ኀዘን እና ደስታ

(click here for pdf)
በየሀገሩ እየዞረች ከልዩ ልዩ ሕዝቦች ጋር መገናኘት የምትወድ አንዲት ፓይለት ነበረች፡፡ በዓለም ላይ ያልዞረችበት ሀገር አልነበረም፡፡
አንድ ቀን ፓይለቷ በሰሐራ በረሃ ላይ ስትበርር የአውሮፕላኑ ሞተር ተበላሸባት እና በፓራሹት ወደ መሬት ወረደች፡፡ የወረደችበትን ቦታ አታውቀውም፡፡ ግን ጭው ያለ በረሃ ነበር፡፡ የት እንዳለች እና ወደ የት መጓዝ እንደምትችል አታውቅም፡፡ በአካባቢዋ ያለው መንደር በምን ያህል ርቀት ላይ እንደሚገኝም ምንም መረጃ የላትም፡፡
ለብዙ ሰዓታት ካሰበች በኋላ ያላት አማራጭ በአንዱ አቅጣጫ መጓዝ እንደሆነ አመነች፡፡ እናም የምት ችለውን ዕቃ ተሸክማ ጉዞዋን ጀመረች፡፡ በዚያ በረሃ ከሚያጋጥማት የአሸዋ አውሎ ነፋስ ጋር እየታ ገለች፣ በአሸዋው ተራራ ላይ እየወደቀች እና እየተነሣች፣ ከሚያጋጥሟት አራዊት ጋር እየተጋደለች ወደፊት መጓዟን ቀጠለች፡፡
መንገዱ በሁለት ምክንያት አድካሚ እና አሰልቺ ሆነባት፡፡ በአንድ በኩል ወደየት እንደ ምትሄድ በርግ ጠኛነት ባለማወቋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ መቼ እንደምትድረስ ለመገመት ባለመቻሏ፡፡ በአንድ ነገር ግን ርግጠኛ ነበረች፡፡ በመንገዷ ከሚያጋጥሟት ፈተናዎች ይልቅ መንፈሷ ጠንካራ መሆኑን፡፡ ባለ ማቋረጥ ከተጓዘች አንዳች ጠቃሚ ቦታ ላይ እንደምትደርስ፡፡ እናም መጓዝ ቀጠለች፡፡
ይደክማታል ትወድቃለች፡፡ ዐቅም ሰብስባ ትነሣለች፡፡ ተስፋ አትቆርጥም ትጓዛለች፡፡

ተሸንፋ አንድ ቦታ በመቀመጥ ሞትን መጠበቅ ትችላለች፡፡ እርሱ ግን አማራጭ የማይሰጥ ሞት ነው፡፡ ሽንፈት ማለት ሞትን ያለ ምርጫ መቀበል ነው፡፡ እየታገሉ መሞት ሞትን በራሱ ጊዜ ብቻ እንዲመጣ ማስገደድ ነው፡፡ ሳይታገሉ መሞት ግን ሞትን ብቸኛ ምርጫ አድርጎ መጋበዝ ነው፡፡
መታገል ሁለት ዕድሎች አሉት፡፡ ማሸነፍ ወይንም መሸነፍ፡፡ አለመታገል ግን ምርጫው አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም መሸነፍ፡፡
እያለቀ ከሚሄደው ስንቋ በቀር ምንም ዓይነት ምግብ በአካባቢው አልነበረም፡፡ የውኃ ጥሙ ከባድ ነው፡፡ ያላትን እየቆጠበች መጓዝ ነበረባት፡፡ ሌሊት እና ቀን ቢፈራረቅም እንኳን እርሷ ማቋረጥ የለባትም፡፡ መጓዝ ብቻ፡፡
