የዘበርጋ ጥያቄ
የማኅበራዊ ጥናት መድረክ ባሳተመው «ባሕል እና ልማት» በሚለው እስትግቡእ ውስጥ ዶክተር ፈቃደ አዘዘ ስለ ፎክሎር የጻፈው ዕውቀት አዘል፣ ልብ መሳጭ ጽሑፍ አለ፡፡ እዚያ ጽሑፉ ውስጥ ዘበርጋ የሚባል አንድ ሰው በመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ወቅት የጠየቀውን አስደናቂ ጥያቄ ለሃሳቡ ማስወንጨፊያ ተጠቅሞበታል፡፡
ዘበርጋ መሠረተ ትምህርት ሊማር ነበር የገባው፡፡ መምህሩ ታድያ ሂሳብ ለማስተማር ወደ ክፍል ገቡና እንዲህ አሉ፡፡ አንድ በግ በአምስት ብር ቢሸጥ አራት በጎች በስንት ብር ይሸጣሉ?
ዘበርጋ ከሁሉም ተሽቀዳድሞ እጁን አወጣ፡፡
መምህሩ ደስ አላቸው፡፡ እንዲህ ሂሳብን ያህል ነገር በቶሎ ተረድቶ የሚመልስ ጎልማሳ በመኖሩ፡፡
«እሺ ዘበርጋ» አሉት፡፡
ዘበርጋ ተነሣ፡፡
«የት?» አላቸው መምህሩን፡፡ ክፍሉ በሙሉ ሳቀ፡፡
ዘበርጋን ያስጨነቀው አንድ በግ በአምስት ብር ተሽጦ አራት በጎች በስንት ብር ሊሸጡ እንደሚችሉ ያለው ውጤት አይደለም፡፡ ለመሆኑ አሁን መምህሩ ባሉት ዋጋ፣ በአራት ብር በግ የት ነው የሚሸጠው? የሦስት ሺ ብር ቮልስ መኪና የሦስት ሺ ብር በግ እየጫነ ባለበት ዘመን እኒህ መምህር በአራት ብር የሚሸጥ በግ ከየት ነው ያመጡት? በእውነት በግ በአራት ብር የሚሸጥ ከሆነ ሮጥ ብሎ መግዛት ዛሬ ነው፡፡
ይህ የዘበርጋ ጥያቄ የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው፡፡ ቢያንስ የእኔም ጥያቄ ነው፡፡ ዘበርጋ ይህንን ጥያቄ የጠየቀው ሞኝ ስለሆነ ወይንም ሂሳብ ስለማይገባው አይደለም፡፡ በአንድ በኩል የዘበርጋ ጥያቄ የትምህርት ፍልስፍና ጥያቄ ነው፡፡ ትምህርት እውነታውን ካላንጸባረቀ፣ ችግርንም ካልፈታ ትምህርትነቱ ለጊዜ ማጥፊያ ይሆናል፡፡ የመምህሩ ምሳሌ እና የዘበርጋ ኑሮ አልተጣጣመም ማለት ነው፡፡ በአሜሪካ እንዲህ ነው፣ በአውሮፓም እንዲህ ነው፣ በእስያም እንዲህ ነው እየተባሉ ለሚሰጡት ትምህርቶች የዘበርጋ ጥያቄ ትክክለኛ ጥያቄ ነው፡፡
አንድ የኅብረተሰብ ሳይንስ መምህር ተማሪዎቹን ሲያስተምር ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ናት? ይላቸዋል፡፡ ወዲያው አንድ አስተዋይ ተማሪ ተነሥቶ «ታድያ ለምን ሥጋ ውድ ይሆናል?» ሲል ጠየቀው፡፡ እውነቱን ነው፡፡ አንደኛ መውጣት ለቁጥር ብቻ ከሆነ ከብት ከሌላቸው ከነ ዱባይ፣ አብዛኛውን ሥጋ ከውጭ ከሚያስገቡት ከነ ግብጽ ባነሠ ዋጋ ሥጋ ካልተሸጠ አንደኛ መውጣት ትርጉሙ ምንድነው? ቁጥር ብቻ፡፡
የሕግ፣ የሲቪክስ፣ የታሪክ፣ የኢኮኖሚክስ፣ የአካውንቲንግ፣ የአስተዳደር ወዘተ ትምህርቶቻችን በዚህ የዘበርጋ ጥያቄ ሊፈተሹ ይገባቸው ነበር፡፡ ይህ ስለ ሕግ ልዕልና፣ ስለ ተከሰሰ ሰው መብት፣ ካልተፈረደበት እንደ ወንጀለኛ አይቆጠርም ስለሚባለው፣ የዳኞች የኅሊና ነጻነት፣ የፕሬስ ነጻነት፣ በዳኝነት ሥራ ውስጥ ማንም ጣልቃ ስላለመግባቱ የም ንማረው ትምህርት ግን የት ነው የሚተገበረው? ወይስ እንደ ሂሳብ መምህሩ የመማርያ ሰሌዳው ላይ ብቻ ነው ያለው? ዘበርጋ የገረመውኮ ይኼ በሰሌዳው ላይ ያለው የበግ ዋጋ የት ነው በአካል የሚገኘው? የሚለው ነው፡፡ ይኼ ነው የዘበርጋ ጥያቄ፡፡ የእኛም ጥያቄ ይኼው ነው፡፡ ይኼ በሕግ ትምህርት፣ በሕግ ዐዋጆች እና በሕግ ንግግሮች ውስጥ ይፈጸማል የሚባለው የሕግ ልዕልና፣ የሕግ እኩልነት እና የሕግ ነጻነት የት ነው ያለው?
ይኼ በሲቪክስ ትምህርት ስለ ዲሞክራሲ፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ መብት ማስከበር፣ ስለ ዜጋ፣ ስለ መንግሥት እና ሕዝብ፣ ስለ ሥነ ምግባር የሚሰጠው ትምህርትስ መጽሐፉ ላይ ብቻ ነው ወይስ መሬትም ላይ ይገኛል? ይኼ የአካውንቲንግ ተማሪዎች በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኩባንያዎች ምሳሌነት የሚማሩት፣ ተፈትነው ከኤ እስከ ኤፍ የሚያገኙበት ነገር የት መሥሪያ ቤት ነው ያለው? ለመሆኑ ከትምህርት ቤት ከወጣችሁ በኋላ አግኝታችሁታል? ወይስ እንደ ዘበርጋ መምህር ለምሳሌነት ብቻ ነው የተማራችሁት?
የት? አለ ዘበርጋ እውነቱን ነው፡፡
ብዙ ዕድገቶች፣ ለውጦች እና ብልጽግናዎች በቁጥር ነው የሚገለጡት፡፡ በዚህን ያህል በመቶ አድገናል፤ በዚህን ያህል በመቶ ተለውጠናል፤ በዚህን ያህል በመቶ ድህነት ቀንሷል የሚሉ አኀዞች ሞልተዋል፡፡ ግን እነዚህ አኀዞች በምድር ላይ የት ነው ያሉት፡፡ የስኳር ምርት እጥረት የለም፣ ዘይትም በሽበሽ ነው፣ ስንዴም ከበቂ በላይ አለ የሚሉን ሰዎች ለምን የት የት እንዳለ አይነግሩንም? ስኳር በስንት ልመና እና ዝምድና እያገኘን እንደሆነ አልሰሙም ማለት ነው? ይኼንን ተከማችቶበታል ብለው የሚናገሩለትን ቦታ ለምን አይጠቁሙንም?
