ዲቪ እና CV
(አሮን ፀሐዬ)
የገጠር የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ነኝ፡፡ መታወቂያዬ ላይ ከስሜ ትይዩ “ሌክቸረር” የሚል ማዕረግ አለበት፡፡ ኑሮ እና ሕይወቴ ግን ማዕረግ አልባ ነው፡፡ ደሞዜ ሁለት ሺሕ ስድስት መቶ ብር ይደርሳል፡፡ ይህ ብር ግርማ ሞገሱ አፍ ይሞላል፡፡ ሲኖሩበት ግን ወፍ ነው፤ ይበራል፡፡ እውነት እውነት እላችኋለሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድሮ የገቡትን ቃል እሳቸው ባያሟሉትም እኔ በራሴ ልወጣላቸው ብዬ በቀን ሦስቴ ያማረኝን ልብላ ብዬ በተውተረተርሁ ቁጥር ወር ሳይደርስ በዱቤ እጥለቀለቃለሁ። አስተማሪ ካልበላና ካላነበበ ራሱንም ትውልድንም ይገድላል፡፡ በርግጥ ማንበብ ከተውኩ ዘመን የለኝም፡፡ መብላት ግን መተው የማኢቻል ኾኖብኝ ይኼው አለሁ።
በደሞዜ ላይ 160 ብር የቤት አበል ጠብ ይደረግበታል፡፡ አንዲት አነስተኛ ክፍል ተከራይቼ፣ አነስተኛ ምግብ በልቼ፣ ጎረቤት ቲቪ እያየሁ እኖራለሁ፡፡ ለነገሩ የተከራየሁት ክፍል ብቻም ሳይኾን እውቀቴም አነስተኛ ነው፤ በግሌ ለዩነቨርሲቲ መምህርነት የሚያበቃ ዝግጅትም ኾነ ክምችት ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ትችላለህ ካለኝ ግን ምን አደርገዋለሁ፡፡ ለምን መንግሥትን “ዋሾ” አስብላለሁ፡፡ ትችላለህ ካለኝ እችላለሁ፡፡ እኔ ከመንግሥቴ በላይ ስለ’ኔ ካወቅኩ ቡዳ ነኝ ማለት ነው፡፡
የገጠር የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ በመኾኔ ብቻ ሰዎች ትልልቅ ጉዳዮችን ያማክሩኛል። እናቴ ሲያማት ሐኪም ቤት ሄዳ ላልተፈለገ ወጪ መዳረግ አትወድም፡፡ የተማረ ልጅ አለኝ እያለች ሰፈራችን አቅራቢያ በሚገኝ “ኪዮክስ” እየሄደች “ሚስኮል” ታደርግልኛለች፡፡ ለእርሷ እኔ ዶክተርም ጭምር ነኝ፡፡ እስካሁን ያልተገለጠላት ነገር ቢኖር ለምን በየወሩ ብዙ ብር እንደማልክላት ነው፡፡ ለምን ትልቅ ቤት እንደማልገዛላትም በደንብ አልገባትም፡፡ ግን ተስፋ ታደርጋለች፡፡ በእውነት እላችኋለሁ እንኳን ቤት ባለቆቡን ሚስማር ልገዛላት አልችልም፡፡ ለእማዬ ግን ይህን ማስረዳት ቅስሟን መስበር ነው፡፡
