳይም፡፡ ሰው በውስጡ ክፉነት ከሌለው በቀር የሰውን ክፉ ነገር ለመስማት አይጓጓም፡፡ ሰው በውስጡ መልካምነት ካለው ነፍሱ መልካምነትን ትጠማለች፡፡ ሰው ግን በውስጡ ክፋት ካለ መላው ሕዋሶቹ ክፋትን ሲጠሙ ይገኛሉ፡፡ የሰውን ክፉ መስማትም ሆነ ለመስማት መጓጓት ከሚሰማው ነገር ይልቅ የሰሚውንና የተናጋሪውን ሰይጣናዊ ማንነት ያሳያል፡፡
የመጨረሻው የሶቅራጥስ ጥያቄ ያ የምንሰማው ነገር በኛ ላይ ምን ይጨምርልናል? ምንስ ይጠቅመናል? ለሕይወታችን የሚበጅ ምን ነገር ይኖረዋል? የሚለውን መመዘኑ ነው፡፡ የሰማነው ሁሉ አይጠቅመንም፣ የሚጠቅምንንም ሁሉ አንሰማም፡፡ አንዳንዱ እንዲያውም ወደ ልቡናችን ገብቶ ሌላ ሥራ የሚፈጥርብን፣ ቂም እንድንቋጥር፣ በማያገባን ጉዳይ ገብተን የማንወጣውን ዋና እንድንዋኝ ያደርገናል፡፡ ሌላ ነገር ልናስብበት፣ ልንሠራበትና ልንፈጥርበት የምንችለውን አእምሮም የሚሻማን ጊዜ አለ፡፡
መስማትና ማዳመጥ ይለያያሉ፡፡ መስማት ድምፆችን ሁሉ ነው፡፡ በአካባቢያችን ብዙ ድምፆች አሉ፡፡ እነዚህን ድምፆች የመስማት ግዴታ ይኖርብን ይሆናል፡፡ የማዳመጥ ግዴታ ግን የለብንም፡፡ ማዳመጥ ልቡናን መስጠት ነውና፡፡ ሰው በጆሮው ይሰማል፣ በልቡናው ግን ያዳምጣል፡፡ ማዳመጥ ልብን መስጠት፣ ስለ ጉዳዩ ማሰብ፣ ማምሰልሰልና ጉዳዩን ማስቀረት ማለት ነው፡፡
የማይጠቅሙንን ወሬዎች እንሰማቸው ይሆናል፡፡ምናልባት ሳንፈልጋቸው እየተነሡ ወደኛ ይመጡ ይሆናል፡፡ ልናዳምጣቸው ግን አይገባም፡፡
ከዚህ በተሻለ ደግሞ የወሬ ሱስ ያለባቸው ሁሉ «እገሌኮ..» ብለው ሲጀምሩ ሦስቱን ጥያቄዎች እንጠይቃቸው፡፡ ይህንን ብናደርግ ስለ እርሱ የሚወራበትን ሰው ብቻ ሳይሆን የሚያወሩትንም ሰዎች እንጠቅማቸዋለን፡፡ ሞያ ያላቸው መስሏቸው እንዳይኩራሩ፣ ውዱን ጊዜያቸውንም ስለራሳቸው በማሰብ እንዲያውሉ አግዘናቸዋልና፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባታውሉትይመረጣል፡