እነዚህስ ስኳሩን፣ ዘይቱን እና ስንዴውን ደብቀው የያዙት «አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች» እነማን ናቸው? ካሉ ለምን አይነገረንም? ለምን እነርሱም እንደ ሜትሮሎጂ አንዳንድ እየተባሉ ይጠራሉ? ስም የሌላቸው አድራሻ ያላወጡ ነጋዴዎች ናቸው እንዴ? ወይስ እንደ ዘበርጋ መምህር ወረቀት ላይ ብቻ ነው ያሉት? እነዚህ በየሚዲያው አበረታች እየተባሉ የሚገለጡ ነገሮች መሬቱ ላይ የት ነው ያሉት?
የኃይል እጥረት የለም፤ የቴክኒክ ችግር ገጥሞን ነው ይሉናል፡፡ እጥረት ከሌለ መልካም፡፡ ግን ይኼ የቴክኒክ ችግር በየሁለት ቀኑ ነው እንዴ የሚከሰተው? ወይስ ችግሩ ራሱ በዕቅድ ነው የሚሠራው? ለመሆኑ የት ጋ ነው ችግሩ የሚከሰተው? ለምን እቅጩ አይነገረንም? በአንዳንድ ትራንስፎርመሮች፣ በአንዳንድ ማስተላለፊያዎች ማለት ምን ማለት ነው? የቱ ጋ ሲበላሽ ነው አንዳንድ የሚባለው?
እነዚህስ በሚትሮሎጂ አንዳንድ ቦታዎች እየተበላ የሚነገርላቸው፤ እነዚህ እንኳን ዝናብ ያገኛሉ የሚባሉት፡፡ የት ናቸው ያሉት፡፡ ይኼ አንዳንድ የሚለውስ እንደ ክርስትና ስም የሜትሮሎጂ ስማቸው ነው እንዴ?
የኢትዮጵያን ዕድገት ለማቀላጠፍ አንዱ ወሳኝ ተግባር ባለ ሥልጣናት እና ጋዜጠኞች ሦስት ቃላትን እንዳይጠቀሙ ማገድ ነው፡፡ «አንዳንድ፣ አበረታች እና አፈጻጸም»፡፡ እነዚህ የት እንዳሉ የማይታወቁ የዕድገት ዕንቅፋቶች ናቸው፡፡ አንዳንድ ስንት ነው? የት ነው? እነማንን ነው? አይታወቅም፡፡ አበረታች ስንት ነው? እስከየት ነው? የበረታውስ ማነው? መልስ የለም፡፡ አፈጻጸም የት ነው? ማን ጋ ነው? አይታወቅም፡፡
ወዳጆቻችሁ ሲያወሩስ ሰምታችሁ አታውቁም «ብዙ ሰው እኮ እንዲህ እያለ ነው፣ ብዙ ሰው እኮ እንዲህ እያደረገ ነው፣ ሕዝቡኮ እንዲህ አለ፣» ሲሉ አልሰማችሁም? እስኪ እንደ ዘበርጋ የት? በሏቸው፡፡ ለመሆኑ ይኼ ሕዝብ የሚባው አካል የት ነው ያለው? መቼ ነው ተሰብስቦ ወይንም ተመካክሮ የወሰነው? ሕዝብ የሚባል አካል ቢኖር ኖሮ ስንቶቹ ተነሥተው በሕዝብ ስም ሲምሉ፣ ሲያሥሩ፣ ሲገድሉ፣ ሲበሉ፣ ሲጠጡ፣ ሀብት ሲያካብቱ፣ ሲነግሡ፣ ሲወጡ፣ ሲወርዱ፣ ራሱ ሕዝብ የሚባለው እውነቱን ይነግረን አልነበረም?
