የመጨረሻዉ ደወል
ከሁለት ምዕተ አመታት በፊት ትልቅነቷ ተዳስሶ የማያልቅ ትመስል የነበረቺዉ ይቺ የምንኖርባት ምድር ዛሬ ቴክኖሎጂ እንደ አበሻ ቀሚስ ጥለት ጠልፎና አጠላልፎ ሁሉም ሰዉ በአንድ ግዜ መተያየት የሚችልበት ክብ ጠረቤዛ አስመስሏታል። ዛሬ የአሜሪካ ህዝብ ምሽት ላይ የሰማዉን ሰበር ዜና አፍሪካን ጨምሮ የሌላዉ ዓለም ህዝብ የሚሰማዉ አሜሪካኖች ዜናዉን የሰሙበትን የቴሌቭዥን ጣብያ ሳይቀይሩት ነዉ። ይህ የሚያሳየን ወደ አገሮች ዉስጥ የሚገባዉና ከአገሮች የሚወጣዉ ዜና ሙሉ በሙሉ በአምባገነን መሪዎች ቁጥጥር ስር የነበረበት ዘመን ዳግም ላያንሰራራ ማክተሙን ነዉ። አገራችን ኢትዮጵያን እንኳን ብንመለከት የአምባገነኑ መንግስቱ ኃ/ማሪያምን ግፍና ሰብዓዊ መብት ረገጣ የዉጭዉ አለም የሚሰማዉ ዜናዉ በወሬ ነጋሪ ከአገር ወጥቶ ዉሎ አድሮ ከሰነበተና የወሬ ቋንጣ ከሆነ በኋላ ነበር። ዛሬ ግን የዘመኑ ቴክኖሎጂ ምስጋና ይግባዉና የወያኔ ዘረኞች የሚፈጽሟቸዉን አፈናዎችና ግድያዎች የአለም ህዝብ የሚሰማቸዉና አንዳንዶቹን በምስል በተደገፈ መረጃ የሚመለከታቸዉ ከመቅጽበት ነዉ። ይህንን ቅጽበታዊ የሆነ የመረጃ ልዉዉጥ ይበልልህ የምንለዉ አለማችንን በማቀራረቡ ብቻ ሳይሆን እንደ ዘረኛዉ መለስ ዜናዊ አይነቶቹን አምባገነን መሪዎች እርቃናቸዉን እንዲቀሩ ማድረግ በመቻሉ ነዉ። ይህ በመሆኑ ይመስላል ዛሬ የወያኔ አገዛዝ ከ3 ሚሊዮን በላይ ዜጎቼ ለረሀብ አደጋ ተጋልጠዋል ብሎ ለምፅዋት በዘረጋበት እጁ ያንኑ የተራበ ህዝብ ከመረጃ ዉጭ ለማድረግና ጨለማ ዉስጥ ለማቆየት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር በልመና የተገኘ የህዝብ ገንዝብ የሚያባክነዉ።
በቅርቡ ቱኒዝያና ግብፅ ዉስጥ የተካሄዱትና እጅግ በጣም አጭር በሆነ ግዜ ዉስጥ ሁለት የለየላቸዉ አምባገነን መሪዎችን አሽቀንጥረዉ የጣሉት ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች የመረጃ ቴክኖሎጂ ዉጤቶች ናቸዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ግብፅና ቱኒዝያ ዉስጥ በአይን ተያይቶ የማያዉቅ ህብረተሰብ በተለይም ወጣቱ ትዉልድ በማይታይና በማይዳሰስ አለም ዉስጥ ተገኛኝቶና መክሮ የጀመረዉን ንቅናቄ ከግቡ እንዲያደርስ የረዱት እንደ ፌስ ቡክ፤የእጅ ላይ ስልክ፤ቲዉተርና እንተርኔትን የመሳሰሉ የመረጃ ቴክኖሎጂ ዉጤቶች ናቸዉ። ቴክኖሎጂ ግዑዝ አካል ነዉና በራሱ የሚሰራዉ ወይም የሚለዉጠዉ ምንም ነገር የለም። ቴክኖሎጂ አንድን ህብረተሰብ በሚገባ እንዲያገለግል በአንድ በኩል የሚያስፋፋዉ በሌላ በኩል ደግሞ አዘዉትሮ የሚጠቀምበት የህብረተሰብ ክፍል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በብዙ አገሮች ዉስጥ ወጣቱ ትዉልድ ከቴክኖሎጂ ጋር ለመተዋወቅ ያለዉ ፍላጎትና ዝንባሌ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ። ሆኖም ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ አገዛዝ የወጣቱን ከቴክኖሎጂ ጋር መተሳሰር የሚያገናኘዉ ከአገር ልማትና እድገት ጋር ሳይሆን ከራሱ የስልጣን ዘመን ማክተም ጋር ስለሆነ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተስፋፋዉ ህዝብን የሚያስተሳስርና አገርን የሚያለማ ቴክኖሎጂ ሳይሆን ድህረ ገጾችን፤ሬዲዮ ጣቢያዎችንና የቴሌቭዥን ጣቢያዎችን የሚያፍን አስቀያሚና ጎታች ቴክኖሎጂ ነዉ። ስለሆነም ዛሬ ኢትዮጵያ በኢንተርኔት አጠቃቀም በአለም ላይ የመጨረሻዋ አገር ናት።
የግብፅ ህዝብ በልዕለ ኃያሏ አገር አሜሪካ በከፍተኛ ደረጃ የሚታገዘዉ የሆስኒ ሙባረክ አገዛዝ የማይነካ እየመሰለዉ የመብትና የነፃነት ጥያቄዉን በፍርሀት ሸብቦት ለብዙ ዘመን በጨለማ ዉስጥ ኖሯል፤ ሆኖም ፍርሀት መቼም ሆነ ዬትም ቦታ ገደብ አለዉና የግብፅ ወጣቶች ፍርሀታቸዉን ተጋፍጠዉ በከፍተኛ የደህንነት ሀይል፤ በመረጃና በስለላ ስራ የተካነዉን የሞባረክ አገዘዝ በ18 ቀን ዉስጥ ብትንትኑን ማዉጣት ችሏል። ከዚህ አጅግ አስገራሚ ከሆነ ህዝባዊ ድል የአለም ጭቁን ህዝቦች በተለይም በዘረኞችና በጎጠኞች በትር ቀንና ማታ የሚደበደበዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ብዙ የሚማራቸዉ ነገሮች አሉ። በእርግጥ በግብፅና በኢትዮጵያ ህዝብ መካለከል የባህል፤የታሪክ፤የቋንቋና የኤኮኖሚ እድገት ልዩነቶች አሉ፤ ሆኖም ግብፃዉያንን “ዛሬስ በቃ” አሰኝቶ ካነሳሳቸዉ የኤኮኖሚ፤ የፖለቲካና የማህበራዊ ችግር የበለጠና እጅግ የተወሳሰበ ችግር ኢትዮጵያ ዉስጥ አለ። አንድ የግብፅ ዜጋ በአመት የሚያገኘዉ የነፍስ ወከፍ ገቢ አስር ኢትዮጵያዉያን ከሚያገኙት ተመሳሳይ አመታዊ ገቢ ይበልጣል፤ እንግዲህ እኛ ኢትዮጵያዉያን አስር ሆነን ከምናገኘዉ ገቢ በላይ የሚያገኘዉ ግብፃዊ ድህነት መረረኝ ብሎ ከተነሳ እኛማ ድህነትና ዘረኝነት እንደ ገና ዳቦ ከላይና ከታች የሚለበልበን ኢትዮጵያዉያን አምርረን ብንነሳ ከዉርደትና ከእርግጫ ሌላ ምን የሚቀርብን ነገር ይኖራል? አዎ- ብዙዎቻችን የወያኔ አስከዛሬ በሥልጣን ላይ መቆየት ጸጽቶናል፤ ሆኖም ባለፈዉ እየተፀፀተና የወደፊቱን ከወዲሁ እየፈራ የሚኖር ህብረተሰብ ግፈኞች እንደ ጭነት ከጫኑበት ቀንበር መላቀቅ አይችልምና የኢትዮጵያም ህዝብ አንደ ግብፅ እንደ ቱኒዝያና እንደ ሊቢያ ህዝብ “ሆ” ብሎ የሚነሳበትን ቀን ካሁኑ መምከርና ማመቻቸት ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ ከምን