ይድረስ ለመስፍን ባሪያው – መለስንና ጳውሎስን ለምን ለየሃቸው? በይሄይስ አእምሮ

ይህ ጦማር የተጻፈበት ዕለት 14/8/2004ዓ.ም፡፡ ‹ኢትዮፒካሊንክ› በሚሰኝ አዝናኝ ፕሮግራሙ ይበልጥ የሚታወቅ ኤፌ’ም 98.1 እሚባል ሬዲዮ አለ – አዲስ አበባ፡፡ በሬዲዮ ፋና ሥር በፕሮፓጋንዳው ግምባር ተኮልኩለው በወያኔው በሬ ወለደ ቱሪናፋና በግድባዊው ዘመነኛ ፈሊጥ የላም አለኝ በሰማይ ቀቢፀ ተስፋ ሕዝቡን እያደነዘዙ የኢሕአዲግን ዕድሜ ለመቀጠል ሌት ከቀን ከሚባዝኑ ኃይሎች ጎን ስለሚመደብ ባለቤትነቱ ሙሉ በሙሉ የወያኔ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ የዚህን ፕሮግራም ‹ውስጥ ዐዋቂዎች› የገመና ዜና አልፎ አልፎ ስለምከታተል የትናንትናውን ሳልተኛ ጠብቄ ሰማሁት፤ አጀብ እሚያሰኝ ጉድ ነው፡፡ ሀገር አለን የምትሉ እንደሌላችሁ ላርዳችሁና ጊዜ ካላችሁ ቢያንስ ለሦስት ቀናት ሀዘን ተቀመጡ፡፡ ቀጠልኩ፡-

ቀደም ሲል ያደመጥኩት ያዘጋጆቹ አጓጊ ማስታወቂያ አንድ ወጣት አግቢ ሦስት የተለዩ ሽማግሌዎችን በዓይነቱም በይዘቱም የተለዬ ስጦታ አሲዞ ሊያገባት ወደሚፈልጋት ‹ኮረዳ› መላኩን ነበር፡፡ ለመሆኑ ይህ ወጣት ተሞሻሪ ማን ይሆን? ይህ የሀገር ተስፋ ወጣት በዚህች ጎስቋላ የድሆች መኖሪያና የሲዖል አብነት ሀገር ውስጥ ምን ዓይነት ሪከርድ ሊያስመዘግብ ተነሳስቶ ይሆን? ይህን ተነሳሽነቱንስ እውን ለማድረግ ምን አነሳሳው? ለሽምግልናውስ ለሰማይና ለምድር የከበዱ የተባሉት አማጭ ረማጮች እነማን ይሆኑ? እኔ ይሄይስ፣ እመት ኑሮ ወገቧን አፈንድዳብኝ ማለትም አዙራብኝ በቀን ሁለቴ እንኳን ራሴንና ቤተሰቤን መመገብ እያቃተኝ -ጤፍ እንጀራም ባቅሙ የወረት እየሆነብኝ በመጣበት ክፉ ዘመን ማለት ነው – በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ የመሞት ሂደት ላይ እያለሁ ይህ የሀገር ዕድገት አለኝታ ወጣት ምን ዓይነት ልዩ ጥሎሽ ልኮ ይሆን? ከየትስ አምጥቶት? በግሩም ደመወዝ መኖር የተሳነኝ እኔ ምሥኪኑ ኢትዮጵያዊ ለዚህ ወጣት ጥሎሽ ያበረከትኩት ድርሻ ምን ያህል ይሆን? በሚሉ ልብ አንጠልጣይ ጥያቄዎች ራሴን ከብቤ መከታተሌን ቀጠልኩ፤ ሰዓቱ ደረሰ፤ ጉዱን በዝርዝር ሰማሁ፡፡ ላልሰማችሁ ላካፍላችሁ፡-

የወጣት ነጋዴው(ልማታዊ ኢንቬስተር ልበለው?) ስም መስፍን መገርሣ ይባላል፡፡ በአባቱ ስም ዙሪያ ብዙም ማሰብ አልፈልግም፤ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል፡፡ ጓደኞቹ በቁልምጫ ‹መስፍን ባሪያው፣ ባርችዬ፣ ባርቾ፣…›ይሉታል አሉ፡፡ ይሄ ልጅ ጥቁር መሆን አለበት እንግዲህ፡፡ ዕድሜው በጣም ወጣት ነው – ለግላጋ፡፡ የሀብቱ ብዛት የሰማይ ከዋክብትንና የምድር አሸዋን እንደመቁጠር ነው፡፡ ለሽምግልና የላካቸው ሰዎች 1ኛ ክልሱ ሼህ አላሙዲን 2ኛ የሼሁ አንጋች የሆኑት አብነት ገ/መስቀል 3ኛ ሙሉጌታ ኃይለ ኪሮስ ናቸው(እስካሁን እኔ የማላውቃቸው ሰው)፡፡ እዚህ ላይ ይህ ወጣት የረሳቸው ሌሎች ታዋቂና የሽምግልና ሂደቱም እንዳያዳግም ሊያደርጉ የሚችሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ያልጋበዛቸው መሆኑን ልብ ብያለሁ፡፡ እነሱም ብፁዕ አባታችን አባ ጳውሎስና የጥፋት ማለትም የልማት መሪያችን አቶ መለስ ዚና ናቸው፡፡(በነገራችን ላይ ዚና ማለት ‹ኃጢያት› ማለት ነው) ‹የልጃችሁን እጅ ለልጃችን ስጡን› ተብሎ ‹ሽማግሌዎች› የተላከባቸው ቤተሰቦች የወደፊቷ ሙሽራ ሃና ሽፈራው የተባለች ቤተሰቦች ናቸው – የታደሉ፡፡ ይህች ‹ኮረዳ› የተዋጣላት ነጋዴና ኢንቬስተር ናት – በፊናዋ፡፡ ‹ቢጽ ለቢጽ ይትራድዑ› ይላል የግዕዙ ብሂል፡፡ በስኬት ላይ ስኬት እየጨመረች መጥታ በሀብት የከበረች ሴት ናት – ያርግላት፡፡ ሽማግሌዎቹ ተሸክመውት የሄዱት ስጦታ የጥቅሉ ርዝማኔ ብቻ 1.5 ሜትር ሲሆን ስጦታው የተጠቀለለበት ወረቀት ራሱ ሌላ የስጦታ ወረቀት መጠቅለያ የሚያስፈልገው በወርቅ ቅብ ያሸበረቀ ውድ መሸፈኛ ነው – ከአላጋጮቹ የሬዲዮ ጋዜጠኞች አንደበት ከሰማሁት የገባኝን ያህል ለመግለጽ፡፡ በዚህ ስጦታ ውስጥ በጡቶች መካከል ደረት ላይ ብቻ ተንጠልጥሎ የሚቀር ሳይሆን ከእምብርትም ወረድ ብሎ ወደ ሙሽሪት እግሮች መባቀያ ግድም የሚዘልቅና ለማዕከላዊ ዕንቁ የሰውነቷ ክፍል የክብር ሰላምታ ሊያቀርብ የሚቃጣው ከአልማዝ የተሠራ ሐብል(ውስጥ ዐዋቂዎቹ ዲያመንድ ነው ያሉት)፣ የአልማዝ የጆሮና የጣት ቀለበቶች (ምናልባትም የእግር አልቦ) በዋናነት ተካትተዋል፤ ፐ! በሕዝብ ገንዘብ የተንፈላሰሰች ሌላኛዋ ሙሽሪት! አንዱ ለአንዱ በሚኖርባት ምድር እኔም ለቁም ነገር በቅቼ ሳልወድ በግዴ በተነጠቅሁት ገንዘብ የምትዳር በጣም የታደለች ‹ሳዱላ›፡፡ ወደ ትንተናየ ላምራ – ጊዜ የለም! ጊዜም ባቅሙ የጊዜን መበሻቀጥ ታዝቦ በተለመደው ተገቢ ፍጥነት መጓዙ ስላሰለቸው አሳቻ ሥፍራና ጊዜ እየመረጠ ብቻ ሳይሆን በገሃድ መክነፉን ተያይዞታል፡፡ ይሄውና ሚያዝያ እንኳን ከመግባቱ ወሩ ተጋመሰ አይደል? የ2004 ዓመተ ፍዳ መስከረም ወር ገና ከመባቱ ዓመቱስ ይሄውና ሊያልቅ ምን ቀረው? እሰይ! ይሁን፡፡ ኖረንስ መች አማረብንና? ውድ ወንድሜ ወይም እህቴ ጊዜ ሆይ! እባክህን/እባክሽን በደንብ ሩጥ/ጪ፡፡ ለነመስፍን ግን ቀስስስ…በሉላቸው፡፡ የሰበሰቡትን እስኪበሉ ሺህ ዓመትም ከዚያም በላይ ቢሆን ሰፊ ጊዜ ስጧቸው፡፡ የሰው ደምና ላብ ከመዓር ወሦከር ይጥማልና ሀብታቸውን አስጨርሱዋቸው፡፡ የነፍሳቸው ነገር ገና ስለሚያጠያይቅ በይደር ይቆይ፡፡ ለአሁኑ ሥጋቸውን ይመቸው፡፡

መስፍን ማንም ይሁን ማን በማንነቱ ዙሪያ ሃሳቡ አይበላኝም ብያለሁ፡፡ እናም የመገርሣም ልጅ ይሁን የሐጎስ ለጊዜው እምብዝም አያሳስብም፡፡ ነገር ግን እንዴት ከበረ? ገና በሃያዎቹ መጨረሻ ወይም በሠላሳዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ጉብል እንዲህ የናጠጠ ሀብታም መሆን የቻለበት ምሥጢር ምንድን ነው? ለጥሎሽ ብቻ ይህን ያህል በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰ ሠርጉ ምን ይመስል ይሆን? እንዲህ ዓይነት ወጪ ሊያውም ገና ከቀለበት ሥነ ሥርዓት አስቀድሞ በአውሮፓና አሜሪካ ቢታይ ስለሰውዬው ማንነትና የገቢ ምንጭ ትክክለኝነት መንግሥታትና ሚዲያዎች ምን ይሉ ነበር? እነአላሙዲንን ለሽምግልና መላኩስ ምን ይሉት ነገር ነው? ‹ከሀብቴ ብዛት የተነሳ በዓለም የማላዝዘውና የማላሽከረክረው የለም› ለማለት ይሆን? ‹ይሄን ቱጃር ሽማግሌ ልኬ ቤተሰቦችሽን አስደነግጣቸዋለሁ!› ብሎ ዝቶስ ይሆን? እሚገርም ነው፡፡ ለሽምግልናው፣ አይደለም አላሙዲንን ቢል ጌትስንና ሜክሲኮኣዊውን የዓለም ቁጥር አንድ ሀብታም ካርሎስ ስሊምን ይላክ፤ ምን አገባኝ? ወደሚያገባኝ ጉዳይ ልሂድ፡፡
