መንፈሳዊነት ጠገግ ወይስ ሕይወት?

click here for pdf 

በዓለም ላይ በሃይማኖት መንገድ አያሌ የጽድቅ ሥራዎች ተሠርተዋል፤ በተቃራኒውም በሃይማ ሽፋን አያሌ ግፎች ተሠርተዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሃይማኖትን የሕይወት መንገዳቸው ሳይሆን የሕይወት ጠገጋቸው በማድረጋቸው ምክንያት፡፡ የእምነቱን ሕግ እና ሥርዓት ለማክበር ሳይሆን በእምነቱ ስም ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞችን ለማነፍነፍ በመጠጋ ታቸው የተነሣ፡፡ ለፖለቲካ፣ ለኢኮኖሚ እና ለሥልጣን ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ሲሉ ሃይማኖትን ተጠግተው ለሃይማኖታቸው ሳይሆን በሃይማኖታቸው ይጠቀማሉ፡፡
ይህ ሲሆን ደግሞ ሃይማኖት ዓላማውን ይስታል፡፡ የሃይማኖት ዋናው ዓላማ በሃይማኖት መመርያ መሠረት ለሰማያዊ ዋጋ የሚያበቃ መልካም ነገርን በምድር ላይ መፈጸም ነው፡፡ ሃይማኖት የፈጣሪን መንግሥት ይሰብካል፣ ፖለቲካ ደግሞ ምድራዊ መንግሥት፣ ሃይማኖት ሰማያዊ ትርፍን ይሰብካል፣ ንግድ ደግሞ ምድራዊ ትርፍ፣ ሃይማኖት ሰማያዊ ሹመትን ይሻል፣ ሥልጣን ደግሞ ምድራዊ፡፡
ሃይማኖት ምድራዊ ሕይወታችንን ሲቃኘው ኑሯችን መንፈሳዊም ሥጋዊም ጤናው የተጠበቀ ይሆናል፡፡ ንግድ፣ ፖለቲካ፣ ዘር እና ሥልጣን ሃይማኖትን ሲቃኘው ግን ሃይማኖት ከሰማያዊው ግቡ ጋር ይቆራረጣል፡፡
በተለይም ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በልዩ ልዩ እምነት የሚያምኑ ዜጎች በአንድ ላይ ተግባብተው እና ተገናዝበው በሚኖሩባት ሀገር ሃይማኖት ሰማያዊውን ዓላማ ለቅቆ ምድራዊ መሆን ከጀመረ የፍቅር እና የአንድነት ማሠርያነቱ ላልቶ የጠብ እና የጦርነት መንሥኤ ሊሆን ይችላል፡፡
ሃይማኖት መሥመሩን ለቅቆ ከማዋሐጃነት ወደ መከፋፈያ መሣርያነት የሚያመራው የሕዝቦች ግንኙነት ሃይማኖትን ብቻ መሠረት እያደረገ መጓዝ ሲጀምር ነው፡፡ በሕዝብ ግንኙነቶች ውስጥ ሃይማኖትን ብቻ መሠረት የሚያደርጉ ግንኙነቶች አሉ፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች በማኅበረሰቡ መካከል ያለውን ተዛምዶ የማያበላሹ እና በየእምነት መጻሕፍቱም የተደነገጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የጋብቻ ግንኙነቶች አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር የሃይማኖት ቤተሰብነትን መሠረት ያደርጋሉ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ሃይማኖትን የግድ መሠረት ማድረግ የሌለባቸው ማኅበራዊ ግንኙነቶችም አሉ፡፡ የፖለቲካ፣ የንግድ፣ የአካባቢ፣ የርዳታ፣ ወዘተ ዓይነት ግንኙነቶች፡፡ እነዚህ ግንኙነቶች ተመሳሳይ አለመካከቶችን፣ ውሎችን፣ የሀገር ሕጎችን እና ሰብአዊነቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡
