የዴሞክራሲ ትግሉ በኢትዮጵያ: የማጥቃት ስልቶቻችን

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በአትላንታ በደደረገ ህዝባዊ ስብሰባ ያደረጉት ንግግር አፕሬል 23 2011

1. መግቢያ

ከዚህ በፊት በሂውስተን ከዚያም በኖርዌይ ባደረግኳቸው ንግግሮች ከሰሜን አፍሪቃና መካከለኛው ምሥራቅ አብዮቶች ልንማራቸው ስለሚገቡ ኣራት ነገሮች አንስቼ ነበር። በነኛ ንግግሮቼ ያነሳኋቸው ነጥቦች በአጭሩ የሚከተሉት ነበሩ።

  1. የነፃነትና የዲሞክራሲ ፍላጎት ለተወሰኑ ዘሮች፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች የተሰጡ ሳይሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ የሚፈልጓቸው እሴቶች መሆናቸውን
  2. የሰሜን አፍሪቃ አብዮቶች አፍሪቃዊያን በራሳቸው ያላቸውን መተማመን በከፍተኛ ደረጃ ያዳበሩበት ክስተት መሆኑን።
  3. ይህ ወቅት አፍሪቃዉያን የአገራቸውና የገዛ ህይወታቸው ባለቤት የሆኑበት ወቅት መሆኑን። በመጨረሻም:
  4. የአምባገነኖችን ባህርይ በሚመለከት በተለይ ከሊቢያና ከየመን የቀሰምናቸውን ትምህርቶች በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ነበር።

የሰሜን ኣፍሪካና የመካከለኛው ምስራቅ ኣብዮቶች ግን ኣብዮቶቹ ከሚካሄድባቸው ኣገራት ውጭ ባሉ ኣምባገነን ስርኣት በሰፈነባቸው ኣገራት ያሉ መንግስታት ይህ ኣብዮት እነሱ ዘንድ እንዳይመጣ ለመከላከል በሚል የሚወስዷቸው ገሚስ ኣስቂኝ ገሚስ ኣሳዛኝ እርምጃዎችም ብዙ ትምህርቶችን እየሰጡን ነው:: ሁሉም ኣምባገነኖች ማለት ይቻላል የመጀመሪያ መልሳቸው “ይህ በፍጹም እኛጋ ኣይደርስም” የሚል ነው:: “እኛ የተለየን ነን:: እኛጋ ሙስና የለም፤ መልካም ኣስተዳደር ኣለ: ህዝቡ ይወደናል… ወዘተ”:: እንደ መሪው ኣይን ኣውጣነት “በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው ስልጣናችን ላይ ያለነው: ኮንትራታችንን ሳንጨርስ የትም ኣንሄድም” የሚሉም ኣሉ:: ደጋፊዎቻችን የሚሏቸውን በገንዘብ ከሚገዟቸው ጋር ቀላቅለው የድጋፍ ሰልፍ ያስወጣሉ:: ይህ ግን ብዙ የማያዋጣ ከመሰላቸውና ትንሽ ገንዘብ ያላቸው ከሆኑ ህዝቡን ለመደለል ለኑሮ መደጎሚያ እያሉ እንደ ሳኡዲ ኣረቢያ ገንዘብ ይበትናሉ:: ገንዘቡ የሌላቸው ደግሞ በገንዘብ ፈንታ ኣስፈላጊ የሚባሉ ሸቀጦችን ነጋዴዎችን ኣስገድደው ለህዝቡ በርካሽ ዋጋ ለማቅረብ ይሞክራሉ እሱም ለረጅም ጊዜ የማያስኬድ ሲሆን የወደፊት እድገት ተስፋ ለመመገብ ይሞክራሉ:: ሁሉም በጣም የተረጋጋ ስርኣት እንዳላቸው ለሚሰማቸው ሁሉ ከመንገር ወደኋላ ኣይሉም:: የሶሪያው ኣሳድ እና ወሬ ኣቀባዮቹ (የምእራብ ኣገራት ኤክስፐርቶችን ጨምሮ) በሶርያ ስላለው ከፍተኛ መረጋጋት ኣውርተው ሳይጨርሱ በዱማ: በጃብላና እንዲሁም በደማስቆስ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጻነት ፈላጊዎች በኣደባባይ ወጥተው ኣሳፈሩዋቸው:: ሁሉም ጉልበትንና ማባበልን እያፈራረቁ ለመጠቀም ይሞክራሉ:: የማባበያ ገንዘብ ባደሉበት እጃቸው: ጅራፍ መዝዘው ህዝቡን ይገርፋሉ:: በትንንሽ ማንኪያ የሚበትኑትን የማባበያ ስኳር ኣልልስም ያለውን በገፍ ከማሰር ኣልፈው በኣጸያፊ ሰቆቃ ቅስሙን ለመስበር ይሞክራሉ:: ከዚህ ሁሉ ጋር በማጣመር ደግሞ የበሬ ወለደ ውሸታቸውን ህዝቡ ጆሮውን እስከሚያመው ድረስ ለብቻቸው ያለጠያቂ በሚቆጣጠሩት የመገናኛ ብዙሃን ይለቁበታል:: ሌላ ቢቀር መስማት ሲሰለቸው ውሸቱን እውነት ነው ብሎ ይቀበላል ከሚል ፈሊጥ በመነሳት::

ይህንን በኣምባገነኖች ጎራ ያለ ትርምስ በጥሞና የሚመረምሩ ተንታኞች ያገኙት ኣዲስ የጊዜ ማሳለፊያ “የነገው ኣመጽ ባለተራ ማን ነው?” የሚል መላምትና ትንቢት መሰንዘር ሆኖኣል:: ይህ ግን በሙያተኞች ኣካባቢ ብቻ ሳይሆን በየኣገሩ የሚኖር የነጻነት ጥማተኛም ጊዜ ማሳለፊያ ከሆነ ሰንብቶኣል:: ለዚህ ይመስለኛል የሊቢያ፤ ሶርያና፤ የመን ወሬ ከማንቼስተርና ከኣርሴናል ግጥሚያ በላቀ የነኝህን ኣገሮች ወጣቶች: ብሎም ጎልማሶች ቀልብ የሳበው:: መቼም እንዲህ ኣይነት የትንቢት ስራ ለባለሙያዎችም እንዴት ከባድ እንደሆነ ይታወቃል:: ስለዚህም ከውጤቱ ይልቅ ወደትንቢቱ ለመሄድ የሚቀርበው ትንተና የበለጠ ትኩረት ይሰጠዋል:: ትንተናዎቹ ደግሞ በሁለት ሰፋፊ ጉዳዮች ዙሪያ ያጠነጥናሉ::

እነኝህም:

  1. ለውጥ ለመፍጠር ኣስፈላጊ የሆኑ ነባራዊ ጥልቅ መዋቅራዊ ምክንያቶች (deep objective structural factors) መኖር ኣለመኖር ላይ ያተኮሩ ጉዳዮች ናቸው:: እነኝህ ዋና ዋና ምክንያቶች የታወቁ ናቸው:: ቅጥ ያጣ ድህነት፤ መያዢያ የጠፋው የዋጋ ግሽበት፤ ብልሹ ኣስተዳደር፤ ሙስና፤ የፍትህ እጦትና ባጠቃላይ ኢዴሞክራሲያዊ ኣስተዳደር ናቸው:: በነኝህ መስፈርቶች ከተጠቀምን በኣፍሪካ ብቻ ለለውጥ የተዘጋጁ በጣም ብዙ ኣገሮች ኣሉ:: ከሰሀራ በታች ካሉት 48 ኣገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ 39ኙ ህዝቡ በቂ ነጻነት የማያገኝበት ወይም በፍጹም ነጻነት የሌለበት የድህነት ድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ነው የሚኖረው:: ሌሎች ኣካባቢዎችን ስሌት ውስጥ ካስገባን ለለውጥ የተዘጋጁ ኣገሮችን ቁጥር የትየለሌ ያደርገዋል:: ስለዚህ በዚህ ምክንያት ላይ ከተመረኮዝን መጪውን ለውጥ በተመለከተ ያሉትን ተረኞች ኣንድ ሁለት ብሎ ለመተንበይ ያስቸግራል::
  2. እነኝህ ጥልቅ መዋቅራዊ ምክንያቶች መኖራቸው ብቻውን ግን ለውጥ ወዲያውኑ ያስነሳል ማለት ኣይደለም:: በኣንድ ወቅት በገዢዎች ውስጥም ሆነ በተገዢዎች ውስጥ የሚገኘው የስነልቦ ሁኔታና ከዚህም ጋር በተያያዘ የሚወስዷቸው የተለያዩ እርምጃዎች በዚያ ተጨባጭ ሁኔታ ለውጥ በምን ፍጥነት ሊመጣ ይችላል የሚለውን ይወስናል:: በተለይ ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ሀይሎች “በመዳረሻው ቦታ” (end game) ላይ የተስማማና ወጥ ኣመለካከት መኖር ለውጡን በቶሎ በማምጣት ላይ ኣስፈላጊነቱ ኣጠያያቂ ኣይደለም:: ስለዚህም ማን ይከተላል የሚለውን ለመተንበይ ሁለተኛው ምክንያት ላይ የበለጠ ማተኮር ይበጃል::

ይህ ግን ቀላል ስራ ኣይደለም:: ኣምባገነን ስርኣቶች ሲወድቁ እንደ ቅል ባዶ መሆናቸው የሚጋለጠውን ያክል በስልጣን ላይ ሳሉ ማህበረሰቡን ፍርሀት መቀመቅ ውስጥ ከትተው ስለሚያኖሩት ህብረተሰቡ በዚያ ስርኣት ላይ ያለውን ስሜት ለማወቅ ኣይቻልም:: እንኳን ያንን ሰርኣት ለመጣል ይነሳ ኣይነሳ ለመተንበይ:: ለምሳሌ የሶቭየት ህብረት ለመፈራረስ ስድስት ወራት ሲቀረው ኣንድ ምዕራባዊ የህዝብ ኣስተያየት ሰብሳቢ ድርጅት ሩሲያ ድረስ ሄዶ ባደረገው ጥናት ከህብረተሰቡ 88% የሚሆነው የኮሙኒስት ፓርቲውንና የኮሙኒስት ስርኣቱን በጽኑ እንደሚደግፍ ነበር ያስታወቀው:: ከላይ እንደጠቀስኩትም ሁሉም ስርኣቶች ምን ኣረመኔ ቢሆኑ ህሊናቸውን ለሆዳቸው የሸጡ (በተለይም ያንን ስርኣት በመጠቀም ንብረት የሰበሰቡ ወይንም ለመሰብሰብ የሚያልሙ) ደካማ ደጋፊዎች ኣያጡም:: እነኝህን ጥቂት ደጋፊዎች ባላቸው የመገናኛ ብዙሀን በመጠቀም ብዙ ለማስመሰል ስለሚሞክሩም የዋሁን ተመልካች ሊያሳስቱ ይችላሉ:: በቅርቡ በሶሪያ ላይ እንደተሳሳቱት ብዙ ባለሙያዎች ማለት ነው:: በመያዚያ 29 1997 የመለስ ሰልፍ እንዳየነው እንደ ኢትዮጵያ ባለ ድሀ ኣገር በ30 ብር ክፍያም ብዙ ሰው ማሰለፍ ይቻላል በነጋታው የምር ስሜቱን ለማሳየት የተቃዋሚውን ሰልፍ በነጻ ቢቀላቀሉም:: ስለዚህ ተመልካቾች በኣንድ ኣብዮታዊ ወቅት በኣምባገነን መንግስቶች እንቅስቃሴዎች ኣካባቢና ለነኝህም እንቅስቃሴዎች በህዝቡ ዘንድ የሚንጸባረቁ ስሜቶችንና መልሶችን በኣትኩሮት በመመልከት ሁኔታው ለለውጥ የበሰለ መሆን ኣለመሆኑ ላይ “ትንተናዊ” ግምት ይሰጣሉ:: በተለይም በመንግሥት ኣካባቢ የሚታዩ የተለዩ መቅበጥበጦች: በህዝቡ ወገን ደግሞ ከወትሮው የተለየ የመዳፈር ስሜቶች ወይንም የመተባበር ምልክቶች ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እየሄዱ መሆናቸውን የሚያመለክቱ ክስተቶች ተደርገው ይወሰዳሉ:: እኔም ከዚህ በታች ለውይይት መተንኮሻ እንዲሆን የሰሜን ኣፍሪካው ኣብዮት ከተጀመረ ጀምሮ የመለስ ኣገዛዝ የሚወስዳቸውን የተለያዩ እርምጃዎችና ማህበረሰቡም ለነኝህ እርምጃዎች የሚሰጠውን ምላሽ በመመርኮዝ የሚቀጥለው የለውጥ ተረኛ መለስ ሊሆን ይችል ይሆን ወይ? በሚለው ጥያቄ ላይ ያለኝን ትንተናዊ ግምት እሰጣለሁ:: ከዚያም ይህ ለውጥ ከተጀመረ ስኬታማ እንዲሆን በጣም ኣስፈላጊ የሆነውን የመዳረሻ ስምምነት በሚመለከት ኣንዳንድ ኣስተያየቶችን ሰንዝሬ ኣጠቃልላለሁ::

2. የሰሞኑ የነመለስ እንቅስቃሴዎች ያሳዩዋቸው ምልክቶች

መቼም ማንም የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተል ሰው ልብ እንደሚለው መለስና ቡድኑ ካለፉት ሁለት ወራት ግድም ጀምሮ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከወትሮው ለየት ያለና ጭንቀት የወለደው እንደሚመስል መካድ ኣይቻልም:: ለወትሮው ነገሮችን በብልጠት ማለፍ የሚችለው ኣውራቸው በየሳምንቱ የተገለባበጠ መልስ ሲሰጥ: ከሳምንት በፊት ያለውን ፍጹም የረሳ ብቻ ሳይሆን ክፉኛ የተጨነቀ ኣእምሮ የወለደው መደናበርና ድንፋታ መሆኑን ሊስተው ኣይችልም:: ኣተኩረን መመልከት ያለብን እርሱ የተናገረውን ብቻ ሳይሆን እሱን ተከትሎ ትንንሾቹ ካድሬዎች በሹክሹክታ ለወሬ ኣናፋሾቹ የሚነግሩትንና በህዝቡ ዘንድ እንዲስፋፋ የሚያደርጉትን ወሬም ጭምር ነው::

