ስኳር

clik here for pdf 
አንድ መምህር ሁለት ትልልቅ የመስተዋት ገንቦዎች ይዞ ወደ ክፍል መጣ፡፡ ሦስት ተማሪዎች ደግሞ በካርቶን ሌሎች ሦስት ነገሮችን ተሸክመውለታል፡፡ ተማሪዎቹ ከመቀመጫ ተነሥተው ተቀበሉት፡፡
መምህሩ ትልልቁን የመስተዋት ገንቦዎች በተማሪዎቹ ፊት ጠረጴዛ ላይ አስቀመጠው፡፡ ሦስቱን ካርቶኖቹን ደግሞ በጎን አደረጋቸው፡፡ መጀመርያ ትልልቅ ድንጋዮች አነሳና በአንደኛው የመስተዋት ገንቦ ውስጥ እስካፉ ድረስ ከተታቸው፡፡ ከዚያም ተማሪዎቹን አንድ ጥያቄ ጠየቃቸው፡፡

 «ይህ የመስተዋት ገንቦ ሙሉ ነውን?´

ተማሪዎቹም በአዎንታ ራሳቸውን ነቀነቁ፡፡
ከዚያም ቀጠለና ትንንሽ የከበሩ ድንጋዮችን አንሥቶ ወደ መስተዋቱ ገንቦ ውስጥ ከተታቸው፡፡ በድንጋዮችና በድንጋዮቹ መካከል በሚገኙ ባዶ ቦታዎች ወስጥ እየገቡ የከበሩት ድንጋዮች ገንቦውን ሞሉት፡፡ መምህሩም ተማሪዎቹን በድጋሚ ጠየቃቸው፡፡
«አሁንስ የመስተዋቱ ገንቦ ሙሉ ነውን?´
ተማሪዎቹም ሙሉ መሆኑን ተናገሩ፡፡
ቀጠለና መምህሩ ከሦስተኛው ካርቶን ስኳር እያፈሰ ወደ መስተዋቱ ገንቦ ውስጥ ከተተ፡፡ በቀሪው ባዶ ቦታ ውስጥ እየገባ ስኳሩ ሞላ፡፡ መምህሩም የተለመደ ጥያቄውን ጠየቀ፡፡ «የመስተዋቱ ገንቦ ሙሉ ነውን?´
ተማሪዎቹም በአዎንታ መለሱ፡፡
እንደገና መምህሩ ሁለተኛውን የመስተዋት ገንቦ አቀረበ፡፡ ከዚያም በተቃራኒው ስኳሩን በመስተዋቱ ገንቦ ውስጥ ሞላበት፡፡ ተማሪዎቹንም ገንቦው ሙሉ መሆንና አለመሆኑን ጠየቀ፡፡ ተማሪዎቹም ሙሉ መሆኑን መሰከሩ፡፡ በመቀጠል ድንጋዮቹን ለማስገባት ሞከረ፡፡ ነገር ግን ስኳሩ ሁሉንም ቦታ ስለያዘው ማስገባት አልቻለም፡፡ ለከበሩ ድንጋዮች የሚሆን ቦታም አላገኘም፡፡
መምህሩ ከሁለቱ የመስተዋት ገንቦዎች ፎት ቆመና ተማሪዎቹን ሃሳብ ጠየቃቸው፡፡ የመጀመርያው የመስተዋት ገንቦ ሦስቱንም ነገሮች ሲያስገባ ሁለተኛው ገንቦ ለምን አልቻለም? የመጀመርያው ገንቦ ድንጋዩን ሲያስገባ ሙሉ ነበረ፡፡ የከበሩ ድንጋዮች ሲጨመሩም ሙሉ ነበረ፡፡ ስኳሩም ሲጨመር ሙሉ ነበረ፡፡ ሁለተኛው ገንቦ ግን በስኳሩ ብቻ ሞላ፡፡ ለምን?
