ማንበር
click here for pdf
ተወዳጁ ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ አስተጋብተው ባረቱት እና «ባሕል እና ልማት በኢትዮጵያ» በሚለው መጽሐፍ ላይ እርሳቸው ያዘጋጁት ጥናታዊ መግቢያ አለ፡፡ ይህንን ጥናታዊ መግቢያ ማንበብ አንድ የዕውቀት ባሕር ውስጥ ገብቶ ከመጠመቅ ይቆጠራል፡፡
ፕሮፌሰር ሺፈራው በገጽ 18 እና 19 ላይ እንዲህ ይላሉ፡፡ «የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ በሀገራችን አድጎ የአማርኛ ቋንቋን አቀላጥፎ የሚናገረው የኖርዌዩ ዜጋ ዶክተር ሄላንድ ስለ ኢትዮጵያ የዕድገት ማነቆዎች በምንወያይበት ወቅት አንድ ትዝብቱን አነሳብኝ፡፡ በአማርኛ ቋንቋ ሜንቴናንስ (maintenance) ለሚለው የእንግሊዝኛ ቃል አቻ እንደሌለውና ጥገና ወይም እድሳት የሚሉት ቃላት አንድ እንደ ሕንፃ፣ አውራ ጎዳና ወይንም ተሽከርካሪ ያለ ቁሳዊ ነገር ወይንም ንብረት እስኪበላሽ ድረስ ቆይቶ ከዚያ በኋላ የሚደረግ ማስተካከልን ማለትም ጥገና ማድረግን እንጂ እየተገለገሉ በዚያውም እንደ ነበር ጠብቆ ማቆየትን እንደማያመለክቱ ታውቃለህ ወይ? ደግሞም የቃሉ አለመኖር እንደ ሚያመለክተው በኢትዮጵያ ሁሌ እንደሚደረገው አንድ ነገር ተበላሽቶ ወይንም አልቆ እስከሚያበቃለት ቆይቶ ከዚያ ወደ እድሳት መግባት እንደሆነ ልብ ብለሃል ወይ? ብሎ ጠየቀኝ» ይላሉ፡፡
ይህንን ሳነብ እጅግ በጣም ነበር የተገረምኩት፡፡ በሁለት ምክንያቶች፡፡ በአንድ በኩል በዶክተር ሄላንድ አስተውሎት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የቋንቋ ጥናት ለሌሎች አያሌ የጥናት ዘርፎች የሚኖረውን ቁልፍ ቦታ በማየት፡፡
ፕሮፌሰር ሺፈራው ሜንቴናንስ (maintenance) የሚለውን «ማንበር» ብለው ተርጉመውታል፡፡ ሲፈቱትም «በጥቅም ላይ እያዋሉ እንደ ነበር ጠብቆ ማቆየት» ይሉታል፡፡ እኔም ይህንን ካየሁ በኋላ ለመሆኑ በባህላችን ማንበር አለ? ብዬ ጠየቅኩ፡፡ ከእምነት እስከ ባህል፣ ከፖለቲካ እስከ ኢኮኖሚ፣ ከሀገር እስከ ቤተሰብ፣ ከሕዝብ መገልገያዎች እስከ ግል ንብረቶች፣ ከአሠራር፣ እስከ ሕግጋት፣ ከሥነ መንግሥት እስከ ሥነ ሕዝብ “ማንበር“ን ፈተሽኩት፡፡ እኔም አላገኘሁትም፡፡
ለሦስት ሺ ዘመናት የሚያህልን የመንግሥት እና የሕዝብ ታሪክ የምንቆጥር ሕዝቦች የመንግሥታችን ታሪክ እየፈረሰ እንደገና ሲሠራ እንጂ ያለውን እየጠበቁ፣ አዳዲስ አሠራሮችንም እየጨመሩ የማንበር ሥርዓት አልነበረንም፡፡ ከኋላ የመጣው ሀገሪቱን እንደ አዲስ ሲጀምራት፡፡ እርሱ መንበር ላይ በተቀመጠ ቁጥር ነጻ ሲያወጣት፡፡ ከዚያ በፊት ለነበራት ህልውና ዕውቅና መስጠት ተስኖት ራሱ የፈጠራት አገር ሲያደርጋት፡፡ ደንቆሮ የሰማ ዕለት ያብዳል እንደሚባለው እርሱ ስለ ነጻነት የሰማበትን ቀን ሕዝብም ያን ቀን የሰማ እየመሰለው፣ እርሱ የነገሠበትን ቀን ሕዘብም ያን ቀን የነገሠ አድርጎ እየቆጠረው ሲያፈረስ ሲሠራ ነው የኖረው፡፡
