በጋሞጎፋ ዞን የ8 ወረዳዎች ህዝብ ለወያኔ አልገዛም በማለት ተነሳ

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የውስጥ ምንጮቹን በመጥቀስ የካቲት 29 ቀን 2003 ዓም ባወጣው ዘገባ በጋሞጎፋ ዞን የ8 ወረዳዎች ህዝብ ዘረኛው የወያኔ አምባገነን አገዛዝ እያደረሰበት ባለው ግፍና በደል በመማረር ለወያኔ አልገዛም በማለት  መነሳቱንና አካባቢውም በፌደራል ፖሊስና ጦር ሃይል  መወረሩን ገልጹአል::

ኢሳት በዘገባው ላይ እንደገለጸው በስምንቶቹ  ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙት  የመንግስት ሰራተኞች ተባረዋል፣  ትምህርት  ቤቶችም ተዘግተዋል:: ህዝባዊ አመጹ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ህዝቡ ወያኔ ከንግዲህ በጉልበት ካልሆነ በፍላጎት አይገዛንም የሚል የጸና አቁአም ይዙአል::

በጋሙጎፋ ዞን  ስምንት ወረዳዎች ውስጥ የተነሳውን አመጽ ተከትሎ ከአስራ አንድ በላይ ንጹሃን ተገድለዋል በመቶዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል:: ባልተጠበቀ አቅጣጫና ሁኔታ የተነሳው  ህዝባዊ አመጽ ያደናበረው የወያኔው ዘረኛ አገዛዝ፣ ከህዝቡ ጋር  እንደራደር በማለት  ሚኒስትሩን ቢልክም  ህዝቡ ድርድር አንፈልግም ማለቱን ኢሳት በዘገባው ላይ ገልጹአል::

በቱኒዚያ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ የሰሜን አፍሪቃ በርካታ ሃገራትን ካዳረሰ ወዲህ በኢትዮጵያ ህዝባዊ አመጽ መነሳቱ እንደማይቀር በርካቶች የገለጹ ሲሆን የዘረኛው ወያኔ አገዛዝ የውሸት ቁንጮ በረከት ስምኦን የኢትዮጵያ ህዝብ በተደላደለ ኑሮ ላይ የሚገኝ በመሆኑና የነገዋን ኢትዮጵያም ብሩህ ተስፋ እየተመለከተ በመሆኑ ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ አይችልም በማለት መናገሩ ይታወቃል::

በሌላ በኩል የግንቦት ሰባት ዘጋቢ የታመኑ ምንጮቹን በመጥቀስ በላከልን ዘገባ በአዋሳ በተነሳ ግጭት በርካቶች እየታሰሩ መሆናቸውንና በአካባቢው የሚገኘው አርሶ አደርም  በዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በመማረሩ ፖሊሶችን ማባረሩና በፖሊሶች ላይም ጉዳት ማድረሱ ታውቁአል:: በአዋሳ የተከሰተው  ውጥረቱ እንዳለ ሲሆን በተፈጠረው ሁከት መኪኖች ተሰባብረዋል::  በአዋሳ የተነሳውን ግጭት ለማብረድ በሚል የአዋሳ ከተማ ሆድ አደር ከንቲባ  የአገር ሽማግሎዎችን  ሰብስቦ ከመጤዎች ጋር አትቁሙ እያለ መምከሩን የደረሰን ዜና የገለጸ ሲሆን ህዝቡ ግን  ለዘመናት ተፋቅረን ከኖርነው ከመጤው ህዝብ ጋር አታጣሉን እያለ መሆኑ ታውቁአል::

በበረከት ስምዖን ሃላፊነት ሥር የሚተዳደረው የወያኔ መገናና ብዙሃን በቲኒዚያ እና ግብፅ የተካሄደውን ህዝባዊ አብዮት የአየር ሽፋን ሳይሰጡት ከሰነበቱ ቦኋላ የሊቢያ ህዝብ የቀሰቀሰውን ህዝባዊ አብዮት ለመቀልበስ ሙአመድ ጋዳፊ በተቃዋሚዎቻቸው ላይ እየወሰዱ ያሉትን ጨካኝ እርምጃ እየተከታተሉ በማቅረብ ላይ እንዳሉ ይታወቃል። በአገሪቱ ግብር ከፋይ ገንዘብ የዘረኛውን ወያኔ እድሜ ለማራዘም ህዝባችንን በባዶ ተስፋና ፕሮፖጋንዳ ለማደንዘዝ የተሰለፈው የኢትዪጵያ ቴሌቭዥን ጣቢያም በሰሜን አፍርካ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ በአገራቺን ሊከሰት የሚችልበት ምንም መሠረት የለም ከማለት ጀምሮ በአጋጣሚ ቢከሰት እንኳ ወያኔ ያስገኘውን ልማት እና እድገት ያወድማል እንጂ ህዝብ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችል ፋይዳ ያለው ለውጥ አያስገኝም የሚል ቅስቀሳ በማሰራጨት ሥራ መጠመዱ ታውቆአል።