“ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ!” [ክፍል ሁለት]

(መሀመድ ሰልማን)

ዶሮ ማነቂያ

በዶሮ ማነቂያ ዶሮ አይታነቅም፡፡ ሰው ግን ይታነቃል፡፡ለምሳሌ ኑሮ አልሞላ ሲለው፤ ወይም ዶሮ እጅግ አምሮት መግዣ ሲያጣ…

ኑሮን ቀለል አድርገው መኖር የሚሹ ዜጎች ዶሮ ማነቂያን ይመርጣሉ፡፡ አንተም ኪስህ ቢነጣ፣ መሄጃ ብታጣ ፒያሳ እንደ ቦሌ “ሂድ ከዚህ!”  ብላ ውሻ አታደርግህም፡፡  ቦሌ ብዙ ፎርጅድ የቦሌ ልጆች እየተሳቀቁ የሚስቁባት ሰፈር እንደሆነች ልንገርህ፡፡ ፒያሳ ግን 32 ጥርስና 12 ጥርስ ያላቸው ዜጎች እኩል የሚስቁባት ቦታ ናት፡፡ “የቦሌ ልጅ የለውም አባይ” ሲባል ሰምተህ ይሆናል፣ የፒያሳ ልጅ ደግሞ የለውም ፎርጅድ፡፡ ድሃና ሀብታም እየተጋፉ የሚዝናኑባት ድንቅ ስፍራ፡፡ ከብሪቲሽ ካውንስል ጀርባ እንደ ፍልፍል ሹልክ እያሉ የሚወጡ ልብን ወከክ የሚያደርጉ ቆነጃጅትን ዐይተህ ይሆናል፡፡ ቤታቸውን ብታየው ትገረማለህ፤ ኩሽና ነው፡፡

ለነገሩ ድፍን አዲስ አበባ ውስጥ ብትዞር ከፎቅ ጀርባ ፎቅ አታገኝም፡፡ በቅርቡ የተወለዱትን ቦሌ መድኀኔዓለምንና አዲሱን ካዛንቺስን ትተህ እግርህ እስኪቀጥን ብትዞር በአዲሳባ ከፎቅ ጀርባ ፎቅ አታገኝም፡፡ካላመንክ እንወራረድ፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ የፎቅ ጥቅም በስንት እንደሚከፈል ታውቃለህ? በሁለት ካልክ ትክክል ነህ፡፡ የመጀመርያው የፎቁ ባለቤት ብ…ዙ መስታወት እንዳለው ማስመስከር ሲሆን ሁለተኛውና ዋነኛው ግን ከፎቁ ጀርባ ያለውን ገመና መሸፈን ነው፡፡ ገመና ስልህ የሰፈሩ ወይም የፎቁ ባለቤት ገመና ሊሆን ይችላል።

ይህ ካልገባህ ሂድ ቦሌ፡፡ የአገርህ ቴሌቪዥን የሚኮራባቸው እነ “ሸራተን” እነ “ደምበል”፣ እነ “ጌቱ ኮሜርሻል”፣ እነ “አበሩስ” ጀርባ ማንም ሳያይህ ግባ፡፡ ትበረግጋለህ፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ፎቆችን ታከብራለህ፡፡ ፎቆች ለአገርህ የዋሉት ውለታ እየታሰበህ ዕንባህ በዐይንህ ግጥም ይላል፡፡ “አገሬ ኢትዮጵያ ተራራሽ አየሩ፣ ፏፏቴሽ ይወርዳል በየሸንተረሩ፣ ልምላሜሽ ማማሩ” የሚለው ዘፈን ለምን ፎቆቹን ገሸሽ እንዳረገ አይገባህም፡፡

ቆራጡ መንጌ ፎቅ አልደርስልህ ሲለው አይደል እንዴ ወሎ ሰፈር ሎሊ ህንፃ ፊትለፊት ያሉትን ገመናዎች በግንብ ፕላስተር የጋረዳቸው? መሌ እሳቱ ግን ረጋ ብሎ አሰበ “ችግሩን መቅረፍ ያለብን ከምንጩ ነው” አለ፡፡ ጭርንቁስ ሰፈሮችን ቡልዶዘር ላከባቸው፡፡ የተማረ ይግደለኝ!!