አሁን አሁን ዩኒቨርሲቲ ማስተማሬን ተከትሎ ሰዎች በተዘዋዋሪ በሚያሳዩኝ አክብሮት እጅግ እየተሰቃየሁኝ እገኛለሁ፡፡ ቢያንስ ክብሬን የሚስተካከል ብር ሊኖረኝ ይገባል ስል አስባለሁ፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥትን ተቀይሜዋለሁ፡፡ ደመወዝ እጨምራለሁ እያለ ሲያወራና ሲያስወራ ይኸው ስንት ዘመኑ፡፡
አብረውኝ ከሚያስተምሩ መምህራን ጋራ በትርፍ ሰዓታችን ስለ ደመወዝ ጭማሪ ማውራት አይታክተንም፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ እንዴት ሰው ስለደሞዝ ጭማሪ ብቻ ያወራል? ወሬውን ማን እንደፈጠረው አላውቅም፡፡ ሆኖም ከአጎራባች ዩኒቨርስቲዎች እንደተሰማ እገምታለሁ፡፡ ወይም ደግሞ ለማስተርስ ትምህርት አዲስ አበባ ሄደው የተመለሱ መምህራን ወሬውን ከዲግሪያቸው ጋራ ይዘውት መጥተው ሊኾን ይችላል የሚል መላምት አለ፡፡
ምንም ይኹን ምን እንዴት ለሁለት ዓመት ሰው አንድ ወሬ ያመነዥካል? ደመወዝ ጭማሪ፤ ደመወዝ ጭማሪ፣ ደመወዝ ጭማሪ. . .፡፡ አንድ ወቅት ሁላችንም ተሰላችተን ይህን ጉዳይ ላናነሳ ተማምለን ነበር፡፡ አዲስ የተቀጠረ አንድ “ጥላቢስ” የኾነ አስተማሪ “ጓደኛዬ ጋዜጣ ላይ ደመወዝ እንደሚጨመር አነበበ” ብሎ በማውራቱ የደመወዝ ወሬ በዩኒቨርሲቲው ዳግም አገረሸ፡፡ ጋዜጣውን አነበበ የተባለውን ልጅ ስልክ እንዲሰጠን ተማጸንነው፡፡ በጄ አላለም፡፡ “ላውድስፒከር” አድርጎ ራሱ ጓደኛውን እንዲያወራው ለመንነው፡፡ በሰበብ ላይ ሰበብ እያበዛ ነገ ዛሬ እያለ አሸን፡፡ በዚሁ ተናደን አገለልነው፡፡ ሲያንሰው ነው፤ በሰው ሕይወት ይቀልዳል እንዴ፡፡ ገጠር ውስጥ ማግለልን የመሰለ ቅጣት አይገኝም፡፡
ሐሳብ ተከሰተ
ሰሞኑን ባልተለመደ ኹኔታ የምኖረው ኑሮ እጅግ መረረኝ፤ አንገሸገሸኝ፡፡ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡ ኾኖም እንደ ድንገት ድንቅ ሐሳብ ተከሰተልኝ፡፡ ዲቪ መሙላት፡፡ ቢንጎ!! ይህ ሐሳብ ለምን እስከዛሬ እንዳልተከሰተልኝ ገረመኝ፡፡ ያን ቀን ምሽት ደስ ብሎኝ አመሸሁ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ የገጠር ሕይወቴ በተስፋ ተሞላች፡፡ ሌሊቱን ደስ ደስ የሚሉ ህልሞችን አየሁ፡፡ በተከታታይ ያየኋቸው ህልሞች መቼታቸው ሁሉ በአሜሪካ ከተሞች ላይ ኾነ፡፡
በነጋታው ጠዋት ስነቃ ግን ሞራሌና ወኔዬ ከዳኝ፡፡ እንዴት ዲቪ እሞላለሁ፡፡ የት ሄጄ እሞላለሁ፡፡ ሰው ቢያየኝስ፡፡ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ እንደ ተራ ሰው ዲቪ ይሞላል እንዴ!
