እኔም ለውጥ አመጣለሁ
እጅግ ሞቃት የሆነ የበጋ ጊዜ ነበር፡፡ በአካባቢው ኃይለኛ ዝናብ አንዳንድ ጊዜም ነጎድጓድ እና መብረቅ እየቀላቀለ ይጥላል፡፡ ፀሐይ ብቻዋን ስትወጣ የአካባቢው ሰዎች ከየቤታቸው ይወጡና ለመንደርዋ ውበት ወደ ሰጣት የባሕሩ$ ዳርቻ ያመራሉ፡፡ ለአመል የምትሆን ብጢሌ ጨርቅ ገላቸው ላይ ጣል ያደርጉና አሸዋው ላይ ተዘርግተው የባሕሩን ነፋስ እና የፀሐይዋን ሙቀት ይኮመኩማሉ፡፡
ዛሬ ግን እንዲህ ማድረግ አልተቻለም፡፡ ዝናቡ ሌሊት ነው የጀመረው፡፡ አብረውት ነጎድጓድ እና መብረቅ ያጅቡታል፡፡ ጋብ አለ ሲባል ደግሞ ውሽንፍር ይነሣል፡፡ ባሕሩም በውሽንፍሩ ቀስቃሽነት ከሥሩ እየተነሣ ዳንግላስ ወደ የብሱ ይጋልባል፡፡ ከዚያም አረፋ ደፍቆ ለምድሪቱም የአክብሮት ስግደት ሰግዶ ይመለሳል፡፡
ከእኩለ ቀን በኋላ ዝናብ እና መብረቁ ቆመ፡፡ ነፋሱ ግን ባሕሩን ማሰገዱን አልተወም፡፡ አካባቢው በቅዝቃዜ ተሞልቶ መንደርተኞቹ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ከመውጣት ይልቅ እሳት እያነደዱ በየቤታቸው እንዲቀመጡ አደረጋቸው፡፡
አንዲት በዐሥርዮሽ ውስጥ ያለች ልጃገረድ ግን ጥቁር ካፖርቷን ለበሳ፣ ቦት ጫማዋንም ተጫምታ፣ ከነፋሱ ጋር እየታገለች ወደ ባሕሩ ዳርቻ ስትሄድ ታየች፡፡ ጃኬቷን አስወልቆ ለመውሰድ ከሚታገለው የባሕሩ ነፋስ ጋር በሁለት እጆቿ የጃኬቷን ጫፍ እና ጫፍ በመያዝ እየተፎካከረች በጽናት ወደ ባሕሩ ዳር ታመራ ነበር፡፡ አልፎ አልፎ ነፋሱ በፀሐይዋ ሲሸነፍ ቀና ብላ የምስጋና ያህል እያየቻት ባሕሩ ዳር ዘለቀች፡፡
በባሕሩ ዳርቻ ስትጓዝ አካባቢው በቀያይ ነገሮች ተሞልቶ አየች፡፡ በነፋሱ የተገፋው ባሕር እንድ ጋላቢ እየሰገረ መጥቶ የብሱ ላይ ሰግዶ ሲመለስ እንድ ግብር ኮከብማ ዐሦችን እየተፋ መሬት ላይ ጥሏቸው ይሸሽ ነበር፡፡ ከሌሊት ጀምሮ እዚያ ዳርቻ የተተፉት ዐሦች አልፎ አልፎ በሚመጣው የባሕሩ ውኃ ነፍስ እየዘሩ ለመኖር ሲታገሉ ቆዩ፡፡ አሁን ግን ዝናቡም አቆመ፡፡ ነፋሱም ጋብ እያለ ነው፡፡ የባሕሩ ውኃም ወደ ዳርቻው መገንፈሉን ትቷል፡፡ ፀሐይዋ ደግሞ እየጋለች በመውጣት ላይ ናት፡፡ እናም ዐሦቹ ከመኖር ወደ አለመኖር ሊሰናበቱ ነው፡፡
ያቺ ለግላጋ ልጃገረድ ይህንን ነበር ያየቺው፡፡ አሁን እዚህ አካባቢ ትልልቅ ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ ስለ ዓሣ የሚያውቁ ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ ልምድ ያላቸው ሰዎች ቢኖሩ ኖሮ፣ የባሕሩ አጽጂዎች ቢኖሩ ኖሮ እያለች አንዳች ተአምር ጠበቀች፡፡ ዓሣዎቹን ማዳን የሚችል ዐቅም ያለው ፈለገች፡፡ ግን ከእርሷ ሌላ በአካባቢው ለጊዜው ማንም አልነበረም፡፡
