አንድ አፍታ ወጣቶችን እናመስግናቸው
(ደጀ ሰላም፤ ጃኑዋሪ 19/2011፤ ጥር 11/2003 ዓ.ም)፦ የፀጋው ሀብት እና ጥልቀት የማይመረመር አምላክ የአባቶችን ልብ ወደ ወጣቶች መልሶ፣ “ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃም” የሚለውን ተረት ሽሮ እሳታዊ እና ነፋሳዊ ባሕርይ ያልተስማማላቸውን ወጣቶች በመንፈሳዊ ምስጢር አርግቶ ዕፁብ ዕፁብ፣ ድንቅ ድንቅ የሚያሰኝ የወጣቶች መነሣሣት ፈጥሯል። እናም ይህንን ያደረገ አምላክ ምስጋና ይገባዋል።
ነቢዩ “አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ። አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ። የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ። የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ” (36፥26) ሲል እንደተናገረው ትልቅ የልቡናና የአስተሳሰብ መለወጥ ተፈጥሯል። የዚህ ወጣት፣ “የወጣት ወጣት”፣ ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ ለቤተ ክርስቲያኒቱም፣ ለአገሪቱም ትልቅ ጥቅም አለው። “የወጣት ወጣት” ያልነው አብዛኞቹ በአሥራዎቹ መጨረሻ እና በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኙ፣ ከእነርሱ ከፍ ካሉ ከሌሎች ወጣቶች (በ20ዎቹ መጨረሻ እና በ30ዎቹ) ከሚገኙት በዕድሜ የሚያንሱ ስለሆኑ ነው።
በነዚህ ተከታታይ ዓመታት የሠሩት እና ያሳዩት ነገር ድንቅ የእግዚአብሔር አሠራር ስለሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱም መንግሥትም በጥንቃቄ ሊይዙት ይገባቸዋል። ወጣቶቹም በበኩላቸው ይህ ሁሉ የተደረገው በእግዚአብሔር ቸርነት መሆኑን አውቀው እስካሁን እንዳደረጉት በብስለት እና በመንፈሳዊ አስተዋይነት ሊመላለሱ ይገባቸዋል። ስለሁሉም ግን በብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች መካከል እንዲህ ዓይነቱን የተስፋ ብልጭታ ማየት ትልቅ ተስፋ መሆኑን በማስተወስ ባላቸው ነገር ሁሉ ለዚህ በዓል መሳካት ደፋ ቀና ያሉ የመላ ኢትዮጵያ ወጣቶችን እናሰግናቸዋለን።
ቸር ወሬ ያሰማን፣
አሜን