አኩስምን የመሰለ ሥልጣኔ ርግፍ አድርገን ስንተወው እና ወደ ሮሐ ስንሻገር ምንም ያልተሰማን ሕዝቦች ነን፡፡ እነዚያን ሰው ደግሞ ሊሠራቸው የማይቻላቸውን የላሊበላ ድንቅ ሥራዎች ከ300 ዓመታት ባላይ እንደ ጠላት ገንዘብ ስንተዋቸው ቅንጣት ታህል ቅሬታ አላደረብንም፡፡ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ የተለፋባትን ጎንደርን የተውንበት ምክንያት ግልጽ አይደለም፡፡ ነገም አዲስ አበባን ትተን ወደ ሌላ ቦታ ላለመሄደችን ምንም ዋስትና የለንም፡፡ አፍርሶ ሠሪዎች ነና፡፡
እንዲህ ዛሬ የትምህርት ሥርዓታችን መከራውን እንዲያይ የፈረድንበትኮ አፍርሶ በመሥራት መንገድ ስለገነባነው ነው፡፡ ለሺ ዓመታት የዘለቀ ነባር የትምህርት ሥርዓታችንን ሳንፈትሸው፣ እንዴት እየተ ጠቀምን እንደምናዘምነው ሳናስብበት አፈረስነውና ከእንግሊዝ እና ከፈረንሳይ፣ ከግብጽ እና ከአሜሪካ በተወሰደ አዲስ የትምህርት ሥርዓት ተካነው፡፡ ታድያ ያ ባህል ሆኖብን አሁንም የራሳችንን ፈትሸን እያነበርን ከመሄድ ይልቅ ችግር እስኪፈጠር እየጠበቅን የትምህርት ሥርዓታችንን ስናፈርስ ስንጠግን እየኖርን ነው፡፡
እስኪ በየቦታው ታዘቡ፡፡ የኢትዮጵያውያን የአሠራር፣ የአስተዳደር እና የሥልጣኔ ፍልስፍና የሚባል መልክ ያለው ነገር ታያላችሁ? ይህንን ያህል ሺ ዓመት ኖረን፣ ይህንን ያህል የተጻፈ ታሪክ ኖሮን፣ የተጻፈ ሕግ እና ጥንታዊ የዳኝነት ሥርዓት ኖሮን፣ ሦስቱ ዓለምን የለወጡ ታላላቅ እምነቶች ኖረውን፣ አፍሪካውያን ሚኒስትር የሚባል ከመሰየ ማቸው በፊት ከመቶ ዓመታት በፊት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ዘርግተን፡፡ ስልክ እና መኪና፣ የቧንቧ ውኃ እና መብራት፣ አውቶሞቢል እና ጋዜጣ ከመሰል ወንድሞ ቻችን በፊት የነበረን ሕዝቦች፤ እንዴት ነው የተዋጣለት የመገናኛ ሥርዓት፣ የዳበረ የፕሬስ ባህል፣የተሳለጠ የትራን ስፖርት አገልግሎት፣ አርአያ የሚሆን የፍትሕ ሥርዓት፣ ግልጽ እና ሥሉጥ የሆነ የመሥሪያ ቤቶች አደረጃጀት እና አሠራር፣ በምሳ ሌነት የሚጠቀስ ቤተ እምነት ሊኖረን ያልቻለው ለምን ይመስላችኋል?
ስናፈርስ ስንሠራ ነዋ የኖርነው፡፡ ማንበር የት እናውቅና፡፡
ያለንን አንብሮ የለለንን ጨምሮ፣ያለውን ከሌለው ጋር አስማምቶ እና አገናዝቦ የመሄዱ ባህል ቢያጥርብን ነው እንጂ በዚህ ሁሉ ሺ ዓመታት ጉዞ ዳኘው የሚባል ልጅ እንጂ ለዓለም የሚተርፍ ዳኛ፣ሃይማኖት የምትባል ልጅ እንጂ ሕዝቡን በሞራል እና በእምነት ልዕልና ላይ የሚያቆም የሃይማኖት ተቋም፤ መብራቱ የሚባል ልጅ እንጂ ከዓመት እስከ ዓመት የማይቋረጥ መብራት፣ ውኃ ልማት የሚባል ፌርማታ እንጂ የዓባይን ልጅ ውኃ እንዳይጠማው የሚያደርግ ዘላቂ የውኃ ልማት፣ በስልክ አነጋግሪኝ በቀጭኑ ሽቦ የሚል ዘፈን እንጂ የሚተማመኑበት የቴሌፎን አገልግሎት እንዴት እስካ ሁን ከኛ ሊርቁ ቻሉ?
ስንት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን አፍርሰን ስንት ሌሎችን ሠርተናል፡፡ አፍርሶ ሌላ መሥራት ብቻ ሳይሆን አፍርሰን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መልሰን የሠራናቸውም አሉ፡፡ በአንዱ መሥሪያ ቤት የነበረ ታሪካዊ መዝገብ ወደ አንዱ ሄዶ፣ ከዚያም አንዱ ተረክቦት፣ በመጨረሻ ሙት ፋይል ያለበት ቦታ ተቆልፎበት የቀረ ስንት ታሪክ አለ?
