«ድንጋይ ፈላጮች»
click here for pdf
አንድ ጥበብ አሳሽ ጥበብን ፍለጋ በየሀገሩ ይዞር ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ አንድ መንደር ሲደርስ ሰዎች ድንጋይ ሲፈልጡ ተመለከተ፡፡ ቀና ብሎ ቢያይ በአካባቢው ምንም የሚገነባ ነገር የለም፡፡
አንድ ጥበብ አሳሽ ጥበብን ፍለጋ በየሀገሩ ይዞር ነበር፡፡ አንድ ቀን ወደ አንድ መንደር ሲደርስ ሰዎች ድንጋይ ሲፈልጡ ተመለከተ፡፡ ቀና ብሎ ቢያይ በአካባቢው ምንም የሚገነባ ነገር የለም፡፡
ወደ አንዱ ድንጋይ ፈላጭ ተጠግቶ «እባክህ ወዳጄ እኔ ለአካባቢው አዲስ በመሆኔ አንድ ነገር ልጠይቅህ ፈለግኩ፣ ለመሆኑ ምን እያደረጋችሁ ነው?»አለው፡፡ ያም ድንጋይ ፈላጭ «ወንድሜ የማደርገው ነገርኮ ግልጽ ነው፤ አንተም ታየዋለህ፤ ድንጋይ እየፈለጥኩ ነዋ»አለው፡፡ ያ ጥበብ አሳሽ ከዚያ እልፍ አለ፡፡ ወደ ሁለተኛውም ሰው ቀረበ፡፡ «ወዳጄ ለሀገሩ እንግዳ ለሰው ባዳ ነኝ፡፡ እባከህ ምን እየሠራችሁ እንደሆነ ንገረኝ?»አለው፡፡ ያም ድንጋይ ፈላጭ «ወዳጄ እኔ የዕለት እንጀራዬን ለማግኘት እየደከምኩ ነው፡፡ ይኼው ነው» ሲል መለሰለት፡፡
ጥበብ አሳሹ አንገቱን ነቅንቆ ወደ ሦስተኛው ፈላጭ ሄደ፡፡ እዚያም ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበ፡፡ ፈላጩ ቀና አለ፡፡ መፍለጫውንም ተደግፎ ቆመ፡፡ ከዚያም «እይውልህ ወዳጄ እኔ ካቴድራል እየሠራሁ ነው» አለው፡፡ ያን ጊዜም «አሁን መልሱን አገኘሁት» ብሎ ሄደ ይባላል፡፡
ዓለምን የሚለውጡት እነማን ናቸው? ችግርን የሚያሸንፉት እነማን ናቸው? ሀገርን የሚያሳድጉት እነማን ናቸው? ታላቅ ሥራ የሚሠሩት እነማን ናቸው?ድንጋይ ሲፈልጡ ካቴድራል እየገነቡ መሆኑን የሚያስቡ አይደሉምን?መሥመር ሲሠሩ ሥዕሉ የሚታያቸው አይደሉምን?ሊጡን ሲያቦኩ ዳቦው፣ ሽንኩርቱን ሲልጡ ወጡ፣ ፊደል ሲጥሉ መጽሐፉ፣ በሬ ሲጠምዱ ብልጽግናው፣ ግሬደሩን ሲጨብጡ ጎዳናው የሚታያቸው አይደሉምን?
