ወያኔ አርሶ አደሮችን የፓርቲ አባል ካልሆናችሁ እያለ በማንገላታት ላይ መሆኑ ተገለጸ
ህዝብን እንደ ጠላት እየፈራ ያለው የወያኔ ዘረኛ ቡድን ሰሞኑን በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ አርሶ አደሮችን የልማት ስብሰባ በማለት እየጠራና የፓርቲው አባላት እንዲሆኑ እያስገደዳቸው መሆኑን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ከላከልን መረጃ ለማወቅ ተችሎአል። እንደዘጋቢያችን ሪፖርት በቱኒዚያ ፈንድቶ የሰሜን አፍሪቃ ሃገራትን እየለበለበ ያለው የህዝብ አመጽ እንደማይቀርለት የተረዳው ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ የህዝብ ተቃውሞ ወደገጠሪቱ የሀገሪቱ ክፍል እንዳይስፋፋ በማሰብ በአርሶ አደሩ ዘንድ መፈራራትንና አለመተማመንን ለመፍጠር በማሰብ ከየዞኑ የሰበሰባቸውን አርሶ አደሮች አባል ካልሆናችሁ እርዳታ አናደርግላችሁም፤ የያዛችሁትንም የእርሻ መሬት ተቀብለን ለሌሎች እናከፋፍላልን እያለና እያስፈራሩ አባል እንዲሆኑ ያስገደዳቸው ሲሆን አርሶ አደሮቹ ወደመኖሪያቸው ቦታ ሲመለሱ እያንዳንዳቸው በስራቸው አምስት አምስት ሰዎችን እንዲያደራጁና የድርጅቱ አባል እንዲሆኑ እንዲያደርጉ መመሪያ እንደተሰጣቸው ታውቁአል።
ይህም ተግባር በተለያዩ የሀገሪቱዋ ክፍል ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን በተለይ በሰሜን ሸዋ ወራ ጃርሶ ወረዳ፣ በኢሊባቡር- በደሌ አካባቢ፣ በአርሲ- አሳሳ፣ ዶዶላ እና ኮኮሳ ወረዳዎች ላይ ሁኔታው መባባሱና በነዚህም አካባቢዎች የሌላ ፓርቲ አባላትን ያለምንም ምክንያት እስር ቤት በመወርወር መንቀሳቀሻ እንዳጡ ለማወቅ ተችሎአል። የወያኔ ባለስልጣናቱም ለአርሶ አደሮች በተዘረጋው የህዋስ አደረጃጀት አልተሳተፉም የተባሉትን አርሶ አደሮች ዝርዝር ሪፖርት እንዲያደርጉ ያስጠነቀቁዋቸው ሲሆን አንሳተፍም ያሉት የተቃዋሚ ድርጅት አባላት መሆን አለባቸው ዋጋቸውን ይከፍላሉ ሲሉም መደመጣቸው ተገልጾአል።
ዘጋቢያችን ያናገራቸው ስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ አንድ አርሶአደር ስለጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ፡ ዪሄ ምን ዪበጀናል ብለው እንደሚያደርጉት ግራ የገባቸው መሆኑን ተናግረው ልብ ከሸፈተ ምን ቢያደርጉለትስ መች በቀላሉ ይመለሳል፡ እስከዛሬ በመልካም ስራ በልማት ያልጎበኙንን ዛሬ የኛ አባል ሁኑና ጥቅም እንሰጣቸሁዋለን በማለት ማስገደዱ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጠኖ መደቆስ ሁዋላ ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ” የሚለውን ስንኝ አስታወሰኝ ባማለት ምሬታቸውን ተናግረዋል። አዛውንቱም አያይዘው አብዛኞቻችን አዛውንቶች ነን እንግዲህ እማ እኛን ምን ያደርጉናል ባይሆን ልጆቻችን የነዚህ መሰሪዎች ቀንበር እንዳያርፍባቸው መታገል ነው እንጂ ሁለት ጊዜ ሞት የለ ባማለት ቁጭታቸውን ገልጸዋል።