አንድ ከርስቲያን የምነግደው ከክርስቲያኑ ጋር ብቻ ነው ካለ፣ አንድ ሙስሊምም በዚሁ መንገድ ከተጓዘ፣ በአንድ አካባቢ ለመሥፈር ወይንም መኖርያን ለመሥራት አካባቢው የክርስቲያን ወይንም የሙስሊም ተብሎ ከተከፈለ፣ በአንድ መሥሪያ ቤት ለመቀጠር የኃላፊዎቹን ወይንም የባለቤቶቹን እምነት ማመን ዋና መመዘኛ ከሆነ፣ ርዳታ ለማግኘት የረጅዎቹን እምነት መቀበል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ከተደረገ ሀገር እንደ ሀገር መኖር ይከብዳታል፡፡
እንዲህ እንደኛ ልዩ ልዩ እምነቶችን የሚከተሉ ሕዝቦች ያሉባት ሀገር ሕዝቦቿ በሰላም እና በጤና መኖር እንዲችሉ ሦስት ነገሮች ያስፈልጓታል፡፡ መተዋወቅ፣ መገናዘብ እና ከድምሩ በላይ ማሰብ፡፡
ለመሆኑ ከእኔ የተለየ እምነት ያለው ወገኔ ምንድን ነው የሚያምነው? ለምን? ከኔ ልዩነቱ እና አንድነቱ ምንድን ነው? የሚጠላው እና የሚወድደው ምንድን ነው? እኔ እና እርሱ ሳንጋጭም ሳንዋዋጥም እንዴት ተግባብተን ልንኖር እንችላለን? በሚሉት ጉዳዮች ላይ አንዱ ስለ ሌላው ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረጉን ነው መተዋወቅ የምንለው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ስለሌሎች የሰማናቸው እና ያወቅን የመሰሉን ነገሮች የተዛቡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በጠላትነት የምንተያየውም በተነገሩን የተዛቡ መረጃዎች ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ የማያምኑትን እንደሚያምኑ፣ የማይቀበሉትን እንደሚቀበሉ፣ የማይደግፉትንም እንደ ሚደግፉ እያደረግን የሰማናቸው እና ያነበብናቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ምናልባትም አንዳችን ስለሌላችን ባለማወቃችን የተነሣ የሌሎችን መብቶች ልንደፈጥጥም እንችላለን፡፡ በቃላት አጠቃቀማችንም እንስታለን፡፡
መተዋወቅ እነዚህን ሁሉ ነው የሚፈታው፡፡ ብዙ ጊዜ መተዋወቅን ከመሳሳብ እና እምነትን ከመለወጥ አንፃር ስለምናስበው መገፋፋት በመካከል ይሰፍናል፡፡ ሰው ሌላውን ማወቅ ያለበት እምነቱን እና አመለካከቱን ለመለወጥ ብቻ አይደለም፡፡ የራስን አመለካከት መለወጥ እና ስለሌላው ያለንን አመለካከት መለወጥ ይለያያሉ፡፡
መገናዘብ የምንለው ምናልባትም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይገኝ የነበረ አሁን ግን እየተዳከመ የሄደ በጎ ጠባይ ይመስለኛል፡፡ አንድን እምነት ዐውቆ፣ ያንን አማኝ ላለማስቆጣት እና ማኅበራዊ ግንኙነትን ላለማበላሸት ተጠንቅቆ፣ ነገር ግን መተጋገዝ እና አብሮ መኖር ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ቤተ ክርስቲያን ለሚሠሩ ክርስቲያን ወገኖቻቸው ርዳታ ሲሰጡ እስልምና አይጠቅምም ብለው የራሳቸውን ትተው፣ ወይንም ክርስትና ከኛ ይሻላል ብለው በክርስትና አምነው አይደለም፡፡ ለክርስቲያን ወገኖቻችን ቤተ ክርስቲያን ሊኖራቸው ይገባል ብለው እንጂ፡፡ ክርስቲያኖችም እንዲሁ፡፡ መገናዘብ ማለት ይሄ ነው፡፡