ሦስቱም ሰዎች በተመሳሳይ ሥራ ላይ ተጠመደዋል፤ ሦስቱም ሰዎች ድካማቸው ተመጣጣኝ ነው፤ ሦስቱም ሰዎች የሚከፈላቸው አንድ ዓይነት ክፍያ ነው፤ ሦስቱም ሰዎች የያዙት መፍለጫ አንድ ዓይነት ነው፡፡ ሦስቱም ሰዎች በቀን የሚሠሩት እኩል ይሆን ይሆናል፡፡ ሦስቱን የለያቸው ግባቸው ነው፣ ርእየታቸው ነው፣ ሥዕላቸው ነው፡፡ አንዱ እጆቹ የሚሠሩትን እንጂ ሥራው የሚያመጣውን ውጤት አያውቅም፡፡ አንዱ ሥራው የሚያስገኝለትን ዕለታዊ ገቢ እንጂ ሥራው የሚፈጥረውን ትልቁን ሥዕል አያውቀውም፡፡ አንዱ ግን የሚያመጣውን ለውጥ እያሰበ ለትልቁ ሥዕል ነበር የሚሠራው፡፡
ለውጥ የሚመጣውኮ በዘመናዊ መሣርያ በመሥራት፣ በቂ በጀት በመመደብ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል በመቅጠር፣ የቢሮ ወንበር እና ጠረጲዛ በማሣመር፣ አይደለም፡፡ እነዚህ ሁሉ አጋዦች እንጂ አንቀሳቃሾች አይደሉም፡፡ ለውጥ የሚመጣው ለምንድን ነው የምሠራው? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛውን መልስ በመመለስ ነው፡፡
ምንም እንኳን በድካም፣ በክፍያ እና በመሣርያ አንድ ቢሆኑም በርካታ ግን ይለያያሉ፡፡ በርካታ ብቻ ሳይሆን በጥራትም ይለያያሉ፡፡ እነዚያ የዕለቱን ብቻ እያሰቡ ይሠራሉ፡፡ ይኼ ግን ትልቁን ሥዕል እያሰበ ለትልቁ ሥዕል የሚሆን ነገር ይሠራል፡፡ እነርሱ ለዕለት እንጀራ የሚሆን ምን ያህል ድንጋይ ፈለጥን?ብለው ይጠየቃሉ፡፡ እርሱ ግን ለካቴድራሉ የሚሆን ምን ያህል ድንጋይ አዘጋጀሁ? ብሎ ይጠይቃል፡፡ ለእነዚያ የዕለቱ ድንጋይ ተፈልጦ ሲያልቅ ሥራቸውን ይጨርሳሉ፡፡ እርሱ ግን ካቴድራሉ እስኪጠናቀቅ ሥራው አያልቅም፡፡
በየመሥሪያ ቤቱ፣ በየንግዱ ሥፍራ፣ በየግል ደርጅቱ፣ በየትምህርት ቤቱ፣ በየማኅበራቱ፣ በየፓርቲዎቹ፣ በየርዳታ ደርጅቶቹ፣ በየሕክምና ተቋማቱ፣ በየግል ኑሯችንም እነዚህ ሦስቱ ሰዎች አሉ፡፡
ሥራቸውን ለደመወዙ ብቻ የሚሠሩ አሉ፡፡ የሚማሩትም ሆነ የሚሠሩት ደመወዙን ብቻ አስበው ነው፡፡ የሥራ ዝርዝራቸውን፣ ቅጣት እና ሽልማታቸውን፣ ብቻ አይተው ነው፡፡ ሥራው ለሀገር እና ለወገን የሚያመጣውን ትልቅ ሥዕል አያስቡትም አያውቁትምም፡፡ እነዚህ ካቴድራል ገንቢዎች አይደሉም፡፡ ድንጋይ ፈላጮች ብቻ ናቸው፡፡ የክፍል ተማሪዎቹን ሲያስተምር አስተምሮ እንጀራ ለመብላት ሲል ብቻ የሚያስተምር መምህር የዘወትር ጭንቀቱ የደመወዝ ቀን መቼ ነው? የሚለው ጥያቄ ብቻ ነው፡፡
