[አንድ ለቅዳሜ] ስለ ፖለቲከኞቻችን ምን ይነበባል? እነርሱስ ምን ያነባሉ?
ባለፈው ሳምንት የአገራችንን ፖለቲካ ለመረዳትም ይሁን ወደ ፊት ለማራመድ ከሚያስፈልጉን ነገሮች አንዱ አዲስ የርእዮተ ዓለም ትንተና መሆኑን ጠቆም አድርጌ ነበር። ይህ የመረዳት ፍለጋ ብዙ ተያያዥ ጥያቄዎችን እንዳነሳ አድርጎኛል። የዛሬው ትኩረቴ በፖለቲከኞቻች በኩል ፖለቲካችንን መረዳት ነው፤ ፖለቲከኞቻችንን መተቸት ብቻ ሳይሆን መረዳት እና መርዳትም እንደሚያስፈልግ ከማመን ጋራ።
በጥያቄዎች ልጀምር። እኛ ስለፖለቲከኞቻችን ምን የምናነበው ነገር አለ? ስለ ፖለቲከኞቻችን ምን ተጽፏል፤ ምንስ እየተጻፈ ነው? ፖለቲከኞቻችንስ ምን ያነባሉ።
ስለ እነርሱ ምን ይነበባል?
የአንድን ማኅበረሰብ ፖለቲካ ለመረዳት የዋና ዋና ተዋናዮቹን ግለሰባዊ ሕይወት ማወቅ እጅግ ጠቃሚ ነው። እኛ በዚህ በኩል የታደልን አይደለንም። እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ፖለቲከኞቻችን የሕይወት ታሪክ የተጻፉ ሁነኛ መጻሕፍት በጣም ጥቂት ናቸው። አሉ ከሚባሉት መካከል ባለታሪኩ ከሞተ በኋላ የተጻፉት ይበዛሉ፤ አለዚያም እርሱ በሕይወት እያለ ተክለ ስብእናውን ለመገንባት የተጻፉ “መወድሶች” ናቸው። እነዚህም ቢሆኑ አይጠቅሙም ማለቴ አይደለም፤ መሪዎቹ በሕይወት እያሉ ለእነርሱው የፖለቲካ ጥቅም ሲባል የተጻፉት እንደሚበዙበት ግን አያጠራጥርም።
ካነበብኳቸው መካከል አምባሳደር ዘውዴ ረታ ያሳተሙት የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ታሪክ በጥልቀቱና በስፋቱ በአርአያነት ሊጠቀስ የሚችል ይመስለኛል፤ ፋይዳው ታሪካዊነት ቢጫነውም። ተቺዎች ጸሐፊው ለንጉሠ ነገሥቱ መጠነኛ ድጋፍ አድርገዋል ቢሉም የመጽሐፉን ደረጃ የሚያወርደው ሆኖ አላገኘሁትም። የልጅ ኢያሱ፣ የአጼ ምኒልክ፣ የአጼ ዮሐንስ፣ የአጼ ቴዎድሮስ ታሪኮች አሉ። ሌሎችም እንዲሁ ይኖሩ ይሆናል። እነዚህኞቹ ግን በምርምር ጥልቀታቸው የአምባሳደር ዘውዴን ያህል ሊጠቀሱ የሚችሉ ስለመሆናቸው እርግጠኛ አይደለሁም።
ገነት አየለ ከኮሎኔል (ፕሬዚደንት) መንግሥቱ ኀይለ ማርያም ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በዋናነት ይዞ የወጣው ባለ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ ጠቃሚነቱ አያጠያይቅም። ነገር ግን በማንኛውም መለኪያ እንደ ጥናት/ምርምር ሥራ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል አይደለም። ስለ መንግሥቱ ለሚሠሩ ቀጣይ ሥራዎች በጥሩ ግብአትነት ሊያገለግሉ የሚችሉ በርካታ መረጃዎችን ግን አካቷል፤ ጥሩ ጅምርም ነው፤ ብቸኛ ሙከራም ነው። በቅርብ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሕይወት ታሪክ የታተሙትን ሁለት መጻሕፍት ስላላነበብኳቸው አስተያየት ከመስጠት ልቆጠብ፤ ስለመጻሕፍቱ የሰማሁት ቢኖርም።