አንድ ቀን እጅግ ደክሟት አሸዋው ላይ ተኝታ እያለ አንድ ፍጡር ታያት፡፡ ከዚህ በፊት አይታው የማታውቀው ዓይነት ፍጡር፡፡ እንዲህም አላት «እኔ አንዳች ነገር ልነግርሽ ነው የመጣሁት፡፡ ተስፋ አትቁረጭ፣ ትካዜ ውስጥም አትግቢ፣ እጅሽንም አትስጭ፣ እኔ የምልሽን በትክክል ሰምተሽ ተግባራዊ አድርጊው፤ መንገድሽ ረዥም እና አስቸጋሪ ነው፣ መጨረሻው ግን ጣፋጭ ይሆንልሻል፡፡ ጠዋት ከዚህ አሸዋ የምትችይውን ያህል አፍሰሽ ያዥ፣ ከዚያም መንገድሽን ቀጥይ፡፡ በመጨረሻም ደስተኛም ኀዘንተኛም ትሆኛለሽ፣  ያኔ አንዳች ምዕራፍ ላይ መድረስሽን ታረጋግጫለሽ» አላት፡፡
ነቃች፡፡ ሕልም ብቻ አልነበረም፡፡ ያንን ፍጡር በርግጠኛነት አይታዋለች፡፡ ከነበረችበት ተነሥታ የምትች ለውን ያህል አሸዋ ዘግና መንገድዋን ቀጠለች፡፡ ሌት እና ቀን ባለ ማቋረጥ ቀጠለች፡፡ እየወደቀች እየተነሣች ተጓዘች፡፡ አንደኛው ቀን ለሌላው ቀን ተስፋ እየወለደ ተጓዘች፡፡ በመጨረሻም አንድ ጉብታ ላይ ደረሰች፡፡ ወደ ታች ስታይ የሰዎች መንደር ታያት፡፡ ያን ጊዜ በደስታ ብዛት ዝላ ወደቀች፡፡
እንግዳ ነገር በጉብታው ላይ ያዩት መንደርተኞቹ እየተሯሯጡ ወደ ጉብታው መጡ፡፡ አንሥተውም ወደ መንደራቸው ወሰዷት፡፡ ምግብ እና ውኃ ሰጧት፡፡ ለረዥም ሰዓታትም ተኛች፡፡ በፍጻሜውም ነቃች፡፡
የተጓዘችበትን መንገድ አሰበቺው፡፡ ውጣ ውረዱን አስታወሰቺው፤ ፍርሃት እና ድፍረቷን ገመገመቺው፡፡ በመጨረሻ ሰው ያለበት፣ ነፍሷ ሊተርፍ የሚችልበት ቦታ በመድረስዋ እጅግ ተደሰተች፡፡ በሕይወቷ ካጣጣመቻቸው ደስታዎች ሁሉ የሚበልጠውን ደስታ ተደሰተቺው፡፡ እጥረት ከሌለ ርካታ አይኖርም፡፡ ርሃብ ከሌለ ምግብ አይጣፍጥም፡፡ድካም ከሌለ ደስታ የለም፡፡ «እንበለ መከራ ኢይትረከብ ጸጋ» እንዲል፡፡
እንደ ገና ደግሞ አንድ ነገር ትዝ አላት፡፡ ያ ሌሊት የታያት ፍጡር የነገራት ነገር፡፡ ወደ ኪሷ እጇን ከተተቺው፡፡ ያንን አሸዋ ዘግና አወጣችው፡፡ ስታየው አሸዋ አልነበረም፡፡ የአልማዝ እንክብሎች ናቸው፡፡ በደስታ እንደገና ወደ ኪሷ ገብታ የያዘቺውን ሁሉ ዘረገፈቺው፡፡ የአልማዝ እንከብሎች፡፡
ደስታም ኀዘንም አንድ ላይ መጡ፡፡ ሕይወቷ በመትረፉ ከዚያም በላይ አንድ እፍኝ አልማዞች በማግኘቷ ተደሰተች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ አልማዞችን ለመያዝ ባለመቻሏ አዘነች፡፡ ኀዘን እና ደስታ በአንድ ላይ፡፡
ያ ፍጡር እንዳላት ፍጻሜዋ ኀዘን እና ደስታ በአንድ ላይ ሆኑ፡፡ ምናለ እንዲህ ባደርግ ኖሮ፡፡ በሁሉም ኪሶቼ ብይዝ ኖሮ፡፡ ምግቡን አውጥቼ አሸዋ ብሞላው ኖሮ፡፡ በጃኬቴ ቋጥሬ ብይዘው ኖሮ፡፡ ኖሮ፣ ኖሮ፣ ኖሮ፡፡
እንደ ገና ደግሞ ደስታ፣ ይህን እና ያንን እንኳን አደረግኩ፣ እንኳንም ተስፋ አልቆረጥኩ፣ እንኳንም አልተሸነፍኩ፣ እንኳንም ባለማቋረጥ ተጓዝኩ፣ እንኳንም ያንን ፍጡር ሰማሁት፣ እንኳንም አሸዋውን ዘገንኩ፡፡ (“the parable of the pebbles” ከሚለው የጥንት ታሪክ የተወሰደ)
