የኢህአዴግ ካድሬዎች ከፌዴራል ፖሊሶች ጋር በመሆን ”የሥልጠና፣ የሥራ ቦታ እና የብድር አገልግሎት መስጫ” ፎርም ማስሞላት ጀመሩ
(ሙሉ ገ)
በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍለ ከተሞች የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች እና ሴቶች (እናቶች) ”የሥልጠና፣ የሥራ ቦታ እና የብድር አገልግሎት መስጫ” የሚል ፎርም በየሰፈሩ እየዞረ ማስሞላት ጀመሩ፡፡
የኢህአዴግ ካድሬዎች ከፌዴራል ፖሊሶች ጋር በየአካባቢው በመዞር ከአካባቢው ወጣቶች በተጨማሪ ለታክሲ ተራ አስከባሪዎች፣ ረዳት ሾፌሮች (ወያሎች)፣ ደላሎች እና ለቀን ሰራተኞችም ፎርሙን በማስሞላት” ከኢህአዴግ ጋር መጪው ጊዜ ብሩህ ነው፤ በፈለጋችሁት ሙያ ሰልጥናችሁ በመደራጀት የብድር አገልግሎትና የሥራ ቦታ በማግኘት የራሳችሁን ሥራ ትሰራላችሁ” እያሉ ማነሳሳታቸውን ሪፖርተራችን ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ ቤት ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመሆን ቅዳሜ እና እሁድ ጥር 21-22 ቀን 2003 ዓ.ም በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተሞች ከወጣቶችና ከሴቶች ጋር ባካሄደው “የልማትና የጸጥታ ስብሰባ” ላይ እንደገለጸው “ በተለይም በኮንስትራክሽንና በጋራ ቤቶች ግንባታ ብዙ የሚሰራ ሥራ እያለ ነገር ግን ወጣቶችና ሴቶች በአግባቡ ባለመደራጀታቸው የስራተኛ እጥረት በማጋጠሙ ወጣቱን በማደራጀት በአምስት አመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ በምላት በማሳተፍ የላቀ እድገት አስመዘግባለሁ” ብሏል፡፡
ሰኞ ጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም በየቀበሌው ያሉ ወጣቶችና ሴቶች በሞሉት ፎርም የሦስት ዞን ወጣቶች በአንድ ቡድን ተዋቅረው (ተጠርንፈው) ከሦስቱም ዞኖች አምስት፣ አምስት ወጣቶችን በአንድ ላይ 15 ወጣቶችን በቡድን በማዋቀር የአካባቢው ወጣቶች ወኪል ሆነው “በመንግሥትና በህብረተሰቡ መካከል ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል (ተሹመዋል)” ሲሉ ምንጮቻችን አስረድተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ኢህአዴግ ጽ/ቤት የሚገኙ የዜና ምንጮቻችን ቀደም ሲል ለሪፖርተራችን እንደገለጹት ፓርቲው ሰሞኑን በቱኒዚያ እና በግብፅ የተነሳው ሕዝባዊ ተቃውሞ በኢትዮጵያም እንዳይከሰት በእጅጉ አሳስቦታል ማለታቸው ይታወሳል፡፡