በሕይወታችሁ ውስጥ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ አለ መምህሩ፡፡ የመስተዋት ገንቦ ሕይወታችሁ ናት፡፡ ድንጋዩ፣ የከበሩት ድንጋዮችና ስኳሩ ደግሞ በሕይወታችሁ ውስጥ ቅድሚያ የምትሰጧቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሚያስፈልጉትም ሆኑ የሚፈልጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የሚያገኙትም ሆኑ የሚያገኛቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የሚገጥማቸውም ሆኑ የሚያጋጥሙት ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ ሁሉም ቦታ ይይዛሉ፡፡
አንዳንዶቹ ነገሮች እነርሱ በሕይወታችን ቀድመው ከገቡ ለሌሎቹ የሚሆን ቦታ የማይኖራቸው ናቸው፡፡ እነርሱ ብቻ ከሞሉ የሌሎችን ቦታ ይይዛሉ፡፡ ለሌሎች ቦታ እንተው ካልን ደግሞ እነርሱ ይጎድላሉ፡፡ በሌላም በኩል አንዳንዶች እነርሱ በሕይወታችን ቢሞሉም ለሌሎች ቦታ ያላቸው ናቸው፡፡
በመጀመርያው ገንቦ ውስጥ ድንጋዩን ስናስገባው ገንቦው ሙሉ ነበረ፡፡ ነገር ግን ለሌሎች መግቢያ የሚሆን ቦታ ነበረው፡፡ ድንጋዩ ምንድን ነው? በሕይወታችን የመጀመርያ ቦታ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ እምነታችን፤የሕይወት መመርያዎቻችን፤ ማንነታችን፣ ቤተሰባችን፣ ሀገራችን፣ ለእውነት የምናደርገው ተጋድሎ እነዚህ መጀመርያ በሕይወት ገንቧችን ውስጥ ከገቡ ሕይወታችን ሙሉ ትሆናለች፡፡
ተመልከቱ መጀመርያ ድንጋዩ ከገባ በኋላ ብንተወው እንኳን ገንቦው ግን ሙሉ ነበር የሚሆነው፡፡ ማለት ምን ማለት ነው፡፡ ገንቦው ሙሉም ጎዶሎም ነበር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ጎዶሎነቱ ሙላቱን አልቀነሰውም፡፡በቃ ገንቦው ሊይዘው የሚችለው የድንጋይ መጠን ያንን ብቻ ነበረ፡፡ ስለዚህ ሙሉ ነበረ፡፡ ገንቦውን ሙሉ ለማድረግም እርሱ ብቻ በቂ ነበረ፡፡ ነገር ግን ቦታም ነበረው፡፡
ከላይ ያነሣናቸው ነገሮች በሕይወታችን ካሉ ሕይወታችን ሙሉ ትሆናለች፡፡ ነገር ግን ለሌሎችም ነገሮች ቦታ ይኖሯታል፡፡ ምናልባት ግን የከበሩ ድንጋዮችና ስኳሩ እንኳን ባይኖር ሙሉ እንደሆነች ትቀጥላለች፡፡ ሀብታም አንሆን ይሆናል፤ ታዋቂ አንሆን ይሆናል፤ ሁሉ ነገር የተሳካልን አንሆን ይሆናል፤ ከኛ ተርፎ ለሌለ የምንሰጥ አንሆን ይሆናል፤ ለመትረፍረፍና ለመዝናናት የሚበቃ ነገር አይኖረን ይሆናል፡፡ እንዲህም ሆኖ እንኳን ሕይወታችን ግን ሙሉ ትሆናለች፡፡