በመሠረቱ ዲቪ ከእኔ ስብእና ጋራ በፍፁም አይሄድም፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ መለመንና የሰው መመኘት አልወድም፡፡ እናቴ እንጀራ ከጎረቤት ተበድረህ ይዘህ ና ስትለኝ እንኳ በጀ ብያት አላውቅም፡፡ ጦሜን ማደር እመርጣለሁ፡፡ ትምህርት ቤትም ቢኾን ላጲስ ተውሼ አላውቅም፡፡ የተሳሳትኩትን ጽሑፍ በምራቄ አክኬ ፈትጌ አጠፋለሁ፡፡ እከካም ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ግን እውነቱ ይኸው ነው፡፡ ሁለተኛ ክፍል አብረውኝ ይቀመጡ የነበሩ ልጆችን መቅረጫ ብያቸው አላውቅም፡፡ እርሳሴን ከግድግዳ ጋር እያፋጨሁ አሾላለሁ፤ እቀርጻለሁ፡፡አሁንም እከካም ልትሉኝ ትችላላችሁ፡፡ ግን እውነታው ይኸው ነው፡፡
ዲቪ አገርህን ትተህ የሰው አገር አኑሩኝ እያልክ የምትለማመጥበት ሕጋዊ ማመልከቻ ነው፡፡ ይህን ማመልከቻ ሞላሁ ማለት የአሜሪካ መንግሥትን ተንበርክኬ ውለታ ዋልልኝ እያልኩት ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ፍፁም ከኔ አፈጣጠር እና ስብዕና ጋራ አብሮ የሚሄድ አይደለም፡፡ የአሜሪካ መንግሥትን በማመልከቻ ከምለምን በእግር ወደ አሜሪካ ብሄድ ይቀለኛል፡፡ የዲቪ መሙላት ሐሳብ ውስጤ ላይ ከፍተኛ መናወጥን ሊያስከትል የቻለው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ራሴን የከዳሁት ያህል ተሰማኝ፡፡
የተፈጠረብኝን ድብታና የስሜት መላሸቅ ለማስታገስ የሥራ ባልደረቦቼ ጋር ሄድኩኝ፡፡ የዲቪ ወሬን እንዴት ብዬ እንደማነሳባቸው እያውጠነጠንኩ፡፡ ቀድሜ ጉዳዩን እኔው ካነሳሁት “አጅሬው! ዲቪ ሞላሽ እንዴ” እያሉ ዓመቱን ሙሉ መዘባበቻ ሊያደርጉኝ ይችላሉ፡፡ በዘዴ ነገሩን ማንሳት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ዘወትር የምንጎለትበት ቦታ ደረስኩ፡፡ ሁሉንም እዚያው ተሰብስበው አገኘኋቸው፡፡ ያው እንደተለመደው የደሞዝ ጭማሪን ጉዳይ እያመነዠኩ ነበር፡፡ ጋሽ ግርማ ወ/ጊየርጊስ በፓርላማ መክፈቻ ንግግራቸው ላይ የደሞዝ ጭማሪ ጉዳይን አንስተዋል የሚል አዲስ መረጃ በመሰማቱ የሁሉም ፊት ፈካ ፈካ እንዳለ ለማስተዋል ቻልኩ፡፡ ኾኖም ጭማሪው ለዩነቨርሲቲ መምህራን ብቻ ሳይኾን ለሁሉም የኢትዮጵያ ሠራተኛ መኾኑ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አንዳንድ ሂሳብ-ዘመም መምህራን ለጉባዔው ለማስረዳት ሞከሩ፡፡ በደስታችን ላይ ዉኃ ቸለሱበት፡፡ የደሞዝ ጭማሪው ወሬ እየበረደ ሲመጣ የዲቪውን ጉዳይ ለኮስ ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ፡፡
“አናንተ! የዘንድሮ ተማሪዎች ደግሞ ጭራሽ የእንግሊዝኛ ፊደል ሳይጨርሱ ነው እንዴ ዩኒቨርስቲ የላኳቸው?” አልኩ ድምፄን ጎላ አድርጌ፡፡ ቀጥል የሚል ምልክት ተሰጠኝ፡፡ አንዱ ስሙን ሲጽፍ አይቼው በጭራሽ “ቫውል” አይጠቀምም፤ ታምናላችሁ? ስሙ ተሻለ ነው፡፡ እንዴት “ስፔል” እንዳደረገ ታውቃለህ “ቲ፣ኤስ፣ኤች፣ኤል”፡፡ ባወራሁት ነገር ማንም አልተገረመም፡፡ ይልቁንም ሁሉም ከዚህ የባሰ የሚሉትን እያነሱ ማስረዳት ጀመሩ፡፡ አሁን ወደ ዲቪው ጉዳይ መግቢያ ሰዓት እንደኾነ ተሰማኝ፡፡ የ“ስፔሊንጓን” ወሬ ኾነ ብዬ እንጀመርኳት አልገባቸውም፡፡
“ስሙኝማ! ከተማ ትናንት ተለጥፎ ያየሁትን ልንገራችሁ፡፡ ዲቪ እንሞላለን የሚለው ጽሑፍ ላይ “Good Luck” የሚለውን ቃል እንዴት ጽፈውት ዐየሁ መሰላችሁ፣ “Good Lack”፡፡” ከገመትኩት በላይ ሳቁልኝ፡፡ ሳቃቸው እንደበረደ ከመሐላችን አንዱ “ዲቪ ተጀመረ እንዴ?” ሲል ጠየቀ፡፡ በቀጥታ ሊመልስለት የደፈረ ግን አልነበረም፡፡ ቀለል አድርገው፣ “እኔንጃ”፣ “መሰለኝ”፣ “ኸረ!”፣ “ይባላል” አሉ፤ የተወሰኑት፡፡
አውቀው ነው፡፡ ሁሉም መቼ እንደተጀመረ አይደለም ስንት ሰዓት ላይ እንደተጀመረ ያውቃሉ፡፡ ዲቪ ሞላ ላለመባል ነው፡፡ ተነቃቅተናል፡፡
DV regardless of CV
ያለንባት ከተማ በኦባማ ፎቶዎች ከተጥለቀለቀች ሁለት ሳምንታት አልፈዋታል፡፡ ዲቪ እንሞላለን የሚሉ ማስታወቂያዎች የትም ነው የተሰቀሉት፡፡ ከሁሉም የገረመኝ ግን ይህን ማስታወቂያ ዩኒቨርስቲያችን ውስጥ በትልቅ ባነር ተሰቅሎ ማየቴ ነው፡፡ የተማሪዎች ካውንስል በቅናሽ ዋጋ ዲቪ መሙላት በመጀመሩ የካፌ ሰልፍን የሚያስንቅ ረዣዥም ሰልፎች በዩኒቨርስቲው ተፈጥረዋል፡፡ ዲቪ ለመሙላት ረዥም ሰልፍ፡፡ ልክ አዲሳባ ኢሚግሬሽን ጠዋት ጠዋት አየው የነበረውን ሰልፍ አስታወሰኝ፡፡ ይህን ያየሁ ቀን ከፍተኛ ድንጋጤም ከፍተኛ ግርምትም ተፈጠረብኝ፡፡
ነገሩ ስላስደነቀኝ ተጨማሪ ነገር ለማግኘት በዩኒቨርስቲው ግቢ መዘዋወር ጀመርኩ፡፡ የዲቪ ማስታወቂያዎች በተማሪዎች ካፌ፣ በመማርያ ክፍሎች ደጅ ባሉ የማስታወቂያ ሰሌዳዎች፣ በቤተ መጻሕፍቱ በር ላይ ወዘተ ተለጣጥፎ አየሁ፡፡ የማስታወቂያው ይዘት ተማሪዎች ዕድሉ እንዳያመልጣቸው እና እንዲጠቀሙበት የሚያባብል ነው፡፡ የተማሪዎች ካውንስል ነው ይህንን የሚስተባብረው፡፡ በኔ ጊዜ የነበረው የተማሪዎች ካውንስል የመንግሥት ለውጥ እንዲመጣ ያስተባብር እንደነበር ትዝ አለኝ፡፡
ወደራሴ ጉዳይ ተመለስኩ፡፡ በእርግጥ አሳፋሪ ነው፡፡ ነገር ግን ማንም ሳያውቅ ዲቪ መሙላት አለብኝ፡፡ እንዴት? በትንሽ ከተማ ውስጥ እንኳን እኔ ያለሰፈሯ የመጣች ዝንብ እንኳ ትታወቃለች፡፡ ለማንኛውም አማራጮችን ለማየት ከዩኒቨርሲቲው ወደ መሀል ከተማ የሚወስድ ታክሲ ለመያዝ ተንቀሳቀስኩ፡፡ ዩኒቨርሲቲው ዋና በር ላይ ታክሲው እስኪሞላ ብዙ ነገር ለመታዘብ ቻልኩ፡፡ ቀድሞ የተማሪ “ሃንድአውት” በማባዛት ይጠመዱ የነበሩ ፎቶኮፒ ቤቶች መስኮቶቻቸው በዲቪ ማስታወቂያ አሸብርቋል፡፡ እዚህም ዲቪ ለመሙላት ብዙ ተማሪዎች ተሰልፈዋል፡፡ በእጆቻቸው የሚባዙ ሃንድ አውቶች ሳይኾን የዲቪ ፎርሞችን ነበር የያዙት፡፡
ከተማ ደርሼ ከታክሲው እንደወርድኩ ወደ አንድ ኢንተርኔት ካፌ ጎራ አልኩኝ፡፡ ከተደረደሩት ኮምፒውተሮች ወደ አንዱ ጠጋ ብዬ ኢንተርኔት የምበረብር መስዬ የቤቱን ደንበኞች መበርበር ጀመርኩ፡፡ ሰዎች ነጭ አቡጀዲ እየተደገፉ በወረፋ ፎቶ “ቀጭ” ይደረጋሉ፡፡ ብዙ ወጣቶች፣ ጥቂት ጎልማሶች፣ ጥቂት ትልልቅ ሰዎች፣ ባልና ሚስት፣ ባል ሚስት እና ሰባት ልጆቻቸው፣ ጋዝ ልትገዛ የተላከች የቤት ሰራተኛ፣ መካኒክ ከነሽርጡ፣ ያስተማርኳቸው ተማሪዎች ወዘተ፣ ቤቱ የማያስተናግደው ዐይነት ሰው የለም፡፡ ሁሉም ለዲቪ የጭንቅ አማላጇን ስም ይጠራል፡፡ ይህ ሕዝብ አገሪቱን አይፈልጋትም እንዴ፡፡ ለምን አንድነቱን በግልፅ ጨረታ ሽጧት አይሄድም?