ስለ ፖለቲከኞቻችን ተጻፉ የምንላቸው መጻሕፍት ጥቂት እና ባለሞያ “ገለልተኛ” ጸሐፊ የሚያጥራቸው ብቻ አይደሉም። ሁሉም ስለ አገር መሪዎች ብቻ መጻፋቸውም ግለሰቦቹ በፖለቲካችን ውስጥ ያለቸውን ቦታ የሚጠቁም ጭምር ነው። ሰዎቹ በሕይወት እያሉ የእነርሱን ሕይወት የሚተች መጽሐፍ ማሳተም እንደማይቻልም ሊያሳይ ይችላል። ከዚህ ውጭ ሊጠቀሱ የሚችሉ ቢኖሩ በንጉሡ ዘመን ፖለቲካ ውስጥ የነበሩ ሰዎች የጻፏቸውና ገና አሁን በመታተም ላይ የሚገኙ ግለ ታሪኮች ናቸው። ፋይዳቸው ከሞላ ጎደል ታሪካዊ ነው። ስለ አገር መሪዎች መጻፉ ባልከፋ ነበር፤ እርሱም ግን በጣም ጥቂት እና ጥልቀት የሚጎድለው ነው።
ስለ አገር መሪዎቹ ግለሰባዊ ማንነት የሚያወሱት መጻሕፍት ትንሽ ናቸው። ከእነርሱ ውጭ በዙሪያቸው፣ በስራቸው ስላሉት አማካሪዎችና ሹመኞች፤ እንዲያም ሲል እነርሱን በመቃወም በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች/ፓርቲዎች ውስጥ ስላሉ ቁልፍ ሰዎች ጭራሹን ደፍረን የምናቀርበው የተጠናቀረ መረጃ የለንም። ቴክኖሎጂ እጅጉን በሚያግዝበት በዚህ ወቅት በመጽሐፍ ደረጃ እንኳን ባይሆን በአጫጭር ጽሑፎች መልክ በርካታ የተጣሩ እና ደርዝ የያዙ መረጃዎችን ማግኘት በቀለለ ነበር። በአገራችን የህትመትም ይሁን የኢንተርኔት ሚዲያ በአመዛኙ ስለፖለቲከኞቻችን የሚነበበው መረጃ በድጋፍና በተቃውሞ ማጽደቂያነት ነው፤ በጠንካራ የጋዜጠኛ ሞያዊ ምርመራ ላይ የተመሠረተ አይደለም። የጽሑፎቹ ጭብጥም ስለግለሰቦቹን መረጃ ከመስጠት በበለጠ አቋማቸውን ከመደገፍ/ከመቃወም አንጻር የሚተረክ ነው። ራሳቸው ግለሰቦቹ የሚሉትን እንዳለ በማተም፤ ተቃዋሚዎቻቸው አለዚያም ደጋፊዎቻቸው የሚተርኩትን ብቻ በማቅረብ ላይ መንጠልጠል ያጠቃዋል።
አለመታደል ሆኖ ፖለቲከኞቻች ደግሞ እንኳን ስለ ግለሰባዊ ታሪካቸውና አቋሞቻቸው ቀርቶ ስለፖለቲካዊ አመለካከታቸው፣ ስለ ፓርቲያቸውም ጭምር መጻፍ የሚቀናቸው አይደሉም። እርግጥ ብዙዎቹ እንጻፍስ ቢሉ መጻፍ የሚችሉ ናቸው ወይ ብሎ ነገር የሚፈልግ አንባቢ አይጠፋ ይሆናል። እንዴትም በተጻፈና በተተቸ ምንኛ መታደል ነበር።
የፖለቲካ መሪዎችን በተመለከተ እንኳን ለሕዝብና ለተመራማሪዎች ቀርቶ ለራሳቸው ፓርቲ አባላትና ረዳቶች የሚሆን በቂ መረጃ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። ታዲያ ፖለቲከኞቻችንን እንዴት እንወቃቸው? እንዴትስ እንረዳቸው? ግለሰቦቹ የሚመሯቸው ፓርቲዎች ስለ አመራሮቻቸው ታሪክ በይፋ የሚነግሩን ነገር በጣም ውስን ነው። የፖለቲከኞችን ሕይወት እንደሚስጥር መያዝ የፖለቲካችን አንድ ባህል ነው። ይህ በአንድ በኩል የዋናው ባህላችን ቅጥያ ተደርጎ ይታይ ይሆናል። ይህ ባህል ጠቃሚ ነው አይደለም ወደሚለው ክርክር አሁን መግባት አያስፈልገንም። ነገር ግን ባህሉ ፓለቲከኞቻችንን ከግለሰባዊ ማንነታቸው አንጻር እንዳናውቃቸው አድርጎናል።
“ስለ ፖለቲካኞቻችን ምን ይነበባል?” ቢሉ “በአብዛኛው ሐሜት” ብሎ መመለስ ስሕተት አይሆንም።
ምን ያነባሉ?
