በዋሺንግተን የወንድማማቾች ቀን በሚል ስያሜ የሚጠራ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ መሆኑ ታወቀ

ማርች ፎር ፍሪደም በመባል የሚታወቀውና በውጭ ሃገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን በማስተባበር ላይ የሚገኘው ኮሚቴ በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ ዋይት ሃውስ ፊት ለፊት  የወንድማማቾች ቀን በሚል ስያሜ የሚጠራ ከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ሊያካሄድ መሆኑን ባወጣው መግለጫ ላይ አስታውቁአል ማርች ፎር ፍሪደም ባወጣው በዚሁ መግለጫው   ዛሬ በዓለማችን ዙሪያ ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለሰብኣዊ መብትና ለዲሞክሲ ስርዓት መከበር ህዝቦች እጅ ለእጅ ተያይዞው፣ መድፍና ታንክ ሳይበግራቸው እምቢ ለነፃነቴ፣ እምቢ ለመብቴ፣ እምቢ ለሰብኣዊ ክብሬ ብለው አደባባይ በመውጣት ለዘመናት ሲጨቁኑዋቸው የነበሩ አምባገነናዊ ስርዓቶች በህዝባዊ ዓመፅና በተባበረ ክንድ ከዙፋናቸው በሀይል መንግለው ሲጥሉዋቸው በዓይናችን እያየን ነው ብሉአል።

ቀጥሎም  በሀገራችን ውስጥ እየታየ ያለው ሁኔታም ለሁላችን ግልፅ ነው። በአንድ በኩል በረሃብ የሚገረፍ፣ ለባዕድ ምፅዋትና ልመና ተጋልጦ ንሮውን መሸነፍ ያቃተው ህዝብ አለን። ህፃናት በቆሻሻ ቦታ የተጣለና የበሰበሰ አጥንት እየለቀሙ ከውሾች ጋር እየተሻሙ የሚበሉበት፣ በችግር ላይ ችግር የወደቀችና የደቀቀች ሀገር ነው የምናየው። በአንፃሩ በሙስና የናጠጡ ጥቂት ጉልበተኛ ቡድኖች ክብረ ልዕልናዋን ደፍረው፣ አንጡራ ሃብትዋን እየዘረፉ፣ ለም መሬትዋን እየሸነሸኑ ለባዕዳን በመቸብቸብ ህዝባችንን የበይ ተመልካች በማድረግ ረግጠውና አፍነው የሚገዙ አምባገነኖች የበቀሉባት ምድር ሆና ትገኛለች ካለ በኋላ እኛ በዲያስፓራ የምንገኘው ኢትዮጵያውያን ያለንን መለስተኛ የአመለካትና የእምነት ልዩነት ወደ ጎን ትተን በቅድሚያ ሀገርንንና ህዝብን ከመበታተንና ከጭቆና ማዳን ዋል እደር የማይባልበት ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ ነው ። ስለሆነም ጎሳ፣ ሀይማኖት፣ ፆታ፣ ህፃን፣ ሽማግሌ ሳይለይ እንደ አንድ ቤተሰብ ሁላችንም ተሰባስበን ለህዝባችን ያለንን የትግል አጋርነታችንን በጋራ የምንገልፅበትና ከጎኑ መሰለፋችንን በተግባር የምናሳይበት የትብብርና የቤተሰብ ቀን (people to people Solidarity day) በተቀናጀ መልኩ አዘጋጅተናል ብሎአል። በመሆኑም ይህ በልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ታጅቦ የሚከናወን የወንድማማቾች ቀን ከወዳጅ ዘመዶቻችሁ ጋር አብራችሁ እንድትገኙልን የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን። በማለት ጥሪውን አስተላልፎአል።