በግንቦት 1997 ካጣነው በላይ ማግኛችን ደርሷል!
በያዝነው ሳምንት የግንቦት 7 1997 ዓ.ም. ምርጫን ስድስተኛ ዓመትና የንቅናቄዓችንን ሶስተኛ የምሥረታ ዓመትን ዘከርን። ከግንቦት 7 1997 ዓ.ም. ወዲህ ስድስት የቁጭት ዓመታትን አክብረናል። ከእነዚህ ውስጥ ሶስቱ ዓመታት ያለፉት ግን ካጣናቸው መልካም ነገሮች በላይ የማስመለስ እልህ በቁጭታችን ላይ ጨምረንበት ነው። ከግንቦት 7 2000 ዓ.ም. ወዲህ በ1997 ካጣነው በላይ በትግላችን እናመጣለን በሚል ተስፋ ተሞልተናል።
የዘንድሮውን ግንቦት 7 የምናስታውሰው ዓለምን ያንቀጠቀጡ የፀረ- አምባገነን ህዝባዊ እምቢተኛነት ትግሎች በሰሜን አፍሪቃና በመካከከለኛው ምሥራቅ በሚንቦገቦጉበት፤ ከሰሃራ በታች ወደአሉ የአፍሪካ ሃገሮችች ዘልቆ የዩጋንዳን በር እያንኳኳ ባለበት እና ወደ አገራችን ኢትዮጵያም እንደሚዘልቅ ምልክቶች እየታዩበት ባለበት ወቅት ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚገኝበት አሰቃቂ ሁኔታ በቅርቡ የህዝብ አመጽ ከተቀሰቀሰባቸው ሀገር ህዝቦች ሁኔታ የከፋ ነው ። ህዝባዊ መነሳሳትን በኢትዮጵያ አይቀሬ የሚያደርገው ይህ ህዝብ ግፈኛ አገዛዞችን በመቃወም ለነፃነቱና ለመብቱ ለመሰዋት ወደ ኋላ የማይል፣ ለዚህም መነሳሳት መሰረት የሚሆን የራሱ የሆነ በቂ የታሪክ ቅርስ ያለው መሆኑ ነው ።
በጭቆና የሚኖሩ ህዝቦች የግፍ በትር መፈጸሚያ ጡንቻዎቻቸውን ያፈረጠሙ መንግሥታዊ ሥርዓቶችን የማይፈሩበት ደረጃ ላይ መድረሳቸው ገሃድ ሆኗል። አፋኝ ሥርዓቶች ህዝብን ለለውጥና ለተቃውሞ እንዲነሳ ማድረግ የሚችሉ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች ማዳከማቸው የህዝብ የነፃነት ፍላጎትን እንደማይገታ ከቱኒዝያ የተነሳው ህዝባዊ ማእበል ማስረጃ ሆኗል። መሪ በሌለበት ወይም በተዳከመበት ሁኔታ ሳይቀር ህዝብ በነፃነት ጥማት ተቃጥሎ፣ በራሱ እልህና የመከራ ሸክም ተገፍቶ ያለመሪ ድርጅትም ቢሆን ህዝባዊ የለውጥ እንቀስቃሴ መቀስቀስ እንደሚችል ገሃድ ሆኗል።
ይህ እውነታ በግንቦት7 1997 የህዝብን ድምጽ ሰርቆ፤ አናሰርቅም ያሉትን ገድሎ፣ አስሮና አሳዶ ስልጣኔን ለልጆቼ አወረሳለሁ በሚል እብሪት ተንሰራፍቶ በተቀመጠው በመለስ ዜናዊ ቤት ሽብር ለቋል። የመለስ ዜናዊ ፍርሃት መቶ በመቶ በሆነ ድምጽ ተመረጥኩ ባለበት ከተማ ውስጥ “በፈቃዱ ሊደግፈኝ ወጣ” ላለው ህዝብ ጥይት በማይበሳው መስተዋት ውስጥ ተደብቆ ንግግር በማድረጉ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። የቤተ መንግስቱን ጥበቃ ከመቼውም በላይ ማጠናከሩም አይደለም። ከተማውን በወታደርና በደህንነት ሰዎቹ ማጨናነነቁ ብቻም አይደለም።
የመለስ ዜና ፍርሃት ልጓም ከማያቀው አፉ በሚፈልቀው ቅጣ ያጣ መቀባጠር እየተገለጠ ነው።