ግዜም በላይ እጅግ በጣም ወሳኝና ወስብስብ ወደሆነ የፖለቲካ ምዕራፍ ዉስጥ እየገባ ነዉ፤ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ከዚህ እጅግ አሳሳቢ ከሆነ ታሪካዊ ዝቅጠት መንጥቆ ለማዉጣት በሚደረገዉ የሞት የሽረት ትግል ዉስጥ ከፍተኛዉን ሚና መጫወት ያለባቸዉ ሁለት የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ – እነሱም የለዉጥ አንቀሳቃሽ የሆነዉ የወጣቱ ትዉልድና ኢትዮጵያን ከዉጭም ሆነ ከዉስጥ ጠላቶች የመከላከል ታሪካዊ አደራ የተቀበለዉ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ነዉ ። የወያኔ የስልጣን ዘመን በረዘመ ቁጥር የወደፊቱ የሚጨልምበትና ስቃይና ዉርደቱ የሚበዛበት የወጣቱ ትዉልድ ሲሆን፤ በአንፃሩ የወያኔ ስርዐት ፈርሶ ኢትዮጵያ ዉስጥ የእኩልነት ስርዐት ሲመሠረት ከማንኛዉም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ተጠቃሚ የሚሆነዉ ይሄዉ የወጣቱ ህብረተሰብ ነዉ። አብዛኛዉ አባላቱ በወጣትነት ዕድሜ ክልል ወስጥ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ የመከላኸያ ሠራዊት ደግሞ የወያኔ ዘረኝነትና ጋጠወጥነት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ካዋረዳቸዉ የህብረተሰብ ክፍሎች አንዱና ዋነኛዉ ነዉ። ስለሆነም ሠራዊቱ ለዉጥ እንደ ዉኃ የጠማዉ ሠራዊት ነዉና ዘረኞች ለዉጥን እንዲዋጋና ወንድሞቹንና እህቶቹን እንዲገድል በየጎዳናዉ ቢያሰማሩትም ይህ ሠራዊት የህዝብ ልጅ ነዉና እንደ ቱኒዝያና እንደ ግብፅ ሠራዊት ህዝባዊዉን እንቅስቃሴ ይቀላቀላል እንጂ እናትና አባቱ ላይ አይተኩስም የሚል የፀና እምነት አለ።
የወያኔ መሪዎች ያሻቸዉን ያክል ሊገድቡት ቢሞክሩም የሰሜን አፍሪካን አምባገነኖች የጠራረገዉ ህዝባዊ ማዕበል እነሱንም ጠራርጎ የታሪክ ቆሻሻ ዉስጥ መጨመሩ የማይቀር ነዉ። ሆኖም ዛሬ የአምባገነኖች ባህል ነዉና “እሳት ሳይቀጣጠል በቅጠል” እንዲሉ ቱኒዝያና ግብፅ ዉስጥ የተቀጣጠለዉ የነፃነት ሰደድ እሳት የኢትዮጵያን ድንበር እንዳያልፍ ለመገደብ ቁጭ ብድጉን ተያይዘዉታል። ከሰሞኑማ የጂቡቲዉ ጉዳይ አስደንግጧቸዉ ግዑዙን ባቡር ጭምር ይጠራጠሩት ጀምረዋል። የሰሞኑ የአዲስ አበባና የሌሎችም ትላልቅ ከተማዎች ሁኔታ በግልፅ እንደሚያሳየን ሰርግና ምላሹ እንዳከተመ የገባቸዉ የህወሀት መሪዎች በከፍተኛ ፍርሀት ተዉጠዋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለአገር አንድነት የሚቆረቆርና ለህገመንግስት የሚገዛ የመከላከያ ተቋም ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደሌለ በዉል የሚያዉቀዉ የኢትዮጵያ ህዝብ አምናና ካቻምና ከደረሰበት ሰቀቀን ዛሬም አልተላቀቀም። ስለሆነም ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በግልጽ የሚታያዉ ወያኔ ህዝብን ከዛሬ ነገ ተነሱብኝ እያለ ሲፈራና የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ዘንድሮ “ምን ያመጡብን” ይሆን እያለ ወያኔዎችን ሲፈራ ነዉ።
ከፍርሀት ዉጭ የሆነ ግለሰብም ሆነ ህብረተሰብ የለም- አልነበረም- አይኖርምም! ግብፃዉያንና ቱኒዝያዉያን ለረጂም ግዜ በፍርሀት ጥላ ስር ኖረዋል። የእነዚህ ሁለት አገሮች ህዝብ ዛሬ የአለማችን የለዉጥ ማዕበል ተምሳሌት የሆነዉ አብሮት የኖረዉ ፍርሀት በቀድዶ ጥገና ከዉስጡ ወጥቶለት ሳይሆን ፍርሀቱን ፊት ለፊት ተጋፍጦ ነዉ። እኛ ሰዎች ክንዳችን የሚበረታዉ ተስፋችን የሚለመልመዉና በራስ መተማመናችን የሚጠነክረዉ እዉስጣችን ያለዉን ፍርሀት ጥሰን ወደ ፊት መጓዝ ስንችል ብቻ ነዉ። የነገዉ የነፃነት ራዕያችን ስፋትና ርዝመት ዛሬ ከርችሞ የያዘንን የፍርሀት ጥልቀት ዘልሎ ማለፍ ካልቻለ የሚጠብቀን ነገር ቢኖር ባርነት ብቻ ነዉ። ባርነት ደግሞ የማንም አማራጭ አይደለም!
ባለፉት ሀያ አመታት ወያኔ የ17 አመት የበረሃ ልምዱንና ወደር የለሽ ጭካኔዉን እያሳየን ሆን ብሎ የፍርሀት መንፈስ ሲረጭብን ቆይቷል። ይህ የተቀነባበረ የወያኔ አፍዝ አደንግዝ የፍርሀት ዘመቻ ደግሞ የዋሁን የህብረተሰባችን ክፍል ብቻ ሳይሆን ለጭንቅ ቀን ይሆኑናል ብለን ያስተማርናቸዉን አንዳንድ ምሁራን ጭምር አዘናግቶ የወያኔን ጥንካሬና ትልቅነት እንዲነግሩን አድርጓቸዋል። የሚገርመዉ እነዚህ ስማቸዉ ላይ ፕሮፌሰርና ዶክተር የሚል ቅጥያ የተቀጠለላቸዉ ምሁራን እነሱ ተምቦቅብቀዉ እኛም እንደነሱ እንድንፈራ የሚነግሩን ይህንን መለስ ዜናዊና ስብሐት ነጋ ጠፍጥፈዉ የሰሩትን ወያኔ የሚባል የዘረኞች ስብስብ ሳይሆን የራሳቸዉ ፍርሀት አምጦ የወለደዉን ወያኔ ነዉ – አለዚያማ ወያኔ ህዝብን ከዛሬ ነገ ይነሳብኛል እያለ በሚፈራበት ዘመን ህዝብ ወያኔን የሚፈራበት ምንም ምክንያት ሊኖር አይገባም። እኛ ኢትዮጵያዉያን ባለፉት ሃያ አመታት ለሠላም፤ለፍትህ፤ ለነፃነትና ለእኩልነት እጅግ በጣም መራራ ትግል አካሂዷናል፡ ነገር ግን ስለ ድልና ስለ ጀግንነት ከሚነግረን የውስጥ ስሜታች ይልቅ ወያኔ በጆሯችን ሹክ የሚለንን የፍርሃት ሹክሹክታ በማዳመጣችን ወዳለምነዉ ግብ መድረስ አልቻልንም።
