የቡና ኤክስፖርት ገቢ ከታሰበው በግማሽ ቀነሰ

(ሪፖርተር) — የቡና ኤክስፖርት ገቢ በግማሽ ያህል በመቀነሱ ከኤክስፖርት ይገኛል ተብሎ የታቀደው አጠቃላይ ገቢ በአንድ ቢሊዮን ብር እንዲወርድ አደረገ፡፡ በ2004 ዓ.ም ይገኛል ተብሎ የታቀደው የኤክስፖርት ገቢ አራት ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው የተገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አልሞላም፡፡

ነባር የቡና ነጋዴዎች የቡና ንግድ ዘንድሮ ከገባበት ችግር በሚቀጥለው ዓመት የማይወጣ ከሆነ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቅበት የቡና ገበያ ውጭ ልትሆን ትችላለች ሲሉ ስጋታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ነጋዴዎች ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ በዚህ ዓመት ለውጭ ገበያ የቀረቡት የቡና ዓይነቶች አንደ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጣቸውና እንደ ጥራት ደረጃቸው ሳይሆን በዘፈቀደ ነው ይላሉ፡፡ “የሐረር ቡና እየተባለ የሌላ አካባቢ ቡና ይላካል” ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቡና ነጋዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በዚህ ምክንያትም በርካታ የውጭ ደንበኞች ቡና መግዛታቸውን አቁመዋል፡፡ በርካታ ነጋዴዎችም መንግሥት በሚያወጣቸው ተደጋጋሚ የማያሠሩ መመርያዎች ምክንያት ከገዥዎቻቸው ጋር የገቡትን ቃል ሊጠብቁ ስላልቻሉ ከገበያ መውጣታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በዚህ ሁኔታ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ከቡና ኤክስፖርት አገሪቱ ታገኛለች ተብሎ ከታቀደው 1.1 ቢሊዮን ዶላር የ2004 በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ አንድ ወር እየቀረው ከቡና የወጭ ንግድ የተገኘው 505.6 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡

መንግሥት ከ32 ዓይነት የኤክስፖርት ምርቶች በዚህ የበጀት ዓመት አገኛለሁ ብሎ ያቀደው አራት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ እየቀረው ከኤክስፖርት የተገኘው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር አልሞላም፡፡

መንግሥት ከበጀት ዓመቱ መጀመሪያ አንስቶ የቡና የኤክስፖርት ገቢን ለማሳደግ በርካታ መመርያዎችን ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ ከእነዚህም መካከል ቡናን እንደተለመደው በጆንያ ማሸግ ሳያስፈልግ በጥቅሉ በኮንቴይነር ታሽጎ እንዲላክና ገዥዎችም ይህንን ቡና በጎተራ (ሳይሎ) እንዲቀበሉ የወጣው መመርያ ይገኝበታል፡፡ ይህ መመርያ አስገዳጅ በመሆኑ በወቅቱ ነጋዴዎች ጠንከር ያለ ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ በወቅቱም መላክ የነበረባቸውን ቡና መላክ አልቻሉም፡፡ ከውጭ ተቀባዮቻቸው ጋር የፈጸሙት ውልም ችግር እንዳጋጠመው ሪፖርተር በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

እነዚህ ችግሮች ተደማምረው የቡና የኤክስፖርት ገበያ ችግሮች የተፈጠሩበት ሲሆን፣ መንግሥት ያቀደውን ያህል ገቢ አለማግኘቱ ደግሞ ንግድ ሚኒስቴርን እንዳበሳጨው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ንግድ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ ላይ የቡና ነጋዴዎችን ጠርቶ ጠንከር ያለ ተግሳጽ ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የቡና ነጋዴዎች እንደገለጹት፣ የንግድ ሚኒስቴርን የስብሰባ ጥሪ በጉጉት እየጠበቁ ነው፡፡ ነገር ግን ውይይቱ ጠንከር ያለና በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር እንደሚመርጡ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ምክንያታቸውን ሲያስረዱ ቡናን በሚመለከት በዓለም ላይ ያለው የገበያ ሁኔታ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከሚያስቡት የተለየ ነው፡፡ መንግሥት የዘረጋው የቡና ሽያጭ መዋቅር ሊታሰብበት እንደሚገባም እነዚሁ ነጋዴዎች አበክረው አስገንዝበዋል፡፡