እርሱ አስተማሪ አይደለም ተናጋሪ ብቻ ነው፡፡ ለልጆቹ የታዘዘውን ይነግራቸዋል፡፡ አላስተማረም እንዳይባል፣ ሥራውንም እንዳያጣ፣ ግዴታውም ስለሆነ፣ ቅጣትም ስለሚመጣበት ብቻ ይነግራቸዋል እንጂ አያስተምራቸውም፡፡ ለምን ያስተምራቸዋል? እርሱኮ ትልቁ ሥዕል የለውም፡፡ አስተማሪ ብቻ እንጂ አገር ቀያሪ፣ ለውጥ አምጭ፣ ካቴድራል ገንቢ አድርጎ ራሱን አያየውም፡፡ የሀገሪቱ ዕጣ ፈንታ በዚያች ክፍል ተማሪዎች እንደሚወሰን አያስብም፡፡
በየቢሮው ድንጋይ ፈላጮችን ታውቋቸዋላችሁኮ፡፡ እነርሱ የተሰጠቻቸውን ሥራ ከመሥራት ያለፈ ምንም የሚያውቁት ነገር የላቸውም፡፡ ጸሐፊዋ ትጽፋለች፣ መዝገብ ቤቱ ዶክመንት ያስቀምጣል፣ ባለ ማኅተሙ ማኅተም ይረግጣል፣ ገንዘብ ቤቷ ገንዘብ ታወጣለች ታስገባለች፣ ኃላፊው ይፈርማል፣ ጥበቃው ይፈትሻል፣ ተላላኪው ይወጣል ይወርዳል፣ ሾፌሩ ይሄዳል ይመጣል፣ የመስክ ሠራተኛው ተራራ ይወጣል ይወርዳል፤ የሚሰበሰበው ይሰበሰባል፣ የሚበተነው ይበተናል፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ድንጋይ መፍለጣቸውን እንጂ ለምን እንደሚፈልጡ አያውቁትም፡፡ አገር እያሳደጉ መሆኑን፣ ለውጥ እያመጡ መሆኑን፣ ታሪክ እየሠሩ መሆኑን፣ አይረዱትም፡፡
እናም ለእነርሱ ኮምፒውተር አይሠራም ብሎ መቀመጥ አሳማኝ ምክንያት ነው፡፡ አለቀ በቃ፡፡ ኮምፒውተር አይሠራም፤ አይሠራም፡፡ ኮምፒውተሩ ሲሠራ የሚያመጡትን ለውጥ ስለማያውቁት ኮምፒውተሩ ሲቆምም የሚያስከትለውን ችግር አይረዱትም፡፡ እነርሱ ድንጋይ ፈላጮች እንጂ ካቴድራል ገንቢዎች አይደሉም፡፡ እነርሱ ሀገሪቱ ስላላደገችበት ምክንያት ተጠያቂ ነን ብለው አያስቡም፡፡ እነርሱ ያ ደብዳቤ ለምን ወጭ እንዳልተደረገ ብቻ ነው የሚጠየቁት፡፡ ለርሱ ደግሞ በቂ መልስ አላቸው፡፡ ኮምፒውተሩ አይሠራም፡፡
እኔን አይመለከትም፡፡ የተቀመጥኩት ይህንን ልሠራ አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ እኔ አልጠየቅም፡፡ የሚሉ አባባሎች ሁሉ የድንጋይ ፈላጮች መልሶች ናቸው፡፡ ድንጋይ ፈላጮች እነርሱ ምን እየሠሩ እንደሆነ እንጂ በአካባቢያቸው ምን እየተሠራ እንደሆነ አያውቁም፡፡ አንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ እንኳን ሆነው ከእነርሱ ጎን ያለው ክፍል ምን እንደሚሠራ አይረዱም፡፡ ለመረዳትም አይፈልጉም፡፡ ይህ ሥራቸው አይደለማ፡፡
በየቢሮው ግድግዳ ላይ አንድ የሚገርም ማስታወቂያ ታያላችሁ፡፡ «ከቢሮ ስትወጡ መብራት ማጠፋትዎን ይመልከቱ» ይላል፡፡ ይህንን ማስታወቂያ የሚለጥፉት የመረራቸው የአስተዳደር እና ጠቅላላ አገልግሎት ክፍሎች ናቸው፡፡ በየቢሮው ያሉት ወገኖች ይህንን ለማሰብ ማስታወቂያ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? በቃ ለእነርሱ ሥራቸው አይደለማ፡፡ የመብራት መብራት እና መጥፋት ስለሚያስከትለው ሀገራዊ ወጭ እና ቁጠባ ማሰብ የለባቸውማ፡፡ እነርሱ ድንጋይ ፈላጮች እንጂ ካቴድራል ገንቢዎች አይደሉማ፡፡
