የቱኒሲያውን ሕዝባዊ ለውጥ
የቱኒሲያውን ሕዝባዊ ለውጥ፤ ለኢትዮጵያ ያለው እንድምታ እና የኢሣት ሚና
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
በቅርቡ በቱኒሲያ የተካሄደው ሕዝባዊ ለውጥ አገሪቷን ለ23 ዓመታት በአምባገነናዊ አገዛዝ ቀንበር ሥር ሲገዙ የነበሩትን ዚኔ ቤን አሊ ከሥልጣን ማስወገዱ በሌሎች የአፍሪካና እና የመካከለኛው ምስራቅ አገሮች ሕዝባቸውን በመርገጥ ለዘመናት በሥልጣን ላይ ተንሰራፍተው ለሚገኙ አምባገነኖች ጭንቀትንና ፍርሃትን እያስከተለባቸው መሆኑ እየታየ ነው። በተለይም በአፍሪካ ይህ የለውጥ ማዕበል ከቱኒሲያ እስከ ዚምባቡዌ እንዲሁም ከሞሪታኒያ እስከ ኢትዮጵያ እየተዳረሰ የመሄዱ ዕውነታ በርካታዎቹን የአፍሪካ አምባገነኖች ዕረፍት እየነሳቸው መጥቷል። ከዚህም ሌላ ይህ በምንም ሊገደብ የማይችል ማዕበል ማቆሚያ እያጣ በአፍሪካ አገሮች ግብጽ፣ አልጄሪያ፣ ሞሪታኒያ እንዲሁም ከአፍሪካ ውጪ አልባኒያንን እና የመንን እያዳረሰ መጥቷል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ኢትዮጵያ መንፈሱም አይቀሬ ነው።