ድንገት አንዳች ነገር መጣላት እና ጎንበስ አለች፡፡ ከዚህ በፊት በሕይወት ያለ ኮከብማ ዐሣ በእጇ ነክታ አታውቅም፡፡ አንዱን ኮከብማ ዐሣ አንሥታ ወርውራ ወደ ባሕሩ መለሰቺው፡፡ ባሕሩ ላይ ሲደርስ ዋኝቶ ሲሰምጥ አየቺው፡፡ እናም ያደረገቺው ነገር ትክክል መሆኑን አረጋገጠች፡፡ ቀጠለቺና ሌላውን፣ ሌላውን፣ ሌላውን፣ ሌላውን፣ ጎንበስ ቀና፣ ጎንበስ ቀና፣ ጎንበስ ቀና እያለች ዐሣዎቹን ወደ ባሕራቸው መመለስ ቀጠለች፡፡ እየደከማት፤ ጫን ጫንም እየተነፈሰች ቀጠለች፡፡
እርሷ ጎንበስ ቀና እያለች ኮከብማ ዐሦችን ወደ ባሕሩ ስትመልስ በአጠገቧ የነፋሱን እና የዝናቡን መቆም ተከትሎ የመጣ አንድ ሰው ገርሞት እየተመለከታት መሆኑን አላወቀቺም ነበር፡፡ ሌላም ሰው ተከተለው፣ ሌላም መጣ፣ ሌላም፣ ሌላም፣ ሌላም፡፡ አያሌ ሰዎች ተሰብስበው ለግላጋዋ ልጃገረድ የምታደርገውን ይመለከቷት ነበር፡፡ እርሷን ለማገዝ የፈለገ አንድም ሰው አልነበረም፡፡ እርስ በርሳቸው እየተያዩ የምትሠ ራውን ብቻ ይመለከቱ ነበር፡፡
በዚህ መካከል አንዱ «ይቺ ልጅ ዕብድ መሆን አለባት» አለ፡፡
«ምን ጥርጠር አለው» አለ ደግሞ ሌላው
«ዕብድ ባትሆንማ በዚህ ብርድ በሺ የሚቆጠሩ ዐሣዎችን እያነሣች ትወረውር ነበር» ሌላው አጽንዖት ሰጠ፡፡
«አሁን እርሷኮ አዲስ ነገር ያየች መስሏት ነው፡፡ በየበጋው ኮከብማ ዓሣዎችን ባሕሩ እያመጣ መዘርገፉ የተለመደ ነው፡፡ በያመቱ ስንት እና ስንት ይሞታሉ፡፡ የተለመደ ነው፡፡» ሌላው ታሪክ ጨመረበት፡፡
«ደግሞስ ቢሆን»አለ ሌላው «እነዚህን በሺዎች የሚቆጠሩ ኮከብማ ዐሣዎች ለቅማ እንዴት ትጨርሳለች፡፡ ለቅማ ከመጨረሷ በፊት እርሷ ደክሟት ትዘረጋለች፡፡»
«አሁን እርሷ ዐሥር ዐሣዎችን አዳነች አላዳነች ምን ለውጥ ይመጣል?» ሌላው ጠየቀ፡፡
«መንደርተኞቹ ወሬ እየተቀባበሉ ዳርቻውን ሞሉት፡፡ ልጂቱን የሚረዳት አልነበረም፡፡ አያሌ ትቺቶች እና ስድቦች ግን ይወርዱባት ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ክብ እየሠሩ ይወራረዱ ነበር፡፡ አንዳንዶቹም ስለ ኮከብማ ዐሣ የተማሩትን እየተነተኑ ነበር፡፡ ሌሎቹም በሌሎች አካባቢዎች በኮከብማ ዐሦች ላይ ስለደረሱ ጉዳቶች የሰሙትን በመግለጥ ላይ ነበሩ፡፡
ልክ በዚህ ሰዓት በአካባቢው ሰዎች ዘንድ እንደ ጥበበኛ እና ዐዋቂ የሚታይ አንድ ሰው መጣ፡፡ እጆቹን ደረቱ ላይ አጣጥፎ ያቺ ለግላጋ ወጣት ስታደርገው የነበረውን ሁሉ በዐጽንዖት ተመለከተ፡፡ ከዚያም ወደ ልጂቱ በቀስታ አመራና «ትንሿ ልጅ» ሲል ጠራት፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ ቀና ብላ አካባቢዋን አየቺው፡፡ ዳርቻውን መንደርተኞቹ ሞልተውታል፡፡ ትቺቱን እና ስድቡን፣ ሃሳቡን እና አስተያየቱን ሰማቺው፡፡ ሰውዬውም ወደ እርሷ ደረሰ፡፡
