6 የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊዎች ታሰሩ
የመንግሥትንና የማኅበሩን የግዢ መመርያ ያልተከተለ የ107 ሚሊዮን ብር የእህል ግዢ በመፈጸም ወንጀል የተጠረጠሩ ስድስት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ኃላፊዎች መጋቢት 6 ቀን 2004 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡ ኃላፊዎቹ ድርጊቱን ፈጽመዋል በሚል በቁጥጥር ሥር አውሎ ያሰራቸው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ፖሊስ ነው፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የማኅበሩ የፋይናንስ መምሪያ ኃላፊ፣ የኦዲት አገልግሎት ኃላፊ፣ የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ፣ የደም ባንክ መምሪያ ኃላፊ፣ የጤና እንክብካቤ መምሪያ ኃላፊና የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት መምሪያ ኃላፊ መሆናቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያረጋግጣል፡፡
ኃላፊዎቹ በ2003 ዓ.ም. በቦረና ሞያሌ አካባቢ ለደረሰው ድርቅ፣ ከውጭ በዕርዳታ በተገኘ ገንዘብ ለተረጂዎች በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በኩል በውስን ጨረታ እህል ተገዝቶ እንዲከፋፈል የግብርና ሚኒስቴር ይጠይቃል፡፡ ኃላፊዎቹ የተጠየቀውን የእህል ግዢ መሠረት በማድረግ የመንግሥትንና የማኅበሩን የግዢ መመርያን በመጣስ፣ በእህል አቅራቢነት ያልተመዘገቡና ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ሁለት ድርጅቶች የጨረታው አሸናፊ ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በተጠረጠሩበት ወንጀል ዙሪያ ምርመራ እየተደረገባቸው ሲሆን፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸውም ታውቋል፡፡ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ምክንያት ይሁን ወይም በግላቸው ባልታወቀ ሁኔታ አገር ውስጥ እንደሌሉ ተሰምቷል፡፡