ለመሆኑ ማንን እያከምን ነው? አንድ በሽተኛ ወይስ ሀገር እያከምን ነው? ሕይወት ስለ ማትረፍ እያሰብን ነው ወይስ የካርድ ገንዘብ ስለመሰብሰብ? በሽታን ለማጥፋት እየታገለን ነው ወይስ ከበሽተኞች ለማትረፍ? የሆስፒታሉን የጥራት ደረጃ የሚወስነው ይኼን ጥያቄ በትክክል መመለስ እና አለመመለስ እንጂ ከውጭ ሀገር የተገዛ መሣርያ መኖር፣ የታዋቂ ሐኪሞች መገኘት፣ የአልጋው እና የወንበሩ ጥራት፣ ወይንም የመደኃኒቶቹ ከጀርመን መምጣት አይደለም፡፡
እኛ አንዲት ጭብጥ ወረቀት ጨባብጠን መንገድ ላይ ስንጠል ምን እያሰብን ነው?በቃ አንዲት ጭብጥ መናኛ ወረቀት፡፡ እኔ አንዲት መናኛ ወረቀት ጣልኩና ምን ይመጣል፡፡ በቃ ጣልኩ፡፡ የጽዳት ሠራተኞቹ ያነሡታል፡፡ ድንጋይ ፈላጮች እንደዚህ ነው የሚያስቡት፡፡ አንድን ነገር ለእነርሱ የዕለት ጥያቄ መልስ ይሆን ዘንድ ማድረጋቸውን እንጂ ያ መልስ የሚያስከትለውን ውጤት አያስቡትም፡፡ ግን እስኪ ቆም ብለን እንደ ካቴድራል ገንቢ ደግሞ እናስብ፡፡
በዚያች ከተማ ሁለት ሚሊዮን ሰዎች አሉ እንበል፡፡ ከሁለት ሚሊዮኖቹ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑት በየቀኑ እንዲህ እንደርስዎ ወረቀት ጨባብጠው ይጥላሉ አሉ፡፡ የአንዷ ወረቀት ክብደት አምስት ግራም ብቻ ነው እንበል፡፡ ይምቱት በአንድ ሚሊዮን፡፡ አምስት ሺ ኪሎ ቆሻሻ በየቀኑ ወደ ከተማዋ ይጨመራል ማለት ነው፡፡ ከከተማዋ ወጣ ብለው እንደ ሀገር ያስቡት፡፡ ቆሻሻው እርስዎን ከነ ቤተሰብዎ ሊውጥዎት ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ጸዳ ያለ ውብ ከተማ በፊልም ወይንም በቴሌቭዥን ሲያዩ ይመኛሉ፡፡ ከተማዎ እንዲህ ባለ መሆንዋ ይቆጫሉ፡፡ ግንኮ ያቆሸሿት እርስዎ ጭምር ነዎት፡፡ እነዚያ የሚያዩዋቸው ከተሞች በካቴድራል ገንቢዎች ንጽሕናቸው የሚጠበቅላቸው ከተሞች ናቸው፡፡ እነዚያ ከተሞች ድንጋይ ፈላጮች ደስ እንዳላቸው ያገኙትን አይወረውሩባቸውም፡፡ ልዩነቱ እዚህ ላይ ነው፡፡
ውኀው ከቧንቧው ላይ ጠብ ጠብ ጠብ ሲል እያዩት ነው አይደል፡፡ ዘጉት ወይስ አለፉት?ለምን ይዘጉታል፤ እርስዎ አይከፍሉበት፡፡ ደግሞ ሥራዎ አይደለም፡፡ ምን ጥልቅ አደረገዎት፡፡ በወሩ መጨረሻ ሂሳብ ሲቆነድደው ባለቤቱ ራሱ ያሠራው የለ፡፡ ይሄ ነው የድንጋይ ፈላጮች አስተሳሰብ፡፡ እያንዳንዷን ጠብታ ውኃ ከወንዝ ወይንም ከሐይቅ ለማምጣት፣ ለማጣራት፣ በቧንቧ ለማስተላለፍ ስንት ወጭ ወጥቷል? ይህ የወጣው ገንዘብ ደግሞ ከእኔ ኪስ የሚወጣ ግብር ነው፡፡ በእያንዳንዷ ጠብታ ውኃ የተነሣ ስንት የሀገር ገንዘብ ይባክናል? ይህቺን ውኃ እኔ ብዘጋት ስንት የሀገር ወጭ አተርፋለሁ? ብለው ካሰቡማ ካቴድራል ገንቢ ሊሆኑ ነው፡፡