ሕይወትን የሚሞላት እንደ ድንጋዩ ጠንከርና ከፍ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እምነትና የሕይወት መመርያዎች ዋነኛ የሕይወት ሙላቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ካሉ የከበረው ድንጋይና ስኳሩ ባይኖሩ እንኳን ሕይወት ግን ሙሉ መሆንዋ አይቀርም፡፡ ሕይወትን በዋናነት የሚሞሏት እምነትና የሕይወት መመርያዎች ወይንም አቋሞች ናቸው፡፡ ችግር ችግር የሚሆነው በራሱ ችግር ስለሆነ አይደለም፡፡ ችግር ችግር የሚሆነው በችግር ዓይን ሲያዩት ነው፡፡
በኢንዱስትሪ አብዮት ዘመን ሁለት ሰዎች ከአንድ የጫማ ፋብሪካ ተልከው ወደ አፍሪካ መጡ፡፡ የጫማ ገበያን ጉዳይ ሊያጠኑ፡፡ ሁለቱም ሰዎች የተለያያ ሪፖርት ይዘው ተመለሱ፡፡ የመጀመርያው ሰው «እዚያ ለጫማ የሚሆን ገበያ የለም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ሰዎች በባዶ እግራቸው ነው የሚሄዱት´ አለ፡፡ ሁለተኛው ሰውዬ ደግሞ «እዚያ ከፍተኛ የጫማ ገበያ አለ፤ ምክንያቱም አንድም ጫማ ያለው ሰው የለምና´ ብሎ ሪፖርት አቀረበ፡፡
አያችሁ ሁለቱም በአንድ እውነታ ላይ ተስማምተዋል፡፡ የሄዱበት ቦታ ጫማ ያደረገ ሰው የለም፡፡ በመርሐቸው ግን ተለየይተዋል፡፡ አንዱ እንደ ችግር የቆጠረውን ሌላው እንደ ዕድል ቆጥሮታል፡፡ ስለዚህ በሕይወታችሁ ውስጥ አምነትና መርሕ ካለ ሕይወትን ሙሉ ያደርጋታል፡፡
ማለት ግን ለሌሎች ነገሮች ቦታ አይኖራችሁም ማለት አይደለም፡፡ አሉ ሌሎች ነገሮች፡፡ ትምህርት፣ ሥራ፣ ዕድገት፣ ትዳር፣ ልጆች፣ ሌሎችም ነገሮች፡፡ በእምነትና በመርሕ አስቀድሞ ሕይወቱ የተሞላ ሰው ለእነዚህ ነገሮች በቂ ቦታ አለው፡፡ ሳይጎድ ልበት መሙላት የሚችል ቦታ አለው፡፡ የዚያኛውን ቦታ ሳያስለቅቅ ነገር ግን ለእነዚህም ቦታ ይኖረዋል፡፡
አለ ደግሞ ሦስተኛው ነገር፡፡ ስኳሩ፡፡ እንደምታውቁት ዛሬ ዛሬ ብዙ ሰዎች ስኳር እየተው ነው፡፡ ካልሆነም ደግሞ እየቀነሱ ነው፡፡ በሕይወታችንም እንደ ስኳር ያሉ ነገሮች አሉ፡፡ ለእነርሱም ቢሆን ግን ሕይወታችን ቦታ አላት፡፡ ግን መጀመርያ ድንጋዩና የከበሩት ድንጋዮች ከገቡ ነው፡፡
አስቀድማችሁ ስኳሩን ቦታ ካስያዛችሁት ለሌላ ነገር የሚሆን ቦታ አታገኙም፡፡እንዲህ ያደረጉ ሰዎች አሉ፡፡ መጀመርያ ሕይወታቸውን በትርኪ ምርኪ ነገር የሞሉ፡፡ በመዝናናት፤ በክብርና ዝና፤ በቧልትና ቀልድ፤ የሞሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች በኋላ ለሌሎች የሚሆኑ ቦታ አያገኙም፡፡ ካልሆነም የግድ የእነዚያን ቦታ ማስለቀቅ ይኖርባቸዋል፡፡ የገባን ማስወጣት ደግሞ ቀላል አይደለም፡፡
አንዳንዶች ከትዳር በፊት የለመዱትን ስኳር በትዳር ወቅት ማስለቀቅ አቅቷቸው መከራ ያያሉ፡፡ አንዳንዶች ከሥልጣን በፊት የለመዱትን ስኳር መላቀቅ አቅቷቸው ለመርሕና እምነት ቦታ አጥተዋል፡፡ አንዳንዶች ከትምህርት በፊት የለመዱትን ክፉ ስኳር በዕውቀት መተካት አቅቷቸው ይሰቃያሉ፡፡
