“… እግር ሲቆረጥም ፈርተው ዝም ያሉት ጅብ እራስን ሲቦጭቅ ቢጀግኑ፤ ‘የጅብ ሆድ የጉማሬ አይደለም’ ”። የጎንቻው!

… ከልብ ደፍሮና ቆፍጥኖ ድንጋይ በሚሰነዝርበት ሕጻን ልጅ ሳይቀር ሆዱ በፍራት የሚንቦጫቦጨውና፣ ኮርማ የሚገረሥሥ ጉልበቱ የሚብረከርከው በፈሪነቱ በንቀት መሣለቂያ የሆነው የዱር አውሬ ጅብ በአሞተ ቢስነቱ የፈርነት መዘባበቻ ነው።

ይህንን ከሚያጠናክሩ አባባሎችም መካከል፣ “ ለጅብ ከፈሩለት፣ ለልጅ ከሮጡለት…” ይባላል።
በሌላ በኩል አንዳንድ እጅግ ከጅብ የበለጠ ፍራት የተጠናወተታቸውን አሞተ ቢስ ሰዎችም እጣ ፈንታ በዘይቤያዊ ምሳሌ ‘አበው’ እንደሚከተለው ያሰረዳሉ።

…መንገድ መሽቶባቸው ዋሻ ውስጥ ለማደር ወስነው ከተኙት መንገደኞች መካከል፣ እኩለ ሌሊት ሲያገባድድ አያ ጅቦ የቢጤውንና፣ የአንደኛውን ፈሪ መንገደኛ እግር አነፍንፍ ይነክስና አጥንቱን እየጠረደመ ሲበላ ሌላው መንገደኛ በዚህ ድንገተኛ ኮቴ ይነቃና ምንድን ነው እባካቹሁ በስተግርጌያችን የሚቆረጣጠመው ድምጽ ሲል፡ ይጠይቃል። ‘እግሩን ገብሮ ሞቱን እየኖረ’ ያለው የባሰበት ፈሪ፤ ደግሞ ራሱን ከሽፈነበት ቡትቶ በትንሹ ገለጥ አድርጐ፣ጥርሱን እንደነከሰ በሹክታ እባክህ ቀስ በል ወንድሜ ይኸ መናጢ ጅብ የእኔን እገር እየበላ ነውና፤ ዝም በልና ተኛ ራሳችንን ጭምር ታስቦጭቀናለህ አለው ይባላል።

ፍርዱን ለሁላችን እተዎዋለሁ!

ይልቅስ ከዚህ ጉዳይ ጋር የቀረበ ንፅፅር ወዳለው የኢትዪጵያ ሕዝብ ወሰን ያለፈ ትዕግሥትና የወያኔ ቡድን በሁለመናችን ላይ እያደረሰ ያለው የእልቂት አባዜ፣ከአያ ጅቦ ኮቴ ሺህ ጊዜ በልጦ ቀስቅሶኝ፣ እረፍትና እንቅልፍ ነስቶኝ ነው።

…ባለፉት ሃያ ዓመታት የወያኔ ቡድን በግልጽና በሥውር የፈጸመውን እጅግ በዘመናችን ወደር የማይገኝለት ዘግናኝ ግፍና በደል ተዘርዝሮ አያልቅም።-

.. በግለሰብ፣ በዘር፣ በብሄር፤ በኃይማኖት፤ በጐጥ፤ በፓለቲካ አመለካከት ልዪነት እያሳበበ የፈጸመውና እያደረሰ ያለው ገደብ የለሽ ጉዳት ከራሱ ከተጐጅው ከኢትዪጵያ ሕዝበ የበለጠ ስቃዪን የሚሰማው ማን ሊሆን ይችላል?

