ሰበር ዜና – ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ አረፉ
(ደጀ ሰላም፤ መጋቢት 8/2004 ዓ.ም፤ ማርች 17/2012/ PDF)፦ ተወዳጁ የቅብጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ሺኖዳ ሣልሳዊ በተወለዱ በ88 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸውን የአገሪቱን ሬዲዮ የጠቀሰው ቢቢሲ ዘግቧል። ለእረፍታቸው ምክንያት የሆነው ምን እንደሆነ ያልተገለጸ ቢሆንም በዕድሜ አረጋዊ የኾኑት ቅዱስነታቸው ለረዥም ጊዜ ሲታመሙ መቆየታቸው ይታወቃል።
የግብጽ ኦርቶዶክስ ምእመናን ከ80 ሚልዮን የአገሪቱ ሕዝብ 10 እጅ (10%) ብቻ ሲሆኑ በአክራሪዎች በሚደርስባቸው ተደጋጋሚ አደጋ ምክንያት ፖፕ ሺኖዳ መንግሥት የበለጠ ጥበቃ እንዲያደርግላቸው ሲማጠኑ ቆይተዋል።
ከዚህ በፊት በደጀ ሰላም ላይ ባቀረብነው አንድ ዘገባችን ፖፑ “በልቤ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ መናገር አልችልም። ዝምታዬን እግዚአብሔር ይሰማዋል” ካሉ በኋላ ምእመናኑ ፊት ሲያነቡ ታይተዋል። ከጻድቁ ፖፕ ከአቡነ ቄርሎስ ቀጥለው በመንበረ ማርቆስ የተሰየሙት 117ኛው ፖፕ አቡነ ሺኖዳ በተለይም በኢትዮጵያ ምእመናን ዘንድ በመጽሐፎቻቸው የበለጠ ታዋቂ እና ተወዳጅ ሆነዋል። ኢትዮጵያን ለመጎብኘት በመጡበትም ወቅት ሕዝቡ ከቦሌ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል እንዳደረገላቸው ይታወሳል።
የቅዱስነታቸው በረከት አይለየን፤ ይደርብን፤ ለግብጽ ቤተ ክርስቲያንም የብፁዕ ወቅዱስ አቡነነ ሺኖዳን ዐይነት አባት ይተካላቸው፤ ይስጣቸው። አሜን