አንድ ሰው በሕይወቱ መጨረሻ ሲደርስ ኀዘን ብቻ የሚሰማው ከሆነ ምንም ባለ መሥራቱ ይፀፀታል ማለት ነው፡፡ ትርጉም ያለው አንዳች ነገር ሳይሠራ፣ ኅሊናውን የሚያረካው አንዳች ነገር ሳይፈጽም ነው እዚያ የደረሰው ማለት ነው፡፡ እድሜው በርሱ ላይ ሠራ እንጂ እርሱ በእድሜው አልሠራበትም ማለት ነው፡፡ ሠርቶ ሳይሆን በልቶ ነው ያረጀው ማለት ነው፡፡
አንድ ሰው በመጨረሻ ደስታ ብቻ የሚሰማውም ከሆነ ያ የጤና አይደለም፡፡ ራሱን አያውቀውም ማለት ነው፡፡ ሰዎች የሠሩትን ሁሉ እንደ ራሱ ሥራ አድርጎ ይቆጥራል ማለት ነው፡፡ ሥራውን ለመገምገም የሚያስችል ብቃት የለውም ማለት ነው፡፡
የሚታገል ሰው፣ የሚሠራ ሰው፣ ጀግና ሰው በመጨረሻ ሁለቱም ነገሮች ናቸው የሚገጥሙት፡፡ ደስታ እና ኀዘን በአንድ ላይ፡፡ እንኳንም ሠራሁት፣ እንኳንም ታገልኩት፣ እንኳንም ወሰንኩት፣ እንኳንም እምቢ አልኩት፣ እንኳንም እሺ አልኩት፤ እያለ የሚደሰትባቸው ነገሮች አሉት፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የሚፀፀትበትም ነገር አለው፡፡ ምነው እንዲህ ባደርገው ኖሮ፣ ይህንን ባላደርገው ኖሮ፣ ይህንን ባልወስን ኖሮ፣ በእገሌ ላይ እንዲህ ባላደረግ ኖሮ፣ እንዲህ ባደርግ ኖሮ፣ ይህንን ብወስድ ኖሮ፣ ይህንን ባልወሰድ ኖሮ እያለ የሚፀፀትባቸው፡፡
ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው የሠራሁት ሁሉ፣ የታገልኩት ሁሉ፣ ያደረግኩት ሁሉ፣ ትክክል ነበረ ብሎ አይሟገትም፡፡ በዚያ ወቅት ትክክል መስሎት ቢሠራው እንኳን፣ አማራጭ አጥቶ ቢሠራው እንኳን፣ ሕግን እና ደንብ፣ ሥልጣን እና አሠራር አስገድደውት ቢሠራው እንኳን፣ አምኖበት ቢሠራው እንኳን፣ ሁሉም ነገር ግን ትክክል ብቻ ሊሆን አይችልም፡፡ እየቆየ ሲያየው የሚገለጥለት፣ እየበሰለ ሲረዳው የሚፀፀትበት፣ እየሰነበተ ሲያስተውለው ድክመት የሚያገኝበት፣ ውሎ አድሮ ሲገመግመው ባይሆን ኖሮ የሚልበት ነገርም ይኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ መከራ ያዩት ቴዎድሮስ ነገሩ ሁሉ ተበላሽቶባቸው መቅደላ ብቻ ስትቀራቸው የተናገሩትን ጸጋዬ ገብረ መድኅን በምናብ ተረድቷቸው
ከዛሬ ላይ ቁጭ ብዬ የትናንቱ ሲታወሰኝ

ከሠራሁት ነገር ይልቅ ያልሠራሁት ነው የሚቆጨኝ
ነበር ያሉት፡፡
