ዘረኛው የመለስ ዜናዊ አገዝዝ የጽጥታ ሀይሎቹ ማንኛውንም ክትትል እንዲያድረጉ አዘዘ
የግንቦት20 በአል አከባባርን ለማደናቀፍና ብሎም ህዝባዊ አመጽ ለመቀስቀስ አንዳንድ ወገኖች እያሴሩ ስለሆነ አስፈላጊው ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል ሲል የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በአገሪቱ ላሉ ወረዳዎች ሁሉ ሰርኩላር ማስተላለፉን ኢሳት የተባለው የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥን ዘገበ።
ኢሳት ኢትዮጵያ ዉስጥ ከተለያዩ ወረዳ ባለስልጣኖች አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት ወያኔ በትረ ሥልጣን የተቆጣጠረበትን 20ኛውን የግንቦት 20 በአል በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ሽር ጉዱን የተያያዘው ሲሆን ፣ በዚህ እለት ረብሻ ለማስነሳት የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች መኖራቸውን ደርሼበታለሁ በማለት በመላዉ አገሪቱ ታላቅ የጸጥታ እንቅስቃሴ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
የመለስ ዜናዊና የባለቤቱ የአዘብ መስፍን አገዛዝ በየክልሉ የሚገኙት የጸጥታ ሀይሎች ሁከትና ረብሻ እንፈጥራለን የሚሉ ሀይሎችን ለመቆጣጠር እንዲችሉ ጥብቅ ትዕዛዝ ያስተላለፈ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሰሜን አፍሪካ ዉስጥ አምባገነኖችን እያርበደበደ ያለዉ ህዝባዊ አብዮት ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዳይደርስ ለመከላከል በሚል ሰበብ በርካታ ንጹሗን ዜጎችን ማዋከብና ማንገላታት ከጀመረ ሰንበት ብሏል። በተለይ ካለፈው ሁለት ወር ወዲህ በኦሮሚያና በአማራ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመረው የዘፈቀደ ፍተሻ አገዛዙ የደረሰበትን ከፍተኛ የስነልቦና መረበሽ ከማሳየቱም ባሻገር በጸጥታ ጥበቃው ሥራ ላይ የተሰማሩት በርካታ የበታች ሠራተኞች እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ አገሪቱ ዉስጥ በተንሰራፋዉ ዘረኝነትና የኑሮ ዉድነት ዘረኛነትና በኑሮ ውድነት የተንገፈገፉ በመሆናቸው ይነሳል ተብሎ የሚጠበቀውን ህዝባዊ አመጽ በቀላሉ መቀላቀል እንደሚችሉ በከፍተኛ እምነት አለ።
ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚደረሱን ዘገባዎች እንደሚያስረዱት በአንዳንድ የአገዛዙ ፖሊሶች እቃ አንጠልጥለው የሚጓዙ መንገደኖችን ሳይቀር እያስቆሙ መፈተሽ መጀመራቸውንና ይህም ወያኔ በምን አይነት ድንጋጤ ውስጥ እንደተዘፈቀ አመልካች ነው ተብሎአል።
በአሁኑ ጊዜ በመላው አገሪቱ በየቀኑ እያሻቀበ የሚሄደዉ የዕቃዎች ዋጋና አላስቆም አላስቀምጥ ያለዉ የመብት አፈና የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቤት ያንኳኳ በመሆኑ አመጽ መቀስቀሱ የማይቀር ሙኑንና ከተቀሰቀሰ ደግሞ ህዝቡ እንደሰሜን አፍሪካው “ሆ” ብሎ በመውጣት በሙስናና ዘረፋ የተጨማለቀውን የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ እንደሚገረስስ ብዙዎች ይስማማሉ።