በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መብራት መጥፋት አውሮፕላኖች በጨለማ ሲያርፉ አመሹ
በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡34 ሰዓት ድረስ የአውሮፕላን መንደርደርያዎች መብራቶች በመጥፋታቸው አውሮፕላኖች በጨለማ ሲያሳርፉ ማምሸታቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ችግሩ መፈታቱን ገልጾ፣ የጉዳዩ ባለቤት ኤርፖርቶች ድርጅት መሆኑን ተናግሯል፡፡
ለመንደርደሪያዎች መብራት መጥፋት ምክንያቱ ኤርፖርቶች ድርጅት በማሠራት ላይ የሚገኘው የአውሮፕላን ማቆሚያ፣ ማረፊያና ማኮብኮቢያ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን የሚሠራው የቻይናው የመንገድና ድልድይ ግንባታ ኮርፖሬሽን (CRBC)፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ሳይበጥሰው እንዳልቀረ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
አውሮፕላን ለማረፍ ትክክለኛ አቅጣጫ በመያዝ ዝቅ ሲል ቀይ፣ ከፍ ሲል ሰማያዊና ትክክለኛ አቅጣጫውን ሲይዝ ደግሞ ነጭ መብራት የሚያሳየው ፓፒ (PAPI) የሚባለው ብርሃን ሰጪ መሣርያ ጠፍቶ እንደነበር ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
አውሮፕላኑ ከማረፊያ ሜዳው ያለውን ርቀት በማንበብ የሚያሳውቀው መሣሪያ (Distance Measuring Equipment) ጠፍቶ እንደነበር የገለጹት ምንጮቹ፣ አውሮፕላኖቹ በጨለማ ያርፉ የነበሩት ካርጐ ተርሚናል ውስጥ በነበረ አውሮፕላን ፓይለቱ ብርሃን እያበራላቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አንድ አውሮፕላን ከአንድ አገር ተነስቶ ወደሚያርፍበት አገር እስከሚደርስ ድረስ የሚበቃውን ነዳጅ ከሞላ በኋላ፣ በሚያርፍበት አገር የተለያዩ አጋጣሚዎች ተፈጥረው ለማረፍ ባይችል፣ ለማረፍ በሚችልባቸው ቅርብ አገሮች ወይም ማረፊያዎች ድረስ የሚያደርሰውን ወይም በአየር ላይ የሚያቆየውን ተጨማሪ ነዳጅ መያዝ እንዳለበት የገለጹት ምንጮቹ፣ ምናልባት አውሮፕላኖቹ በጨለማ እንዲያርፉ የተደረገው፣ መጠባበቂያ ነዳጅ ስላልነበራቸው ሳይሆን እንደማይቀር ግምታቸውን ገልጸዋል፡፡ ያ ባይሆን ኖሮ በቅርቡ ወደምትገኘው ጂቡቲ በመሄድ ማረፍ ይችሉ እንደነበርም አክለዋል፡፡
የኢትዮጵያውያን ፓይለቶች በአየር መንገዱ ረጅም ዓመታት የሠሩና ለአውሮፕላን ማረፊያው እንግዳ ባለመሆናቸው፣ ባካበቱት ልምድ በጨለማ ለማሳረፍ መቻላቸውን የገለጹት ምንጮቹ፣ አውሮፕላኑ የማረፊያ ሜዳውን ስቶ ቢያርፍ ችግር ይከተል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን መጠባበቂያ የኤሌክትሪክ ኃይል (ከፍተኛ ጄኔሬተር) ማዘጋጀት እንደነበረበት የተናገሩት ምንጮቹ፣ ባለሥልጣኑ መጠባበቂያ እንዳለውና እንደሌለው ካረጋገጠ በኋላ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በራሱ ማዘጋጀት እንደነበረበት አስገንዝበዋል፡፡ ዩፒኤስ (UPS) እንኳን ቢኖር ኖሮ ከሁለት ሰዓታት በላይ ብርሃን ማግኘት ይቻል እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡
ሌላ ጊዜ በአውሮፕላን ማረፊያው ተመሳሳይ የመብራት መጥፋት ችግር ያጋጥም እንደነበር የጠቆሙት ምንጮቹ፣ ወዲያውኑ መብራት ይመጣ ስለነበር መዘናጋት የተፈጠረው ምናልባት ተመሳሳይ ክስተት ነው በሚል ሳይሆን እንደማይቀር ተናግረዋል፡፡
በ25 ሺሕ ጫማ ከፍታ ላይ ጂቡቲን ጨምሮ በአገሪቱ ያሉትን አየር መንገዶችን የሚቆጣጠረው የአካባቢ መቆጣጠሪያ ማዕከልም ጠፍቶ ማምሸቱን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ ምሽቱ 2፡34 ሰዓት ድረስ ጠፍቶ ስለነበረው የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳ መብራት ጉዳይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽንና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣ ‹‹በሕጉ መሠረት ወይም በዓለም አቀፍ የአቪዬሽን ሕግ፣ መብራት ለ24 ሰዓታት መሥራት አለበት፡፡ ግዴታም ነው፡፡ ለማንኛውም አሁን ችግሩ ተፈትቷል፤›› ካሉ በኋላ፣ በዋናነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኤርፖርቶች ድርጅትን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሊሳካልን ባለመቻሉ ምላሻቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
ኤርፖርቶች ድርጅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ማረፊያን ለማስፋፋት ለቻይናው የመንገድና ድልድይ ግንባታ ኮርፖሬሽን በ66 ሚሊዮን ዶላር ኮንትራት ሰጥቶ እያሠራ ይገኛል፡፡ ፕሮጄክቱ ሲጠናቀቅ ቦይንግ 747 እና 777 ግዙፍ አውሮፕላኖችን ጨምሮ 44 አውሮፕላኖችን በአንድ ጊዜ ለማቆም እንደሚችል ታውቋል፡፡ እስካሁን ግን 19 አውሮፕላኖችን ብቻ ነበር ማቆም የሚቻለው፡፡