በሠፈራችን አንድ ሀብታም አለ፡፡ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከአንድ አነስተኛ ሆቴል ተነስቶ ሚሊዮኔር መሆኑን የታዛብን ሰዎች በብዙ ነገር እናማዋለን፤ በጠንቋይ ቤት አማኝነቱም ራሴን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ያነሱታል፤ የሰውን አደራ በመብላትና ጓደኛን በመክዳት ረገድም ዘወትር እንደተቦጨቀ ነው፡፡ ጓደኛሞች በዚህ ሰዉዬ ሕንፃዎች አጠገብ ስናልፍ ‹የዚያችኛዋ ክፍል የዳረኛዋ ግድግዳ በኔ ገንዘብ የተሠራች ናት› እያልን እንሳሳቃለን፡፡ መኪናውንም ስናይ ‹ይቺኛዋ ጎማ የኔ ገንዘብ ናት› እንላለን፡፡ ይህን የምንለው የተደገመብን ይመስል ከእርሱ ቡና ቤት ሳንወጣ ገንዘባችንን እዚያው አስረክበን እኛ በድህነት ስለቀረንና እርሱ ግን የኛን ያሳደግነውን ዜጎች መፈጠር እስኪረሳና ሰላምታውም ያንገት በላይና የይስሙላ ዓይነት እስኪሆን ሽቅብ ስለተወነጨፈ ነው፡፡ ቅናት ቢጤም ሾጥ ሳያደርገን አልቀረም፡፡ ያስጠንቁልም ያስተብትብም እሱ እንደሆነ አሁን ቢጠሩት የማይሰማ ቀብራራ (ቀጭን)ጌታ ሆኗል፡፡ መጨረሻውን ያሳምረው ፤ኧረ የሰማዩን ያሳምርለት ይሄኛውንስ ጨርሶታል፡፡ ለምን ይዋሻል? ሞቷል፡፡

ሰው ሠርቶ ሲያልፍለት ደስ ይላል፡፡ ሠርተው የሚያልፍላቸውን እናወድሳቸዋለን፤ በመንፈስ እንቀናባቸዋለን፡፡ በአርአያነትም ልንከተላቸው እንመኛለን፡፡ ‹እንደነገሌ ሁኑ› እያልንም ሰውን ለመምከር በዋቢነት እንጠቀምባቸዋለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ሰው ምንም ሳይሠራ በሚሠሩት ግን በቅናት እየተብተከተከ ራሱ የማይሠራና ሌላውን የማያሠራ አለ፡፡ አንዳንዱ ቢሠራም ቀን የሠራትን ማታ እያወደመ ከኑሮው ፈቀቅ እማይል ነገር ግን ዕድሉን የሚያማርር አለ፡፡ በሌሎች ስኬት የሚያር የሚተክን ቢያገኝም እጁ ገንዘብ የማይቋጥር ወይም የሚጠበቅበትን ያህል በትጋት የማይሠራ ሠነፍና ገንዘብ አባካኝ አለ፡፡ አንዳንዱ ከመሥራት ይልቅ በልመናና በምፅዋት እንዲያልፍለት የሚጠብቅ አለ፡፡ አንዳንዱ ውስጡን ፈትሾ ሀብትና ኑሮ የሚያገኝበትን ብልሃት ከመፈለግ ይልቅ ዝም ብሎ ተቀምጦ ፈጣሪን የሚጨቀጭቅ፣ ዘመድ ወዳጅን የሚያስቸግር የሃሳብም የገንዘብም ድሃ የሆነ አለ፡፡ የሰው ዓይነቱ ብዙና ብዙ ነው፡፡ ይህን መሰሉን የታወቀ ነገር ለጊዜው በይደር እናስቀምጠውና በሰው ላብ በሚከብሩ ‹ሰዎች› ላይ ጥቂት ልበል፡፡ ሰው በጥረቱና በልፋቱ ከመሰል ወገኖቹ ጋር እየተያየና ዕድገቱን ከሌሎች ጋር እያመዛዘነ በህገ ልቦናና በህገ መንግሥት ተወስኖ በአግባቡ ሲያድግ ጥሩና የሚገባ መሆኑን በጨረፍታ አይተናል፡፡ ከዚህ እውነት በማፈንገጥ በሰዎች ሕይወት እየተረማመደና ሰዎችን በማይታይ ጩቤ እያረደ በደም ባሕር ዋኝቶ በአንድ አዳር ከከበረ ግን ይህ ሰው ሰው ሳይሆን ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ በቃ ሰይጣን ብቻ! በሞት ተነጥቆ ሳይሆን በሕይወት እያለ ሰው ሰው መሆን ሲያቆም አንድም እንደሌሎች እንስሳት በባሕርያዊ እንቅስቃሴዎቹ ብቻ የሚታዘዝ እንስሳ ይሆናል አሊያም ሰይጣን ይሆናል፡፡ በመካከል ሌላ አማራጭ የለም፡፡ በዚህም መሠረት በመካከላችን የሚገኙ አላሙዲንንና የርኩስ መንፈስ ልጁን መስፍንን የመሳሰሉ ‹ሰዎች› በሰው አምሳል ይንቀሳቀሱ እንጂ በግብራቸው የለየላቸው የአጋንንት መንግሥት ወራሾች ናቸው – እነሱም ሰብኣዊ አጋንንት፡፡ አለቀ፤ደቀቀ፡፡ ጊዜና ቦታ የሚፈጁ ማስረጃዎችን አላቀርብም፡፡