መንገዱ ካልተሰባበረ፤ ሕንፃው ካልተሰነጣጠቀ፣ መኪናው አጓርቶ አጓርቶ በራሱ ጊዜ ካልቆመ፤ ወንበር እና ጠረጲዛው ተንቃቅቶ ተንቃቅቶ «በ – ቃ – ኝ» ብሎ ካልተጋደመ፡፡ የውኃ ቧንቧው አንጠባጥቦ አንጠባጥቦ ሲመረው ካልፈነዳ፤መስተዋቱ ተተርትሮ ተተር ተሮ ሲመረው «ምነው እቴ» ብሎ መሬት ላይ ካልተዘረገፈ፤ ፍራሹ ተቦጭቆ ተቦጭቆ ወደ ምንጣፍነት ካልተቀየረ፤ ምጣዱ እንኳን ተሰንጥቆ ተሰንጥቆ ሊጡን ማፍሰስ ካልጀመረ ማን ይደርስላቸዋል፡፡
ይገርማችኋል ይሄ ነገር በቁሳዊው ነገር ላይ ብቻ አይደለም የሚታየው፡፡ እስኪ የሕክምና ልማዳችንን ተመልከቱ፡፡ ለመሆኑ በየጊዜው የመታየት ልማድ አለን? በዓመት በተወሰኑ ጊዜያት ወደ ሐኪም ቀርበን ያለንበትን ሁኔታ የማወቅ ሥርዓት አለን? የሕመም ስሜት ሲሰማን እንኳን ወድቀን ካልተንከባለልን መቼ ወደ ሕክምና እንመጣለን፡፡ ካልፈረስን መሠራት አይሆንልንም ማለትኮ ነው፡፡ ልማዳችን ታምሞ የመዳን እንጂ ጤናን ጠብቆ የማቆየት አይደለማ፡፡
ታላላቅ የሀገሪቱ ሰዎች ደከሙ፣ ታመሙ፣ ተቸገሩ ይባላል፡፡ አብዛኛው ጸጥ ይላል፡፡ ከበደ ሚካኤል «ጽጌረዳ እና ደመና» በሚለው ግጥማቸው እንዳሉት
በችግሩ ብዛት ቆይቶ ሲጉላላ
ደክሞት እና ርቦት ከሞተ በኋላ
የመሞቱ ዜና ሲሰማ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ለቀብር ይወጣል፡፡ ጥቁር ይለብሳል፡፡ መታመማቸውን ያልገለጠው ሚዲያም ልማዱ ነውና ሞታቸውን ያስጌጠዋል፡፡ ከመሞታቸው በፊት ያልታተመው መጽሐፋቸው ከሞቱ በኋላ እየወጣ ይቸበቸባል፡፡ ታሪካቸውን እናቆይ፣ ሙት ዓመታቸውን እናስብ፣ ሐውልት እናሠራ፣ የምናምን ምሽት እናዘጋጅ ይባላል፡፡ ካለቀ ከደቀቀ በኋላ፡፡ ምን ይደረግ ማንበር አንችልበትማ፡፡
እስኪ በባህላችን የወለደ የሚያስጠይቅ፣ የታመመ የሚያሳክም፣ የቸገረውን የሚረዳ፣ ጀግናውን የሚሸልም፣ የደከመውን የሚያበረታ ዕድር ለምን አልፈጠርንም? ኢትዮጵያ ውስጥ ዕድር ተጀመረ የሚባለው በ14ኛው መክዘ ነው፡፡ እንግዲህ ስድስት መቶ ዓመታትን ያህል አስቆጥሯል ማለት ነው፡፡ እንዴት በስድስት መቶ ዓመታት ውስጥ ሞትን ብቻ ስናስብ ኖርን፡፡ መኖር ጉዳያችን አይደለም ማለት ነው? ሲፈርስ መምጣት እንጂ እንዳይፈርስ የማድረግ ባህል የለንም ማለት ነው?