ለውጥ ለለውጥ በቆረጡ፣ መለወጥ እንችላለን ብለውም በሚያስቡ፣ ከዕለት ጉዳይ አልፈው ታላቁን ሥዕል ለማየት በሚችሉ ሰዎች የምትመጣ ናት፡፡ በመሥራት ብቻ አትመጣም፡፡ በመፈክር አትመጣም፣ በሰልፍ አትመጣም፣ በስብሰባ ብቻ አትመጣም፡፡ ቃል በመግባት ብቻ አትመጣም፡፡ በውብ ፖሊሲዎች ብቻ አትመጣም፡፡ እርሱ የሚፈልጣት ድንጋይ ካቴድራሉን የምትገነባው እርሷ መሆንዋን ተረድቶ ለትልቁ ካቴድራል የሚሆን ውብ፣ ጠንካራ፣ አስተማማኝ፣ ተገቢ፣ ድንጋይ በሚያዘጋጅ ገንቢ ነው የምትመጣው፡፡ እንዲሁ በሚፈልጥ ብቻ አትመጣም፡፡ ለውጥ እጅ ላይ አይደለችም አእምሮ ውስጥ ናት፡፡
ታክሲ ነጅው፣ ወያላው፣ የአውቶቡስ ሾፌሩ፣ አስተናጋጁ፣ ጉልት ሻጯ፣ የሱቁ ባለ ቤት፣ ምግብ አብሳዩ፣ ሞግዚቷ፣ ፖሊሲ አውጭው፣ ዳኛው፣ ፖሊሱ፣ ዐቃቤ ሕጉ፣ ጠበቃው፣ የፓርላማ አባሉ፣ ካድሬው፣ የሂሳብ ባለሞያው፣ ኦዲተሩ፣ ወታደሩ፣ ጋዜጠኛው የየራሱን ሥራ ለትልቁ ሥዕል እያሰበ ሲሠራ ነው ለውጥ የሚመጣው፡፡ ሁላችንም በተመሳሳይ ደረጃ፣ ፍጥነት፣ ዐቅም፣ ችሎታ፣ ዕውቀት እና ሥልጣን አንድ ዓይነት ተግባር ልንከውን አንችልም፡፡ የተለያየ ፍላጎት፣ የተለያየ መንገድ፣ የተለያየ ርእዮት፣ የተለያየ ስትራቴጂ፣ የተለያየ ደረጃ ሊኖረን ይችላል፡፡ አንድ ነገር ላይ ግን መግባባት አለብን፡፡ የሁላችንም ጥረት ካቴድራሉን ለመገንባት መሆኑን፡፡
ካቴድራሉን ለመሥራት የብዙ ድንጋይ ፈላጮችን ላብ፣ ችሎታ እና ጊዜ ይጠይቅ ይሆናል፡፡ ብዙ ትውልድ ይሳተፍበት ይሆናል፡፡ በአንድ ዕለት አያልቅ ይሆናል፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቹ ካቴድራሉ ተገንብቶ ለማየት አይታደሉ ይሆናል፡፡ አንዳንዶቹም ከካቴድራሉ ጥቅም ላይቋደሱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሁላችንም ለካቴድራሉ ግንባታ አስተዋጽዖ ማድረግ አለብን፡፡ መኖር ማለት ከመኖር በላይ ለሆነ አንዳች ነገር አስተዋጽዖ ለማድረግ መቻል ነው፡፡ የመኖራቸውን ያህል የሚሠሩ እንስሳት ናቸው፡፡
ካቴድራሉ ያማረ የሚሆነው ድንጋዩን የሚያዘጋጀው፣ በሩን የሚሠራው፣ መስተዋት የሚቀርጸው፣ መብራት የሚተክለው፣ ወለል የሚያነጥፈው፣ ቀለም የሚቀባው፣ ግድግዳ የሚለስነው፣ ጣራ የሚመታው፣ ውስጡን የሚያሳምረው፣ ስለ ካቴድራሉ ውበት እያሰቡ እነርሱ የየራሳቸውን ድርሻ ወብ አድርገው ከሠሩት ብቻ ነው፡፡ እያንዳንዱ ውብ አድርጎ ያልሠራውን፣ ድምሩ እንዴት ውብ ይሆናል?