ለመሆኑ በገንዘብ፣ በሥልጣን፣ በቆንጆ ወንዶችና ሴቶች፣ በግብዣና በስጦታ በቀላ የሚደለሉ ሰዎች አላያችሁም? ለምን ይመስላችኋል? እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸው በስኳሩ ብቻ የተሞላ ስለሆነ ነው፡፡ በሕይወታቸው ውስጥ ምንም ዓይነት ጠንካራ ዐለት የለም፡፡ ምንም ዓይነት የከበረ ድንጋይ አልገባም፡፡ እነርሱ በስኳር ብቻ የተሞሉ ናቸው፡፡
ያንን ስኳር ደግሞ ማሟሟት ቀላል ነው፡፡ ዐለቱ ግን አይሟሟም፡፡ የለመዱትን ስኳር እያላሱ እንደፈለጉ እምነታቸውንም ሆነ አመለካከታቸውን መቀያየር ቀላል ነው፡፡ አያችሁ በዐለት የተሞሉ ሰዎች ውስጥ የተወሰነ ስኳር መክተት የምትችሉትን ያህል በስኳር የተሞሉ ሰዎች ውስጥ ግን የተወሰነ ዐለት መክተት አትችሉም፡፡
እናም እነዚህ ሰዎች ለሕይወት ርባና ያለው ምንም ዓይነት ፋይዳ የላቸውም፡፡ እነርሱ ገንዘብ እስከተከፈላቸው ድረስ ለየትኛውም ቡድን ይጫወታሉ፡፡ ዛሬ ገጥመውት ከእጁ ዋንጫ የነጠቁትን ቡድን ነገ ደግሞ አብረውት ሆነው ዋንጫውን ለማንሳት ዝግጁ ናቸው፡፡ ሥልጣንና ክብር እስካገኙ ድረስ ከመላእክት ወገን ወርደው ከሰይጣን ጋር ለመሰለፍ አይዳግታቸውም፡፡
ለእነዚህ ሰዎች በሕይወታቸው ሜዳ ላይ ምንም ዐይነት መሥመር የላቸውም፡፡ አረንጓዴም፤ ቢጫም ሆነ ቀይ መሥመር የላቸውም፡፡ ሁሉንም ይሻገሩታል፡፡ «ከዚህ በመለስ ከመጣማ ሕይወቴ ያልፋል እንጂ፤´ የሚሉት ነገር የለም፡፡ አካባቢያቸውን ለመለወጥ ሳይሆን እንደ እስስት ከአካባቢያቸው ጋር ለመለወጥ ዝግጁ ናቸው፡፡ እንደ ስኳር ለመድረቅም፤ ለመሟሟትም ይችላሉና፡፡
ሰው ሲፈጠር ለሁለቱ ነገሮች የተፈጠረ መሆኑን ተፈጥሮው ይነግረናል፡፡ አእምሮ፣ ልቡናና ኅሊና እንዲኖረን የተደረገው ለምን ይመስላችኋል? አእምሮ ለማወቂያ ነው፡፡ ዓለምን የምናውቅበት፡፡ በአምስቱ የስሜት ሕዋሳት በኩል በሚገባው ዕውቀት የምንረዳበት፡፡ ኅሊናስ? ኅሊናማ የሕይወት የምትባለው መርከብ ካፒቴኗ ነው፡፡ ሕይወት በዚህ ካፒቴን ካልተመራች በማዕበል መካከል እንደተተወች የነጋዴዎች መርከብ ትሆናለች፡፡ ኅሊና የተቀመጠው ሕይወት በመርሕ እንድትመራ ነው፡፡ አንድ ሰው እሺም እምቢም የሚላቸው፤ የሚያከብራቸውና የሚሞትላቸው፤ የሚታገልላቸውና፤ መሥዋዕትነት የሚከፍልላቸው መርሖች ከሌሉት እርሱ ሰው ሳይሆን ካልዕ ፍጥረት ነው ማለት ነው፡፡
ልቡናስ ምንድን ነው? ልቡና የእምነት ቦታ ነው፡፡ ምንም እንመን ምን፣ ግን እምነት ያስፈልጋል፡፡ የሚያበረታና የሚያጠነክር፤ ኃይልና ብርታት የሚሆን፤ የማይታዩትን ነገሮች ልናይበት የምንችል፤ ከሞት ወዲያ ዓላማ እንዲኖረን የሚያደርግ፤ ሞትን ሊያሸንፍ የሚችል እምነት፡፡ እነዚህ ናቸው ዐለቶቹ፡፡ እነዚህም ናቸው የከበሩት ድንጋዮቹ፡፡ ከእነዚህ በመለስ ያለው ቢመጣ የማይጨምር፤ ቢቀርም የማያጎድል ስኳር ነው፡፡ ችግሩ አስቀድሞ ስኳሩ ከሞላ ለሌሎች ነገሮች ቦታ የለውም፡፡
አሌክሳንድርያ፣ ቨርጆንያ፣ ዩኤስ
 © ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ በመሆኑ በተመሳሳይ ኅትመት ላይ ባታውሉትይመረጣል፡