የወያኔ ቡድን፡-
• የሕዝቡን አንጡራ ልጆቹ በየአደባባዩ በጥይት አርግፎ በርካታ ወላጆች ጧሪ ቀባሪ አጥተዋል።
• የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድ ድምፅ የመረጣቸውን የአወቁ የላቁ መሪዎች፤ እውነተኛ ኢትዪጵጵያዊ አጀንዳ ያላቸውን ዲሞክራቶች፡ የቁርጥ ቀን ልጆች ሁሉ አንጋግቶ በስቃይ ወህኒ አጉሮ የሰማኒያ ሚሊዮኖቻችን ፍዳና የመከራ አራጣ ከፋይ አድርጎ ነበር።
• ሕግን፤ መርሕን፤ እውነትን አሰንድቀው እንደ ቅርጣን የሚወጡትን ሐቀኛ ወጣቶች፤ ዜጎች፤መሪዎች፤ በጨለማ እሥር ቤት በመወርወር ለመንስፈስና ለአካል ጉድለት አብቅቶ መቀጣጫ ሲያደርግ ኖሯል።
• ሰላማዊ ሰልፍ ለምን ወጣችሁ ብሎ እስከ ሃምሳ ሺ የሚጠጉትን ሰላማዊ ዜጎች እንደ እቃ በካሚዎን እየጫነ በየበረሃውና በየጫካው እያጎረ ሲገርፍ፤ ሲገድል ቆይቷል።
• በሺዎቹ የሚቆጠሩት በየቤታቸው ታድነው የተውሰዱ ወገኖቻችን እጣ ፈንታና ድብዛቸው እስካሁን አይታወቅም።
• እንደ ውሻ ያደለባቸውን ተናካሽ አጋዚዎችና የስለላ ጅቦች በየጓዳውና በአደባባው እየሳደደ ወጣቶችን፤ አዛውንቶችን እናቶችን ያንገላታል፡ ያሰቃያል፡ ይገድላል።
• ከሰፊው የኢትዪጵያ ሕዝብ አብራክ የወጣውን ወታደርና የመከላከያ ኃይል በቁጥጥርና በጥቅምም ተብተቦ ለወገኑ የችግርና የቁርጥ ቀን ዳራሽ በመሆን ፈንታ በዘርና በዝምድና በሾማቸው፤ በአዋቀራቸው ሚስጥራዊ ወታደራዊ የአመራር ሰንሰሎቶች፤ አስገድዶ የወያኔው ቡድን የግል ዘበኛ አድርጐታል።
• የሐገር አንጡራ ሀብት፣የሕዝብ ንብረት በማናለብኝነት ከጉልት እስከ ኩባንያ ተደራጅቶ ይዘርፋል፤ ከምስኪኖች አፍ ሞልቅቆ ከፍተኛ የውች ምንዛሬ ወደ ባዕዳንም ሀገር ያሸሻል።
• ሐገር፤ታሪክ ያፈርሳል።
• መጠነ ሰፊ የሆነ ለሙን የሐገራችን ለም መሬት ለውጭ ቱጃሮች በሃራጅ እየቸርቸረ፤ ብርቅዬይ የደን፤ ሃብታችን እንዲመነጠር፤ የአራዊት፤ እጽዋት መተኪያ በማይገኝለት ሁኔታ እንዲጠፉ፤ በርካታ ወገኖቻችን ከትውልድ ቀያቸው፤፣ከባኃላዊ ኑሯቸው በጠመንጃ እየተፈናቀሉ፤ ይባረራሉ፤
• በስይጣናዊ ምግባሩ ለዘመናት ተመሳስለው በሚኖሩ ብሄሮች መካክል ነገር እየጠነስሰ እርስ በእርስ እንዲተላለቁ ያደርጋል።
• በየትምህርት ተቋማት፣ምግብ ቤቶች፣ አደባባይና የሕዝብ ማዘውተሪያ ቦታዎችና መጓጓዣዎች ቦምብ እያጠመደ የሰው ኃይዎት በከንቱ ይቀስፋል።
• በአጠቃላይ ሰብ-አዊና ሁለንተናዊ መብታችንን ገፎ እራቁታችንን ይገርፈናል።

ኧረ ስንቱ!! የለየለት ‘የቀን ጅብ’ ሆኖ በቁማችን ‘ ሁለመናችንን ይቆረጥማል’

አሁን፤ እድሜ ለቱኒያዚያኖች፤ለግብጻዊያን፤ለሊቢያዊያን፤ከሰላሳ እስከ አርባ ዓመት፤ ስልጣን ቁንጮ ላይ ተንፈራጠው ለልጅ ልጅ ሊያወርሱ ከሚያንቀላፉበት የስልጣን ዙፋን ላይ ወጣት አዛውንቱ ደፍሮ፤ተባብሮ፤እኒዚህን የሻገቱና የነቀዙ ገዥዎች በሰለጠነና በተባበር ትኩስ ሃይሉ አሽቀንጥሮ የሰላም አየር ከተነፈስ ውሎ አድሯል፤ የነጻነት አየር፤የነጻነት ጸሃይ፤የነጻነት ኃይዎት፤ የነጻነት፤ ለሰብ አዊክብር፤ ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ነጻነታቸውን የተቀዳጁት ጐረቤቶቻችን በቃል፤ ለመግለጽ እስኪሚያጥጣቸው ሁለንተናቸው ሲያሰተጋባ በመጎምጀት፤በቅናት፤እያየን ነው።

ይሁንና ነፃነት በነፃ የማይገኝ መሆኑንም እያየን ነው።

… ታዲያ እጅግ የሚያስደነግጠውና የሚያስፈራው ጉዳይ እስካሁን ‘ሕዝቡ’ የሚያሳየው ትዕግሥት ወሰኑን የሚያልፈው ወያኔ ‘እግሩን ቆርጦ ራሱን ሲቀላው’ እንዳይሆን ብዬ እሰጋለሁ።

“… እግር ሲቆረጥም ፈርተው ዝም ያሉት ጅብ እራስን ሲቦጭቅ ቢጀግኑ፤ ‘የጅብ ሆድ የጉማሬ አይደለም”። የጎንቻው