ስለ ፖለቲከኞቻችን ማንነትና ሕይወት በቂ መረጃ አለማግኘታችን አንዱ ችግር ነው። ከዚሁ ከንባብ ጋራ በተያያዘ ግን “ፖለቲከኞቻችንስ ምን ያነባሉ? ምን አንብበዋል?” ብሎ መጠየቅ የቅንጦት ጥያቄ አይደለም። “ሰዎቹ የሚያነቡት መጽሐፍ ቀጥተኛ ውጤት ናቸው ወይም ይሆናሉ” ብሎ መደምደም አይቻልም። ፖለቲከኞች እንደ ማንኛውም ሰው የሚያነቧቸው መጻሕፍት ተጽእኖ ያደርጉባቸዋል፣ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ። ከዚያም አልፎ የመጽሐፍ ምርጫቸው ስለ ሰዎቹ የሚነግረን ነገር ይኖር ይሆናል።
የንባቡን ነገር በሌላ አንጻር እንመልከተው። ለመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የመሪነት ሚና የመጫወት ፍላጎት ያለው ሰው እንዲያነባቸው የሚመከሩ መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? አንዳንድ ጊዜ የምንረዳበት መንገድና መጠን ቢለያይ እንኳን ስለ አገራችንም ይሁል ስለሌላ ስለሚጠቅመን ጉዳይ ተቀራራቢ መረጃ (ትርጉም አላልኩም) እንዲኖረን ሊነበቡ ይገባቸዋል የምንላቸው መጻሕፍት (ግምታዊ) ዝርዝር ቢኖረን የሚጠላ አይደለም። “የተሳሳቱ መረጃዎች የተሳሳተ ሕግ ይወልዳሉ” የሚባለው እንዳይደርስብን ፖለቲከኞቻችን ቢያውቁት፣ ቢገነዘቡት የምንላቸውን መሠረታዊ ጉዳዮች እንዲረዱልን ልናግዛቸው ይገባል፤ በአንድ በኩል ፖለቲከኞች የእኛው ስራ ውጤቶች ናቸውና።
ነገሩ ሰፊ ክርክር የማጫር እድል ቢኖረውም አንባብያን የአገራችን ፖለቲከኞች ሊያነቧቸው ይገባል ወይም ቢያነቧቸው ጥሩ ነው የምትሏቸውን መጻሕፍት ዝርዝር እንድታካፍሉኝ ልጋብዝ። በመጨረሻ የመጻሕፍቱን ዝርዝር እዚሁ መልሰን እናትማቸዋለን። መጻሕፍቱ በየትኛውም ቋንቋ የተጻፉ፤ ኢልቦለድም ልቦለድም ሊሆኑ ይችላሉ። ታሪክ፣ ፖለቲካ፣ የሕዝብ አስተዳደር፣ ኢኮኖሚ፣ ሕግ ወዘተ እያሉ ማሰቡ ያግዝ ይሆናል። የመጽሐፍ ርእስ ከጠፋ በርእሰ ጉዳይ ለምሳሌም “ሐሳብን ስለመግለጽ ነጻነት፤ ስለ ሕግ ልእልና ወዘተ ቢያነቡ” ብሎ ሐሳብ መስጠት አይከፋም።