እስከ ሰባት ትውልድ

በበዙ የሀገራችን ጥንታውያን መጻሕፍት እና ትውፊቶች ዘንድ ሰባት ትውልድ የሚለው ብሂል የተለመደ ነው፡፡ «እስከ ሰባት ትውልድ እምርልሃለሁ» የሚለው ቃል በየገድላቱ ይገኛል፡፡ እስከ ሰባት ትውልድ አለመጋባት በአያሌ ማኅበረሰቦቻችን ትውፊታዊም ሃይማታዊም ሕግ ነው፡፡
ከቀደምት የአሜሪካ ሕዝቦች አንዱ የሆኑት የኢሮቆዩስ ሕዝቦች በዚህ የሰባት ትውልድ አስተሳሰብ ያምኑ ነበር፡፡ እነዚህ በዛሬዋ ኒውዮርክ እና አካባቢዋ የነበሩ ጎሳዎች ተባብረው የኢሮቆዩስ ፌዴሬሽን የሚባል አስተዳደር መሥርተው ነበር፡፡ የራሳቸውም ሕገ መንግሥት ነበራቸው፡፡ አሜሪካኖቹ የፌዴራሊዝምን ጽንሰ ሃሳብ የወሰዱት ከእነዚህ ማኅበረሰቦች ነው ብለው የሚከራከሩም አሉ፡፡
 ከ500 ዓመታት በፊት በተጻፈው በኢሮቆዩስ ሕገ መንግሥት ውስጥ ይገኙ ከነበሩት ሕጎች አንዱ እንዲህ ይላል «በኮንፌዴሬሽኑ ውስጥ ስታገለግሉ፣ ሕግ ስታወጡ፣ የመንግሥትንም ሥራ ስታከናውኑ፣ የግል ፍላጎታችሁን ወዲያ አውልቃችሁ ጣሉት፤ ስሕተት ትሠሩ ዘንድ የሚገፋፏችሁን የእኅት እና የወንድ ሞቻችሁን ግፊቶች በኋላችሁ ተዋቸው፤ ነገር ግን እውነት እና ርቱዕ ወደ ሆነው ወደ ታላቁ ሕግ ተመልከቱ፡፡ ለሕዝቡ የሚበጀውን ስሙ፣ ተመልከቱም፡፡ ስትሠሩም የአሁኑን ብቻ ሳይሆን መጭውን ትውልድም አስቡ፤ ገና ይህችን መሬት ያላዩትን፣ ያለተወለዱትን መጭዎቹን ትውልዶች፡፡ የመሪዎች ቆዳ ስስ መሆን የለበትም፤ እንዲያውም ከሌላው ሰባት ጊዜ እጥፍ የወፈረ መሆን አለበት፡፡ ቁጡነትን፣ ተናዳ ፊነትን እና ትችትን መቋቋም እንዲችሉ፤ ይህንንም ሁሉ ታግሠው ትክክለኛ ውሳኔ እንዲሰጡ» ይላል፡፡
«በማናቸውም ውሳኔ ጊዜ ውሳኔያችን በሚቀጥሉት ሰባት ትውልዶች ላይ የሚያመጣውን ነገር አስቀድመን ማሰብ አለብን» የሚለው ብሂል እጅግ ከሚጠቀሱት የኢሮቆዩስ አባባሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ አያሌ የፖሊሲ ባለሞያዎች በየአጋጣሚው የሚያነሱት በተለይም የአካባቢ ጥበቃ ባለሞያዎች የሚከራከሩለት መርሕ ነው፡፡
እንስሳት ያለፈ ታሪክም ሆነ የሚመጣ ተስፋ የላቸውም፡፡ ስለዚህም ለልጅ ልጆቻቸው የሚያስቡትም የሚያስቀምጡትም ነገር የለም፡፡ የእነርሱ ውሳኔ በደመ ነፍስ እና ለጊዜው የሚረዳ ብቻ ነው፡፡ ሰው ግን ከዚህ ይለያል፡፡ የትናንት ታሪክም የነገ ተስፋም አለው፡፡ ከፋም ለማም ሰው የራሱ ዘመን ብቻ ውጤት አይደለም፡፡ ያለፉት ትውልዶች ውሳኔ እና ተግባር ውጤትም ጭምር ነው፡፡ ወላጆቻችን የሚወስኑት ውሳኔ የነገ ማንነታችንን ይወስነዋል፡፡ አስተዳደጋቸው፣ አመራራቸው፣ የሚያስገቡን ትምህርት ቤት፣ የሚያሟሉልን ነገሮች እና የቤተሰቡ አያያዝ ማንነታችንን ይቀርፀዋል፡፡