«ልጄ በሺዎች የሚቆጠሩ ኮከብማ ዐሣዎች በባሕሩ ውኃ ታጥበው በዳርቻው ላይ ተዘርግተው እያየሽ እንዴት ለውጥ የማያመጣ ሥራ ትሠሪያለሽ?» ሲል ጠየቃት፡፡ የከበቧት ሁሉ አንገታቸውን በስምምነት ነቀነቁ፡
«ምናለ አጉል ድካምሸን ትተሽ እንደ ጓደኞችሽ ብትጫወቺ» አለና መከራት፡፡
ሞቋታል፣ ደክሟታል፣ እናም ዕንባ ዕንባ አላት፡፡ ያንን ሰው ትኩር ብላ አየቺው፤ ከዚያም የከበቧትን ሁሉ ተመለከተቻቸው፡፡ ድንገት ሁሉም አንድ ጊዜ እንደ ብራቅ ሳቁባት፡፡
«አሁን አንቺ ምን ለውጥ አመጣለሁ ብለሽ ነው?» አላት ዐዋቂው ሰው፡፡
ሁሉም ጸጥ ብለው ምላሿን መጠባበቅ ያዙ፡፡
ምናልባት እርሱ እውነት ይሆን ይሆን? ምናልባትም እነዚህ ሰዎች እውነታቸውን ይሆን? ይህንን ያህል ሰዓት መድከሜ ምንም ለውጥ አያመጣ ይሆን? ከእኔ በፊት እንደዚህ ደክመው ሰዎች ምንም ለውጥ አላመጡ ይሆን? ሰዎች የሳቁት እነዚያ ለውጥ ሳያመጡ እኔ እንዴት ለውጥ ላመጣ እችላለሁ ብለው ይሆን? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ያልገባቸውን እንዴት እኔ ብቻ ይገባኛል? እነዚህ ሁሉ ሰዎች ያልተቀበሉት ነገርስ እንዴት ትክክል ይሆናል? ይህ ዐዋቂ ሰው ነው፡፡ መንደርተኞቹም ምክር የሚጠይቁት እርሱን ነው፡፡ ይህ ዐዋቂ ሰው ከእኔ የተሻለ ያውቃል፡፡ ታድያ እንዴት ከእርሱ እበልጣለሁ ብዬ እቀጥላለሁ? ታሰላስል ጀመር፡፡
ቀና ብላ አየች፡፡ ኮከብማ ዐሣዎች ገና ዳርቻውን እንደሞሉት ናቸው፡፡ ደክሟታል፡፡ ርቧታል፡፡ ክንዶቿ ዝለዋል፡፡ ምን ያህል ሰዓት ሊወስድባት እንደሚችል ስታስበው ደከማት፡፡ እናም በእጇ ይዛው የነበረውን ኮከብማ ዓሣ ጣለቺውና ከአሸዋው አካባቢ መውጣት ጀመረች፡፡
«ትክክል» አለ ዐዋቂው፡፡ «ሂጅና ተጫወቺ፡፡ ለውጥ ላታመጭ ያውም ባንቺ ዕውቀት እና ዐቅም መልፋት የለብሺም» አላት እየተከተለ፡፡
ስትሠራ ያላጨበጨቡላት የአካባቢው ሰዎች ርግፍ አድርጋ ትታ ተሸንፋ ስትወጣ አጨበጨቡላት፡፡
ይሄኔ መንገዷን ገታ አድርጋ ቆመች፡፡ «ተሸነፍኩ ማለት ነው?» ብላ አሰበቺ፡፡ «እኔ የምችለውን አደርጋለሁ፡፡ የምችለውን የማድረግ እንጂ የሚያስፈልገውን የማድረግ ግዴታ የለብኝም» አለቺ፡፡ ይሄኔ የዛለው ክንዷ ሲበረታ፣ የተጫናት ድካም እንደ ቅርፊት ሲቀረፋ፣ የሞተው ሞራል እንደ አልዓዛር ሲነሣ ተሰማት፡፡
