98%

በአሁኑ ጊዜ የዝቋላ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም ከሥጋት 98 በመቶ ነጻ ሆኗል፡፡ አልፎ አልፎ ገደል ውስጥ ከሚታየው ጢስ በስተቀር እሳቱ ጠፍቷል ማለት ይቻላል፡፡ ገዳማውያኑ ላለፉት አምስት ቀናት በአሳት ማጥፋቱ ሥራ የተሳተፉን ወጣቶች በጸሎት ለማሰናበት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡
አሁን ገዳሙን በዘላቂነት ስለመርዳት፣ እሳቱ እንዳይነሣ ስለማድረግ መነጋገር ያለብን ጊዜ ነው፡፡

በዚህ ሥራ ላይ የአዲስ አበባ፣ የናዝሬት እና የደብረ ዘይት ሕዝብ በተለይም ወጣቶች ያሳዩት ኦርቶዶክሳዊ ቆራጥነት ለካስ ቤተ ክርስቲያን ሰው አላት ያሰኘ ነው፡፡ ልዩ ልዩ የመንግሥት አካላት፣ ነጋዴዎች እና የመኪና ሾፌሮች እግዚአብሔር ብቻ የመዘገበው አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ ከተባበርን የማንፈታው ችግር፣ የማናመጣው ለውጥ፣ የማንራመደው ገደል፣ የማንሻገረው ሸለቆ እንደሌለ አይተናል፡፡ ይኼ በዝቋላ እሳት ምክንያት የታየው ኅብረት እና ፍቅር በሀገሪቱም ሆነ በቤተ ክርስቲያኒቱ ዕድገት ላይ ተሠማርቶ ችግር ወደሚፈታበት መንገድ መሻገር አለበት፡፡

ከዚህ በኋላ ወደ ዝቋላ መሄድ ያለብን እሳት ለማጥፋት ሳይሆን ታሪክ ለማየት እና በረከት ለማግኘት ብቻ መሆን አለበት፡፡
የረዳን እግዚአብሔር ከኛ ጋራ ለዘለዓለም ይሁን፡፡