ለነገሩ ምን ይደረግ
ይብላኝ ለሟች እንጂ ልጅስ ያድጋል በእጁ
እንደ ጎታ ፍራሽ ወድቆ በየደጁ
እያልን አይደለ የምናለቅሰው? ከነዋሪው ይልቅ የምንጨነቀው ለሟቹኮ ነው፡፡ ለሟቹ ምርጥ መቃብር እያሠራን ልጆቹ ግን በቁማቸው በየደጁ እንዲወድቁ ተስማምተናል፡፡
ባለ ትዳሮች ሲጣሉ ለማስታረቅ የሚመጡ ሽማግሌዎች እና ቤተሰቦች እንጂ በትዳር ጸንተው እንዲኖሩ የሚያግዙ እና የሚመክሩ ሽማግሌዎች እና ቤተሰቦች መች በብዛት አሉን፡፡ ለመሆኑ ስንቶቻችሁን ሚዜዎቻችሁ እየመጡ ይጠይቋችኋል? ብትጣሉስ? ስንቱ ነው ሊመክራችሁ የሚመጣው፡፡ ለምን አትሉም? እንዳይሰበር የሚያነብር ሳይሆን ሲሰበር የሚጠግን ነዋ ያለን፡፡
እስኪ በየአካባቢያችን፣ በየድርጅታችን እና በየማኅበራችን የሚደረጉ ስብሰባዎችን ገምግሟቸው፡፡ አብዛኞቹ አንዳች ችግር ሲፈጠር ለችግሩ መልስ ለመስጠት ወይንም ችግሩን ለመፍታት የሚደረጉ ናቸው፡፡ ችግሩ እንዳይፈጠር፣ የተዘረጋው አሠራር ወይንም ሥርዓት ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ሥራውን እያስቀጠሉ ችግሩን ለመፍታት የሚደረጉ አይደሉም፡፡ እንዲያውም አንዳንዶቹ ከዚህም ብሰው ሥራ አስቁመው፣ ቢሮ አስዘግተው የሚከናወኑ ናቸው፡፡ የማንበር ችግር፡፡
ማስታወቂያዎቻችንንስ አይታችኋል? ማስጠንቀቂያዎቻችንን ልበላችሁ እንጂ፡፡ እንዲህ ማድረግ ክልክል ነው፣ እንዲህ ማድረግ ያስቀጣል፡፡ የተሸጠ ዕቃ አይመለስም፤ ፎቶ ግራፍ ማንሳት ክልክል ነው፤ መቆም ክልክል ነው፣ መቀመጥ ክልክል ነው፤ መጸዳዳት ክልክል ነው፤ ስለ ማፍረስ ብቻ ነው የሚነግሯችሁ፡፡ ስለ ማንበር አይነግሯችሁም፡፡
የተሸጠ ዕቃ የማይመለስ ከሆነ አስቀድማችሁ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ የሚነግር አታገኙም፡፡ ፎቶ ማንሳት ክልክል ነው ይላል እንጂ የት ቦታ ደግሞ እንደተፈቀደ አይገለጥላችሁም፡፡ እዚህ መቆም ክልክል ከሆነ ታድያ የት እንቁም? ይህንንም ተውት መቆም ክልክል ነው ካለ ለምን መቀመጫ አያዘጋጁም፡፡ መቀመጥ ክልክል ነው ይሏችሁና ከጎኑ መቆምም ክልክል ነው ይሏችኋል፡፡ ታድያ መቆምም መቀመጥም ከተከለከለ ምነው አልጋ አያዘጋጁ? ሰው ሳይጸዳዳ መኖር አይችልም፡፡ መጸዳዳት ክልክል ነው ብሎ ቋንቋ ምንድን ነው? በአካባቢው የመጸዳጃ ቦታ ሳይኖርስ መጸዳዳት ክልክል ነው ብሎ ማስጠንቀቂያ ተፈጥሮን ከመቃወም ውጭ ምን ትርጉም ይኖረዋል፡፡
ሥርዓቱን፣ ንጽሕናውን፣ ጸጥታውን፣ ልማዱን፣ እንድንጠብቅ የሚያደርጉ የማንበር ሕጎች የሉንም፡፡ ስናፈርሳቸው እንዴት እንደምንቀጣ የሚነግሩን እና የሚያስጠነቅቁን ግን ሞልተዋል፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ አካባቢዎች አፍራሾቹን የሚቀጡ እና የሚጠብቁ ሰዎች እንጂ ማክበር ለሚፈልጉ መረጃ የሚሰጡ እና የሚተባበሩ ባለሞያዎች አታገኙም፡፡ መጸዳዳት ክልክል ነው ከማለት ይልቅ የመጸዳጃ ቤቶችን መገንባት የተሻለ ጤናን እና አካባቢን ያነብር ነበር፡፡
እናመሰግናለን ፕሮፌሰር ሺፈራው፡፡ አሁን ስለ ማንበር እንድናስብ አድርገውናል፡፡ ይኼንን በየመሥሪያ ቤቱ «የጥገና ክፍል» የሚባለውን ሁሉ ከስሙ ጀምሮ የማንበር ክፍል ልንለው ነው፡፡ በየቤታችንም መጠገን እና ማስጠገንን ትተን ማንበር ልንጀምር ነው፡፡ እንጠግናለን እያሉ ንግድ የከፈቱ ሁሉ «እናነብራለን» ሊሉ ነው፡፡
እኛም እናነብራለን፡፡