ወንድሜ መስፍን – ልጄ ልበው እንዲያውም (ከዕድሜ አንጻር ነው ታዲያ!) – ልጄ መስፍን ሥራ ሠርቶ እንዳላለፈለት በአካላዊው ዐይኔ አይቼ ሳላውቀው በመንፈሳዊው ዐይኔ በምናቤ ተመልክቼ በሚገባ አውቀዋለሁ፡፡ እርሱ በሚዲያ ስለተገለጠ እንጂ በየአካባቢያችን ብዙ መስፍኖችና ብዙ አላሙዲኖች አሉ፡፡ ሚዲያ የማያውቃቸው ሰይጣኖች ሞልተውናል፡፡ በምድር በተለይ በአሁኑ ወቅት ንጉሠ ነገሥቱ ገንዘብ ነው፤ የገንዘብ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ደግሞ ከሰባተኛው ሰማይ ወደ ምድር የተወረወረው ፊልድ ማርሻል ዲያቢሎስ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፊ. ማርሻል ዲያቢሎስ ከነሠራዊቱ ከትሞ እሚገኘው በኢትዮጵያ ውስጥ ስለመሆኑ ደግሞ እማኝ መጥቀስ ሳያስፈልገን ከአጠቃላዩ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች የምንረዳው ፀሐይ ያርገበገበው ሃቅ ነው፡፡ በዚህች ኢትዮጵያ ከብረህ ለመገኘት አንድ ነገር ብቻ ሁን – የሰይጣን አምልኮትና የወያኔ ተከታይ ጭፍራ! በቃ፡፡ ከዚያ በላይ ብዙም አይጠበቅብህም፡፡ ምናልባት ገንዘብ መቁጠር እንድትችል መጠነኛ የሂሳብ ዕውቀት እንዲኖርህ ያስፈልግ ይሆናል – ሊያውም ያን ተግባር የሚያቀለጣጥፍልህ አጋዥ ከሌለህ፡፡ በተረፈ የአስተዋይነትና የጥበብ ክሂሎች በፍጹም እንዲኖርህ አይገባም፤በወያኔም ሆነ በሰይጣን አትመከርምም፡፡ በተንኮል የተራቀቀ ሰይጣናዊ ዕውቀት እንዲኖራቸው የሚፈለጉት በአመራር ላይ ያሉ ወያኔዎችና የሃይማኖቱ ዘርፍ ብዔል ዘቡላዊ ኤታ ማዦር ሹሞች ብቻ ናቸው እንጂ ተራው የሉሲፈር ሠራዊት አባል እንዲሆን የሚጠበቀው ቢበዛ ስሙን መጻፍ የሚችል ፍጹም ማይም ነው፡፡፡ የወያኔ ሎሌ ፌዴራል ወታደርም ይሁን ፖሊስ፣ ካድሬም ይሁን ነጋዴ፣ ‹ምሁር›ም ይሁን የቤተ አምልኮት አገልጋይ፣ የወጣት ሊግም ይሁን የሴቶች ክንፍ፣ ተለጣፊም ይሁን ተደራቢ የብሔር/ብሔረስበ ድርጅትና ንቅናቄ(ዲዶች) … ሁሉም እሚጠበቅበት እንዲገድል ሲታዘዝ ‹እነማንንና ስንት?›፣ እንዲያስርና እንዲያሰቃይ ሲታዘዝ ‹የትኞቹንና እስከምን የእስርና የስቃይ ደረጃ?›፣ የሕዝብን ኑሮ እንዲያስወድድ ሲታዘዝ ‹በስንት ፐርሰንት ዋጋ ልጨምር ጌታየ?› ብሎ ጃዝ ሲሉት የሚሰማራ አንጎል እሚባል ያልተፈጠረበት ለሆዱ ብቻ ያደረ ድፍን ቅል ነው ፡፡ መልካም ዕውቀትን ባወቅህ ጊዜ ከዚያ መንጋ ትባረራለህ – ድሃ ነበርክና ወደድህነትህ ሂድ ትባላለህ፤ ሊያውም ይሄም ከቀናህ፡፡ አለበለዚያ ‹የማንን ምሥጢር አውቀህ ወዴት ትሄዳለህ› ከሚል ለአጋንንቱ አለቃ ለሊቃነ ሣጥናኤል ብፃይ መለስ ወጳውሎስ ከማሁ ወአላሙዲን ጭዳ የመሆን ዕጣም ሊደርስህ ይችላል፡፡ ወደተግባዊ ትንተና እንውረድ፡፡

አንድ ሰው ‹ይህ ሰው እንዲህ ነው› ለማለት የሚያስችሉን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የሚነገሩም የማይነገሩም፡፡ በቃላት ሊገለጹም ላይገለጹም የሚችሉ፡፡ ‹ጣፋጭ ፍሬ ከዛፉ ላይ እያለ ይታወቃል›፡፡ጥሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ነባር ብሂል፡፡ ጥሬን ከብስል ፍሬን ከገለባ ለመየት ዕድሜና አመዛዛኝ አስተውሎትም በጣም ይረዳሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ለመስፍን