በመጀመሪያ ሁላችንም የሰማነው ሁሉም ኣምባገነኖች እንደ በቀቀን የሚደጋግሙትን “ይህ ችግር እኛጋ ኣይደርስም” የሚለውን፤ እውነትን ላለማየት ኣውቆ የታወረ ሰው የሚሰጠውን መልስ (ፈረንጆች denial የሚሉት) ነበር:: መለስ ኣይኑን በጨው ኣጥቦ እኛ ዴሞክራሲያዊ ስርኣት ነው ያለን: ህዝብ የሰጠንን ኮንትራት ሳንጨርስ የትም ኣንሄድም የሚል የራሱን ሰዎች ለማረጋጋት የተሰጠ መልስ ነበር:: ይህ ግን ከሀሰትነቱ በተጨማሪ በተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ያስፈልጋሉ ከሚባሉት መስፈርቶች ኣኳያ ሲታይ ውሀ የሚቋጥር መልስ ኣልሆነም:: ስለዚህ በመጀመሪያ የተመረጠው ስለዚህ ነገር ጭራሹኑ ኣለማውራት ነበር:: የሊቢያው ኣብዮት እስከሚጀመር ድረስ በረከት የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙሀን ምንም ነገር ኣያወሩም ነበር:: ከውጭ የሚተላለፉ የሚዲያ ተቋማትም (የኣሜሪካ ድምጽ: የጀርመን ድምጽ: ኢሳት: ኣልጀዚራ ወዘተ) ከዚህ በፊት ከነበረውም በላይ ኣገር ውስጥ እንዳይሰሙ በሞገድ ተመቱ:: ጋዳፊ ህዝቡን በኣውሮፕላን መደብደብ ሲጀምር ራሳቸው ወሬውን በሰፊው ማናፈስ ጀመሩ:: መልእክቱ እኛም እንደዚህ ነው የምናደርገው ብለው ሽብር ለመንዛት ነበር:: ጋዳፊ በተራው በምእራባውያን በኣውሮፕላን መደብደብ ሲጀምርና መውደቁ ኣይቀሬ መሆኑ ሲታይ: ህዝቡም ቀልቡን በሙሉ እዚሁ የነጻነት እንቅስቃሴ ላይ ማድረጉን ሲረዱ እሱንም ትተው የማህበረሰቡን ትኩረት በፍጹም የሚያስቀይሱበት መንገድ ማሰላሰል ውስጥ ገቡ::

ይህ ኣቅጣጫ የማስቀየር ኣካሄድ መቼም ተክነንበታል ብለው የሚያምኑበት ስልታቸው ነው:: እንደምታስታውሱት እነሱ ብር በማተም የፈጠሩት የዋጋ ግሽበት ማህበረሰቡን ኣስመርሮ ኣመጽ ውስጥ ሊከተው ነው ብለው ሲፈሩ ያላግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን እናስራለን ብለው በ 17 እቃዎች ላይ የዋጋ ገደብ ኣስቀመጡ:: ለሁለት ሳምንታት የህዝቡን ቀልብ ለመሳብ ቢችሉም እቃዎቹ ባጠቃላይ ከገበያ ሲጠፉ የነበረው ችግር ተባብሶ መቀጠሉ ይታወቃል:: ለነመለስ ግን ቀድሞውንም ችግሩን ለመፍታት ሳይሆን ኣቅጣጫ ማስቀየስ ስለሆነ ኣላማቸው ይህንንም እንደ ጊዜያዊ ድል ሳይቆጥሩት ኣልቀረም:: ጊዜያዊ ከጭንቅ መውጫ መፍትሄዎች ችግራቸው ግን መሰረታዊ ችግሮቹን ኣለመፍታታቸው ብቻ ሳይሆን ኣንዳንዴ ችግሩን ለማባባስ መቻላቸው ነው:: ችግሮቹን ከመሰረታቸው ለመፍታት የማይችሉ ስርኣቶች ግን ሌላ ምንም ኣማራጭ የላቸውም:: እስከመውደቂያቸው ድረስ ለኣንድ ቀንም ቢሆን ከስልጣን ያቆየናል ያሉትን ጊዜያዊ ማስቀየሻ እየፈጠሩ: ቀናቸውን ይቆጥራሉ::

ደንበኛው የማስቀየሻ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከዚህ በኋላ ነበር:: የትኛው የህዝቡን ቀልብ እንደሚይዝ ለመፈተን በተለመደው “የውጭ ሀይሎች መጡብህ” ማስፈራሪያ የተጀመረው በግብጽ ላይ ነበር:: መለስ ከመሬት ተነስቶ ለውጭ መገናኛ ብዙሀን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “ግብጽ መንግስቴን ለማናጋት ተቃዋሚዎችን ትረዳለች” ኣለ:: እነማንን? ቢባል መልስ የለም:: ለምን ይህን ታደርጋለች ለሚለው መልሱ ግልጽ ኣይደለም ምክንያቱም ከዚያ በፊት ብዙም ሳይቆይ ግብጽና ኢትዮጵያ ስላላቸው ወዳጅነትና ግብጾች በኢትዮጵያ ኢንቬስት ስለማድረጋቸው ነበር የሚነገረን:: መለስም በሚገርም ሁኔታ በዚሁ ቃለምልልስ “ግብጽ ኢትዮጵያን ብትወር ለወሬ ነጋሪም ሰው ኣይተርፋትም” ብሎ ደነፋ:: የኣገሬውን ህዝብ ኣቅጣጫ ለማስቀየር መሆኑ ያልገባቸው የውጭጋዜጠኞች “ሰውየውን ምን ነካው? ጦርነትን ምን ኣመጣው?” ብለው የሰውየውን ጤንነት መጠራጠር ጀመሩ::

የግብጽ መጣብህ ወሬ በሙከራ ላይ እያለ መለስ ሌላ ጭቃ ወረወረ: የህዝቡን ሰሜት ለመለካት:: በዚህኛው ደግሞ ዋናው ተዋናይ የተለመደችው ኤርትራ ሆና ኣሁን ግን መልእክቱ “የኛ ትእግስት ስላለቀ እኛ በጉልበት የኤርትራን መንግስት እንቀይራለን” የሚል ሆነ:: ምነው? ሲባል “ተቃዋሚዎቼን ይረዳሉ” ኣለ:: እንዴ ታዲያ ይሄ ጦርነት ለመግጠም በቂ ምክንያት እንዴት ይሆናል? ኣንተስ የሱን ተቃዋሚዎች በግላጭ ትረዳ የለም ወይ? ለሚለው ጥያቄ ምንም ኣጥጋቢ መልስ የለም:: ውስጥ ለውስጥ ግን በካድሬዎቹ ኣማካይነት “ኣሁን ጉዳያችንን ጨርሰን ነው የምንመለሰው፤ ኣሰብንም እናስመልሳለን” የሚል ወሬ በሰፊው ማስነገር ጀመረ:: በጎን ደግሞ በተቃዋሚዎች ሬድዮ ላይ ለኤርትራውያን በትግርኛ ባስተላለፈው መልእክት እሱ የኤርትራ ነጻነት ዋና ደጋፊ እንደሆነ፤ በዚህም እንደሚኮራ:: ኣይደለም ኣሰብን ማስመለስ የሱ መንግስት በኣለም ኣቀፉ ውሳኔ መሰረት ባድመንም ሆነ በኢሮብ የሚገኘውን መሬት ለኤርትራ እንደሚመልስ የሚገልጽ ቃለምልልስ ሰጠ:: ትግርኛ ለማይሰማው የኣገሩ ህዝብ ግን ኤርትራን ለመውጋትም ሆነ ኣሰብን ለማስመለስ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የወታደር ምልመላ እንቅስቃሴ ተጀመረ ተባለ:: ነገሩን ግን ያለም ኣቀፉ ማህበረሰብም ሆነ ያገሩ ሰው እንዳልተዋጠለት ሲረዳ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ “ኣይ ይህ ማለት እንወራለን ማለት ኣይደለም፤ ይልቁንም በትንሹ ስንረዳቸው የነበሩትን የኤርትራ ተቃዋሚዎች ኣሁን በሰፊው እንረዳለን ለማለት ነው” ሲል ቀላመደ:: ይህ ለምን ወሬ ሊሆን እንደሚችል ግን ግልጽ ኣይደለም::