በዚህ ኢንተርኔት ቤት ጠረጴዛ ላይ ዲቪ የተሞላበት ወረቀት ተከምሯል፡፡ በአመቱ መጨረሻ የማርማቸውን የተማሪዎቼን ፈተና ወረቀቶች አስታወሰኝ፡፡ ለነገሩ የዚህን ዘመን ተማሪዎች ፈተና ከማረም የሰሊጥ እርሻ ማረም ይሻላል፡፡ ወይም ደግሞ ይህንን የዲቪ ክምር ማረም ሳይሻል አይቀርም፡፡ ሁለቱም ‹‹ስቤሊንግ›› ማረም ስለሆነ ብዙም አይራራቁም፡፡ የአሜሪካ መንግስት ዲቪ አራሚ አድርጎ ቢቀጥረኝስ ብዬ አሰብኩ፤ ለአፍታ፡፡ ሐሳቤ በራሱ ፈገግ አሰኘኝ፡፡ አይ አሜሪካ ስላንቺ ማሰብ በራሱ ፈገግታን ይፈጥራል ለካ፡፡
በዚህ ኢንተርኔት ካፌ ብዙ ሰው ዲቪ ለመሙላት የሚሽቀዳደመው ከዚህ ቀደም በዚህ ቤት ዲቪ የሞሉ አራት የከተማዋ ነዋሪዎች ዲቪ ደርሷቸዋል በመባሉ ነው፡፡ ገድ አለው ይባላል ይህ ቤት፡፡
ወደራሴ ጉዳይ ልመለስ፡፡ ዘንድሮ እንዴትም ብዬ ዲቪ መሙላት እንዳለብኝ የተነጋገርን መሰለኝ፡፡ ስለዚህ እዚሁ ገድ አለው የሚባልለት ቤት ለምን አልሞላም፡፡ የማስተምራቸው ልጆችና የሚያውቀኝ ሰው በቤቱ አንደሌለ ሳረጋግጥ ፎቶ የምታነሳዋን ልጅ ዲቪ መሙላት ፈልጌ እንደመጣሁ ነገርኳት፤ የሞት ሞቴን፤ በሹክሹክታ፡፡
“ይቻላል፣ አስር ብር ከፍለህ ፎቶ ትነሳና ይህን ፎርም ሞልተህ ነገ ማረጋገጫ እንሰጥኻለን፡፡” አለችኝ ጮኽ ብላ፡፡አሳቀቀችኝ፤ምን አለ እኔ እንደማወራው ቀስ ብላ ብታወራ፡፡ ተማሪዎቼ እንዲሰሙ ነው? ምቀኛ!
