የዘረኛው አገዛዝ ቁንጮ ባለቤት የሆነቺው አዜብ መስፍን የቅንጦት ኑሮ መጋለጡን ቀጥሉአል
የዘረኛውና አምባገነኑ አገዛዝ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ባለቤት አዜብ መስፍን ለሸቀጣ ሸቀጥ ሸመታ የካቲት 19 ቀን 2003 አም በቻርተር አውሮፕላን ወደ ዱባይ በረራ አድርጋ እንደነበር የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥን የአየር መንገድ ምንጮችን በመግለጽ ዘግቦአል። እንደ ኢሳት ምንጮች መረጃ አዜብ መስፍን በደህንነት ሰዎች ታጅባ በቤተመንግሥት መኪና ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰች ቦኋላ ያለምንም ፍተሻና ቁጥጥር በልዩ መግቢያ በር ወደ ውስጥ እንድትገባ ተደርጎ 12 ሰዎችን ብቻ ለመጫን በተዘጋጀ ቻርተር አውሮፕላን ከሁለት አጃቢዎቿና ከአንዲት የውጪ አገር ዜጋ ከሆነች ሴት ጋር ወደ ዱባይ ተጉዛለች። ዱባይም እንደደረሰች በዱባይ የወያኔ ኤምባሲ ሰራተኞች የክብር አቀባበል ከተደረገላትና ወደ ኤምባሲው ማረፊያ ከተወሰደች ቦኋላ ወድ በሆነ የሚቾት መኪና የቅንጦት ዕቃ ወደሚሸመትበት የተዋቡ ሱቆች እንደተወሰደች የኢሳት የአየር መንገድ ምንጮች አጋልጠዋል።
በሚያማምሩ የዱባይ ህንጻዎች ውስጥ ለሃብታሞች ብቻ በተዘጋጁት ውድ ሱቆች የምትፈልገውን ሁሉ ዕቃ በውጭ ምንዛሪ የሸመተቺው አዘብ መስፍን፤ የገዛቺውን እቃዎች በሙሉ የኤምባሲው ሰራተኞች ለኢትዮጵያ ዓየር መንገድ እንዲያስረክቡ ትዕዛዝ በመስጠት ከነ አጃቢዎችዋ በመጣችበት ቻርተር አውሮፕላን ወደ አዲስ አበባ ተመልሳለች:: አዜብ መስፍን የሸመተቻቸው እቃዎች በጠቅላላ ወደ ለንደን በሚበር የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ተጭኖ እንደሄደና ከባለበቷ መለስ ዜናዊ ጋር በለንደን ከተማ በገዙት የግል መኖሪያ ቤት ውስጥ እንደሚቀመጥ መረጃው ያመለክታል። ለንደን ከተማ የሚገኘውን አዲሱን መኖሪያ ቤታቸውን በሃላፊነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝብ በሚከፍለው ግብር ደመዎዝ የሚከፈለው በዩናይትድ ክንግደም የኢትዮጵያ አምባሳደር ተብሎ የተሰየመው ብርሀኑ እንደሆኑ ታውቁአል።
በተመሳሳይ መልኩ ቀደም ብሎ በወጣ ዘገባ ኤቢሲ የተባለው የስፔን ጋዜጣ አዜብ መስፍን አባካኝ የሆነች ሴትና በአውሮፓና በአሜሪካ በሚገኙ ውድ ሱቆች ውስጥ እቃዎችን እንደምትገዛ የሚገልጽ መረጃ ከአወጣ በሁዋላ፣ አዜብ የአውሮፓ ጉዞዋን ገትታ በዱባይ እቃዎችን ለመግዛት ተገድዳ ሊሆን እንደሚችል ተገምቱአል። ጋዜጣው አዜብ መስፍን የባሉዋ ሀብት ከሆነው ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዩሮ ወይም ወደ 33 ቢሊዮን ብር ከሚጠጋ ሀብት ውስጥ እያፈሰች እጅግ ውድ የሚባሉት እቃ እንደምትገዛ አጋልጧል።
በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን በቀን አንድ ጊዜ መብላት ተስኑአቸውና የለት ከለት ኑሮአቸውን መግፋት አቅቶአቸው በሚገኙበት በዚህ ወቅት የዘረኛው አገዛዝ ቁንጮ ባለቤት አዜብ መስፍን እጅግ ውድ የሆኑ እቃዎችን በግል አውሮፕላን እየተዟዟረች የምታደርገው ሸመታ በርካታ ኢትዮጵያውያንን የሚያስቆጣ ተግባር ነው።
ይህ በንዲህ እንዳለ የቱኒዚያው ቤን አሊ መኖሪያ ቤቴመንግሥት ሲፈተሽ በመቶ ሚሊየኖች የሚቆጠር ዶላር እንዲሁም ውድ ጌጣጌጦች ደብቆ መገኘቱን የተመለከቱ አንድ በውጭ ሃገር የሚገኙ ኢትዮጵያዊ በሰጡት አስተያየት፣ የቤን አሊ አይነት ዝርፊያና ብልግና በእጥፍ ሃገራችን ውስጥ በነ አዜብ መስፍን ብቻ ሳይሆን በዙሪያቸው በተኮለኮሎ ዘረኞች ጭምር እየተፈጸመ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያም ውስጥ እንደነ ቤን አሊ ዘረፋው የሚቆምበትና ሌቦቹም የሚጋለጡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም ብለዋል::