አል አሙዲ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለገዛቸው ካምፓኒዎች ክፍያ አልፈጸመም
(ሪፖርተር) — በሼክ መሐመድ አሊ አላሙዲና በሸሪኮቻቸው የተመዘገቡ ኩባንያዎች የአምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ያሸነፉት ጨረታ ከፀደቀላቸው በኋላ፣ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ቅድሚያ ክፍያ ስላልከፈሉና ርክክብ መፈጸም ባለመቻሉ፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመጨረሻ ጥሪ ሊያደርግላቸው ነው፡፡
በሼክ መሐመድ አሊ አላሙዲና በሸሪኮቻቸው የተመዘገቡ ኩባንያዎች የአምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ያሸነፉት ጨረታ ከፀደቀላቸው በኋላ፣ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ቅድሚያ ክፍያ ስላልከፈሉና ርክክብ መፈጸም ባለመቻሉ፣ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የመጨረሻ ጥሪ ሊያደርግላቸው ነው፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ለሽያጭ አቅርቧቸው ከነበሩ ስምንት ድርጅቶች፣ አምስቱን ለመግዛት ጨረታን ማሸነፋቸው የተገለጸላቸው የሼክ አላሙዲና የሸሪኮቻቸው ኩባንያዎች ድርጅቶቹን ለመረከብ ቅድሚያ ክፍያውን በአሥር ቀናት ውስጥ እንዲከፍሉ ተጠይቀው ነበር፡፡
የኤጀንሲው ቦርድ አምስቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ያቀረቡትን መጫረቻ ዋጋ ካፀደቀ በኋላ፣ አሸናፊ በሆኑበት መስፈርት መሠረት ቅድሚያ መክፈል የሚገባቸው ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንደነበር ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ የመጀመሪያ ጥሪው ከደረሳቸው ከአንድ ወር ተኩል በላይ በመሆኑ፣ ቀጣዩ ዕርምጃ የአምስት ቀናት የጊዜ ገደብ የሚሰጥ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አምስቱን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ለመግዛት አሸናፊ መሆናቸው የተገለጻላቸው ሆራይዞን ፕላንቴሽን፣ ሳዑዲ ስታር፣ ናሽናል ማይኒግ ኮርፖሬሽንና ሚድሮክ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ የግዥው ጨረታም ፀድቆላቸው የነበረው መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ነው፡፡
በሼክ አል አሙዲና በሸሪኮቻቸው ባለቤትነት የተመዘገቡት እነዚህ ኩባንያዎች አሸናፊ ባደረጋቸው የጨረታ ሰነድ መሠረት በቅድሚያ ከ35 እስከ 100 በመቶ ክፍያ መፈጸም እንደነበረባቸው ታውቋል፡፡ ኩባንያዎቹ አሸናፊ በሆኑበት ጨረታ ሜድሮክ ኢትዮጵያ የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪን ለመግዛት ከፀደቀለት 860 ሚሊዮን ብር ውስጥ 50 በመቶውን በተጠቀሰው ጊዜ መክፈል ነበረበት፡፡ ሆራይዘን ፕላንቴሽን የተባለው ሌላው ኩባንያም የጐጀብ እርሻንና የቡና ማዘጋጃ ማከማቻን በድምሩ በ263.8 ሚሊዮን ብር ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ ቢፀድቅለትም፣ በተመሳሳይ መክፈል የሚገባውን ቅድሚያ ክፍያ እንዳልከፈለ ታውቋል፡፡
አቦቦ እርሻ ልማትን በ90 ሚሊዮን ብር መግዛት እንደሚችልና ቅድሚያ ክፍያውን 35 በመቶ በመክፈል ዕድል የተሰጠውም ሌላው የሼክ አል አሙዲና የሸሪካቸው ኩባንያ የሆነው ሳውዲ ስታር የቅድሚያ ክፍያ እንዲፈጽም ከኤጀንሲው ለቀረበለት ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠም ተብሏል፡፡
የካቲት 15 ቀን 2004 ዓ.ም. ለጨረታ ከቀረቡት ስምንት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢትዮ ማርብል ኢንተርፕራይዝ፣ በ110 ሚሊዮን ብር ለመግዛት የቀረበው ናሽናል ማይኒንግ ኮርፖሬሽን በጨረታው አሸናፊ ከሆነበት መስፈርት አንዱ ኩባንያውን ለመግዛት ያቀረበውን ዋጋ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ለመክፈል ቢሆንም፣ እንደሌሎቹ ኩባንያዎች ይህም ኩባንያ የሚፈለግበትን አለመክፈሉ ታውቋል፡፡