ምንም ዓይነት ትክክል ነገር የማይሠራም ሆነ ምንም ዓይነት ስሕተት የማይሠራ ሰው የለም፡፡ ሥርዓቶች፣ ፖሊሲዎች፣ ዐዋጆችም ሆኑ አሠራሮች የሰዎች ውጤቶች ናቸውና እንከን አልባ ሊሆኑም ሆነ ጥቅም አልባ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ባይሆን የትኛው ያመዝናል? ነው ጥያቄው፡፡
ፍጻሜው ኀዘንና ደስታ መሆኑ የጤነኛነት እንጂ የስሕተት መለኪያው አይደለም፡፡ እነዚህ ነገሮቼን ዛሬ ሳስባቸው ማድረግ አልነበረብኝም ብሎ መናገር ለጠላት ከመሸነፍ ለምን ይቆጠራል? ጠላትንኮ ትክክል በመሆን ብቻ ሳይሆን ስሕተትን በማመንም ማሸነፍ ይቻላል፡፡ እነዚህን ነገሮች ማድረጌ ትክክል ነበረ ብሎ መመስከርም ከትዕቢት የሚቆጠር አይደለም፡፡ ሰው ያመነበትን ሊሟገትለት ስለሚገባ እንጂ፡፡ ችግሩ የሚከሰተው ምንም ችግር ያልፈጠሩ እና ችግር ብቻ የፈጠሩ ሰዎች ከኖሩን ነው፡፡
የደቡብ አፍሪካው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላ «ለነጻነት የተደረገ ረዥሙ ጉዞ» በሚለው መጽሐፋቸው ላይ «ላለመሳሳት ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፣ ነገር ግን በመንገዴ ላይ ብዙ ስሕተቶችን ሠርቻለሁ፡፡ ያም ቢሆን በጉዞዬ አንድ ምሥጢር ተገልጦልኛል፡፡ አንድን ተራራ ከወጣን በኋላ የምናገኘው ነገር ልንወጣቸው የሚገቡን አያሌ ተራራዎች መኖራቸውን ነው» ብለው ነበር፡፡
እናም እስኪ እንገምግመው፡፡ ባለ ትዳሮች፣ ጓደኛሞች፣ ባለ ሽርኮች፣ ማኅበርተኞች፣ ጎረቤታሞች፣ አብሮ አደጎች እስኪ ጉዟችንን እንደ ማንዴላ እንገምግመው፡፡ የግምገማችን ውጤት ኀዘን እና ደስታ ነውን?የመጀመርያዎቹን ተራሮች ወጥተናቸዋል፡፡ ማንዴላ እንዳሉትም አያሌ ተራሮች ከፊታችን አሉ፡፡ የዚህኛውን ተራራ ጉዞ ካልመረመርነው በቀጣዮቹ ተራሮችም ከዚህ የባሱ ስሕተቶች መሥራታችን አይቀርም፡፡
ሀገር የመራን፣ ሕዝብ የመራን፣ ፓርቲ የመራን፣ የታገልን፣ ያታገልን መሪዎች፡፡ የዕውቀት መሪዎች ሆነን ለሕዝብ ዕውቀት ስናቀብል የኖርን ምሁራን፣ ሊቃውንት፡፡ ሕዝብን በእምነት ጎዳና እየመራን ያለን የሃይማኖት መሪዎች፣ ተቋማት፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎች፡፡ እስኪ ረዥሙን ጉዞ እንየው፡፡ ኀዘን እና ደስታ ካመነጨልን ጤነኞች ነን፡፡ ታግለን ይሆናል፣ ተጉዘን ይሆናል፣ አያሌ ፈተናዎችን አልፈን ይሆናል፣ ብዙ አስተዋጽዖ አበርክተን ይሆናል፣ የማይተካ ሚና ኖሮን ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲደመደም ግን የሚያስደስተንም የሚቆጨንም ነገር ሊኖር ይገባል፡፡
አቡዳቢ