በማኅበራዊ ግንኙነቶቻችን ውስጥ ይህንኑ ነው የምናየው፡፡ በሙስሊሞች በዓል እንኳን አደረሳችሁ ለማለት ክርስቲያኖች በቤታቸው ሲገኙ ሙስሊም ወገኖቻቸው ለምግባቸው ተጠንቅቀው ነው፡፡ ይገናዘባሉና፡፡ ለእነርሱ ተብሎ የተዘጋጀውን የሚያቀርቡት የክርስቲያኖቹን ፍላጎት ተገንዝበው ነው፡፡
ሦስተኛው ከድምሩ በላይ ማሰብ መቻል ነው፡፡ ከእኛ ከአማኞቹ በላይ የሆነች ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አለች፡፡ ሁላችንም እንደልባችን ልንሆን የምንችለው ይህቺ ሀገር እንደ ሀገር ስትኖር ነው፡፡ እናም ይህቺን ሀገር እንደ ሀገር ለማኖር ስንል የምንከፍለው ሰማዕትነትም አለ፡፡ እኛ የየራሳችንን እምነት ብቻ እየተመለከትን በምናደርገው ሥጋዊ ፉክክር ይህቺ ሀገር እንዳትጎዳ የመጠንቀቅ ግዴታም አለብን፡፡ ስለ ክርስትና ቅርሶች፣ ስለ እስልምናም ታሪካዊ ቦታዎች ስናስብ ስለ ኢትዮጵያ ሀብቶች ማሰብ አለብን፡፡ ከወዲህ ማዶ እኛ ድንበሩን በገፋነው መጠን ከወዲያ ማዶም የሚገፋ መኖሩን መርሳት የለብንም፡፡
አለቃ ገብረ ሐና ቤት ወይዘሮ ማዘንጊያ በሌሉበት አንዲት ሴት የስድስት ወር ልጇን ይዛ ትመጣለች፡፡ የመጣችበት ምክንያት አልታወቀም፡፡ በድንገት ወይዘሮ ማዘንጊያ ሲገቡ ሴቲቱ ደንግጣ የራሷን ልጅ ትታ የማዘንጊያን ልጅ ይዛ ትሮጣለች፡፡ ማዘንጊያ አለቃ የባለጉ መስሏቸው ተናደዱ፡፡ ወዲያው ልጁን አነሡና እሳት ውስጥ ሊጨምሩት ወደ ምድጃው ሲሄዱ አለቃ «ተይ ማዘንጊያ እዚያም ቤት እሳት አለ» አሏቸው ይባላል፡፡
እዚህ ቤት አንዳች ነገር ሲደረግ እዚያም ቤት ሊደረግ እንደሚችል ማሰብ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ለምናቃጥላት ቤተ ክርስቲያን ወይንም መስጊድ በሌላ አካባቢ ዋጋውን ልንከፍልበት እንችል ይሆናል፡፡ እዚህ ሙስሊሞች አንሰው ክርስቲያኖች ስለበዙ የምንጨቁን ከሆነ እዚያ ክርስቲያኖች አንሰው ሙስሊሞች በሚበዙበት ቦታ ደግሞ ተመሳሳዩ እንዲፈጸም እያሳሰብን ነው ማለት ነው፡፡ አለቃ እንዳሉት እዚያም ቤት እሳት አለና፡፡
አሁን አሁን በዚህች ሀገር ከሚያሳስቡኝ ነገሮች አንዱ በሃይማኖት ንጣሌ የማሰብ አመለካከት ነው፡፡ በሃይማኖት ንጣሌ የማሰብ አመለካከት ማንኛውንም ነገር በሃይማኖት መነጽር ብቻ የማየት አስተሳሰብ ነው፡፡ አክስዮን ለመመሥረት ተመሳሳይ ሃይማኖት፣ ገንዘብ በባንክ ለማስቀመጥ ተመሳሳይ ሃይማኖት፣ አንድ አካባቢ ለመኖር ተመሳሳይ ሃይማኖት፣ አንድን ነገር በጅምላ ወይንም በርካሽ ለማግኘት ተመሳሳይ ሃይማኖት፣ ርዳታ ለማግኘት ተመሳሳይ ሃይማኖት፣ ሥራ ለማግኘት ተመሳሳይ ሃይማኖት መጠየቅ እየተጀመረ ነው፡፡
ፈጣሪያቸውን አምነው፣ እርሱ የፈቀደውን አድርገው የርሱን መንግሥት ለመውረስ የተሰባሰቡ ወገኖች ዓላማቸውን ቀይረው የአማኙን ስብስብ እንደ አማራጭ ገበያ፣ እንደ ደንበኛ ማፍሪያ፣ እንደ ገንዘብ መሰብሰቢያ፣ ለሥልጣን እንደ መሸጋገርያ፣ የድምጽ ማግኛ፣ የርዳታ እህል መለመኛ ካደረጉት በዚህች ሀገር ንጥያ እየተባባሰ ነው ማለት ነው፡፡
