በዝቋላ ገዳም የእሳት አደጋ መከላከል ጥረት ፖሊሶች እንቅፋት እየፈጠሩ ናቸው

የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በዝቋላ ገዳም ተገኝተው የአደጋ መከላከሉን ሥራ እያስተባበሩ ይገኛሉ፡፡ አሁን በስልክ እንደገለጡልኝ እሳቱን የመከላከሉ ተግባር በወጣቶቹ በሚገባ እየተሠራ ነው፡፡ በፈቃዳቸው እና በራሳቸው ቁሳቁስ በኢትዮጵያዊ እና ኦርቶዶክሳዊ ወኔ ወጣቱ ትውልድ ያደረገውን ሃይማኖታዊ ተግባር አድንቀዋል፡፡

የአካባቢው ፖሊሶች ተጨማሪ የሰው ኃይል አያስፈልግም፣ ያለው በቂ ነው በሚል ሌሎችን ተጓዦች ያገዱ ሲሆን፣ ተጓዦቹ እንደገለጡት የያዙት ምግብ ማለፍ ባለመቻሉ እየተበላሸ ነው፡፡ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከሩ ነው፡፡ ቢያንስ ውኃው እና ምግቡ እንዲያልፍ ለማድረግ፡

ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በገዳሙ ተገኝተው ቅዳሴ በመቀደስ፣ በወጣቶቹ እና በፖሊስ መካከል ችግር በተፈጠረ ጊዜ በማረጋጋት፣ እንደ ወጣቱ እኩል እሳቱን ተጋፍጠው ያሳዩት አባትነት በቦታው በተገኙት ወጣቶች ዘንድ አድናቆት እና አክብሮት አትርፎላቸዋል፡፡

ዝቋላ ካለፉት ቀናት በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ አልፎ አልፎ ገደሉ ሥር ከሚታየው ጭስ በስተቀር ይህ ነው የተባለ የጎላ እሳት አሁን የለም፡፡ ከየአካባቢው የሄዱት ወጣቶች ከገዳማውያኑ እና ከአደጋ መከላከል ባለሞያዎች ጋር በቅንጅት ባደረጉት ተጋድሎ ገዳሙን ከአደጋ ታድገውታል፡፡ ምንም እንኳን በአካባቢው ያለው ሙቀት ቀትር ላይ ሲጨምር የሚሆነው ባይታወቅም በአሁኑ ደረጃ ግን እሳቱ ከገደሉ በላይ እንዳይወጣ አካባቢውን የማጽዳት እና የእሳት መከላከያ የመሥራቱ ሥራ ተጠናክሯል፡፡