እነኝህ ሁለት ማስቀየሺያዎችም ቢሆኑ በቂ ቀልብ ኣልሳቡም:: ከኣንድ ከሁለት የዜና ሳይክል ያለፈ የህዝቡን ቀልብ ቆንጠጠው ለረጂም ጊዜ ሊይዙት ኣልቻሉም:: በዚህን ጊዜ ነው ኣለኝ የሚለውን የመጨረሻ ካርድ የመዘዘው:: በኢትዮጵያውያን ስሜትና ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውን: ብዙ ዘፈኖች የተዘፈኑለትን: የኣባይን ወንዝ መገደብ ጉዳይ ከኪሱ ኣውጥቶ የፖለቲካ ጨዋታው ውስጥ የወረወረው:: የነመለስን ኣይንኣውጣነት በቅጡ ያልተገነዘቡ ወገኖች ይህንን የመሰለ ከፍተኛ የኣገር ጉዳይ ኣንድን ኣገር እንመራለን በሚሉ ሰዎች እንዲያው በደንብ ሳይታሰብበት ለጊዜያዊ የፖለቲካ ቁማር መጠቀሚያ ያውሉታል ብሎ ለማመን ሲቸገር ይታየኛል:: በዚህም ምክንያት የተወሰኑ ሰዎችን (በተለይም ኣውቀው መታለል ለሚፈልጉና እንደ ኤርትራው ጦርነት ጊዜ ኣጋጣሚውን ከመንግስትጋ ለመጠጊያ ሊጠቀሙበት ለሚፈልጉ) ሲያነሆልል ይታየኛል:: ነገር ግን መለስ ባለፉት 20 ኣመታት በኢትዮጵያ መሰረታዊ ሀገራዊ ጥቅሞች ላይ ሲቆምር በጥሞና ለተከታተለ፤ ይህ በፍጹም ሊገርመው ኣይገባም:: ቢገርመው የሚገርመው ኣሁንም በዚህ የሚታለሉ ሰዎች ኣሉ ብሎ መገመቱ ብቻ ነው የሚሆነው:: በዚህ ደረጃ ምን ያህል ኣይነደረቅ እንደሆኑ ለማሳየት ኣንድ በሰፊው የሚታወቅ ምሳሌ ጠቅሼ ልለፍ::

የኢትዮጵያና የኤርትራ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔውን እንዳሳለፈና ማንበብ ለፈለገ ሁሉ በኢንተርኔት ካሰራጨ በሁዋላ በጊዜው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ስዩም መስፍን የኢትዮጵያን ህዝብ “እንኳን ደስ ኣለን፤ የጠየቅነውን ብቻ ሳይሆን ያልጠየቅነውን መሬት: ባድመን ጨምሮ ለኛ ተወሰነልን”: የሚል መግለጫ በመገናኛ ብዙሀን ሰጠ:: በጊዜው በኣገር ውስጥ የሚታተሙ የግል ጋዜጦች: የለም ይህ ውሳኔ እንደዚያ ኣይልም: ባድመ ለኤርትራ ነው የተወሰነው ብለው ውሳኔውን ተርጉመው ቢያቀርቡም የመለስ መንግስት “የሌባ ኣይነደረቅ” እንዲሉ ያልሆነውን ሆነ ብሎ ባደባባይ ከመናገር ኣልፎ ይባስ ብሎ ህዝቡን ደስታህን ኣደባባይ ወጥተህ ግለጽ ብለው የድጋፍ ሰልፍ ኣስወጡ:: ይህ ኣሳዛኝ ድርጊት ከተፈጸመ ከኣምስት ኣመት በኋላ በምርጫ 97 ወቅት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲን በሚመለከት ለክርክር በቀረብንበት ጊዜ ይህንን ጉዳይ ለስዩም ኣነሳሁበት:: በቀጥታ ለህዝብ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ሰርጭት ላይ እንደገና ባድመ በፍርድ ቤቱ የተወሰነው ለኛ ነው ብሎ ሽምጥጥ ኣድርጎ ዋሸ:: መለስ በበኩሉ ላገኘው የውጭ ባለስልጣን በሙሉ (ባለፈው ሁለት ሳምንት ለኤርትራውያን በትግርኛ ሬድዮ እንደተናገረው) “እኔ ባድመ ለኤርትራ እንዲመለስ እፈልጋለሁ የትግራይ ብሄረተኞች ኣስቸግረውኝ እንጂ” እያለ በሌላ በኩል እንደሚናገር ይታወቃል::

እንደ ኢትዮጵያ ኣቆጣጠር በ1993 ዓ:ም መለስ ዜናዊ ካይሮ ድረስ ሄዶ ከሙባረክ ጋር “ኢትዮጵያም ሆነች ግብጽ የኣባይን ወንዝ የውሀ ፍሰት የሚቀንስ ምንም እርምጃ ኣይወስዱም” የሚል ስምምነት ተፈራረመ:: ኧረ ይህ ስምምነት በጎ ኣይደለም የሚልን ኣገር ወዳድ ሁሉ ጦር ሰባቂ፤ ትምክህተኛ ተብሎ ሲዘለፍ ነበር:: ታዲያ ዛሬ የኣባይ ወንዝ ግድብ ጉዳይ እንደ ትልቅ ኣገራዊ ኣጀንዳ በዚሁ ምንም ባልተቀየረ ሰው መነሳቱ ምንም እውነተኛ የልማት ኣላማ የሌለው ተራ ኣቅጣጫ ማስቀየሻ: ሲያልፍም ከህዝቡ ገንዘብ መዝረፊያ ተራ የውንብድና ስራ መሆኑን ለማሳየት በጣም ትልቅ ምርምር ኣይጠይቅም:: በመጀመሪያ መለስ ራሱ ጠበቅ ኣድርጎ ሲጠየቅ “ምንም ባይሳካም እንኩዋን መሞከሩ ጥሩ ነው” ነበር ያለው:: መቼም ሰማንያ ቢልዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት ኣይደለም ሰማንያ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ፕሮጀክት እንኳን በኣዋቂዎች ኣስር ጊዜ ኣዋጭነቱ ከተለያየ ኣቅጣጫ ተመርምሮና ተረጋግጦ ነው ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚኬደው:: ሁለተኛ የመለስ ኣገዛዝ ኣገሪቱን ወደ መካከለኛ ገቢ ደረጃ በኣምስት ኣመት ጊዜ ውስጥ ያሸጋግርልኛል ብሎ: በብዙ ባለሙያዎች የተጠና ያለውንና ግን በምን ገንዘብ እንደሚሰራው ምንም የማይገልጸውን “የኣምስት ኣመቱን የትራንስፎርሜሽን እቅድ” ካወጀ ገና 6 ወራት ቢሆኑት ነው:: በዚህ ኣስደናቂ እቅድ ላይ ኣባይ የሚባል ግድብ ኣይደለም ስሙም የለም:: ኣባይ ለመለስ የተገለጸለት ከእቅዱ በኋላ ነው ማለት ነው? ከዚያ በፊት ኣባይ የት ሄዶ ነበር? እሺ ዘግይቶ እንኳን ቢገለጽለት: ምነው ትንሽ ዘርዘር ያለ ጥናት ቢጤ በመጀመሪያ ኣያስጠናም ህዝቡን ገንዘብ ኣዋጡ ከማለትና በጣም ብዙ ገንዘብ ኣውጥቶ ከ50 በላይ ከፍተኛ ካድሬዎቹን ለሽያጭ ስራ ከመላኩ በፊት? እነኝህን ሰዎች የላከበት ገንዘብ እኮ መነሻ ጥናት ለማስጠኛ የማያንስ ወጪ ነው! ሶስተኛ መለስ እኮ በመንግስቱ ጊዜ የተሰሩ ግድቦችን ተግባራዊ እንዳይሆኑ ሆን ብሎ እንቅፋት ሲሆን የነበረ ሰው ነው:: በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ (በዛሬ ብር ወደ 3 1/2 ቢሊዮን ያክል) ወጥቶበት በጣልያኖች የተሰራውንና የኣገሪቱን የእርሻ ምርት ከ10% በላይ ይጨምራል የተባለ ግድብ መና ኣስቀርቶ: ጣሊያኖች እኛ በገንዘባችን ስራ እናስጀምረው ብለው ሲለምኑት እምቢ ብሎ በስፍራው የተሰሩትን የመሰረተ ልማት ኣውታሮች ነቃቅሎ ያስፈረሰ “የልማት ጀግና” ነው! በጋምቤላ ክልል የተሰራውን የኣልዌሮን ግድብ በተመሳሳይ መልኩ እንዳይሰራበት ያደረገ ሰው እኮ ነው:: መለስ እኮ ስልጣን ላይ ሲወጣ በኣባይ ላይ የሚሰሩ የኣገሪቱን ባለሙያዎች ሁሉ ኣባሩልኝ ብሎ ከስራ ኣባሮ ለስደት የዳረገ መሰሪ ሰው ነው:: ዛሬ ስለ ኣባይ: ያውም ያለምንም ጥናት: ልገድብ ነው ሲል የሚታመነው በምን ሂሳብ ነው? ምን ያህል ጅል ብንመስለው ነው? ወይንስ እኔ እንደምገምተው ጭንቀት የወለደው ትርምስ?