ከዚያም ወደ ኋላዋ ተመለሰቺና አንደኛውን ኮከብማ ዐሣ አነሣቺው፡፡ መንደርተኞቹም ገርሟቸው ያይዋት ነበር፡፡ አንሥታም አልቀረች ወረወረቺው፡፡ በባሕሩ ውኃ ላይ ዋኝቶ ሲጓዝ «ይኼው ቢያንስ ለዚህ ዓሣ ለውጥ አመጣሁ» ብላ ጮኸች፡፡ ያኔ አንድ በርሷው እድሜ ያለ ወጣት ከከበቡት ሰዎች መካከል ወጥቶ አንድ ኮከብማ ዓሣ አነሣ፣ ወረወረ፡፡ ዓሣው ባሕሩ ውስጥ ዲንቁል ብሎ ሲገባ «እኔም ለዚህ ዓሣ ለውጥ አመጣሁ» ብሎ ጮኸ፡፡
ሌላም ሰው መጣና እርሱም ወረወረ፡፡ የዓሣውን ወደ ሕይወት መመለስ ሲመለከትም «ይኼው እኔም ለውጥ አመጣሁ» አለ፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ወደ ታች ወረዱና መወርወር ጀመሩ፡፡ እነርሱም «እኔም ለውጥ አመጣሁ» እያሉ ይጮኹ ነበረ፡፡
ይመለከቷት የነበሩት ሁሉ ወደ እርሷ እየመጡ ዓሣዎቹን በመወርወር «እኔም ለውጥ አመጣሁ» እያሉ ይጮኹ ነበር፡፡
የአካባቢው መልክ ተቀየረ፡፡ የሚታየው ጎንበስ ቀና እያሉ ኮከብማ ዐሣዎችን ወደ ባሕሩ የሚመልሱ ሰዎች ነበሩ፡፡ የሚሰማውም «እኔም ለውጥ አመጣሁ» የሚሉ ድምፆች ነበሩ፡፡
አንድ ሰዓት አልፈጀም፡፡ ዐሣዎቹ ሁሉ ወደ ባሕራቸው ተመለሱ፡፡ ያን ጊዜ ሁሉም ተሰበሰቡና
«በአንድ ላይ ሁላችንም ለውጥ አመጣን» ሲሉ በደስታ ጮኹ፡፡
ከብዙ ዘመናት በኋላ በተመሳሳይ እድሜ ላይ ያለች ከሌላ ቦታ የመጣች ልጃገረድ በበጋው የዝናብ ወቅት ወደ ባሕሩ ወጥታ ነበር፡፡ በባሕሩ ዳርቻ አሸዋ ላይ አያሌ ኮከብማ ዐሣዎች ወጥተው አየች፡፡ የሚገርመው ግን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ዓሣዎቹን ወደ ባሕሩ በመመለስ ተግባር ተጠምደው ነበር፡፡
እጅግ ገርሟት በአካባቢው የነበሩትን አንድ አዛውንት «እንዴት እነዚህ ሁሉ ሰዎች በዚህ ሥራ ላይ ተጠመዱ? ማንስ አሠማራቸው?» ስትል ጠየቀቻቸው፡፡
አዛውንቱም «ከብዙ ዘመናት በፊት በዚህ ወቅት አንዲት ልጃገረድ ወደ ባሕሩ መጥታ ዐሣዎቸን አየቻቸው፡፡ እርሷም ቆማ ከመመልከት ይልቅ የምትችለውን ማድረግ ፈለገቺና እያነሣች ወደ ባሕሩ መለሰቻቸው፡፡ እኛ በመጀመርያ ተቸናት፣ ወቀስናት፣ ሳቅንባት፣ ቀለድንባት፣ አንጓጠጥናት፣ ምንም አታመጣም ብለንም አጣጣልናት፡፡ በኋላ ግን በሥራዋ አሳመነቺን፡፡ መጀመርያ አንድ ልጅ ተከተላት በኋላም ብዙዎች ተከተሏት፡፡ ያም ባህል ሆኖ በየዓመቱ ሁላቺንም እየወጣን «እኔም ለውጥ አመጣለሁ» እያልን ዓሣዎቹን ወደ ባሕሩ እንመልሳለን፡፡ በዚያ ጊዜ ልጅ ሆኖ እርሷን የተከተላትም የመጀመርያ ሰው ዛሬ ሽማግሌ ሆኖ ላንቺ ታሪኩን እየነገረሽ ነው» አሏት፡፡
“the star thrower( Loren c. eiseley, 2004)” k¸lW m{/F t²Mì yttr¯mÝÝ