ነፃነቱንና ሰብዓዊ ክብሩን የተቀማ ህዝብ ገዢዎቹን ፈርቶና ሰጥለጥ ብሎ አንገቱን ደፍቶ የኖረበትን አጋጣሚ ታሪክ መዝግቦት አያዉቅም። የሰዉን ልጅ ከሌላዉ ፍጡር የሚለየዉ ዋናዉ ነገር ነፃነቱን ተቀምቶ ትርጉም የለሽ ኑሮ ከሚኖር ለነፃነቱ ተዋግቶ በክብር መሞትን የሚመርጥ ፍጡር መሆኑ ነዉ። እኛ ሰዎች መፍራት የሚገባን ለነፃነት መሞትን ሳይሆን ያለነፃነት መኖርን ነዉ። ነፃነት ደግሞ የወያኔ ካድሬዎች እንደሚሰብኩን በኤኮኖሚ ካደግን በኋላ እነሱ የሚሰጡን ምፅዋት ሳይሆን ነፃነት የኤኮኖሚና የማህበራዊ ዕድገታችንን የሚያፋጥን የትግላችን ትልቁና ዋነኛዉ ግብ ነዉ።
በኮሎኔል መንግስቱ ዘመን ሁሉም ሰዉ ኢትዮጵያን እናቴ ወይም እናት አገር እያለ ይጠራት ነበር፤ ዛሬም ከወያኔ ሹሞች አንደበት ባይደመጥም ብዙ ሰዉ ኢትዮጵያን እናት አገር እያለ ሲጣራ ይደመጣል። ለመሆኑ ማነዉ የኢትዮጵያ ልጅ? ማነዉ እዉነተኛዉ የኢትዮጵያ ልጅ? – ማነዉ አንደ መቅደላዉ ጀግና “አንቺ እማማ ቃልኮ የእምነት ዕዳ ነዉ እንጂ የእናት የአባትኮ አይደለም” ብሎ እየፎከረ እናት አገሩን ከዘረኞችና አይን ካወጡ ዘራፊዎች ለማደን እንደ አፄ ቴዎድሮስ የክብር መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ? እናት አገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ልጆች ወልዳለች- እዉነተኛዎቹ ልጆቿ ግን ይህንን ጥያቄ በአዎንታ ለመመለስ የተዘጋጁ ብቻ ናቸዉ።
እዉነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች የነሱና የእናት አገራቸዉ የኢትዮጵያ የወደፊት ዕድል ለኢትዮጵያም ሆነ ለዜጎቿ ምንም ደንታ በሌላቸዉ ዘረኞች ሲወሰን ቁጭ ብለዉ አይመለከቱም። አገራችንን ላለፉት ሃያ አመታት የመሩት የወያኔ መሪዎች ወዴት እየወሰዱን እንደሆነ ሁላችንም የተረዳን ይመስላል፤ስለዚህ ለአገራችን አንድነትና ለልጆቻችን ነፃነት፤ እኩልነት፤ ሠላምና ብልጽግና የምንቆረቆር ኢትዮጵያዉያን አንድ ትልቅ ነገር ማድረግ የሚገባን ግዜ ቢኖር ያ” ግዜ አሁን ነዉ።
እኛ ኢትዮጵያዉያን ረጂም የነፃነትና የዲሞክራሲ ጉዞ ተጉዘን ዛሬ የመጨረሻዉ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። ይህንን የነፃነት ጉዞ በድል እንዳናገባድድ መንገዳችን ላይ ተገትሮ ደንቃራ የሆነብን ወያኔዎች የጫኑብን የፍርሀት መንፈስ ነዉ እንጂ የነሱ ጥንካሬ ወይም ግዙፍነት አይደለም። ፍርሀት ደግሞ ጥላዉ ነዉ እንጂ ትልቅ እሱ ራሱ እዚህ ግባ የማይባል ትንሽ ነገር ነዉ። መለስ ዜናዊ የለየለት ጨካኝ ሰዉ ስለሆነ ከቱኒዝያዉ ቤን አሊና ከግብፁ ሞባረክ የተለየ መላ ያስፈልገዋል ብሎ በከፍተኛ ጥንቃቄ ለህዝባዊ ለዉጥ መዘጋጀት ኢትዮጵያዊ አርቆ አስተዋይነት ነዉ። በፍርሀት እጅና እግርን አስሮ ለባርነት እጅ መስጠት ግን ከኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከሰዉ ልጆች ባህሪይ ዉጭ መሆን ነዉ። ነፃነታችንንና አገራችንን እየረገጠ ለሚገዛን ኃይል ለዚያዉም ህዝባዊ መሠረት