እስኪ ለኣንድ ደቂቃ መለስን እስከ ዛሬ በሰራው ሳይሆን ከኣሁን በኋላ እሰራለሁ በሚለው እንመዝነው እንበል: ያ ከታማኝ ጋር ቪኦኤ ላይ የተከራከረው ካድሬ እንዳለው:: መለስ እስከዛሬ ሲያደርግ የነበረውን ጥፋት ኣምኖና ተጸጽቶ ከኣሁን በሁዋላ ልማት ለማምጣት ወስኖኣል:: መለስ የተቀየረ ሰው ነው እንበል:: ይህም ከሆነ እሰዬው ነው:: ግን የተቀየረ ከሆነና እውነትም ለኣገሪቱ ልማትን ከተመኘ ብዙ ወጪ ሳያስወጣ ልማት የሚያመጡ ብዙ ነገሮችን በቀላሉ ማድረግ ይችላል:: በኢኮኖሚክስ ትምህርት ትልቅ ስምምነት የተደረሰበት ኣንድ ግኝት ልማት የሚመጣው በነጻነት ማሰብ የሚችል ህዝብ ባለበት: መልካም ኣስተዳደር በሰፈነባቸው: ኣገሮች መሆኑን ነው:: መልካም ኣስተዳደር ማለት ደግሞ ከሙስና የጸዳ: የማህበርሰቡ ተጠያቂነት ያለበት: ነጻ ሚዲያ ያለበት: የህግ የበላይነት የሰፈነበት ኣገር ማለት ነው:: መለስ ለኢትዮጵያ ካሰበ እነኝህን ነገሮች ሳንቲም ሳያወጣ በኣንድ ፊርማ ማድረግ ይችላል:: ግን ይህን መቼም ኣያደርግም:: ይልቁንም ስለኣባይ በሚሰብክበት በኣሁኑ ጊዜ በኣገር ውስጥ እያደረገ ያለው ነገር ከዚህ ፍጹም ተቃራኒውን ነው::

ከፍተኛ ካድሬዎቹን ውጭ ኣገር ለስብሰባ በላከበት ከሁለት ሳምንታት በፊት የቀበሌ ወጣቶችና ሴቶች ማህበራት ኣባላቱን ሰብስቦ ከኣሁን በኋላ ሁሉም ሰው እንግዳ ቤቱ ካሳደረ ለቀበሌ ማስመዝገብ እንዳለበት መመሪያ ሰጠ:: ደርግ እንኳን ሞክሮ ያልተሳካለት ኣፈና:: ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ያውም በህዝብ ተመርጠው የነበሩ እንደራሴዎችን ያለምንም ጠያቂ ዘብጥያ ወርደዋል:: በሚዛን ቴፒ ተማሪዎች ላይ የተወሰደው ጨካኝ የግድያ እርምጃ: በዚህ ሁለት ሳምንት ውስጥ ነው የተካሄደው:: ባለፈው ሳምንት ከተለያዩ የኣገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በሌሊት እየታፈኑ የተወሰዱትና የት እንደደረሱ ያልታወቁ የኦሮሞ ተማሪዎች “ከኣባይ ልማት ጋር በጋራ የሚደረጉ” የልማቱ ኣስፈላጊ ግብኣቶች ነው የሚመስሉት:: መብት ከልማት በሁዋላ የሚለው ጊዜ ያለፈበት ፈሊጥ በዛሬው ኣለም እንደማያዋጣ ያለመረዳት ኣስከፊ የመሸበት ስህተት ነው:: ከዚህ ሁሉ ደግሞ በከፋ መልኩ የሚታየው ማህበረሰቡን ለመከፋፈል የሚከተለው ዘይቤ ነው:: ኦሮሞዎችን ለብቻቸው ጠርቶ “ኣዲስ ኣበባን ፊንፊኔ ብለን እንሰይማታለን ከሌላው ጋር ኣትተባበሩ” ሲል፤ ሌላውን ደግሞ “ኦሮሞዎች ኣገሪቱን ሊገነጥሉ ነው ኣትተባበሩዋቸው” እያሉ በካድሬዎች ማስወራት:: ፖሊስ ዝም ብሎ እያየ በክርስቲያንና በሙስሊሙ መሀል በቅርቡ በጅማ ዞን እንደሆነው ግጭት ሲፈጠር ኣውቆ ኣለመከላከል:: ይህንን ነው እንግዲህ “የኣባይ ልማት የመጀመሪያ ክፍያ” (down payment) ኣድርገን እንድንቀበለው የሚነግረን:: ስለዚህ የኣባይ ግድብ ወሬ ልማትን ኣስቦ የተነሳ ወሬ ኣይደለም::

ልማትን ኣስቦ የተነሳ ወሬ ካልሆነ እንግዲያው ምን ሊሆን ይችላል? ከላይ እንዳልኩት የማህበረሰቡን ቀልብ ከለውጥ ፍላጎት ለማስቀየሺያ የታሰበ ነው:: የኣባይ ጠንካራ ስሜታዊ ስበት (imotional appeal) በሁለት መክንያቶች የማስቀየሻ ኣላማውን ያሳካልኛል ብሎ ያመነ ይመስላል:: ኣንደኛ በኣገር ውስጥ ማህበረሰቡን እያስመረረ ያለው የኑሮ ውድነት (በዚህ ወር ብቻ በመንግስት በራሱ ኣሀዝ የዋጋ ግሽበት 25% ገብቶኣል) በኣካባቢ ኣገሮች ከታየው “የለውጥ ይቻላል” ልበ ሙሉነት ጋር ተባብሮ ስልጣኑን ክፉኛ ሊፈታተነው እንደሚችልና ነገሩም ከተጀመረ እንደቀደሙት ጊዜያት በጉልበት ብቻ ሊወጣው እንደማይችል በመረዳት ሳይጀምር በእነጭጩ ለማስቀረት:: ሁለተኛ በኣገር ውስጥ የሚካሄደው እንቅስቃሴ በውጭ ባለው ኢትዮጵያዊ መታገዙ ለስኬቱ ወሳኝ ነው ብሎ ስለሚያምን በውጭ ያለውን ኢትዮጵያዊ ለመከፋፈያ: በተለይም የኣገር ፍቅር ያማለለውን የዋህ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ሊታገለው ቆርጦ ከተነሳው “ኣክራሪ ዳያስፖራ” ለመለየት በዚህም በኣገር ውስጡ ወጣት ይነሳል ብሎ የሚጠብቀውን የለውጥ እንቅስቃሴ ነጥሎ ለመምታት የታለመ ይመስላል::

