ኢትዮ-ላይፍ ወደ አጠቃላይ የኢንሹራንስ ዘርፍ ሊገባ ነው

 

(በአስራት ሥዩም)

ኢትዮ-ላይፍ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማበር የተቋቋመበትን የሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ብቻ ያተኮረ አልግሎት የመስጠት ዕቅዱን በመተው አጠቃላይ የኢንሹራንስ ሥራ ውስጥ ሊገባ መሆኑን አስታወቀ፡፡


በጥቅምት 2001 ዓ.ም. በአገሪቱ ብቸኛው በሕይወት ኢንሹራንስ ላይ ብቻ የሚሠራ ኩባንያ ሆኖ የተቋቋመው ኢትዮ-ላይፍ፣ የኢንሹራንስ ዘርፍ ያለውን የአረቦን ዕድገት በመመልከት አጠቃላይ የኢንሹራንስ ዘርፉን ለመቀላቀል መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተሾመ በየነ እንዳሉት፣ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ዘርፉ በአማካይ 25 በመቶ የሚደርስ የተስብሳቢ አረቦን ዕድገት የሚጠብቅ ሲሆን፣ ኢትዮ-ላይፍ ይህንን ዕድል የመጠቀም ፍላጐት አድሮበታል፡፡ “አሁንም ቢሆን የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያልተሠራበትና እስካሁንም በቅጡ ያልተነካ ገበያ አለው፤” ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ነገር ግን በአጠቃላይ የኢንሹራንስ አገልግሎት ዘርፍ ያለውን ዕድል መናቅ አይቻልም ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

በአጠቃላይ 30 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ተጨማሪ አክሲዮን በሽያጭ ያቀረበው ኢትዮ-ላይፍ ኩባንያ 30,000 አክሲዮኖችን ለመሸጥ መዘጋጀቱን፣ አቶ ሽመልስ ገብረ ጊዮርጊስ የኢትዮ-ላይፍ ዋና ሥራ አስኪያጅና የቦርዱ ፀሐፊ ገልጸዋል፡፡ እስከ መጪው ሐምሌ ወር ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንገባለን ብለን እናስባለን፤” ብለዋል፡፡

የኢትዮ-ላይፍ አክሲዮን ባለቤቶች በተጨማሪ ለገበያ የሚቀርቡትን አክሲዮኖች የመግዛት ቅድሚያ የሚያገኙ መሆኑንና የአገልግሎት ክፍያ 70 ብር በአክሲዮን የመክፈል ግዴታ የለባቸውም፡፡

ኢትዮ-ላይፍ በ117 ባለአክሲዮኖች በተፈረመ ካፒታል 4,738,000 ብርና በተከፈለ 4,262,000 ብር በ2001 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ የሕይወት ዋስትናን ብቻ ለመሸጥ ዓላማ አድርጐ የሚንቀሳቀስ ኩባንያ ነበር፡፡

ከማስፋፊያ ዕቅዱ ጋር በተያያዘ ታዋቂ ሰዎች የቦርድ አማካሪ ሆነው ከኩባንያው ጋር እንደሚሠሩ፣ አቶ ብሥራት ንጋቱ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ እንዲሁም ዶክተር ወልዳይ አመሐ የኢትዮጵያ ማክሮ ፋይናንስ ማኀበር ዋና ዳይሬክተር ከቦርድ አማካሪዎች መካከል ይገኙበታል፡፡