“ገጽታን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያበላሹ ዘገባዎች” በመንግሥት ሚዲያዎች እንዳይተላለፉ ለፕሮግራም አስፈጻሚዎች ብርቱ መመሪያ ተሰጠ

(ሙሉ ገ.)

በአቶ በረከት ስምዖን የሚመራው” የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት” በመንግሥት ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚሠሩ አርታኢያንና ፕሮግራም አስፈፃሚዎች  የኢትዮጵያንና የመንግሥት ገጽታን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚያበላሹ ዘገባዎችን ንቁ ሆነው እንዲቆጣጠሩ የሚያዝ አዲስ መመሪያ አስተላለፈ፡፡  ከኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በቀጥታ የወረደው አዲስ መመሪያ ይበልጡኑ የሚመለከታቸው የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት እና የአዲስ አበባ መስተዳድር ብዙሃን መገናኛ ኤጀንሲን አርታኢያንና ፕሮግራም አስፈፃሚዎች ሲሆን ትላንት በከፍተኛ ኃላፊነትላይ ያሉ የተቋማቱ ሠራተኞች በኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አወያይነት መሰብሰባቸውን የዜና ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

እንደ ምንጮቻችን ገለፃ ለአዲሱ መመሪያ መውጣት ምክንያት የሆነው ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ መስተዳድር ቴሌቭዥን (ኢቲቪ 2) የተላለፈው በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ  ከተማ ውስጥ የሚገኘው ረጲ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ሕፃናት ተማሪዎች በረሃብ እየተጠቁ በመሆናቸው መምህራን ልጆቹን ለማስተማር ተቸግረው በቅድሚያ ገንዘብ አዋጥተው ዳቦና እንጀራ በመግዛት የሕፃናቱን ረሃብ ለማስታገስ ጥረት ሲያደርጉ የሚያሳይ የሃያ ደቂቃ የቴሌቭዥን ፕሮግራም በጣቢያው መተላለፉ ነበር፡፡

የሕፃናቱን እና የወላጆቻቸውን መራብ የሚያመላክተው ፕሮግራም ከሁለት ሣምንት በፊት በአዲስ አበባ መስተዳድር ቴሌቭዥን ቀርቦ ታይቷል። ፕሮግራሙ ከተላለፈ በኋላ  በአቶ በረከት ስምዖን የሚመራው የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት  የሁለቱን የቴሌቭዥን ጣቢያዎች አርታኢያን እና ፕሮግራም አስፈፃሚዎች ሲያሸብር እንደሰነበተ የዜና ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