በአዲስ አበባ ‘ያለ ጉቦ ምንም መስራት የማንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል’ ሲሉ ዜጎች አማረሩ

በአዲስ አበባ ከተማ ሙስና እጅግ መስፋፋቱን ሰሞኑን ከመዲናይቱ የደረሰን ዘገባ አሳይቷል።

አንዳንድ ነዋሪዎች “ጉቦ ሳይሰጥ እርምጃ እንኳ መራመድ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” ሲሉ ለግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ስሞታቸውን አሰምተዋል። ዘጋቢያችን ያናገራቸውና በቤቶቻቸው ላይ ተጨማሪ ግንባታ ለመስራት ፈልገው ፈቃድ ለመጠየቅ ወደሚመለከተው የአስተዳደር አካል የሄዱ ዜጎች፤ በግልጽ ጉቦ እንደተጠየቁ ተናግረዋል።

የወያኔ ሹመኞች የሆኑት የአስተዳደር ሰራተኞች እርስበርስ ተቧድነው እንደሚሰሩ እና ያገኙትን ጉቦም እንደሚካፈሉ ለማወቅ ተችሏል። የደረሰባቸውን ግፍ ለዘጋቢያችን ካካፈሉት ውስጥ አንዱ ግለሰብ፣ አንድ የአስተዳደር ሰራተኛ የሆነ የወያኔ ካድሬ፣ “ይቺማ ለማን ተሰጥታ ለማን ትተርፋለች” በማለት የተሰጠው ጉቦ ትንሽ መሆኑን እና ለሱና ለተባባሪዎቹ እንደማይበቃ በግልጽ አስረድቷል።

የወያኔ አገዛዝ በተለይም በ1997ቱ ምርጫ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አባላትን ለማግበስበስ ሲል ከተጠቀማቸው ስልቶች ውስጥ አንዱ ሙስናን መፍቀድ እና ማበረታታት እንደሆነ ይታወቃል።