እንደተረዳሁት ከሆነ የኢንተርኔት ፍጥነቱ ቀን ቀን ቀርፋፋ ስለሆነ ኢንተርኔት ቤቶቹ ዲቪ ፎርሙን በወረቀት ብቻ እያስሞሉ ሌሊት ሌሊት በኢንተርኔት ይልኩታል፡፡ በነጭ ወረቀት ለሞሉት ሰዎች በነጋታው የማረጋገጫ ደብዳቤ ይታደላቸዋል፡፡ በዚህ መሀል የስም ስህተት ቢከሰት ግን ማን ተጠያቂ እንደሚሆን አልገባኝም፡፡ እድሌን ማበላሸት የለብኝም፡፡ “እመለሳለሁ” አልኩና ሹልክ ብዬ ወጣሁ፡፡
በከተማዋ ያሉ ሁሉም ኢንተርኔት ቤቶች ደንበኞቹ እያዩ ዲቪ እንደማይልኩ ተረዳሁ፡፡ ይህ መልካም ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ ሌላ አማራጭ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ በከተማዋ ወደሚገኘው አንድዬ ፖስታ ቤት አመራሁ፡፡ በሩ ላይ ከፍተኛ መጨናነቅና ፀብ የሚመስል ግርግር አየሁ፡፡ በቅርቤ ያገኘኃትን የገጠር ልጅ ስለጉዳዩ ጠየቅኳት፡፡ ዲቪ ለመሙላት ጠዋት ወረፋ የያዙ ሰዎች ጎረምሶች ያለወረፋቸው እየገቡ አስቸግረዋቸው ረብሻ እንደተፈጠረ ነገረችኝ፡፡ የፖስታ ቤቱ ሰራተኞች ደግሞ በስነስርዓት ወረፋ ካልተያዘ አናስተናግድም ብለው ማመፃቸውን ጨምራ አብራራችልኝ፡፡
ፖስታ ቤት በር ላይ ያሉትን ማስታወቅያዎች ለማንበብ ሞከርኩ፡፡ ዲቪ ዘንድሮ ለአንድ ወር ብቻ እንደሚቆይ፣ የቀሩት ቀናት ጥቂት እንደሆኑ፣ ዲቪ በፖስታ ቤት መሙላት ብዙ ጥቅሞች እንዳሉት፣ ለምሳሌ ዲቪው ሲመጣ የስም ስህተት ቢኖረው ፖስታ ቤት ለአሜሪካ ኤምባሲ ቀጭን ደብዳቤ የመፃፍ ብቸኛ ባለመብት እንደሆነ ወዘተ ይናዘዛል፡፡ፖስታ ቤት መንግስታዊ ድርጅት ነው፡፡ ዜጎቹን በተዘዋዋሪ ሌላ አገር እንዲሄዱ ተግቶ እየሰራ እንደሆነ ነቃሁበት፡፡
ለነገሩ እኔ ብቻ ሳልሆን የመንግስት ባለስልጣናትም ዲቪ ይሞላሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ዲቪ ደርሷቸው ቀስ ብለው ሊሄዱ ሲሉ አይደል እንዴ የተደረሰባቸው፡፡ እኔ የምሰራበት ዩኒቨርሲቲ የ‹‹ሪሰርች›› ፕሬዝዳንትም ሰሞኑን ዲቪ ሲሞሉ እንደታዩ በወሬ ወሬ ሰምቻለሁ፡፡ ሰውየው እድሜያቸው ገፍቷል እኮ፡፡በዚያ ላይ አሜሪካ ነው የተማሩት ሲባል ነበር፡፡ ተንቀዥቅዠው መጥተው ነው ጉድ የሆኑት ማለት ነው፡፡ ዲቪ ሲቪ እንደማይመርጥ ተረዳሁ፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ዲቪ መሙላት ይፈልጋል፡፡ከሊቅ እስከ ደቂቅ በሚባለው ውስጥ ደግሞ እኔ እገኛለሁ፡፡ ስለዚህ ዲቪ እሞላለሁ፡፡ ቅድም ወደነበርኩነት ኢንተርኔት ካፌ ሄድኩኝ፡፡ ፈገግ ብዬ ፎቶ ተነሳሁ፡፡ኮስተር ብዬ ፎርሙን ሞላሁ፡፡ ከኢንተርኔት ቤቱ ስወጣ ከሸሌ ጋር ያደርኩ ያህል ቀፋፊ ስሜት ተሰማኝ፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ ሆይ አንቺም ዲቪ ሞልተሸ ብትሄጂ ይሻልሻል አልኩ በሆዴ፡፡