እነርሱም ቢሆን እነዚህን ነገሮች በእኛ ላይ እንዲወስኑ የሚያደርጓቸው ካለፉት ወላጆች ያገኟቸው ቅርሶች፣ ልምዶች፣ ሀብቶች እና ጠባዮች ናቸው፡፡ እንዲህ እያለም ይቀጥላል፡፡ ሰው የትናንቱን መተው፣ ለነገውም አለመጨነቅ የማይችለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ወደድንም ጠላንም ይህ ትውልድ የዐፄ ቴዎድሮስ፣ የዐፄ ምኒሊክ፣ የዐፄ ኃይለ ሥላሴ እና የደርግ ፖሊሲዎች፣ አሠራሮች፣ አስተሳሰቦች፣ ውሳኔዎች እና ሥራዎች ውጤት ነው፡፡ ቢፈልገውም ባይፈልገውም የእነርሱ ተጽዕኖ እንዲህ አድርጎ ፈጥሮታል፡፡ በጎ ተግባራቸው ጠቅሞታል፡፡ ስሕተታቸውም ጎድቶታል፡፡ ወይ ሥራ ቀንሶለታል፤ ወይ ሥራ ጨምሮበታል፡፡ የኢሕአዴግም አመራር፣ አሠራር እና አስተሳሰብ እንደዚሁ በቀጣይ ትውልድ ላይ መንፀባረቁ የማይቀር ነው፡፡
እስኪ ፖሊሲዎቻችን እና መመሪያዎቻችን ይታዩ፤ በቀጣዮቹ ሰባት ትውልዶች ላይ ምን ያመጣሉ? እስኪ የምንገነባቸው ግንባታዎች ይመርመሩ? በቀጣዮቹ ሰባት ትውልዶች ዘንድ ምን ያስከትላሉ? የተዋዋልናቸው ውሎች፣ የተበደርናቸው ብድሮች፣ የዘረጋናቸው መሥመሮች፣ የመሠረትናቸው አስተዳደሮች፣ ያቋቋምናቸው ድርጅቶች፣ የፈጠርናቸው ባህሎች፣ ያመጣናቸው አስተሳሰቦች በቀጣዮቹ ሰባት ትውልዶች ዘንድ ምን ሊያመጡ ይችላሉ?
እኛ ስንሞት ሰርዶ ሳይሆን ሀገር ናት መብቀል ያለባት፡፡ ስለ ሰባት ትውልድ የማናስብ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እያንዳንዱ ትውልድ እንደገና እያፈረሰ የሚሠራት ሀገር ትሆናለች፡፡ ለሰባት ትውልድ ያሰቡ የአሜሪካ መሥራች አባቶች የሠሩት ሕገ መንግሥት እየተሻሻለ ላለፉት ሦስት መቶ ዓመታት ጸንቷል፡፡ ትውልድ አልፎ ትውልድ ሲተካ በአባቶቹ መሠረት ላይ እየመሠረተ ሕንፃውን እንዳይፈርስ መጠበቅ፣ ይበልጥ ማስዋብ እና የተሻለ ነገር መጨመር እንጂ ከሥር ከመሠረቱ ሲንደው አልታየም፡፡
እኛ ግን የንጉሡን ሕገ መንግሥት ትቶ ደርግ ሌላ አወጣ፣ የደርግን ሕገ መንግሥት ሠርዞ ኢሕአዴግ ሌላ አረቀቀ፡፡ ነገ የሚመጣው ትውልድም የቀደመውን እየሠረዘ እና የየራሱን ሕገ መንግሥት እያረቀቀ የሚሄድ ከሆነ ኢትዮጵያ ማለት እንደ ልጆች ጨዋታ በየጊዜው እየፈረሰች የምትሠራ የዕቃ ዕቃ ቤት ሆነች ማለት ነው፡፡ የሦስት ዘመን ነጻነት ታሪክ እየተናገረች ሁሌ ግን ነጻ የምትወጣ፡፡ «ሀገረ አግዓዝያን» እየተባለች ነገር ግን አያሌ ነጻ አውጭዎች ያሉባት ሀገር፡፡