የተላኩለት ሰዎች የሰይጣን ባሪያዎች፣ ገንዘብን አምላኪዎች፣ የወሲብ ዳንኪራ ረጋጮች፣ በሕዝብ ጫንቃ ካይ ተደላድለው የተቀመጡ ደም መጣጭ መዥገሮች፣ እንቅልፍ የማያስተኙ ኅሊናን ቦጥቧጭ ትኋኖች፣ የሀገርን ሀብትና ጥሪት አሟጣጭ ነቀዞች፣ ከወቅቱ ሰይጣናዊ መንግሥት ጋር ተሻርከው ሕዝብን የሚግጡ ፒራናዎች ናቸው፡፡ ግም ለግም ተያይዞ ማዝገሙ ትናንት የተፈጠረ አይደለምና ሁሉም አንድ ናቸው፡፡ ንጹሕ ከቆሻሻ ኅብረት የለውም፡፡ ለዚህ ምንም ጥርጥር አይግባን – አላሙዲን የሰይጣን አምላኪ መሆኑን እንዳብራራለት ከፈለገ በሚሰግድለት የአጋንንት መንፈስ በኩል – አይቻለውም እንጂ ከተቻለው – አፈላልጎ ያስጠራኝና ያነጋግረኝ፡፡ አጠገቡ አለሁ፡፡ እናም እኔ እነሆ እንዲህ እላለሁ – መለስ፣ አባቱና አጎቱ እሚባለው ጳውሎስ፣ እንዲሁም አላሙዲን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከዋናው ሠራዊተ አጋንንት አዛዥ ከሉሲፈር መንደር የተላኩ የወቅቱ ገዢዎቻችን ናቸው – ናቸው በቃ፤ ይህን ታሪካዊ መጥፎ አጋጣሚ ማመን አለማመናችን በንግሥና ግዛታቸው የሚያሳድረው ተፅዕኖ በእስካሁኑ አካሄድ ከሆነ አንዳችም የለም፡፡ በእግረ መንገድ ከእኛም መካከል ብዙዎቻችን እያወቅንም ሆነ በመታለልና ሳናውቅ የአምልኮተ ሰይጣን ሰለባዎች የሆንን ወገኖች መኖራችንንም ልንዘነጋ አይገባንም፡፡ ሚዛኑን እየጠበቀ የአጋንንት ግዛት እንዲቀጥል – አጋንንት እንዳሻቸው እንዲጨፍሩብን እያደረገ ያለው ነገር ይህ እኛም ልናስተካክለው ያልቻልነው የሁለት ጌቶች ተገዢነታችን ነው – ለፈጣሪና ለሰይጣን፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ ፍጹማዊ የልብ ምርኮኝነትን ይፈልጋል፡፡ በጥርጣሬና በይሆናል አይሆንም የሚያወላውልን ልብ አይሻም፤ ጧት ቤተ ክርስቲያን፣ ከሰዓት አዶ ከብሬ ቤት፣ አመሻሽ ላይ ቢሾፍቱ አካባቢ፣ ውድቅት ላይ ጥቁር አህያ ጀርባ፣ ንጋት ላይ መጣፍ ገላጭ ቤት መገኘትን ፈጣሪ ይጠላል፤ ይፀየፋልም፡፡ እናም በሰይጣኖች መካከል ‹ጣልቃ ላለመግባት› ይጠነቀቃል፤ አይፈረድበትምም፡፡ አንድ ሰው የገደለና አንድ ሚሊዮን ሰው የገደለ ልዩነቱ ምንድን ነው? ቤተ መንግሥት ውስጥ ሆኖ ሰውን መሳደብና ከቤተ መንግሥት ውጪ ሰውን መሳደብ ልዩነቱ ምንድን ነው? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆኖ ኃጢያትን ማድረግና ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ሆኖ መሞሰን ልዩነቱ ምንድን ነው? ልዩነቱ የቅርጽ ነው ወይንስ የይዘት? ‹በጓደኛህ ዐይን ውስጥ ያለውን ትንሽ ጉድፍ ለማውጣት ከመሞከርህ በፊት በራስህ ዐይን ውስጥ የተጋደመውን ዕርፍ እሚያህል ጉድፍ አውጣ፡፡› ፐ! ምን ዓይነት ግሩም አባባል ነው፡፡ የለም፣ ክርስቶስ አሁን ነበር መፈጠር የነበረበት፡፡ … ስለሆነም ዘንድሮ መቼም ጥሩ ምክርን እሚቀበል ከስንት አንድ ነው – ምክሬን ላንሻፍና ላስቀምጥ፡- በተያያዝነው የጥፋት መንገድ ለመንጎድ እኛም በያዝነው መንገድ እንቀጥል፤ ፈጣሪም ጥንቃቄውን ይቀጥል – እንዴ ለማን ያዳላል? እነሱም እኮ ልጆቹ ናቸው፡፡ ማን የተጣለ ማንስ ያልተጣለ መሆኑን የምናውቅበት ብልሃት የቱ ነው? በምግባራችን ሁለታችንም የጠፋን ከሆን ዘንድ በደንብ ጠፉ የምንላቸው ወገኖች በደንብ ጠፋን የማንለውን በምን