ወዳጄ! ለውጥ፣ ዕድገት፣ ብልጽግና፣ የተሻለ አሠራር፣ የተሻለች ዓለም፣ ሥልጣኔ ከሌላ ቦታ ይመጣል ብለህ አትጠብቅ፡፡ ያለው በአንተ እጅ ነው፡፡ ለውጥ ከሩቅ አይጀመርም እዚሁ ካንተ ዘንድ ነው፡፡ ጀግኖች ሌሎች አይደሉም፤ አንተ ነህ፡፡ ቤትህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ ትዳርህን የተሻለ ዓለም ማድረግ ትችላለህ፡፡ መሥሪያ ቤትህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ ንግድህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ ሆስፒታልህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ ጉልትህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ የጫማ መስፊያ ቤትህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ አሠራርህን መለወጥ ትችላለህ፡፡ ትልቁን ሥዕል እያሰብክ ከሠራህ፡፡
የግድ የሀገሪቱ መመርያ እስኪለወጥ፣ ቢ ፒ አር እስኪሠራ፣ ሥልጠና እስኪሰጥህ፣ መመርያ እስኪወጣ፣ ቅጣት እስኪጣልበህ፣ ውድድር እስኪመጣ፣ ጓደኛህ እስኪበልጥህ፣ በስብሰባ እስኪነገርህ፣ አለቃህ እስኪስማማ፣ ውሳኔ እስኪወሰን፣ የሌላ ሀገር ልምድ እስኪቀሰም ለምን ትጠብቃለህ? «ልታየው የምትፈ ልገውን ለውጥ መጀመሪያ አንተው ራስህ ሁነው» ይልሃል ማኅተመ ጋንዲ፡፡
በአንዲት ጎጆ ውስጥ ዘመንዋን ሁሉ የኖረች አንዲት ሴት ነበረች፡፡ ቀኑን ሙሉ በሥራ ስትደክም ውላ ማታ የምትጽናናው አጋፔ በምትባለው ወፏ ነበር፡፡ ይህንን ነገር ያወቁ ሁለት ጎረምሶች ተመካከሩና አንድ ቀን በሌለችበት ቤቷን ሠብረው ወፏን ወሰዱባት፡፡
ማታ ስትመጣ ቤቷ ተሰብሯል፡፡ ወፏም የለችም፡፡ ደንግጣ ፍለጋ ስትወጣ ሁለቱን ወጣቶች አገኘቻቸው፡፡ ወደ እርሷም ቀረቡና ሁለቱን እጆቻቸውን ጨብጠው፡፡ «እማማ ወፏ በእጃችን ውስጥ ናት፡፡ ግን አንድ ጥያቄ እንጠይቅዎትና መልሱን ከመለሱ እንሰጥዎታለን´ አሏት፡፡
«ምን?» አለቻቸው፡፡
«ወፏ አለች ወይስ ሞታለች?»
አሰበች፡፡ ሞታለች ብትላቸው መልሱን አላገኘሽም ብለው ይለቋታል፡፡ ከዚያም በኋላ አታገኛትም፡፡ አለች ብትላቸውም ተሳስተሻል ብለው በእጃቸው ጨፍልቀው ይገድሏታል፡፡
እናም በመጨረሻ እንዲህ አለቻቸው «መኖርዋም መሞቷም በእጃችሁ ውስጥ ነው»
ኢትዮጵያም እንዲህ ናት፡፡
አቡዳቢ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬት
© ይህ ጽሑፍ በሮዝ አሳታሚ ኃ. የተወሰነ የግ.ማ በሚታተመው “አዲስ ጉዳይ መጽሔት” ላይ ያወጣኹት ነው። ጽሑፎቹን በድጋሚ በመጽሔት፣ በጋዜጣ ወይም በተመሳሳይ የሕትመት ውጤት ላይ ማተም አይገባም።