ፒያሳ ፎቅ አልባ ናት፡፡ በእርግጥ የቀድሞው የአገሪቱ ሰማይ ጠቀሱ ሕንጻ “አራዳ” አራዳ ላይ ነው የሚገኘው፡፡ በእርግጥ በጃንሆይ ጊዜ 8 ሚሊዮን ብር የተከሰከሰበት የማዘጋጃ ቤት ሕንጻ ደረቱን ነፍቶ የቆመው በፒያሳ እምብርት ነው፡፡ ግን ፒያሳ ከነቦሌ ጋር ስትነጻጸር ብዙ ፎቆች አሏት ለማለት አያስደፍርም፡፡ ስለዚህ ፒያሳ ብዙ ፎቅ ከሌላቸው የምስራቅ አፍሪካ ሰፈሮች አንዷ ናት ብለን መናገር እንችላለን፡፡

ፒያሳ ፎቅ አልባ ናት ካልን “ገመናዋን ማን ሸፈነላት?” የሚለው ጥያቄ ይከተላል። መልሱ ቀላል ነው፤ ወርቅ ቤቶች፡፡ በፒያሳ ወርቅ ወርቁን ስታይ ከጀርባ ምን እንዳለ ትረሳለህ፡፡ በፒያሳ ቆንጆ ኮረዶች ሽው እልም ሲሉ ስታይ ማሰቢያህ ይሰለባል፡፡ ደፈር ብለህ አንዷን የፒያሳ ቆንጆ ዳሌ ዳሌዋን እያየህ ብትከተላት ግን በብሪትሽ ካውንስል ወይ በአምፒር ወይ በሠራተኛ ሰፈር ቀጭን መንገድ ውስጥ ትገባለች፡፡ መጨረሻዋን ልይ በለህ   ትከተላታለህ፤ እስከ ውስጥ፡፡ ድንገት ትሰለብብኻለች፡፡ በዚህ ቅፅበት ምን ሰወራት ብለህ ለራስህ ስታንሾኳሽክ ከጭርንቁስ ቤቷ ወጥታ “ምን አልክ?” ልትልህ ትችላለች፡፡ ስለዚህ የፒያሳ ልጅ አትከተል፡፡ ከተከተልክም እጇን ይዘህ ተከተላት።

ቆንጆ የፒያሳ ልጅ ጠብሰህ ተሳክቶልህ ያውቃል? እንግዲያውስ ልሸኝሽ አትበላት፡፡ ትቀየምኻለች፡፡ “ለምን?” ብለህ ከጠየከኝ ልጅቷ አምልጣሃለች።

ኢትዮጵያዊ ጨዋ፣ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያደረበት፣ የሰው የማይመኝ ሕዝብ እንደሆነ ለመመስከር ፒያሳ በቂ ናት፡፡ ፒያሳ የሚገኝን አንድ ቱባ ወርቅ ቤት በህሊናህ አስብ፡፡ ከጀርባው ያለውን ቤትና ቤተሰቡንም ለማስታወስ ሞክር፡፡ ትገረማለህ፡፡ የኋለኛው ቤት ባለቤትና አስራምናምን ልጆቹ ወርቅ ቤቱን ሰርስሮ ስለመግባት አስበው አያውቁመም፡፡ የሸዋ ዳቦ በልተው ሆዳቸውን እያከኩ ወርቅ ቤቱን ተደግፈው ኅብረ-ትርዒት እያዩ ይተኛሉ፡፡

ወርቅ ቤቶችን ከተደገፉ ቤቶች በአመዛኙ የሚገኙት በዶሮ ማነቂያ ነው፡፡ በመሆኑም  ለዶሮ ማነቂያ ክብር ስንል ሰፈሩን በዶሮ በረር እንቃኛለን፡፡

ሂድ ዶሮ ማነቂያ፡፡ ውስጥ ውስጡን፡፡ ፒያሳን ፒያሳ ያደረጋት አንዱ ሀብቷ ምን ይመሰልሃል? ዶሮ ማነቂያ ነው፡፡ በሃያ ብር 24 ሰዓት ቀብረር ብለህ የምትኖርባት ጉደኛ የፒያሳ ጓዳ፡፡ በቸርነቷ የሚስተካከሏት “አራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ሰፈር” እና  “አውቶብስ ተራ” ብቻ ናቸው፡፡ እስኪ ለአፍታ የዶሮ ማነቂያን ድርሳን እንግለጥ፡፡