እንደሚበልጡን ወይም እንደምንበልጣቸው እንዴት እናውቃለን? (ይቺን ፍልስምና በየግላችን እናብሰልስላት፤ ‹ቆሞ ያለ እሚመስለው ይጠንቀቅ›፡፡) እነአዜብና አላሙዲንም ዲያቢሎሳቸውን በሙሉ ልባቸው ማስደሰታቸውን ይቀጥሉ – እስከ አንዲት ቀን ድረስ! ያቺ ቀን ስትደርስ ግን ሁላችንም የየድርሻችንን እንከፈላለን፡፡ ይህንን በርግጠኝነት እናውቃለን፡- እነመለስ ለሰይጣን የሚገዙት በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ተመስጠኣቸው ነው፡፡ የሚፈልገውን ዕለታዊ፣ ሣምንታዊ፣ ወርኃዊና ዓመታዊ የደምና የሶዶም ገሞራዊ ግብር እየከፈሉ ነው ጌታቸውን እያስደሰቱ ያሉት፡፡ በነሱ ይኮራል፡፡ ከሚገባው በላይ ያኮሩታል፡፡ አደግድገው ነው የቆሙለት(ዝጉብኞቻቸውንና የራቁት ቤት ጭፈራ ቤቶቻቸውን አስታውሱ – ከመጠጡና ሀሽሹ ጭምር)፡፡ ለግብር እሚሆን የሰው ጭዳ ደግሞ የጭቁን ኢትዮጵያውያት ማሕጸን ውሎ ይግባ፤ ድሃ ሞልቷል፡፡ ጦርነት እየፈጠሩና የፖለቲካውን ንፋስ መዘውር አለቃቸው ደም በጠማው ቁጥር በምርቃና ወጀብ እየቀሰቀሱ ድሆችን በድራማ ጦርነት እየማገዱ የሕዝብ አለኝታዎችንም በሰበብ አስባብ በማሰርና በማንገላታት በመግደልም ጭምር የሕዝብን የነጻነት ትግል እያደናቀፉ የጌታቸውን የደም ጥማት ያረካሉ፡፡ … ይህን ማን ያጣዋል?

ለማንኛውም መስፍን እንኳን ደስ ያለህ፤ ልትኮራ ይገባሃል፡፡ አባትህን ዲያቢሎስን አኮራኸው፤ እርሱም አኮራህ፡፡ ሮጠህ ሳትጠግብ ገና በጭቅላነት የእምቦቀቅላ ዕድሜህ እኔ በሽምግልና ዕድሜየ መልኩን በቲቪም አይቼ እማላውቀውን አልማዝ ገዢና ሸላሚ ሀብታም ሆንክ – ምንም እንኳን ገንዘቡን ከኔው ቀምተህ ለቁም ነገር ሳይሆን ለታይታና ለጉራ ብታውለውም አሁን የኛን ገንዘብ የት ልጣለው እያልህ በገንዘብ ብዛት አእምሮህን የሳትክ ‹ሀብታም› ነህ፡፡ በዓለም ከታወቀ ሴቴኒስት(የቤተ ሰይጣን አምላኪ) ጎን ያስቀመጠህና እንዲያውም ጀምኣውን ይግረመው ብለህ ባላጣኸው ሰው ይህን ጀፈጀፍ እምቢ አላረጅም ሰውዬ ለሽምግልና በመላክህ አዲስ ሪከርድ ተይዞልሃልና አሁንም ደስታህ እጥፍ ድርብ ይሁን፡፡ ምናባቱ ሊያልፍ ዓለም! እንዲህ ነው ‹ወጣት የነብር ጣት› ማለት፡፡ ይበልጥ በርታ፡፡ አሁንም የቀረችንን ጥቂት አንጡራ ሀብት በተለያየ መንገድ ዝረፍና እንደዴቪስ ቲቶ በሕዋ ቱሪስትነት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሰው ሁንልን፡፡ እኛ ግን የአንተን ድህነትና ርሃብ ድንቁርናና እርዛት ከራሳችን ጋር ደርበን በችጋርና በችግር አለንጋ እንገረፍልሃለን፤ በርሱ በኩል አለንልህ ሥጋት አይደርብህ – ላንተና ለመሰሎችህ ጥቂት ራስ ቅሎች ያልሆን ለማን ልንሆን ነው? ጌቶችህ እነመለስና ሰሞኑን አንተም በተራህ ጌታው የሆንከው አላሙዲንስ ያለርህራሄ እየዘበጡን ይሄውና 21 ዓመት ሆናቸው አይደለም? አንተ ብቻ ማድረግ ያለብህ ከታላላቅ የአጋንንት ሠራዊት ጋር መጨፈርና ማስጨፈር ማጨፋፈር ነው፤ ማታ ማታ ደግሞ በነዚያ በምናውቃቸው ቤቶች እየተነሳ ለሚጨፍር ተስፈኛ ሁሉ ብር ሳይሆን መቶ መቶውን ዶላር እያነሳህ እንደጭቃ ለጥፍላቸው፤ እኛ አንለቅብህ እንጂ ገንዘቡ እኛ እስካለን የት ታጣው ብለህ? ሙሽራህን ግን አደራህን ጠንቀቅ በል፡፡ በአጋንንት ቤት ሞራልና ሃይማኖት ብሎ ነገር ስለሌለ ቢያንስ የራሴ የምትለው መሰልህን ልጅ እስክትወልድልህ ድረስ ሙሽራህን ለማንም አታሳይ – ሞራለቢስነቱ ያው ያንተም ባሕርይ በመሆኑ ለነገሩ ያንተንም ልጅ በሌሎች ቤት ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ለዚህ ጉዳይ የነእንትናን ታሪክ ላስታውስህ እችል ነበር፡፡ ሀብታሞችን በደንብ አውቃቸዋለሁ፡፡ ማን ከማን ቤት እንደሚያመሽና እንደሚያድር፣ ማንኛዋ ከማንኛው እንደምትወልድ አይታወቅም፡፡ እንደከብት ናቸው፡፡ ከጠገቡ ከማንም ጋር ቢጋደሙ ግድ የላቸውም፡፡ ስብና ሞራ ኅሊናቸውን ስለሚጋርደው በርግጥም በስሪያ ወቅትም ይሁን በሌላ ጊዜ ከብትና እንደነዱሽ ናቸው፡፡ ሁሎቹም ባይሆኑ ብዙዎቹ፡፡ ምግብና መጠጥ ያደነዘዘው ማይም ጭንቅላት በአግባቡ ማሰብ አይችልም፡፡ ያቆማል፡፡ ማሰብ እሚጀምረው ከሀንጎቨሩ ሲወጣ ሲሆን እሚያስበውም ስለገንዘቡ ነው፡፡ ማሰብ ቢችሉማ ኑሮ ከ30 አይበልጡም እሚባሉቱ ልማታዊ ነጋዴዎች በስልክ እየተመሳጠሩ ሕይወታችንን እንዲህ መቅኖ አሳጥተው እነሱ እንዲህ እላያችን ላይ ባልተምንአሉ ነበር፡፡ ወጣት መስፍን የዝንጀሮው ማኅበረሰብ አባልነትህን ገና በጧቱ አረጋግጠሃልና ስለነፍስህ አታስብ፡፡ …

አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ – የጉድ ከተማና ሀገር፡፡ ሀብታም ሆኖ እምታዩት ድፍን ወያኔያዊ ወጣት ነው – ወያኔያዊ በዘርም – በተጋቦትም – በዓላማ አንድነትም፡፡ ገና የሃያ አምስት ዓመቱ ወጣት እንትን ሃያና ሠላሳ ሃይገርባስና መቶ ሁለት መቶ ገልባጭ ስካኒያ ወይም የነዳጅ ቦቲ ባለቤት ሆኖ ሲያሰማራ ብታዩ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላላችሁ አይግረማችሁ፡፡ ገና ሠላሳን በቅጡ ያልደፈነ ለአቅመ ጭፈራ እንጂ ለአቅመ ማሰብ በወጉ ያልደረሰ ጉብል በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ሲያንከባልልና እኛን ብዙኃኑን በችግርና በሰቆቃ መሬት አጋድሞ ሲያንከባልለን ብታዩ አሁንም አይግረማቸሁ – ሀገሪቱ ኢትዮጵያ ናትና፡፡ ምድረ ወያኔና የወያኔ ጭፍራ ነጋዴ ሁሉ በፉክክር ከበርቴ ለመሆን በሚያደርገው ሩጫ ሕዝብ እንዴት በጠራራ ፀሐይ እየታረደ እንደሆነ ብታዩ ትገረማላቸሁ፡፡ የአሥር ብሩን ዕቃ ሦስት መቶ ብር የሚሸጥልኝ ሰው ጩቤ ባለመያዙ ብቻ አላረደኝም አልልም፡፡ ከብት ብቻ አይደለም እየታረደ ያለው በሀገራችን፡፡ የገንዘብ አወጣጣቸውን ስትመለከቱ ይበልጥ ትገረማላችሁ፡፡ በአንዳቸው ሠርግ ወይም የልጃቸው ልደት ብትታደሙ ለነፍስ ወከፍ የፈለጋችሁት ዓይነት ውስኪ በየጠረጴዛችሁ ሊቀርብላችሁ ይችላል፡፡ እነመስፍን እንደዚህ እያረዱን ነው እንግዲህ እኛ የዕለት ጉርስ ስናጣ፣ እኛ ምናምኒት እያጣን ልጆቻችን ከትምህርት ገበታ ሲለዩ፣ እኛ በቀላል ህክምና ሊድኑ በሚችሉ ቀላል በሽታዎች ሳይቀር ስንታጨድ፣ እኛ በጥቅሉ መኖር ሲያቅተን እነሱና እነሱ ብቻ ግን በሚሊዮን የሚገመት ገንዘብ በጥሎሽ መልክ ለአሮጊት ሴቶች ሳይቀር እየሰጡ ያሉት – ሊያውም ላላቸውና ለተትረፈረፋቸው፡፡ ‹ላለው ይጨመርለታል› አይደል ብሂሉስ? አንዳንድ ሽማግሌ ሀብታሞች ደግሞ በኔ ገንዘብ አቶዝን የመሳሰሉ አውቶሞቢሎችን እየገዙ መኖሪያ ቤትም እያሠሩ ለየቅምጦቻቸው ያድላሉ – ልብ አድርጉ – በኔ አንጡራ ገንዘብ! ይህን ነገር ፍትሃዊ ነው ትላላችሁ? ይህን ‹ሠርቶ› ነው ወይንስ ‹ሠርቆ› ወይም በንግድ ስም ማጅራት መትቶ የምንለው? አዎ! እደግመዋለሁ – ዓለምዋን ለጨረሰች ‹ልጃገረድ› ሴት ሳይቀር የኛ ገንዘብ በጥሎሽ መልክ ሌላ ሰው ይወደድበታል፤ በኔ ገንዘብ መስፍን እያዘዘበት ነው፤ በገንዘቤ የማላዝባት ሀገር ውስጥ መኖር ምን ያህል የቁጭት እሳት እንደሚለቅ ደግሞ እንደኔ ሁናችሁ አስቡልኝ፡፡ ጥቂቶችን ለማንደላቀቅ የምንከፍለው መስዋዕትነትም ይታያችሁ፡፡

