አባይ ፍሰስ ብለው ከካይሮ አዲሳባ
ከኦባም የምርጫ ፉክክር ወዲህ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት የሳበ የውጭ ክስተት ካለ የግብጹ አብዮት የመጀመሪያ ይመስለኛል። ሁለቱንም በጉጉት ከተከታተልንባቸው ብዙ የግልና የጋራ ምክንያቶች አንዱ ሁለቱም በአገራችን እንዲሆኑልን ስለምንፈልግ መሆኑ አያከራክርም። ቢቻል ሁለቱንም ባይቻል አንዱን ማግኘት ትልቅ ነገር ነው፤ ሁለቱንም አለማግኘት ደግሞ ያስቆጫል። ቢያንስ ለጊዜው የእኛ እጣ ይህ ነው፤ መቆጨት። መቆጨት የለውጥ መሠረት ሊሆን ይችላል፤ መቆጨት በራሱ ሕይወት እንዳይሆን ከማስፈራቱ በቀር።
እነሆ ሙባረክ በመጨረሻ ባልተመኙት መልኩ ሥልጣናቸውን ለቀቁ። የተመኙትም ቢቀር ከዚህ በተሻለ ክብር ከሥልጣን ለመውረድ የነበራቸውን ዕድል ቀን በቀን አንድ በአንድ ሲያበላሹት ለሚመለከት ግርምት መፍጠሩ አይቀርም። አምባገነኖች የሥነ ልቦና ብቻ ሳይሆን የጤነኛ ግምት (ኮመን ሲኔስ) ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡ የሚያስታውስ አጋጣሚ ሆኖብኛል። የግብጽ ሕዝብ እንደ ኅብረተሰብ የደረሰበት የፖለቲካ ብስለት ደረጃ የሚፈተንበት ሁለተኛውና ዋናው ምዕራፍ ሊጀመር ነው። መስቀለኛው መንገድ ለተላላፊዎች ክፍት ሆኗል። ግብጽ ወዴት ትሔዳለች? አንድ የታህሪሪ አደባባይ ታዳሚ “ግብጻውያን አራተኛውን የነጻነት ፒራሚድ አቁመናል” ብሏል። በተስፋ እንመለከታቸዋለን፤ ከመልካም ምኞት ጋራ።
ብዙዎቻችን የግብጽን አብዮት ለኢትዮጵያ እንደምንመኝ እገምታለሁ። ከምኞቱ ወጣ ብለን ጉዳዩን መመልከት ስንጀምር ግን መግባባት ቀርቶ መደማመጥ መቻላችንን እጠራጠራለሁ። በዚህ ዙሪያ የሚነሡት ክርክሮች በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው። ከጥያቄዎቹ መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል።
1. ¬የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ይህን አይነት እንቅስቃሴ ለመጀመርና ለመምራት የሚያስችለው ዝግጅት አለው? (የግብጹ አብዮት “መሪ የለውም” ቢባልም ድንገት ከሰማይ የወረደ አለመሆኑንም መዘንጋት የለብንም። ወጣቶች በተለያየ መንገድ ሲያብላሉትና ሲያቀጣጥሉት የሰነበቱት ጥያቄ ነበር።)
2. የኢትዮጵያ መንግሥት (መለስና የቅርብ ጓዶቻቸው)፣ እና በአምሳላቸው የተፈጠሩት ብሔር ተኮር ድርጅቶች ምን እርምጃ ይወስዳሉ? ከእነርሱ በተጻራሪ የቆሙት የፖለቲካ ኀይሎችስ ምን ሚና ይጫወታሉ?
3. እንቅስቃሴት ከሚፈጥረው “የማይቀር” ግጭት ባለፈ “ያልታሰበ” ደም መፋሰስ ሲያስከትል የሚችልበትን አደጋ ምን ያህል መቆጣጠር ይችላል?
4. የኢትዮጵያ ጦር ሚና ምን ሊሆን ይችላል?
5. ይህን መሰል አብዮት ቢቀሰቀስ በአገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር፣ ኢኮኖሚ እና የጸጥታ ጉዳይ ላይ የሚያስከትለው ውጤት ምን ሊሆን ይችላል? ጎረቤት አገሮች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
6. ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምን አቋም ይወስዳሉ፤ በሒደቱስ የሚኖራቸው ተሳትፎ ምን ሊሆን ይችላል?
7. ከሙባረክ በኋላ የምትኖረው ግብጽ እና ከመለስ በኋላ የምትኖረው ኢትዮጵያ ይመሳሰላሉ? ለምን/እንዴት?
8. የምርጫ 97 ልምድ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊፈጠሩ ስለሚችሉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች የተወው ትምህርት ምንድን ነው?
እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን ማንሣት “የእኛ ጉዳይ ተስፋ የለውም፤ አደጋው ስለሚያል ያለው ባለበት ከመቀጠሉ ሌላ መውጫ የለም፤ ወይም ሕዝቡ ለነጻነት ያለውን ጥያቄ መግፋትና ትግሉን መቀጠሉ አያዋጣም፤ ጥያቄው ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ” ብሎ እንደመጠየቅ መወሰድ የለበትም። ንግግሩን በየአጋጣሚው “የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻነት፣ ፍትሕ፣ ዴሞክራሲ ይገባዋል አይገባውም? ይህን ታምናለህ አታምንም?” ወደሚል ደረጃ ማውረድ ከጀመርንም በተዘዋዋሪ ለዴሞክራሲ ይደረጋል የሚባለውን ትግል መጉዳታችን አይቀርም፤ ባለህበት እርገጥ።
እውነቱን ለመናገር ከጭቆናና ከአፈና በቀር ከግብጻውያን ጋራ የምንጋራው ብዙ ነገር የለም። ይህን መሰል ውጫዊ ልምዶችን የብሶት ማረሳሻ አድርጎ ከመቁጠር የበለጠና የተለየ እውነተኛ ፍላጎት ካለን እነዚህንና መሰል ጥያቄዎችን መዝለል አንችልም። ራሳቸውን የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንደራሴዎች አድርገው የሚመለከቱት ብዙዎቹ ብድኖች/ግለሰቦች ይህን መሰል ጥያቄዎችን እያነሱ ለመተንተን (ትንተናው ምንም ይሁን) እና ነገሩን ለማብላላት የተዘጋጁ አይመስሉኝም። ቢያንስ ይህን እያደረጉ ስለመሆኑ ያሳወቁን ነገር ጥቂት ነው። አሁን በየአቅጣጫው የተያዘው ተራ ፉከራና ቀረርቶ ነው። “እኛ የነጻነትና የዴሞክራሲ ታጋዮች! ካይሮ ደርሰናል!” አይነት ፉከራ።
ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳች አይነት ሕዝባዊ ተቃውሞ እንደሚቀሰቀስ ለመገመት የተለየ ምጡቅ እውቀት የሚጠይቅ ነገር አይደለም። ይህንን እንኳን ሌላው ሕዝብ ኢሕአዴግ ራሱም የሚክደው ሐቅ አይደለም። አቶ መለስ ይህን አደጋ አስቀድሞ ለመከላከል “ይበጀኛል” ያሉትን እየሠሩ ነው። ጥያቄው የመለስን አምባገነናዊ አገዛዝ የሚቃወመው የተደራጀም ይሁን ያልተደራጀ ኀይል ምን እያሰበና ምን እያደረገ ነው የሚል ነው። ሕዝባዊ ተቃውሞን በራሱ የዴሞክራሲ ግብና ተስፋ አድርጎ መመልከት ግን ግማሽ አደጋ ያረገዘ አመለካከት ነው። ሲብስ ደግሞ የማሰብ ስንፍና የተጠናወተው አመለካከት ነው። ለተሻለ ነጻነትና ልማት ተጀምረው የባሰ አፈናንና ውድመትን የወለዱ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን/አብዮቶችን ማስታወስ አስቸጋሪ አይደለም።
የግብጽን እና የቱኒዚያን ሰላማዊ አብዮች ማድነቅና መመኘት አንድ ጥሩ ነገር ነው። እነዚህ አብዮቶች በአንድ ወይም በሌላ መልኩ በኢትዮጵያ እንዲደገሙ መቀስቀስና መዘጋጀት ደግሞ ሌላ ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያው አብዮት ሊኖረው የሚችለውን ገጽታ (ቢያንስ በግምት) ከወዲሁ መተንበይ እና ራስን ከፖለቲካዊ ድጋጤ ለማዳን የምር ማሰብ ግብጻውያን ለሁላችንም የተዉልን የቤት ሥራ ነው። ይህን ፈተና ምን ያህል እንደምንወጣ ለመገምገም ይህ ጉዳይ በየግላችን በኢትዮጵያ ሚዲያ (የአገር ቤትም የውጭም) እና የፖለቲካ ኀይሎች ዘንድ ለምን ያህል ጊዜ መነጋገሪያ ሆኖ እንደሚቆይ መመልከቱ የመጀመሪያው አመላካች ሊሆን ይችላል።
የጥንቱ አገርኛ ግጥም እንደሚለው አባይን ለመሻገር ወይ መታገስ ወይ ድልድይ መሥራት ግድ ነው።
አባይ ጉደል ብለው አልኝ በትሳስ፣
የምን ሆድ ይችላል እስከዚያው ደረስ።
ሰሞኑን ደግሞ አባይ ጥያቄው ሌላ ነው።
አባይ ፍሰስ ብለው ከካይሮ አዲሳባ፣
ሰልፍ አሳምር አለኝ ሆድህ እንድገባ፤
ሰልፍ አሳምሪ አለኝ ሆድሽ እንዳይባባ።