መቼ ለታ ዶሮ ማነቂያ ሄድኩ፡፡ ኪሴ ማፍሰስ ስለጀመረ ሰፈሩን ከሞሉት ማዘር ቤቶች ወደ አንዱ ጎራ አልኩኝ፡፡ ሁሉም የምግብ ዝርዝሮች የቤቱ ግድግዳ እየተፋቀ ተጽፈዋል፡፡ የምግቦቹ ዋጋ ከ10 ብር እንዳይዘል ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ “ጥብስ 9ብር ከ75 ሳንቲም” ይላል፡፡ በዚህ ድንቅ ቤት ድንቅ ምሳ በልቼ ልወጣ ስል እንዲህ የሚል ጽሑፍ ከበሩ የውሰጠኛው ክፍል አነበብኩ፡፡ “ቅሬታዎን ለኛ፣ አድናቆትዎን ለጓደኛ!!” በመጨረሻም ተመጋቢዎቹ ከቤቱ ከመውጣታቸው በፊት ከተሰነጣጠቀው የቤቱ ግድግዳ ቀጭን እንጨት ሲመዙ አየሁ፡፡ ስቲኪኒ መሆኑ ነው፡፡ ሲሉ ሰምታ ዶሮ ታንቃ ሞተች!

ሂድ ዶሮ ማነቂያ፤ እነ “መካ ቤት”፣ እነ “ሸመሱ ቤት”፣ እነ “ኑሪያ ቤት”፣ እነ “ቦስ ሺሻ ቤት”፡፡ በቴሌቪዥን ተንሰፍስፈህ የምታያቸው አርቲስቶች አንድ ጥግ ይዘው በነጻነት ሲጋራቸውን ሲያቦኑት፣ በርጫቸውን ቦርጫቸው ላይ አስቀምጠው ሲበርጩት ትመለከታለህ፡፡ ከዚህ ስፍራ ማንም ፈርሙልኝ አይላቸውም፡፡ ማንም አይቁለጨልጭባቸውም፡፡ እነርሱን ከዶሮ አስበልጦ የሚያያቸው ሰው በድፍን ዶሮ ማነቂያ አታገኝም ፡፡ ስለዚህ ነጻነታቸውን ለመጎናጸፍ ዶሮ ማነቂያን መረጡ፡፡ እርሷም የነጸነት መሬታቸው ሆነች፡፡

በየትያትር ቤቶች እጅህ እስኪቀጥን ያጨበጨብክለት ድርሰት የተፈጠረው ዶሮ ማነቂያ ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ የድርሰቱ ቃለ ተውኔት የሚሸመደደውም በእነ “መካ ቤት” የጫት ጉዝጓዝ ላይ ነው፡፡ ደግሞ አርቲስት ብቻ አይምሰልህ የዶሮ ማነቂያን መታወቅያ የወሰደው፡፡ የተማሩና የተመራመሩ፣ ኢትዮጵያ ጨረቃ ላይ ከወጣች መወጣጫ መሰላሉን ያዋቅራሉ የሚባሉ ምሁራን ተራ ሰው መስለው ዶሮ ማነቂያ ይሽሎኮሎካሉ፡፡ ማን መሆናቸውን የምታውቀው ግን ከእነርሱ ጋር ለማውራት እድሉ ሲገጥምህ ብቻ ነው፡፡ እውቀታቸው መሬትን ከሰማይ ይደባልቃል፡፡ እነርሱ ግን ከዶሮ ጋር አባሮሽ ይጫወታሉ፡፡

ዶሮ ማነቂያ ሺሻና ጫት ቤቶቿ በየጊዜው በዘመቻ ይታሸጉባታል፡፡ በዚያ ስታልፍ በቤቶቹ በር ላይ በቀይ ቀለም “ታሽጓል” የሚል ጽሑፍም አንብበህ ይሆናል፡፡ ግን እውነት የታሸገ እንዳይመስልህ፡፡ በጀርባ በኩል መስኮት የሚመስል በር አለው፡፡ የቤቱ ደንበኞቹ ብቻ ናቸው በር መሆኑን የሚያውቁት፡፡ ቀበሌዎችን ለማዘናጋት ዶሮ ማነቂያዎች የፈጠሯት መላ ናት፡፡

ዶሮ ማነቂያ የራሷ መግባቢያም አላት። ለምሳሌ በዶሮ ማነቂያ “ዛሬ የፈረንሳይ ምርጥ ካራቴ ይታያል!” የሚል ማስታወቂያ አንብበህ ይሆናል፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልኾንክ ግን ይህ ምን እንደኾነ አይገባህም፡፡ የወሲብ ፊልም ማስታወቅያ ነው፡፡