በዳንስ ቤት ላለቀ ጋብቻ እኛን የተረፈን ዕዳው ነው፡፡ ለመሆኑ በዛሬ ጊዜ ይህን ያህል ውድ ጥሎሽ የሚገባት ልጃገረድ ከጋንዲ ሆስፒታል ካልሆነ የት ልትገኝ ትችላለች? ስንተዋወቅ አንተናነቅ፡፡ጋብቻ ዱሮ ቀረ ወዳጄ፡፡ ብር አምባር መስበር ዱሮ ቀረ፡፡ ከፈለግህ ብርጭቆ ገዝተህ ስበር እንጂ እንኳን የናጠጠች ሀብታም ነጋዴ ዘንድ ይቅርና የኔዋ የልጄ ልጅ የ15 ዓመትዋ ሚጢዬም ጋ ‹ሎጋው ሸቦ›ን እያስጨፈረ ‹አሳዩን የደሙን ሻሽ› የሚያስብል አንዳችም ተፈጥሯዊ ምልክት ይኖራል ብዬ አልገምትም፤ ዘመኑን እያየሁት? ኧረ አይኖርም! ያን አምባር እምትሉትን ነገር ‹ባለንብረቶቹ በወጉና በባህሉ መሠረት እጥቅም ላይ ስላላዋሉት› ከሚል እሳቤ በመነሳት እመብርሃን ራስዋ ፈጣሪን ተማልዳ ከሥሩ ከመሠረቱ እንዳይፈጠር አስቀርታዋለች እየተባለም ይታማል፡፡ ስለዚህ ገንዘባችን እሳት የገባ ቅቤ ሆኗል እባካችሁን፤ ወይ ነዶ! በስንቱ ነው የምንጎዳው? ሻሹን ባየሁ በገንዘቤ መቅለጥ ባልተቆጨሁ፡፡ በከንቱ ነው ጥቂት ሰይጣኖቻችንን ከአቅማችን በላይ እየገፈገፍን የምንድረው፡፡ በሰው ገንዘብ ይህን ያህል መዘባነን ግን ነውር አይደለም?

ለምርቃት ያህል ፡- አንድ በቁጥር የሚጠራ ሣሙና የሚያመርት ነጋዴ አውቃለሁ፡፡ የናጠጠ ቱጃር ነው፡፡ የቤቱ መግቢያ ዋናው አጥር ብቻ የአሜሪካንን ኤምባሲ ያስንቃል፡፡ ግን ሣሙናና መሰል ሸቀጦችን ነግዶ ነው እንዲህ የናጠጠው ይባላል፡፡ የሱን የያኔ የብር ከሃምሣ ሣሙና አሁን አሥርና አሥራ ሁለት ብር እየገዛሁ እኔ ሲጎድልብኝ እሱ ግን እየሞላለት ነው፡፡ ሕይወት እንደዚህ ናት፡፡ እንደዚህም ነበርች፡፡ ማን ያውቃል እንደዚህ እንደተጨማለቀችም ላልተወሰነ ጊዜ ትቀጥል ይሆናል – ማንን ፈርታ! ግን አያ ሞት ውሎ ይግባ – ልጅም ይውጣለት፡፡ በመጨረሻው መጨረሻ እኩል እሚያደርገን እሱ ነው፡፡ የእግዜሩንና የወያኔውንማ እያየነው አይደል?ኢትዮጵያን እኮ ከነአካቴው የሲዖል ምሳሌ አድርገዋት ቁጭ አሉ፡፡ ሕግ የሌለባት፣ ማንም በምንም ስም እየዘረፈ ሚሊዮኖችን የሚያደኸይባት፣ መንግሥትና ሥርዓት እሚባል ነገር ጨርሶውን የሌለባት በጠቅላላው በጥቂት ጉልበተኞች ቁጥጥር ሥር የዋለች የኳስ አበደች ሀገር ሆና ትቅር?

‹ሀብታም መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል› የተባለው እውነት ከሆነ ሀብታሞች ጉዳቸው ፈላ፤ያቺ የንስሃ ነገር ስትታወሰኝ ደሜ ይፈላል፡፡ አዳሜ አብዛኛውን የዕድሜውን ክፍል ሕዝበ አዳምን ሲያስለቅስ ከርሞ እንደታምራት ላይኔ በመጨረሻው ሲያለቃቅስ የሚምር አምላክ መኖሩ በበኩሌ በፍትሃዊነቱ ረገድ እንደሰው ቅሬታ ይሰማኛል፡፡ ነገር ግን የእግዜሩ ጥበብ እንደኔ (እንደሰው) ሳይሆን የረቀቀ መሆኑ በጄ፡፡ እኔ ብሆን ፍርዴ ይለይ ነበር፡፡ በማጠቃለያየ የገንዘብ ስኬትና የሕይወት ስኬት ለዬቅል መሆናቸውን በማሳሰብ ላብቃ መሰለኝ፡፡ ነገሬን እንዲህ ባጭሩ ካልቋጨሁት አውሎ ያሳድራል፡፡ … ለመስፍን መልካም አላሙዲናዊ የጫጉላ ሽርሽር ለኔ ቢጤ ‹ምቀኞች› ደግሞ መልካም ችግርና ቅዠትና ቅብዥር የሌለበት ጦም ማደር ይሁንልን፡፡