“በአምስት ዓመታት ውስጥ ሁላችሁም ዲታዎች እናደርጋለን”፤ “ኤርትራን እንወራለን”፤ “አባይን እንገነባለን” የሚሉ የማደናገሪያ ቱልቱላዎችና ድንፋታዎች አምባገነኑ እራሱ በማይቀረው ህዝባዊ አመጽ መርበትበት መጀመሩን የሚያሳዩ ናቸው። ጉልበት፣ ማጭበርበር፣ ድንፋታና ምልጃ ቤን ዓሊንና ሙባረክን እንዳላዳናቸው ሁሉ መለስም የፈለገውን እኩይና አሳዛኝ ድራማ ቢስራ ሊድን ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
የግንቦት7 1997 ምርጫ ሰጥቶት የነበረውን በክብርና በሞገስ ሥልጣን የመልቀቅ ታላቅ ታሪካዊ እድል ላይ የእብሪት ትፋቱን ተፍቶ ለዘላለም እገዛለሁ በማለት ታብዮ የነበረው መለስ ዜናዊ አይዋረዱ ውርድት ተዋርዶ ስልጣን የሚለቅበት፤ ለፈጸመው ወንጀል እና ለዘረፈው ሃብት ተጠያቂ ከሚሆንበት የታሪክ ደጃፍ ላይ ቆመን ነው የዘንድሮን ግንቦት7 የዘከርነው።
ግንቦት7 ንቅናቄ የተመሰረተበትን ሶስተኛ አመት በሚያከብርበት በዚህ የግንቦት ወር የሃገራችን ህዝብ አመጽ እያስገመገመ ነው። ንቅናቄያችን የማይቀረውን ህዝባዊ የለውጥ አመጽ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቆርጦ መነሳቱን ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ማናቸውም ድርጅቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመመስረት፣ በጋራ በመስራትና ህዝብን ለመታደግ ዝግጁ መሆኑን አሁንም እንደ ትናንንቱ የማይናወጥ አቋሙ መሆኑን ግልጽ ያደረጋል።
ከዚህ በተጨማሪ የግንቦት 7 ንቅናቄ በኢትዮጵያ ወስጥ የሚቀሰቀሰውን ህዘባዊ የነፃነት፣ የፍትህና የእኩልነት አመጽ አቅጣጫውን ለማሳትና በስልጣን ለመሰንበት የመለስ ዜናዊና የጥቂት ባልደረቦቹ ግፈኛ አገዛዝ ህዝብን በዘርና በሃይማኖት ልዩነት ለማፋጀት የሚሸርቡትን ደባ ለማክሸፍ ይሰራል። ህዝብ ከዚህ በፊት የከፈለውና ወደፊትም የሚከፍለው መስዋእትነት የሌላ አምባገነናዊና ግፈኛ ሥርዓት መቋቋሚያ እንዳይሆን ትግሉ የሚጠይቀውን ማንኛውንም ተግባር በተናጠል ይሁን ከሌሎች መሰል ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመፈጸም ዝግጁ ነው።
ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ሁሉም የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መቀሰቀሱ ከማይቀረው ህዝባዊ እምቢተኛነት ጎን እንዲቆሙ፤ በጋራም ተባብረን ህዝብን እንድንደግፍ ግንቦት 7 ንቅናቄ ጥሪ ያቀረባል። በጋራ በመቆም ከወያኔ አምባገነናዊ አገዛዝ ውጭ ሌላ የነጻነት የዲሞክራሲ አማራጭ እንዳለ ለህዝብ ሆነ ይህንን መስማት ለሚፈልጉ የህዝብ ወዳጆች እናሳውቅ እንላለን።
በስህተትም ይሁን በሌላ ምክንያት ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በህዝብ ጫንቃ ላይ ተንሰራፍቶ ከሚገኘው አጸያፊ ሥርዓት ጋር በመወገን በወገናቸው ላይ የስቃይ በትር የሚያሳርፉ አካላትና ኃይሎች በሙሉ ቀኑ ሳይጨልምባቸው ከህዝብና ከመጪው ብሩህ ዘመን ጎን እንዲሰለፉ ወገናዊ ጥሪያቸንን እናቀርባለን።
በቃ!!! ጋዬ!!! ይአከል!!! አሎኒ!!! ዲታህ!!! ወጣንደም!!! በስ!!! ጊዴስ!!!