ለሌላዉ አናሳ ኃያል አስረክበን የምንተኛዉ እያንዳንዱ መኝታ ሊቆረቁረን ይገባል። የወያኔ ዘረኞች ኢትዮጵያዊነትን ለማደብዘዝና የኢትዮጵያን ህዝብ ረግጦ ለመግዛት የ17 አመት መስዋዕትነት ከከፈሉ እኛማ እነሱ ከጫኑብን ዉርደትና ዘረኝነት ለመላቀቅ ምን የማንከፍለዉ መስዋዕትነት ሊኖር ይችላል? ነፃነት የጎደለዉና ጀግንነት ያልጎበኘዉ ህይወት በቁሙ የሞተ ህይወት ነዉ፤ ጀግና ማለት ደግሞ ፍርሀት በፍፁም የሌለበት ሰዉ ማለት አይደለም- ጀግና ማለት ከፍርሀት ባሻገር ትልቅ ነገር እንዳለ በዉል የተረዳና ፍርሀቱን ዉጦ ይህንን ትልቅ ነገር ለመጨበጥ ህይወቱን ጭምር ለመሰዋት ፍቃደኛ የሆነ ሰዉ ነዉ! ስለዚህም ነዉ ያለ መስዋዕትነት ድል የለም የሚባለዉ!
ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉን ዘረኝነት፤ፍትህ አልባነትና አይን ያወጣ ዝርፍያ ጋዜጣ ላይ አንብበን የምንረሳዉ ወይም በሬዲዮ ሰምተን ከንፈራችንን መጥጠን የምናልፈዉ ጉዳይ አይደለም። አርዶ ሊበላዉ ከሚዘጋጅ ጠላቱ ጋር ተመቻምቾ የሚኖር ለማዳ እንስሳ ብቻ ነዉ። እንስሳም ቢሆን አንዳንዴ ሲነሳበት ጠላቱን አሳድዶ ሲቦጫጭቅ በተደጋጋሚ ሰምተናል።ታዲያ የኛ ትከሻ ምን ያህል ተሸካሚ ቢሆን ነዉ እነዚህን ግዑዟ መሬት እንኳን የከዳቻቸዉን የቀን ጅቦች 20 አመት ሙሉ የተሸከምናቸዉ? እስከመቼ ነዉ ሂዱ ሲሉን ሄደን፤ ሲገፉን ተገፍተን፤ ሲረግጡን ተረግጠን አሜን ብለን የምንኖረዉ? በያንዳንዳችን ላይ መጡብን፤ በግዛት አንድነታችን ላይ መጡብን፤ በመብታችንና በነፃነታችን ላይ መጡብን- ከዚህ በላይ ምን እስኪያደርጉን ነዉ የምንጠብቀዉ? እነሱኮ ካሁን በኋላ የሚያደርጉት ምንም ነገር የለም! ካሁን በኋላ የቀረዉ ነገር እኛ ምን እናደርጋለን የሚለዉ ጥያቄ ብቻ ነዉ። ነፃነታችንን አሜሪካኖች አይሰጡንም- እንግሊዞችና ጀርመኖችም ነፃ አያወጡንም። እዉነቱን ለመናገር ተንበርክከን ስንፀልይ ብናድርም እኛ ያልታገልንለትን ነፃነት እግዚአብሔርም ቢሆን አይሰጠንም- እሱ አንዴ ሰጥቶናል። ከዛሬ በኋላ የኢትዮጵያ ነፃነት ብቸኛ ምንጭ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ አንደሆነ ሁላችንም ልንረዳ ይገባል። ስለዚህ በአንድ በኩል ልክ እንደ ግብፅ ህዝብ ክርስትናና እስልምና ሳይለያየን ወይም በዘር ሳንከፋፈል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሊቢያ ህዝብ የመሳሪያዉ ጋጋታና የቃላት ማስፈራሪያ ሳይበግረን ባጭር ግዜ ዉስጥ ዝግጅታችንን አጠናቅቀን የወያኔን ስርዐት በህዝባዊ ትግል ማስወገድና ነፃነታችንን ማስመለስ የእያንዳንዳችን ሐላፊነት ነዉ።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ትግል ነፃ ትወጣለች!