 በ13ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው የጎጃሙ ባለ ቅኔ ተዋነይን ሊጠይቀው ንጉሡ እስክንድር ሄዶ ነበር አሉ፡፡ እንዴት አድርጌ ሀገር ልምራ? ሲል ጠየቀው፡፡ ተዋነይ እንዲህ አለ «ለመሆኑ ስንት ዓይን አለህ ንጉሡም መለሰለት «ሁለት ዓይኖች አሉኝ»፡፡ «መልካም» አለ ተዋነይ፡፡ «አንዱን ዓይንህን አሁን ያለህበትን ዘመን እይበት፤ በሁለተኛው ዓይነህ ግን ነገ የሚመጣውን እይበት፡፡ የዛሬን እና የነገን በሁለቱ የዓይን ሚዛን መዝነህ ሚዛን ሲደፋልህ ሥራ» አለው ይባላል፡፡
የሕዝብ መሪዎች ሁለቱን ዓይናቸውን እንደ ተዋነይ ምክር መጠቀም ቢችሉ እንዴት መልካም ነበር፡፡ ነገን ብቻ ሳይሆን ዛሬንም፣ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም ጨምሮ ማየት፡፡ በመስቀል ጦርነት የአውሮፓን ጦር አሸንፎ ኢየሩሳሌምን የተቆጣጠራት ሳላህዲን የሚነገርለት አንድ አስተውሎት አለው፡፡ ኢየሩሳሌምን ከተቆጣጠረ በኋላ የክርስቶስን መቃብር ለማየት ወደ ጎልጎታ መጥቶ ነበር፡፡ በዚያ የነበሩ ክርስቲያኖች ቦታውን እያስጎበኙት እያለ የስግደት ሰዓት ደረሰበት፡፡ ጒብኝቱንም አቋርጦ ወጣ፡፡ በወቅቱ የነበሩት መነኮሳት እዚያው እንዲሰግድ ጠየቁት፡፡ ሳላህዲን ግን አርቆ አስተዋይ ነበርና «አይሆንም፤ እኔ እዚህ ከሰገድኩ ወደፊት የሚመጡ ሰዎች ሳላህዲን የሰገደበት ነው ብለው በዚሁ ይቀጥላሉ፣ ለእናንተ መልካም አይሆንም» አለና ከጎልጎታ ወጣ ብሎ በነበረው ቦታ ላይ ሰገደ፡፡
ያለው አልቀረም፡፡ በሰገደበት ቦታ ላይ መስጊድ በኋላ ዘመን ተሠርቶበታል፡፡ ሳላህዲን በጎልጎታ ቢሰግድ ኖሮ በክርስቲያኖች እና በሙስሊሞች መካከል ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ቦንብ ይጠመድ ነበር፡፡ በሳላህዲን አስተዋይነት ቀረ እንጂ፡፡
በሀገራችን «ጉድጓድ ስትቆፍር ማን እንደሚወድቅበት አታውቅምና እጅግ አታርቀው» ይባላል፡፡ ምናልባት ቆፋሪው ራሱ ሊወድቅበት ስለሚችል፡፡ ትናንት በግዴለሽነት የጻፍናቸው እና የተናገርናቸው ነገሮች ሰባት ትውልድ ቆጥረው ዛሬ ዛሬ ጎሳ ከጎሳ እያባሉን፣ ሕዝብ ከሕዝብ እያዋቀሱን እና ዋጋ እያስከፈሉን ናቸው፡፡ መሪዎቻችን ቤተ መንግሥቶቻቸውን እንጂ እሥር ቤቶችን በሚገባ አልሠሩልንም፡፡ እንኖራለን እንጂ እንታሠራለን ብለው ስላላሰቡ፡፡ በሚገባ ያልተሠሩት እሥር ቤቶች ግን ከታሠረው ተራ ሕዝብ ይልቅ የጎዱት የታሠሩትን እና የሚታሠሩትን መሪዎች ነው፡፡ ድኻውማ ያንን ችግር ቀድሞ ያውቀዋል፡፡ እነርሱ እንጂ፡፡
የኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በአዲሱ ትውልድ ዘንድ 1960ዎቹ ብቅ ሲል በግደል ተጋደል መርሕ ነበር የተቀጣጠለው፡፡ አንዱ ቀይ ሲል ሌላው ነጭ ሽብር እየወለደ ነበር የተካሄደው፡፡ ምታ፣ ደምስስ፣ ርምጃ ውሰድ፣ ረፍርፍ፣ በሚሉ ቃላት ነበር የታጀበው፡፡ ትውልድ ያረደው የጦስ ዶሮ ይኼው እኛ ዘመን ደርሶ ትውልድ ከአሣሪ እና ታሣሪ፣ ከደምሳሽ እና ተደምሳሽ፣ ከመቺ እና ተመቺ፣ ከሕዝብ እና ፀረ ሕዝብ ፖለቲካ መላቀቅ አልቻለም፡፡
እኔ ለልጆቼ ቆሎው ያርብኛል
ያባቴ ውቃቤ ያስገፈግፈኛል
አለች አሉ ሴትዮዋ፡፡ እርሷ በድህነት ጉልት ሽጣ የምትኖር ነበረች አሉ፡፡ ለልጆቿ የላመ የጣመ መብላት ቀርቶ ቆሎ ቆርጥመው ለማደር እንኳን ይቸገሩ ነበር፡፡ በየዓመቱ ግን «የአባቷ ውቃቤ» እያስጓራ ሲያንዘፈዝፋት ለፍታ ባጠራቀመችው ገንዘብ ወሰራ ዶሮ አርዳ ትለማመነው ነበር፡፡ የውቃቤ ዶሮ ሦስት ጊዜ በጭንቅላት ላይ ዙሮ መንገድ ይጣላል እንጂ ሰው አይበላውም፡፡ እነዚያ ድኾች ልጆቿ የዶሮን ድምፅ ሰምተው እንጂ በልተው አያውቁም፡፡ ከአያት ከቅድመ አያቶቿ የተቀበለችው ውቃቤ ግን ዶሮ እያረደች እንድትበላ ሳይሆን ዶሮ እየወረወረች እንድትኖር ያደርጋታል፡፡
እንዴው ግን እኛም ውቃቤ ይኖርብን ይሆን እንዴ? ለልጆቻችን የሚያስፈልገውን፣ ለሀገር የሚጠቅመውን አስትቶ ለዕለት ዛር መወጫ ሲያስደገድገን የሚኖር፡፡ አንዳንዴ የምንሠራቸውን ለአፍታ፣ ለጊዜው፣ ለሆነ ችግር መወጫ፣ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ፣ የሚውሉ ነገሮች ስታዩ ውቃቤ ያለብን እንጂ ለሰባት ትውልድ የሚሆን ኃላፊነት የተጣለብን ዜጎች አንመስልምኮ፡፡
አሜሪካ ዛሬ የምትቸገርበትን የኢራን የኒኩልየር መሣርያ ለኢራን ያመጣችላት ራሷ ናት፡፡ ኢራናውያን ኒኩልየር እንኳን መኖሩን በማያውቁበት ዘመን በራቸውን አንኳኩታ ኑክልየርኮ ለኃይል ምንጭ ይጠቅማል ግዙኝ ብላ የሄደችው ራሷ ነበረች፡፡ ይኼው አሁን ማጣፊያው አጠራት እንጂ፡፡
እናም ከመወሰናችን፣ ከመገንባታችን፣ ከመሸጣችን እና ከመግዛታችን፣ ከመጻፋችን እና ከመዝፈናችን፣ ከማስተማራችን እና ከመግለጣችን፣ ከማደራጀታችን እና ከማዋቀራችን፣ ከማወጃችን እና ከመፍረዳችን በፊት ይህ ጉዳይ እስከ ስንት ትውልድ ሊጠቅም እንደሚችል ለአፍታ እናስብ፡፡ ለልጆቻችን ውቃቤ እንዳናወርሳቸው፡፡
አቡዳቢ