ለወያኔ ጥቃት የኤርትራ መንግስት ምላሽ

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ለተሰነዘረባት ጥቃት አፀፋ ለመመለስ እንደማትሻ አመለከተች። የሐገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በሰጡት መግለጫ መንግስታቸዉ የኢትዮጵያ መንግስት ይህን ጥቃት የሰነዘረዉ ከዩናይትድ ስቴትስና ከተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ድጋፍ ሳያገኝ ነዉ ብሎ እንደማያምንም አስታዉቀዋል። ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የሐገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ የጦርነትን አስከፊነት የማያዉቅ ወደጦርነት ያምራ እንጂ ኤርትራ ይበቃታል፤ ለትንኮሳዉ ምልሽ አትሰጥም ብለዋል። ኢትዮጵያ የጥቃት ርምጃ ኤርትራ ላይ መሰንዘሯን መግለጿ ሁለቱ አገሮች ዳግም ወደሌላ ጦርነት ሊገቡ ይሆን ወይ የሚለዉን ስጋት አስነስቷል። ፈረንሳይ ሁለቱም ሐገሮች ለዉይይት እንዲቀመጡ ስትጠይቅ፤ ዩናይትድ ስቴትስ በበኩሏ ኢትዮጵያም ሆነች ኤርትራ አደብ እንዲገዙ ተማፅናለች። ጣሊያንም እንዲሁ ሁለቱ ወገኖች በመካከላቸዉ የተካረረዉን ዉጥረት እንዲያረግቡ አሳስባለች። የአውሮፓው ኅብረት የውጭ ፖለቲካ ኀላፊ ወ/ሮ ካትሪን ኤሽተንም ተመሳሳይ መልእክት ነው በመግለጫቸው ላይ ያስተላለፉት። የአፍሪቃዉን ቀንድ ፖለቲካ የሚከታተሉ ተንታኞች በበኩላቸዉ ለኢትዮጵያ ጥቃት ኤርትራ ወታደራዊ አፀፋ ላትመልስ ትችላለች ባይ ናቸዉ።

ያዳምጡ
* ለኢትዮጵያ ጥቃት የኤርትራ ምላሽ
* የኢትዮ ኤርትራ ግጭት በተንታኞች እይታ
* የአውሮፓው ኅብረትና የኢትዮ-ኤርትራ ውዝግብ