የኢትዮጵያ ወጣቶች ከቱኒዝያና ግብፅ እኩያዎቻቸው ሊማሯቸው የሚገቡ ቁምነገሮች

“በሰሜን አፍሪቃ እና መካከለኛው ምሥራቅ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አብዮት ከሰሃራ በታች ወደ አሉ የአፍሪቃ አገሮች ይዳረሳል ወይስ አይዳረስም?” በሚል አፍሪካዊያን በየቦታው ክርክሮች ይዘዋል። ቤን ዓሊ ከቱኒዝያ እንደተባረረ ከፊል ግብፃዊያን ግብፅን ከቱኒዝያ የሚለዩዋት ነገሮች ላይ አጽንዖት እየሰጡ “ግብፅ ቱኒዝያ አይደለችምና እዚያ የሆነው እዚህ ሊደገም አይችልም” እያሉ ሲከራከሩ ነበር። እርግጥ ነው ግብፅ ቱኒዝያ አይደለችም፤ ነገር ግን ቱኒዝያ የሆነው እግብፅም ተደገመ። ህዝባዊው ቁጣ ግብፅ ውስጥ አላበቃም። “ትናንት ሙባረክ፤ ዛሬ አብደላ!!!” የሚሉ መፈክሮች በችጋር በተጎዳችው፤ ውስጣዊ አንድነት በሌላት እና በኢንተርኔት ስርጭትም እጅግ ኋላቀር በሆነችው የመን ውስጥ ተፋፍሟል። በአንፃሩ ደግሞ የኑሮም ሆነ የሥራ አጥነት ችግር እጅግም ያላጠቃትን ባህሬንን አልማራትም። ከአመት በፊት በምርጫ ሰበብ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመጽ በጉልበት በታፈነባት ኢራን ውስጥም አዲሱ አብዩት እግሩን አስገብቷል። ባጭሩ ይህ በዓይነቱ አዲስ የሆነው ህዝባዊ ቁጣ እጅግ በተለያዩ የኑሮና የቴክኖሎጂ እድገት ደረጃዎች ላይ ወደአሉ አገሮች ተዳርሷል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ቱኒዝያ ወይም ግብፅ አለመሆኗ ወይም በአንዳንድ አመላካከቶች እነሱን አለመምሰሏ እዚያ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አብዮት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይዘልቅ ይከለክለዋል ማለት አይደለም።   በዚህም ምክንያት “እኛ ዘንድ ይደርሳል፤ አይደርስም?” በሚል ከመከራከር “ከእነዚህ አገራት ህዝባዊ አብዮቶች  የምንማራቸው ቁም ነገሮች ምንድናቸው?” ብሎ መጠየቅና የጎደሉንን አሟልቶ መገኘት ከፍተኛ የሆነ ተግባራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ ነው ።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ከቱኒዝያና ግብፅ የእድሜ አቻዎቻቸው በርካታ ነገሮችን መማር ይችላሉ ብለን እናምናለን። በተለይ ደግሞ ወጣቶቻችን የሚከተሉት ነጥቦችን እንዲያጤኑ እንመክራለን።

