የነጋዴው የዋጋ ጥማትና የሸማቾች ስጋት በምንደኞች ኢኮኖሚ

ጥር ወር ዑደቱን ጠብቆ ከበራፍ ደርሷል፡፡ ወሩ ጥምቀት እና አገሩን ለሚሞሉት ሰርግን መሰል ማኀበራዊ ትውፊቶች ብቻ አልነበረም የተናፈቀው፡፡ ለመንግሥት ሠራተኛው በዚህ ወር እንደሚጨመር የሚጠበቀውን ደመወዝ ተከትሎ  የሚከተለውን  የኢኮኖሚ ጣጣ ሦስት አካላት ወሩን እንዲጠብቁት አድርጓቸዋል፡፡  የመንግስት ተቀጣሪው ፣ ነጋዴው እና የአቶ መለስ መንግሥት ከአንድ መነሾ የተለያየ ግብ  ይጠብቃሉ፤ በዚህ ጥር ወር።

የኑሮ ውድነቱ የተጫነውን ሠራተኛ ደመወዝ ከፍ ለማድረግ መንግስት ጥርን እንደ መነሻ መውሰዱን ቀደም ሲል ተናገሯል፡፡ በዚህም በፖለቲካም ኾነ በኑሮ መወደድ ምክንያት ያኮረፈውን ማኀበረሰብ ልብ አራራለሁ ብሎ ይገምታል፡፡ ይህ የመንግስት ውሳኔ የኑሮ ጉስቁልና ምርታማነቱን ለተጫነበት “ምንደኛ” ግን የደስታ ምንጭ ሊኾን አልቻለም፡፡ ከጭማሬው ከሚያገኘው አንጻራዊ እፎይታ ይልቅ ደመወዝ ጭማሬውን ተከትሎ የሸቀጦቻቸውን ዋጋ ጣራ ለማስነካት አሰፍሰፈው የሚጠብቁ ነጋዴዎችን ማሰቡ ተጨማሪ ስጋት ይዞበት መጥቷል፡፡ እናም መንግስት ነጋዴውን በማስፈራራት እንዲኹም “በልማታዊ ነጋዴነት” አስተምርሆ ከሚጠበቀው የዋጋ ለውጥ የምንደኛውን የገንዘብ ጭማሬ ለመታደግ ሙከራ ይዟል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የደመወዝ ጭማሬውን ተከትሎ የሸቀጦችን ዋጋ በሚያንሩ ነጋዴዎች ላይ ርምጃ እንደሚወስድ መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ  በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናው አማካኝነት ከ584 ኩባንያዎች እና ነጋዴዎች ጋራ ውይይት ለማድረግ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡ ይህ የሰሞኑ የመንግስት ሩጫ፣ የምንደኛው ስጋት እና የነጋዴው የዋጋ ጥማት ማክሮኢኮኖሚው በአንድ የኢኮኖሚያዊ ተለዋዋጭ ማለትም በመንግስት ሠራተኛው ምንዳ ላይ ምን ያህል ጥገኛ እና ስሱ እንደኾነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም ኾኖ “ነጋዴው ከሚሻው የዋጋ ጭማሬ ሊገታ፣ በዚህም ማኅበረሰቡን ለአመታት ከዘለቀው የዋጋ ግሽበት ለመታደግ የአቶ መለስ መንግስት ይቻለዋል” የሚለው እምነት እጅጉን የጠበበ ነው፡፡

ምንዳና የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ

ባለፉት ስድስት አመታት የኢትዮጵያ መንግስት የደመወዝ ጭማሪን እንደ አንደ ዋነኛ የኑሮ ማረጋጋጊያ   መፍትሔ አድርጎ በመውሰድ በተደጋጋሚ ተጠቅሞበታል፡፡ የአሁኑን ወር ሳያካትት ለሦስት ጊዜ ያህል ለሲቪል ሠራተኞች ጭማሬ የተደረገ ሲኾን  የጭማሬዎቹ ምክንያትም “የኑሮ ውድነትን ማረጋጋት” የሚል ነበር፡፡ ይኹንና አንድም ከኑሮ ውድነቱ ጋር የሚስተካከል ጭማሬ ባለመደረጉ ሁለትም ደግሞ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባውን የገንዘብ መጠን ተከትሎ በሚከሰተው የዋጋ ጭማሬ ምክንያት ሠራተኛው የኑሮ ደረጃ ከመሻሻል ይልቅ እያደር እየባሰበት እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ ይህ ክስተትም የደመወዝ ጭማሬዎችን በጉጉት ከመጠበቅ ይልቅ አስከትለው የሚመጡትን አሉታዊ ውጤቶችን እንዲፈራ ሠራተኛው ተገዷል፡፡