3. በህዝቡ ውስጥ የሚታየው ስሜት

በኢትዮጵያ ለውጥ የመነሳቱን ሁኔታ ከሚወስኑት ጉዳዮች ኣንዱ ማህበረሰቡ ለዚህ ማስቀየሻ የሚሰጠው ምላሽ ነው:: ይህንንም በሚመለከት ከሰሜን ኣፍሪካው ኣብዮት ጀምሮ መለስ ለሚወስዳቸው እርምጃዎች በኣገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ የሰጠው ምላሽ የነመለስ ፕላን እንዳልሰራና እንደማይሰራ ነው የሚያሳየው:: ኣገር ውስጥ ባለው ህዝብ ብንጀምር: ከኤርትራ ጋር ስለሚደረገው ጦርነትና ኣሰብን ስለማስመለስ የሚወራውን ወሬ በኣርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቅርብ የተበተነው ወረቀት እንዳለው “እስኪ በመጀመሪያ በባድመ፤ በሶማልያና በሌሎቹም የመለስ ጦርነቶች የሞቱትን ወገኖቻችንን ብዛትና ስማቸውን ለህዝቡም ሆነ ለቤተሰባቸው ንገርና፤ ከዚያም በነሱ መሞት ቤተሰቦቻቸው እርማቸውን ያውጡና: በነኝህ ጦርነቶች ኣገራችን ያገኘችውን ጥቅም ንገረንና ከዚያ በኋላ ስለመጪው ግጭት ጠቃሚነት እናወራለን” ነው:: ስለ ኣባይ ግድብ የተሰጠው መልስ (በኢትዮጵያ እያደገ ከመጣው የውስጥ ለውስጥ ሚዲያ (underground press) በተረብ መልክ የተነገረው “መጀመሪያ የገደብከውን ልሳናችንን፤ የገደብከው ሆዳችንን ፍታና ስለሌላ ግድብ እናወራለን፤ በሰማይ ላይ ስላለው ላም ከምታወራልን በኣይናችን የምናየው፤ በእጃችን የምንጨብጠውና በቀላሉ ልንደርስበት የምንችለውን ለውጥ ስጠን” ነው ያሉት:: የኣውራምባ ታይምሱ እውቅ ሀያሲ ኣቤ ቶክቻው የኣባዩን ግድብ ኣስመልክቶ የህዝቡን ስሜት በሁለት ጉዋደኛሞች ጭውውት ኣስመስሎ ሲገልጽ ኣንደኛው “ለኣባይ ግድብ ያሰብኩትን ብር በሙሉ ጠራርጎ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ሙልጭ ኣድርጎ ባዶዬን ኣስቀረኝ: ምናባቴ ይሻለኛል?…ለዚህ የነዳጅ ጭማሪ ጸረ_ኢትዮጵያ ሀይሎች በተለይም የሻእቢያ ነጭ ለባሾችን መጠርጠር የለብንም ትላላችሁ?” ሲለው ሌላኛው “ሀይል ለማያመነጩት ግድቦች የሚያወጡትን ገንዘብ ለሀይል ማመንጫው ቢያውሉት፤ እንኳን ኣባይንና ኣጠቃላይ ድህነታችንን መገደብ በተቻላቸው ነበር…ሀይል የማያወጡት ግድቦች ለመሆኑ እነማን ናቸው ስለው: ፈጠን ብሎ “እነ ኣሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ: እነ ጀርመን ሬዲዮ: እነ ኢሳት ቴሌቪዥን ኣለኝ: እሱን ወደ ግድቡ ያዙሩት: እኛ ችግር ጠብሰን ይበቃናል:: በመዋጮ ደግሞ መጠበስ የለብንም ኣለኝ::” ብሎ ነበር ባለፈው ሳምንት ኣምዱ የከተበው:: የቅዱስ ገብረኤል ኣንደኛና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ለኣባይ ግድብ ገንዘብ ኣዋጡ ከምትሉን መጀመሪያ በህይወት ኣኑሩን ብለው ነው ገንዘብ ለመሰብሰብ የመጡ ካድሬዎችን ያባረሯቸው:: ስለ መለስ/ኢህኣዴግ “ሳይንሳዊና ልማታዊ” ኣመራር ሳይሆን የኣገሪቱ ወጣት “መለስ በቃ” እያለ ነው በየግድግዳው የሚጽፈው:: ከሰሞኑ ከኦሮሞ ወጣቶች: ከሚዛን ቴፒ: ሀዋሳ: ኣዲስ ኣበባ ዩኒቨርሲቲና ሌሎችም ቦታዎች የሚበተኑ ወረቀቶችም ሆኑ በፌስ ቡክና በቴክስት የሚራቡ መልእክቶች የሚጠቁሙት መቼ እንቅስቃሴው ይጀመራል የሚለውን እንጂ ኢህኣዴግ በኣስቂኝ መግለጫው (በኣይጋ ላይ ተመልከቱት) እንዳለው ስለ ድንቁ የመለስ/ኢህኣዴግ ሳይንሳዊ ኣመራር ኣይደለም::

የነመለስ የማስቀየሻ እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ባፍጢሙ የተደፋው ግን ከኣይነደረቅነታቸው (ወይም ከጭንቀታቸው) የተነሳ ይህንን የማሳሳቻ ተልእኮ በጣም ብዙ ብር ኣውጥተው የውጭ ነዋሪውን ለማማለል በተላኩት የመለስ መልእክተኞች ፊት ነው:: የማስቀየሺያ እስትራቴጂው በነመለስ “ሳይንሳዊ” ስሌት ሁለት ከፍተኛ የፖለቲካ ግኝቶችንና ኣንድ የእግረ መንገድ የገንዘብ ትርፍ ያስገኛል ተብሎ የተሰላ ነበር: እነኝህም:

  1. በውጭ የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ በተቻለ መጠን መከፋፈል (በዘር: በሀይማኖት: በፖለቲካ ኣመለካከት…ወዘተ)
  2. በውጭ ያለውን የተቃዋሚ ሀይል ማዳከም: ይህንንም በመንደራችሁ መጥተን እንደፈለግን ፎልለን: በዳያስፖራው የልማት መንግስት ተብለን ኣስጨብጭበን: ኣውራ ተቃዋሚዎችን ለኣገር ልማት ያልቆሙ “ጽንፈኞች” ኣስብለን እንሄዳለን:: ከዚያ በኋላ እስከወዲያኛው ድረስ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ኣይነሳም…ወዘተ
  3. በዚህ ኣጋጣሚ “ከልማቱ ልጠቀም” የሚሉ ደካሞች (suckers) ኣይጠፉምና ከነሱ ደግሞ ትንሽ የቦንድ ገንዘብ በዶላር ከሰበሰብን “ዝበለጸ” ብለው ይመስላል መለስ ኣዜብና በረከት ከዳያስፖራ ኣማካሪዎቻቸው ጋር ያሰሉት::