  1. ድርጅት፤ አምባገነንነት በሰፈነባቸው አገሮች የዘመኑ ወጣቶች  የሚፈጥሯቸው ድርጅቶች ቀድሞ ከምናውቃቸው የድርጅት ዓይነቶች በእጅጉ የተለዩ ናቸው። የቱኒዝያም ሆነ የግብጽ ወጣቶች ራሳቸውን በጥሩ ሁኔታ ያደራጁ ቢሆንም እንኳን ድርጅቶቻችው በልማድ የምናውቃቸው ዓይነት ግትር መዋቅር ያላቸው አይደሉም። ድርጅቶቻቸው በኦፊሴል ያልተመዘገቡ፤ እየታዩ የማይጨበጡ ዓይነት ኢንፎርማል ስብስቦች ናቸው። እነዚህ ስብስቦች የሥራ ቡድኖች በመሆናቸው እንደ ሥራው ብዛትና ማነስ በቀላሉ የሚሰፉና የሚጠቡ ናቸው። እነዚህ የወጣቶች ድርጅቶች በተለያየ ጊዜዓት የተለያዩ ቅርጾችን ይዘዋል። አንዳንዶቹ በአካል የማይተዋወቁ የፌስ ቡክ ጓደኞች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ደግሞ የኳስ አድናቂዎች ናቸው። ቱኒዚያዊያንና ግብፆች በእንዲህ አይነቱ ተጣጣፊ አደረጃጀት የመንግሥት ሰላዮችን ጭንቅላት አዙረዋል። የኢትዮጵያም ወጣቶች ከቱኒዚያና ግብጽ ወጣቶች በመማር ከኢትዮጵያ ባህልና እድገት ጋር ተስማሚ የሆነ ሆኖም ተጣጣፊ የሆነ አደረጃጀት ሊከተሉ ይገባል።
  2. የመረጃ ልውውጥ፤ በወያኔ  ደባ ምክንያት ኢትዮጵያ አገራችን በኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ እጅግ ወደ ኋላ የቀረች ቢሆንም ወጣቱ ልዩ ልዩ የፈጠራ ዘዴዎችን ተጠቅሞ  የመረጃ መረቡን ማስፋት፤ ዘመናዊውንም ባህላዊውንም የመረጃ ልውውጥ አቀናጅቶ  መጠቀም ይኖርበታል። ለምሳሌ ከውጭ አገር ወደ አገር ቤት የሚተላለፉ ለእውነት ወገንተኛ የሆኑ የፌድዮና የቴሌቪዥን ስርጭቶች በኢትዮጵያ በስፋት እንዲታዩ ዘመቻ በማድረግ የመረጃ አድማስን ማስፋት ይቻላል። ለእነዚህ ሬድዮዎችና  ቴሌቪዥኖች መረጃዎችን በመስጠትም የጠበቀ  ግኑኝነት መፍጠር ይገባል። ወጣቱ የማያልቅ የፈጠራ ክህሎቱን ለመረጃ ልውውጥ ማዋል ይኖርበታል።
  3. መቻቻል፤ ሰዎች ለትላልቅ ዓላማዎች ሲሰለፉ መለስተኛ ቅራኔዎች ፋይዳ አይኖራቸውም። የነፃነት ትግል ግብፃዊያንን አፋቅሯል። በክርስቲያኖች ጥበቃ ሞስሊሞች ሲሰግዱ፤ ለክርስትያኖች ቅዳሴ ሞስሎሞች ከለላ ሲሰጡ ማየት ችለናል። የሁለቱም ሃይማኖቶች ተከታዮች በጋራ በየእምነቶቻቸው ለነፃነት ፀልየዋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ከዚህ ጠቃሚ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል። የነፃነት ትግል ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታና እድሜ  አይለይም። ነፃነት ሰው በሰውነቱ ብቻ ሊያገኘው የሚገባ  ፀጋ ነው። ሆኖም ግን በግብጽ ሙባረክ እንደሞከረው፤ በየመን አሊ አብደላ ሳልህ እንዳደረገው ሁሉ ወያኔም ህዝብን ከህዝብ በጎዳና ለማጣት እና እሱ ገላጋይ ሆኖ ለመግባት መሞከሩ አይቀርም። ወጣቶች ይህን ቀዳዳ በተቻለ መጠን  ማጥበብ ይኖርባቸዋል። ለዚህ አንዱ መፍትሄ የተቃውሞ  ዓላማን ግልጽ ማድረግ ነው። ዳቦ፣ ሥራ፣ ፍትህና ነፃነት ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታና እድሜን አይለዩም።
  4. በራስ የመተማመን ስሜት: ቱኒዚያዊያንና ግብፃዊያን ፍርሃትን ማሸነፍ የቻሉ በራስ የመተማመን ስሜት በመፍጠራቸው ነው። ግብፅ መለዮ ለባሽ ከሆነው የጦርና የፓሊስ ሠራዊት ውጭ 350 000 የሚደርስ ሰላይና ነጭ ለባሽ አላት ተብሎ  ይገመታል። ይህ ሁሉ ሠራዊት ግን አመጹ እንዳይነሳ ማገድ፤ ከተነሳም በኋላ ማፈን አልቻለም። በራስ የመተማመን ስሜት መተሳሰብን፣ መተጋገዝን፣ የጋራ ጥቅምን ማስቀደምን ይፈጥራል። ወጣቱ በራሱ ሲተማመን ከታላላቆቹ “አመራር” መጠበቅ ይተዋል። ያኔ ነው እውነተኛ ህዝባዊ አብዮት ማካሄድ  የሚቻለው።
  5. መብት፣ ክብር እና ባለቤትነት: በቱኒዝያና ግብፅ ሰብዓዊ መብቶች፣ ሰብዓዊና አገራዊ ክብር እና የሃገር ባለቤትነት ጉዳይ በስፋት የተነሱ ፍሬ ሃሳቦች ናቸው። አገራችን በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓለምን ትመራለች። አገራችን ፓሊስ የወንዶችን የዘር ፍሬ፤ የሴቶችን ደግሞ ጡት በመቀጥቀጥ የሚደሰትባት አገር ናት። እንዲህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባር የሚፈጸመው ደግሞ  ሩቅ ሳይሆን በዋናው ከተማ  አዲስ አበባ ውስጥም ነው። በአንድ ወቅት የጂኖሳይድ ዎች ፕሬዚዳንት ዶ/ር ግሪጎሪ ስታንተን እንደተናገሩት አገራችን በአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ውስጥ ትገኛለች። በአንድ ትንሽ ቡድን ቅኝ የመገዛትን ያህል አዋራጅ ነገር የለም። ወጣቱ ከዚህ ውርደት ራሱን ነፃ  አውጥቶ የራሱን ክብር ለማስጠበቅ መነሳት ይኖርበታል። ወጣቱ “ኢትዮጵያ የኔ ናት!” ብሎ እንዲነሳም ያስፈልጋል።

የኢትዮጵያ ወጣት እነዚህ አምስት ነገሮች ከሰሜን አፍሪቃ አቻዎቹ መማር አለበት ብለን እናምናለን። ጊዜ የለም። ሁኔታዎች በፍጥነት እየተቀያየሩ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣት ለመብቱ፣ ለክብሩና ለሃገሩ ሲል ዛሬውኑ ይነሳ!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!!