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተገቢው ቁጥጥር ያልተደረገበት የገንዘብ አቅርቦት ፍሰት በኢኮኖሚው ውስጥ እየበረከተ መምጣት የዋጋ ግሽበትን ለመሰሉ አሉታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ነው፡፡ ከብሔራዊ ባንክ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያሳዩትም ባለፉት አምስት ዓመታት የገንዘብ አቅርቦቱ በአማካይ  በዓመት 20 በመቶ ደርሶ ነበር፡፡ ከኢኮኖሚው አቅም ጋራ ያልተመጠነ የገንዘብ ፍሰት ሚናው የሸቀጦችን እሴት ማናር ብቻ ሊኾን ችሏል፡፡

ሌላው ጉዳይ የምርት መጠን ከሚያድገው የሕዝብ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ አለመኾን እጥረቱ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ነጋዴው ከሸማቹ ተጨማሪ የ “እጥረት ዋጋ” ማግኘት ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ብዙሃኑ አምራች ገበሬ ምርቱን ከተመቸው ለገበያ ካልኾነለት ደግሞ ለቤተሰብ ፍጆታ የሚያውል በመኾኑ ለነጋዴው ቀላሉ የትርፍ ማጋበሻ ምንጭ የሚኾነው ከአጠቃላይ ሕዝቡ 1.2 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው ምንደኛ ነው፡፡ ይህም በመኾኑ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የተለመደው የጥር ወር የግብርና ምርቶች የዋጋ ቅናሽ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሚመስል ኹኔታ ኢኮኖሚውን እንዳይጎበኘው የኾነው፡፡

ከሰሞኑ ከመንግስት እንደተደመጠው አገሪቷ የተሻለ ምርት ታፍሳለች የሚል ትንበያ ቢኖርም የዋጋ ጭማሬውን ሊገታው አልቻለም፡፡ ይህም የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ለማንኛውም የገንዘብ ጭማሬ ስሱ መኾኑን እና አጠቃላይ የምርት ደረጃ ካልተስተካከለ በስተቀር የደመወዝ ጭማሬ ብቻውን ማኅበረሰቡን ካለበት የመረረ የኑሮ ውድነት ይታደገዋል የሚል መደምደሚያ ላይ አያደርስም፡፡

ውይይት እና ማስፈራሪያ እንደ መፍትሔ

በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው ለኑሮ ውደነቱ ሁለት ምክንያቶች ከመንግሥት በኩል ይሰነዘራሉ፡፡ “ስግብግብ” ነጋዴዎች እና የኢኮኖሚ ዕድገት፡፡ ሁለቱ የመንግስት የመጫወቻ ካርታዎች እንደ አስፈላጊነቱ ጥቅም ላይ ቢውሉም በአሁኑ ወቅት ግን “የስግብግብ” ነጋዴዎችን የመሰለ የተሻለ ምክንያት የተገኘ አይመስል፡፡ ለዚህም ከሳምንታት ቀደም ብሎ የአላግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ላይ ቁጥጥር ለማድረግ መፍትሔ መዘየዱን በመንግሥት ሚዲያዎች እየተነገረ ነው።

ይህ የአሁኑ የአቶ መለስ መንግሥት እንቅስቃሴ ከሚያስገኘው ፋይዳ ይልቅ ለዓመታት በዕድገት ላይ እንደኾነ የተነገረለት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከአጠቃላይ ሕዝብ 1.2 በመቶ ብቻ ድርሻ ያለው የመንግስት ሠራተኛ አሁንም የኢኮኖሚው እምብርት መኾኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የምንደኛው የገንዘብ ድርሻ ከአጠቃላይ አመታዊ በጀት 15 በመቶ የዘለለ ባይኾንም የማክሮ ኢኮኖሚው ዋነኛ የችግር ምንጭ መኾኑ የመንግስት የቁጥጥር መንገዶች ደካማ መኾናቸውን በግልጽ የሚናገር ነው፡፡

ወቅቱ የዕድገት እና የኢኮኖሚ ሽግግር ዕቅድ ብቻ የሚወራበት ነው። ነገር  ግን በቂ የኾነ ምርት በሌለበት  አገር ነጋዴዎችን በመቆጣጠር ብቻ ምንደኛውን ከጉስቅልና መታደግ እንደማይቻል ግልጽ ነው፡፡ የነጋዴውን የሸማቹ መድረኮች እንደ ሸቀጦቹ ብዛት በጣም ሰፊ ናቸው፡፡ በዚያ መድረክ ደግሞ አቅርቦት እና ፍላጎት ብቻ የገበያው ወሳኝ ኃይሎች ይኾናሉ፡፡ ከጥር ወር ደመወዝ ጭማሬ በኋላም የምንደኛው ፍላጎት ጎልብቶ ሲመጣ አቅራቢው ደግሞ ቀድሞ የያዛቸውን ሸቀጦች ብቻ ይዞ መድረኩን ይቀላቀላል፡፡ገበያው መናገር ይጀምራል፡፡  ያን ጊዜ የአቶ መለስ ቁጣ እና ተግሳጽ የለም፡፡