የመለስ መንግስት ይህ ኣላማው በፍጹም ኣለመሳካቱ ብቻ ሳይሆን እንዲያውም ከታሰበው በተቃራኒው ውጤት ማስከተሉ ከላይ እንዳልኩት ይህ መንግስት ኣንድ ሀሙስ የቀረው መሆኑን እንድንገምት ያደርገናል:: እከፋፍላለሁ ብሎ መጥቶ እንዲያውም ዳያስፖራው ከዚህ በፊት ሆኖ በማያውቅ መልኩ በጎሪጥ ይተያዩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን “ኣሁንስ በዛ: በቃ_ጋዬ” ብለው ኦሮሞው፤ ኦጋዴኑ፤ ኣማራው፤ ጉራጌው፤ ጋምቤላው፤ ባጠቃላይ መላው ኢትዮጵያዊ በጋራ ተቃወማቸው:: ይህ ብቻ ኣይደለም:: በዚህ በዛሬው ስብሰባ እንደምታዩት ከኣንድ ጊዜ የተቃውሞ ሰልፍ ኣልፎ ትግሉን በጋራ ለማስኬድ የሚያስፈልገውን የመተሳሰብ፤ የመተማመን፤ በጋራ የመወያየትና የጋራ ራእይ የመቅረጽ እንቅስቃሴ በጥንካሬ ገፋበት::

ኣዳክሜ እሄዳለሁ ያለውን ዳያስፖራ እንዲያውም እልህ ውስጥ ከትቶት የበለጠ ኣጠናክሮት ኣረፈው:: በኣሜሪካን ኣገር በተለያዩ እስቴቶች እንዲሁም በኣውሮፓ በእንግሊዝና በፍራንክፈርት በተደረጉት ስብሰባዎች ሁሉ የተሳተፉ ወገኖች እንደገለጹት ምናልባት የቅንጅት ኣመራሮች ከታሰሩ ጊዜ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የሰው ሀይልና እልህ የተቀላቀለበት ስሜት ነው ፈጥረው የሄዱት:: ለዚህም ነው ለነሱም የስትራቴጂው መባረቅ ኣስደንግጧቸው ወዲያውኑ ማስፈራራት ወደለመዱት የኢትዮጵያ ህዝብ ተመልሰው ልክ ድሮ ደርግ “የጨለቅለቅቱ ገበሬዎች የኣሜሪካ ኢምፔሪያሊዝምን ኣስጠነቀቁ” ይል እንደነበረው ገበሬውና ተማሪው ዳያስፖራውን “በሰልፍ እንዲያወግዝ” በካድሬዎች መቀስቀስ የጀመሩት:: ምን ያህል ግራ እንደተጋቡ የሚያሳየው ግን ካድሬዎቹ ዳያስፖራውን ኣውግዙ እያሉ በራሳቸው የመገናኛ ብዙሀን ደግሞ በውጭ የተካሄደው ስብሰባ እንዴት የተሳካ እንደነበረና ዳያስፖራው ገንዘብ በገፍ ሊያዋጣ ቃል እንደገባ ለህዝቡ ያበስሩታል::

ሶስተኛው በቤታቸው ያራዳ ወይም የ “ወዲ ሹቅ” ስራ የነበረው በኣባይ ቦንድ ስም ዶላር የመሰብሰቡም ነገር ብዙ ኣላዋጣም:: እስካሁን ኣይደለም ብዙ ዶላር ሊሰበስቡ ለትርኢቱ ያወጡትን ቢያንስ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ ወጪ እንኳን ለማግኝት ኣልቻሉም:: ባጠቃላይ ትርኢቱ እንደቀሺም ዘፋኝ ኮንሰርት በባዶ ኣዳራሽ: የዘፋኙ የቅርብ ወዳጆች ብቻ በተገኙበት: በፍጹም ኪሳራ ተደመደመ:: ባጠቃላይ ከነመለስ የሰሞኑ መንቀዥቀዥም ሆነ ከህዝቡ ምላሽ መገንዘብ የሚቻለው ሁኔታው ለለውጥ የተዘጋጀ መሆኑን ነው:: ለውጥ ተጀመረ ማለት ግን ሙሉ ለሙሉ ወዲያውኑ ይሳካል ማለት ኣይደለም:: ለስኬቱ ኣስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ትግሉን በሚያካሂዱ ሀይሎች ዘንድ መፈጸም ያለባቸው ብዙ ስራዎች ኣሉ:: የዛሬ ንግግሬን ለመቋጨት ከነኝህ ኣስፈላጊ ነገሮች ውስጥ በጣም ወሳኝ በሆነው በዴሞክራሲ ሀይሎች መሀል በጋራ ሊኖር ስለሚገባው “የመዳረሻ ቦታ” (end game) ኣመለካከት ላይ ድረጅታችን ያለውን ኣቋም ውይይት ለመቆስቆሻ ያክል ላቅርብና ላብቃ::

4. ኣሁን ኣጥቂዎች እኛ ነን:

የዚህ የመዳረሻ ቦታ ኣመለካከት ሁለት ገጽታዎች ይኖሩታል:: ኣንደኛው በስነልቦና ደረጃ የዴሞክራሲያዊው ሀይሎች ሊኖራቸው የሚገባው የመንፈስ ዝግጁነት ነው:: በዚህ ዙሪያ ከዚህ በፊት በኖርዌይ ንግግሬ እንደገለጽኩት ትግላችን እንደከዚህ በፊቱ ወያኔ የሚወረውረው ነገር ላይ የመከላከል እርምጃ መውሰድ ሳይሆን ቀጥታ የማጥቃት እርምጃ የሚወሰድበት ደረጃ ላይ መድረሳችንን መረዳት ነው:: ይህ ኣስፈላጊ የሆነ የስነልቦና ለውጥ ነው:: ኣሁን ተነሳሽነቱ (initiative) የኛ መሆኑን መቀበልና የምንወስደው እርምጃ ሁሉ ይህንን ከስሌት ያስገባ ማድረግ ያስፈልጋል:: ይህ ከተከላካይነት ወደ ኣጥቂነት የሚደረግ ሽግግር ደግሞ ከዚህ በፊት እንዳልኩት 1ኛ) ጠላትን መነጠልና፣ 2ኛ) ወዳጅን ማብዛት፣ ከያንዳንዱ እርምጃችን ጋር የተሳሰረ የሁልጊዜም ስሌታችን ኣካል ማድረግን ይጠይቅብናል::

ሁለተኛውና ወሳኙ ቁምነገር ደግሞ የዴሞክራሲ ሀይሉን በኣንድ የመታገያ ኣጀንዳ ዙሪያ ማሰለፍና ቆይቶም በዚህ መስመር ዙሪያ ላይ የታጠረ ህብረ ድርጅታዊ ኣመራር ስር ማሰባሰብ ነው:: ኣሁን ኣገራችን ባለችበት ሁኔታ ሁለቱም ጊዜ ሳይወስድ መፈጸም ያለባቸው ቢሆኑም የኋለኛው ትንሽ ጊዜ የሚወስድ ቢሆን እንኳን የመታገያ መስመሩን በተመለከተ ሁሉም በየድርጅቱ ኣሁኑኑ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ስለሆነና ባጠቃላይ ህዝቡም ዘንድ መናበብን ማዳበር ስለሚገባ ኣሁኑኑ ማድረጉ ኣስፈላጊ ይመስለኛል:: በኣገራችን ይህንን የጋራ የመታገያ ኣጀንዳ ግን የግድ የፖለቲካ ድርጅቶች ማውጣት የለባቸውም:: እንደ ግብጽና ሌሎች የሰሜን ኣፍሪካ ኣብዮቶች ሁኔታውን እየኖሩበት ያሉትና ትግሉንም ከዳር የሚያደርሱት ወጣቶች የሚታያቸውን ማድመጥ: በጣም ኣስፈላጊ ነው::