የሰፈረህ አውራ ዶሮ በቤትህ ጓሮ ሄዶ ሴት ዶሮህ ላይ ቂብ እንደሚለው ሁሉ በዶሮ ማነቂያም ሰዎች እንደዚያ ሲያደርጉ በቴሌቪዥን ታያለህ፡፡ ያለ ምንም ሐፍረት፤ ያውም ሻይ እየተፈላልህ፤ ያውም ለውዝ እየተፈለፈለልህ፡፡ ይህን የሚያሳይህ ቤት የግራና ቀኝ ግድግዳዎቹ በኳስ በምታብድላቸው የአውሮፓ ቡድኖች ፎቶ የተሞላ ነው፡፡ ማዘናጊያ ነው፡፡እግር ኳስ የሚታይ እንዲመስል የተሰቀሉ ናቸው፡፡ በዚህ ቤት ግን እውነት እልኻለሁ ነግቶ እስኪመሽ የአልጋ ጨዋታ ካልኾነ የሜዳ ጨዋታ አይታይም፡፡

በእርግጥ የአልጋ ጨዋታንና የኳስ ጨዋታን እያፈራረቁ የሚያሳዩ ቤቶች በዶሮ ማነቂያ የሉም አልልህም፡፡ ለምሳሌ “አድማሱ ቤት”፣ “ቴዲ ቤት”፣ “ገዛኸኝ ሚስት ቤት” “አንደርግራውንዱ ቤት” ይህንን ያደርጋሉ፡፡ ቀሪዎቹ ግን ለማዘናጊያ ካልሆነ ኳስ ድቡልቡል መሆኗንም የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ በነገራችን ላይ የወሲብ ፊልምን የሚያስኮመኩሙት ቤቶች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየተመናመነ መሆኑን ስነግርህ በታላቅ ኀዘን ነው፡፡  ዛሬ አንድ ሰባት የሚሆኑ ጓሮዎች ብቻ ናቸው በድፍን ዶሮ ማነቂያ ወሲብ የሚያስኮሞኩሙት፡፡ ሰዎች የራሳቸውን ፊልም ወደመሥራት አዘንብለዋል ወይም ሌላ ተፎካካሪ ማሳያዎች በአጎራባች ሰፈሮች ተፈጥረዋል ማለት ነው።

በጠቀስኩልህ ቤቶች ግን ልቅ ወሲብ ከማለዳው ሦስት ሰዓት እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት ይታጨዳል፡፡ የጠጅ ቤት አግዳሚ ወንበሮች ተዘርግተው፣ መብራት ጠፍቶ፣ ትንፋሽ ተውጦ፣ ዝምታ ነግሶ ወሲብ ይነግሣል፡፡ የአረብ ወሲብ፣ የህንድ ወሲብ፣ የፈረንሳይ ወሲብ፣ የቻይና ወሲብ፣ የአፍሪካ ወሲብ፣ ሊፍት ውስጥ፣ ጫካ ውስጥ፣ መኪና ውስጥ፣ ኮሪደር ውስጥ፣ ማድቤት ውስጥ፣ ሶፋ ላይ፣ ሼልፍ ላይ፣ ወለል ላይ፣ ደረጃ ላይ፣ በቡድን በተናጥል በተመሳሳይ ፆታ፣ በተቃራኒ ፆታ፣ ከፈረስ ጋር፣ ከሜዳ አህያ ጋር፣ በመጨረሻም ከዶሮ ጋር ይወሰባል፡፡በዶሮ ማነቂያ፡፡ በቴሌቪዥን፡፡

የዶሮ ስጋና ዶሮ ማነቂያ

ዶሮ ማነቂያ ስድስት ሰዓት ሲሆን በአራራ ታብዳለች፡፡ ድሬዳዋን ታስንቃለች፡፡ ሰዎች ባህርያቸው ይለወጣል፡፡ ይገላምጡኻል፡፡ በዚህ ሰዓት አንደበትህን ለመግራት ሞክር፡፡ በአራራ ጫማ ጥፊ ትመታለህ፡፡