ሼክ አል አሙዲና ሸሪኮቻቸው አሸናፊ በሆኑበት ጨረታ ላይ ተሳታፊ በመሆን ቢልቱ ሲራሮ እርሻን በስድስት ሚሊዮን ዶላር ለመግዛት ተስማምቶ የነበረው ሞሬል አግሮ ኢንዱስትሪ የተባለው የአሜሪካ ኩባንያ፣ በተመሳሳይ ቅድመ ክፍያውን አለመክፈሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሞሬል አግሮ ኢንዱስትሪ አሸናፊ የሆነው ከስድስት ሚሊዮን ዶላር ውስጥ ሦስት ሚሊዮን ዶላሩን በቅድሚያ፣ ቀሪውን በአምስት ዓመት ለመክፈል ነበር፡፡ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃም አሸናፊነታቸው ከተረጋገጠ በኋላ ቅድመ ክፍያውን መክፈል የነበረባቸው እነዚህ ኩባንያዎች ክፍያውን አለመፈጸማቸውን አረጋግጧል፡፡
ከዚህ በኋላ ኤጀንሲው ምን ዓይነት ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ለቀረበው ጥያቄ፣ ከዚህ በኋላ የተወሰኑ ጊዜያት ተጠብቀው ክፍያውን ካልፈጸሙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደሚጻፍላቸው ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ በማስጠንቀቂያ ጥሪውም ክፍያውን ካልፈጸሙ ጨረታው እንደሚሰረዝባቸው ተገልጿል፡፡ ወደዚህ ዕርምጃ ከመገባቱ በፊት ግን በድጋሚ ጥያቄው የሚቀርብላቸው መሆኑን የሚያመለክተው ኤጀንሲው፣ ጨረታውን መሰረዝ ብቻ ሳይሆን ለጨረታ ማስከበሪያ ያስያዙት ሁለት በመቶ ቢድ ቦንድም ለመንግሥት ገቢ ይደረጋል፡፡ ሆኖም አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ አሸናፊው ድርጅት ያቀረበው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ ከታመነበትና ክፍያውን ያልፈጸመበትን በቂ ምክንያት ካቀረበ የተወሰነ ጊዜ ሊሰጠው ይችላል ተብሏል፡፡ አራቱ ድርጅቶች ለጨረታ ማስከበሪያ ያስያዙት ገንዘብ በጥቅሉ ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከስምንቱ የልማት ድርጅቶች አንዱ የሆነው ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካን ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ ለመግዛት ብቸኛ ተወዳዳሪ የነበረው ፀሐይ ኢንዱስትሪስ ግን በቀረበው የመወዳደሪያ መስፈርት መሠረት የሚፈልግበትን ክፍያ በማጠናቀቅ ላይ ነው ተብሏል፡፡ ይህ ኩባንያ በወቅቱ አሸናፊ ሊሆን ቢችልም ሽያጩ የሚፈቀድለት ኩባንያው ክፍያውን የመፈጸም አቅሙ ይጣራ የሚል ውሳኔ ተላልፎበት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚሁ የኤጀንሲው ውሳኔ መሠረት የድርጅቱ አቅም ተፈትሾ መክፈል እንደሚችል ማረጋገጫ በመገኘቱ፣ ክፍያውን በማጠናቀቅ ቃሊቲ ብረታ ብረትን ለመረከብ በዝግጅት ላይ መሆኑም ታውቋል፡፡ አቅም ላይኖረው ይችላል በሚል አሸናፊ የሆነበት ውጤት ሳይፀድቅለት የቀረው ፀሐይ ኢንዱስትሪ አቅም አላቸው ከሚባሉት ከሼክ አል አሙዲናና ሸሪኮቻቸው ኩባንያዎች በፊት ቃሊቲ ብረታ ብረትን ይረከባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ፀሐይ ኢንዱስትሪስ አሸናፊ ከሆነበት ዋጋ ውስጥ በቅድሚያ ለመክፈል የተስማማው 35 በመቶውን ወይም 157.3 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ቀሪውን 65 በመቶ በአምስት ዓመት ለመክፈል እንደሆነ ታውቋል፡፡ ፀሐይ ኢንዱስትሪስ አዲስ ኩባንያ ሲሆን የኩባንያው መሥራቾች ፀሐይ ባንክ በሚል መጠሪያ ባንክ ለማቋቋም አክሲዮን በማሰባሰብ ላይ እንዳሉ ባንክ ለማቋቋም የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር መሆን እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ አቅጣጫቸውን እንዲቀይሩ ያደረጋቸው ባለአክሲዮኖች ናቸው፡፡