ዓረና ትግራይ ፓርቲ የአመራር አባላት ጥቃት ተፈጸመባቸው
ዓረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዲሞክራሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ፣ በ13 አመራር አባላቱ ላይ አካላዊ ጥቃትን ጨምሮ እስራት፣ ግርፋት፣ ከሥራ መባረርና ሁለንተናዊ እንግልትና ድብደባ እንደተፈጸመባቸው አሳወቀ፡፡ ዓረና ትግራይ፣ ፓርቲው ከምድር እንዲጠፋ ሁለንተናዊ ጥቃት እየተፈጸመበት መሆኑን ገልጾ፣ በተለይ በ13 አመራር አባላቱ ላይ እየተፈጸመባቸው የሚገኘው ጥቃት ግን እጅግ አሳሳቢ ሆኖ እንዳገኘው በመግለጫው አመላክቷል፡፡ ጥቃቱ በአስቸኳይ እንዲቆም ያሳሰቡት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ገብሩ አስራት፣ በአባላቱ ላይ በሚፈጸመው እንዲህ ዓይነት ዘመቻ ምክንያት ፓርቲው ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን መቼም እንደማያቆም ለሪፖርተር ነግረዋል፡፡
የፓርቲው መግለጫ እንደሚያመለክተው፣ አምስት አባላት ማለትም፣ ወጣት አያሌው በየነ (በ2002 ምርጫ በውቅሮ ማራይ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ ተወዳዳሪ)፣ ወጣት አምዛ ደሪ (በኢሮብ ልዩ ወረዳ የዓረና ተወካይ)፣ አቶ ተሾመ ገብረ መድህን (በሽሬ አካባቢ የፓርቲው ተጠሪ)፣ መምህር ይልማ ይኹኖ (በማይጨው ከተማ ተጠሪ)፣ ኢንጂነር አብዱልውሃብ ቡሽራ (የዓረና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል)፤ በቀንና በሌሊት በተለያዩ የሕወሓት አባላት አካላዊ ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ፣ አቶ አስገደ ገብረ ሥላሴ (የሥራ አስፈጻሚ አባል) አቶ ተሾመ ገብረ መድህንና ቄስ ጉዕሽ አረጋይ (የተምቤን ነዋሪዎች)፣ አቶ አማረ ተወልደ (የሁመራ ነዋሪ)፣ አቶ ዜናዊ አስመላሽ በፖለቲካ የተቀነባበረ ክስ፣ እስራትና ድብደባ ከደረሰባቸው መካከል በመግለጫው ተጠቅሰዋል፡፡
በሦስተኛ ደረጃ የዓረና ትግራይ ፓርቲ አባል በመሆናቸው ምክንያት በተለያዩ ሰበቦች ከሥራ ተባረሩ ያላቸው መምህር ኃፍቶም ፀጋይ፣ ጋዜጠኛ ስልጣኑ ሕሽ፣ ጋዜጠኛ አንዶም ገብረ ሥላሴ፣ መምህር ጐሽ ገብረ ፃድቅ (የሥራ አስፈጻሚ አባል) ይገኙባቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በትግራይ ክልል ገዢው ፓርቲ ሕወሓት የመንግሥትን መዋቅር ተጠቅሞ፣ ዓረና በክልሉ አንድም አባል እንዳይኖረውና ምንም ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ከፍተኛ የፖለቲካ ጫና እየተደረገበት መሆኑን፣ “የመንግሥት አካላትና የደኅንነት ሰዎች በቤተሰብ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በፓርቲው አባላት ላይ ከፍተኛ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እየፈጠሩባቸው ይገኛሉ፤” ብሏል፡፡ “ሌላው ቀርቶ ባለትዳር የሆኑ አብዛኞቹ የዓረና አባላት በፖለቲካው ጫናና ጣልቃ ገብነት ምክንያት ትዳራቸው ፈርሷል፤ ቤተሰባቸው ተበትኗል፤” ይላል መግለጫው፡፡
ዓረና ትግራይ አገር ወዳድ የሆኑ ዜጎች በፓርቲው አባላት ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማስቆም ከፓርቲው ጎን እንዲቆሙ የጠየቀ ሲሆን፣ “አሁንም ቢሆን በሰላማዊ ትግሉ እስከመጨረሻ መታገላችንን እንቀጥላለን፤” ብሏል፡፡ ዓረና ትግራይ የመድረክ ፓርቲ አባል ሆኖ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀስ ተቃዋሚ ፓርቲ ሲሆን፣ በምርጫ 2002 የፓርቲው የፓርላማ ተወዳዳሪ የነበሩት የአቶ አረጋዊ ገብረ ዮሐንስ ግድያን ጨምሮ በተለያዩ አባላቱ ላይ እስራት፣ ድብደባ፣ ከሥራ ማባረርና ግርፋት እንደሚፈጸምባቸው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ የሚመለከታቸው የክልሉ ባለሥልጣናት የዓረና ፓርቲ መግለጫን በተመለከተ ለማናገር የተደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