በተለይም ቢቻል ከአባቶቻችን የተሻለ እንሠራለን፣ ባይቻልም አባቶቻችንን እናበረታለን ብለው የሚሰባሰቡ ወጣት መንፈሳውያን ለጽድቅ የተሰባሰቡባቸውን ማኅበራት ወደ ንግድ «ኢምፓየር» የሚቀይሯቸው ከሆነ፣ በመንፈሳዊ ዓላማ እና በሰማያዊ ግብ ያሰባሰቧቸውን አባላት ከሰማይ አውርደው በአክስዮን እና በካፒታል መዋጮ የሚያሰባስቧቸው ከሆነ፤ መንፈሳዊነቱ ሕይወት ሳይሆን ጠገግ ሆኗል ማለት ነው፡፡
በመንፈሳውያን መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት መንፈሳዊነትን ብቻ መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡ የሚሠሯቸውም ሥራዎች ዓላማቸው ጽድቅ መሆን አለባቸው፡፡ መንፈሳውያን በምድር ላይ በሥጋ ሊጠቀሙ ሳይሆን ሊጠቅሙ ነው የሚመጡት፡፡ መንፈሳውያን በሃይማኖት የሚሰባሰቡት መክሊታቸውን ሊያተርፉ እንጂ አክስዮናቸውን ሊያተርፉ አይደለም፡፡
እስካሁን ድረስ በእምነት ስም የተነሡ ግጭቶች ራሳቸው እምነቶቹ የፈጠሯቸው አይደሉም፡፡ እምነቶቹን ለግላዊ ጥቅማቸው ማዋል የሚፈልጉ አካላት የፈጠሯቸው እንጂ፡፡ እነዚህ ሰዎች የመጀመርያቸው ሥራ ደግሞ በእምነቶቹ ሰማያዊ ዓላማ ላይ ምድራዊ ዓላማ መጨመር ነው፡፡ የግጭቱ መነሻም ይኼው ምድራዊ ዓላማ ይሆናል፡፡
እነዚህ እየታዩ ያለ ክስተቶች እኛው ኢትዮጵያውያን ማረም አለብን፡፡ አሁን የሚያስፈልገን የኦርቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንት፣ የእስልምና፣ የይሆባ፣ ባንክ አይደለም፡፡ እጅግ ዘመናዊ የሆነ የኢትዮጵያ ባንክ ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን በሃይማኖት ስም የተመሠረተው የማኅበረ እገሌ ወይንም እገሌ የአክስዮን ማኅበር አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የአክስዮን ማኅበር ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን የሙስሊም ወይንም የክርስቲያን ሆስፒታል አይደለም፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ሆስፒታል ነው፡፡
አሁን የሚያስፈልገን የሙስሊም ወይንም የክርስቲያን የርዳታ ድርጅት አይደለም፡፡ የተቀበለውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ የሚያውል የርዳታ ድርጅት ነው፡፡ አሁን የሚያስፈልገን የክርስቲያኖች ወይንም የሙስሊሞች ሠፈር አይደለም፡፡ ተስማሚ የመኖርያ ሠፈር ነው፡፡
ይህ ጉዞ ኢትዮጵያውያንን ተነጣጥለን ብቻ የምናስብ፣ በአንድ ሀገር ከመኖራችን በቀር የመግባቢያ ሰነድ የሌለን ያደርገናል፡፡ ምናልባትም በንግድ እና በገንዘብ ምክንያት የሚመጡ ግጭቶችም ወደ እምነቶች ውስጥ ገብተው እንዲያተራምሱ ዕድል ይከፍታል፡፡ እናም ሃይማኖትን ለጽድቅ እና ለድኅነት እንጂ ለንግድ «ኢምፓየር» መገንቢያነት አንጠቀምበት፡፡
© ህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔትላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።