አሁን ሰሞኑን የመምህራን ደመወዝ እያወዛገበ ነው፡፡ መንግሥት ደመወዝ ጨምሬያለሁ፤ የጠየቁትን አሟልቻለሁ ይላል፡፡ መምህራኑ ደግሞ የተሰጠን እራት ሳይሆን ዳረጎት ነው፡፡ ድሮ ሕፃን ሆነን
«የታረደው አምሳ ዶሮ
የደረሰኝ አንድ ዶሮ» እንደምንለው ነው፡፡ እኛ ያልቻልንበት
«ያቺን ይዤ ወደ ጓሮ» የሚለውን ነው ይላሉ፡፡ ምናልባትምኮ ጥያቄው የደመወዝ ጭማሪ ሳይሆን የዘበርጋ ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ የተጨመረው ብር የት ነው ያለው? የሚል፡፡
ለመምህሩ ደመወዝ ተጨመረ ተባለ፡፡ የቤት ኪራይ ጨመረ፡፡ ጤፍ ጨመረ፡፡ ምግብ ጨመረ፡፡ ሻሂ ጨመረ፡፡ ዳቦ ጨመረ፡፡ አሁን ጭማሪው የት ላይ ነው ያለው? ነው ጥያቄው፡፡ የተጨመረው ለአከራዩ ነው ለመምህሩ? ለባለ ሆቴሉ ነው ለመምህሩ? ለሱቅ ጫሹ ነው ለመምህሩ) ያቺ የመጣችው ገንዘብ የት ገባች? ወይስ ፔሮል ላይ ብቻ ነው የምትታየው?
ታዋቂው ተረበኛ ናስሩዲን መሬቱን ቆሞ ያሳርሳል አሉ ኢራኖች፡፡ በዚያ ቦታ በፈረስ እየሸመጠጠ አንድ አዳኝ መጣ፡፡
«ሆጃ» አለው አዳኙ፡፡ «አንበሳ ወደ ጫካ ሲገባ አይተዋል እንዴ?» ሲል ጠየቀው፡፡
ሆጃ ናስሩዲንም «በሚገባ» ሲል በኩራት መለሰለት፡፡
አዳኙ ፈረሱን ነቅንቆ ወደ ጫካው ሸመጠጠ፡፡
ከአራት ሰዓታት በኋላ አዳኙ ፈረሱን እየጎተተ በኀዘን ተመለሰ፡፡
«ምነው ሆጃ» አለው ናስሩዲንን፡፡
«ምን ሆንክ» አለው ናስረዱኒን፡፡
«አንበሳ ወደ ጫካ ሲገባ አይቻለሁ አላሉም» አዳኙ አንገቱን እየነቀነቀ ጠየቀው፡፡
«አዎ አይቻለሁ»
«እኔኮ ጫካውን ሙሉ ፈተሽኩ እንኳን አንበሳ ላገኝ የአንበሳ ዱካ እንኳን ለማየት አልቻልኮምኮ» አለው አዳኙ፡፡
«ልክ ነህ ልታገኘው አትችልም» አለው ናስሩዲን
«እንዴት ሆጃ»
«አንበሳውን ወደ ጫካ ሲገባ ያየሁትኮ እዚህ አይደለም»
«ታድያ የት ነው»
«ቱርክ ውስጥ በሚገኝ ጫካ ነዋ»
«ታድያ ለምን አለፉኝ?»
«አንተኮ አንበሳ ጫካ ውስጥ ሲገባ አይተሃል ወይ አልከኝ እንጂ፣ አንበሳ እዚህ ጫካ ሲገባ አይተሃል ወይ ብለህ አልጠየቅከኝም» አለው ሆጃ ናስሩዲን፡፡ አዳኙ እያዘነ ወደ መጣበት ሲሄድ ሆጃ ናስሩዲን ድምፁን ከፍ አድርጎ «ለወደፊቱ የት? ብለህ ሳትጠይቅ ወሬ ሰምተህ አትሩጥ» አለና መከረው፡፡
የዘበርጋ ጥያቄ የናስሩዲንም ጥያቄ ነው፡፡ የኛም፡፡
© ይህ ጽሑፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ የወጣ ነው፡፡ በሌላ መሰል ኅትመት ባይወጣይመረጣል፡፡