በዚህ ረገድ የኦሮሞ ወጣቶች ማህበር የህዝብ ቁጣ ሊያነጣጥርባቸው የሚገቡ መሰረታዊ ነጥቦችን በቅርቡ ዘርዝሮ በጽሁፍ አውጥቷል። ይህ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ( Freedom, Liberty and democracy shall prevail! ) በሚል ርእስ በብሄራዊ ወጣቶች የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የተዘጋጀ ሰነድ በውስጡ በርካታና በደንብ የታሰበባቸው የህዝባዊ እምቢተኛነቱ ትግል ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አስቀምጧል። እያንዳንዱ ድርጅት፣ ቡድን ወይም ታጋይ የራሱን የመታገያ ነጥብ በየግሉ እያነሳ የመታገል መብት ያለው መሆኑ ቢታወቅም ትግሉን ለማቀላጥፍና በጋራ ስምምነት የተደረሰባቸን መሰረታዊ ጉዳዮች አስቀድሞ አውቆ መንቀሳቀስ ለውጤታማነቱ ኣስፈላጊ ነው። ይህን እውን ለማድረግ የኦሮሞ ወጣቶች ባቀረቡት ሰነድ ላይ የሰፈሩትን ህዝባዊ ጥያቄዎች የመታገያ አጀንዳዎች ተቀብሎ በእነዚህ ላይ የሚጨመር ካለ እንዲጨመር እያደረጉ መቀጠሉ የተሻለ ውጤት ያስገኛል ብሎ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ያምናል። ሌሎችም ድርጅቶች: ቡድኖችና ታጋዮች ይህ የኦሮሞ ወጣቶችን የመታገያ ሰነድ እንደሚቀበሉት በመግለጽ የቀረበው ጥያቄና የመታገያ አጀንዳ የመላ ሃገሪቱ ህዝብ የወጣቱና የአረጋዊው፣ የሴቱና የወንዱ፣ የክርስቲያኑና የሙስሊሙ እንደሆነ በማያሻማ ቋንቋ መግለጽ ትግሉን ወደፊት ያራምደዋል የሚል እምነት ንቅናቄያችን አለው። ከዚህ በመነሳት የሚከተሉትን በኦሮም ወጣቶች መግለጫ ላይ የተወሰዱትን (ለግልጽነት እንዲረዳ ካደረግናቸው ጥቃቅን ለውጦች ጋር) አቋሞች በሙሉ ልባችን እንደግፋለን። ሌሎችም አካላት የተባለውን ሰነድ አጥንተው ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ ወገናዊ ጥሪያችንን እናቀረባለን።

  1. የወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ የህዝብን ፍትሃዊና ህጋዊ መብቶችና ጥያቄዎች ለማፈን ባለፉት 20 አመታት በተለያዩ የኣገሪቱ አካባቢዎች በተለይ ደግሞ በኦሮምያ፣ በኦጋዴን: በጋምቤላና በሌሎችም ክልሎች ህዝቦች ላይ የሚያካሄደውን ወታደራዊ የእመቃ ዘመቻ አሁኑኑ ያቁም።
  2. በሃገሪቱ እስር ቤቶች የሚማቅቁ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ ይፈቱ።የሰው ልጆች ቄራ የሆነውና የሰቆቃ ስራ መፈጸሚያ የሆነው የማእከላዊ እስርቤት ባስቸኳይ ፈረሶ ለዘላለሙ ይዘጋ
  3. የአገዛዙ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማስተካካያ እስኪበጅለት ድረስ ይህ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግር ላይ ለጣላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ዳቦ፣ ስኳር: እህልና ዘይት የመሳሰሉት የመሰረታዊ ፍጆታ እቃዎች ባስቸኳይ ከመነሻው የመንግስት ድጎማ ተደርጎላቸው ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚደርስበት መንገድ ይመቻች::
  4. የመለስ ዜናዊና የቤተሰቡ ንብረት ባስቸኳይ እንዲወረስ፤ ልኩ በውል በማይታወቀው የመለስ ቤተስብና የቅርብ ባለሟሎቹ የሙስና ተግባራት የምርመራ ስራ አሁኑኑ ይጀመር።
  5. የኢትዮጵያን ህዝብ ለአለም አቀፍ ጌቶች ባሪያ የሚያደረገው መሬት ለባእዳን አሳልፎ የመሸጥ ፐሊሲ አሁኑኑ ይቁም። በዚህ ረገድ የተደረሱ አለም አቀፍ ውሎች በሙሉ አሁኑኑ ይሰረዙ።
  6. መለስ ዜናዊ ባስቸኳይ ከጠቅላይ ሚስትርነቱ ይነሳ የመንግስትን ስልጣን ባስቸኳይ ይልቀቅ።
  7. ህገ ወጥ በሆነና በተጭበረበረ ምርጫ የተቋቋሙት የህዝብ መወሰኛና የፌደራል ምክር ቤቶች አሁኑኑ ይፍረሱ። ሁሉም የነጻነት ንቅናቄዎችና ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የተሳተፉበት ዓላማው ማህበራዊ ፍትህንና ዴሞክራሲን ማንገስ የሆነና በኣጭር ጊዜ በነጻ የምርጫ ተቋምና ኣለምኣቀፍ ታዛቢዎች ሙሉ ለሙሉ በተመሰከረለት ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚያቋቁም የሽግግር መንግስት ይቋቋም።

ከነዚህ በላይ በኦሮሞ ወጣቶች ከቀረቡ ጥያቄዎች በተጨማሪ ንቅናቄያችን የሚከተሉትን ቁልፍ ነጥቦች የመታገያ አጀንዳዎቻችን ወስጥ እንድንጨምራቸው ጥሪ ያቀርባል።

8. በቅርቡ በነዳጅ ላይ የተደረገው የዜጎችን ህይወት ለከፋ የኢኮኖሚ ስቃይ የሚዳርገው የዋጋ ጭማሪ ባስቸኳይ እንዲነሳ

9. በኦፊሴል ያልታወጀው ግን በተግባር በስራ ላይ የዋለው የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ይነሳ:: በሃገሪቱ ህገ መንግስት የተደነገጉት የመናገር: የመጻፍ: የመሰብሰብ: ስላማዊ ስልፍ የማድረግ መብቶች ሙሉ በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሁኑኑ እንዲከበሩ። እነዚህ መሰረታዊ የሰብአዊና የሲቪል መብቶችን ለመጣስ የተደነገጉ ህጎች በሙሉ፤ ባለፉት ጥቂት አመታት የወጡትን የጸረ ሽብር ህግ፤ የፕሬስ ህግና፤ የመያድ ህጎችን ጨምሮ እንዲሰረዙ።

10. የኢትዮጵያ ህዝብ የኣባይን ወንዝ የመገደብና በኣግባቡ መጠቀምን ጨምሮ፤ ኑሮውን ለማሻሻልና ኢኮኖሚውን ለማሳደግ ያሉትን የተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ በኣለም ኣቀፍ ህግ መሰረት የመጠቀም መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በትራንፎርሜሽን፤ በአባይ ግድብና በሌላም ግንባታ ስም ወያኔ የሚያደረገው ተራ ማጭበርበር ባስቸኳይ እንዲቆምና በዚህ ማጭበርበሪያ ስም ወያኔ/ኢህአዴግ ክህዝብ የሰበሰበውን ገንዘብ ለባለቤቶቹ ባስቸኳይ እንዲመልስ።

ከዚህ በላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ጥያቄዎቹን የጋራ አድርገን በጋራ እንነሳ ።

ኣመሰግናለሁ::