ዶሮ ማነቂያ ቡናን እየተካ ያለውን አረንጓዴ ቅጠላችንን ለፒያሳ ሕዝብ ኤክስፖርት በማድረግ ትራንስፎርሜሽኑን በማፋጠኑ ረገድ የምትጫወተው ሚና የዋዛ አይደለም፡፡ ዶሮ ማነቂያ ጫትን በብዛትና በስፋት ለዜጎቿ በማዳረስ ከሲኒማ ራስ ቀጥሎ በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ እንደሆነች በሬዲዮ ሰምቻለሁ፡፡ ያም ሆኖ ከዶሮ ማነቂያ እሴቶች መሀል ወሲብ ቤቶችንና ጫት ቤቶችን ብቻ ዘርዝሮ ይህንን ጽሑፍ መዝጋት የበሉበትን ወጪት መስበር ይሆናል፡፡ በመሆኑም የዶሮ ማነቂያን ድርሳን የምንዘጋው በመልካም ዜና ይሆናል፡፡

የጨርቆስ ልጆች “ከሰፈሮች ሁሉ ማንን ትወዳላችሁ?” ቢባሉ “ዶሮ ማነቂያን አሉ” አሉ፡፡ ለምን ይመስልኻል? በዶሮ ማነቂያ ስጋ እንደተራ ምግብ በየበረንዳው በመስቀያ ተሰቅሎ ስለሚያዩ ነው፡፡ የጨርቆሶችን የሥጋ ፍቅር ደግሞ ያው እንደምታውቀው ነው፡፡ ከራሱ አስበልጦ ሥጋን ይወዳል፡፡ ሥጋን የፈጠረ አምላክ ከፈቀደ “ጨርቆስና ሥጋ” የሚል መጽሐፍ አሳትም ይሆናል፡፡ ማን ያውቃል?

የከተማችን ሥጋ በል ሕዝብ የማያባራ የስጋ አምሮቱን ከሚወጣባቸው ሰፈሮች ውስጥ ከልደታ ቀጥሎ ዶሮ ማነቂያ ትጠቀሳለች፡፡ በጊዮርጊስ በኩል ባለው የዶሮ ማነቂያ “የባህር በር” ያለውን ትእይንት ስትመለከት አዳም የተሳሳተው በበለስ ሳይሆን በሙዳ ሥጋ ሊመስልህ ይችላል፤ የበግ፣ የበሬ እና የፍየል ስጋ እንደጉድ ይነገዳል፡፡ የሚገርመው በዶሮ ማነቂያ የዶሮ ሥጋ አለመገኘቱ ነው፡፡

ገና ወደ ዶሮ ማነቂያ ግዛት አንድ እግርህን እንዳስገባህ ነጭ ጋውን የለበሱ ሥጋ አራጆች ልክ እንደ ጆፌ አሞራ እና ጭልፊት ያንዣብቡኻል፣ ያዋክቡኻል፡፡ ቢላቸውን እያፋጩ፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልሆንክ አንተኑ አርደው የሚበሉህ ስለሚመስልህ ትፈራለህ፡፡በነጻ የሚጋብዙህ ይመስል እነርሱ ቤት እንድትገባ ያባብሉኻል፡፡ ቁራጭ ሥጋ አፍህ ውስጥ ወርውረውልህ ኪስህን ሊያራቁቱት እኮ ነው፡፡

እነ “በቀለ” እነ “ባንቡ” እነ “አዱኛ” እነ “ፋሲካ” እነ “ቤተልሄም” እነ “ታደሰ” መስኮታቸውን የሥጋ መጋረጃ አሰርተውለት እንቁልልጭ ይሉኻል፡፡ አይንህ ሥጋዎቹን በደንብ እንዲያይ ስልሳ ሻማ አምፖል በሥጋው ትይዩ ያበሩልኻል፡፡ የኃይል እጥረት በከተማችን እንዲከሰት ከሚዳርጉ ግዙፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቀጥሎ የሥጋ ቤት አምፖሎች ዋንኛዎቹ ናቸው ብዬ ብጮኽ የሚሰማኝ አጥቻለሁ፡፡

ለማንኛውም እንደ አብዛኛው የአገርህ ዜጋ ሥጋን ለአውድ ዓመት ብቻ የምታገኝ ከሆነ ወይም እንደ ጨርቆስ ልጆች ሥጋን እንደ ኦሎምፒክ በየአራት ዓመቱ የምትበላ ከሆነ በዶሮ ማነቂያ እየተመላለስክ አምሮትህን ልትወጣ ትችላለህ፡፡ “መብላት ነበር!” እያልክ ትዝታለህ፤ ሥጋውን በቅርብ ርቀት እያየህ። ልክ ቅድመ አያቶችህ ጥልያን ላይ እንደፎከሩት፤ አንተም ታቅራራለህ፤ “መብላት ነበር!” እያልክ። በዶሮ ማነቂያ!