ዘረኛው መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ ከወጣን ገና 10 ወራችን ነው ስለዚህ የቱኒዚያው አይነት አብዮት በአገራችን ሊከሰት አይችልም አለ
ባለፈው ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን በወያኔ ቁጥጥር ሥር ላሉት የመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው የወያኔ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በህዝብ ምርጫ ሥልጣን ላይ ከወጣን ገና 10 ወራችን ስለሆነ ህዝቡ በአመጽ ከሥልጣን ሊያስነሳን ምንም ምክንያት የለውም ሲል የቱንዚያው አይነት ህዝባዊ አመጽ በአገራችን ሊፈንዳ እንደማይችል እርስ በርሱ በሚቃረን ቋንቋ መግለጹ ታውቆአል።
ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ ስጋት እና መረበሽ መንፈስ ውስጥ ሆኖ መግለጫውን የሰጠው መለስ ዜናዊ ምንም እንኳ ህዝባችን በምርጫ የሰጠንን የ5 አመት ኮንትራት በሰጠን በ10 ወራት ዕድሜ ውስጥ በአደባባይ ነውጥ ሊቀማን ይችላል ብለን ማሰብ ባንችልም፤ ሻቢያ ያደራጃቸውን አክራሪ ተቃዋሚዎች በማሰማራት የአደባባይ ነውጥ ማስነሳቱ እንደማይቀር ሰሞኑን “አዲስ አበባን ሌላኛው ባግዳድ አድርጋታለሁ”ብሎ እየሰጠ ካለው ዛቻ እና ድንፋታ መረዳት ይቻላል በማለት ብዙዎችን ፈገግ ያደረገ ውንጀላ አቅርቦአል። ኮለኔል ጋዳፊ በአገራቸው ውስጥ የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ “አልካይዳ ያደራጀው ነው “ በማለት የምዕራቡን ድጋፍ ለማግኘት እንደሞከሩት ሁሉ፤ ዘረኛው መለስ ዜናዊም “ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ባላንጣ ነች” እያለ ላልፉት 10 አመታት ዘመቻ የሚያካሂድባትን ኤርትራ ለመወንጀል መዳዳቱ ግለሰቡ የገባበትን ከፍተኛ የሆነ የስነልቦና መረበሽ ያመለክታል ሲሉ ቃለመጠይቁን የተከታተሉት ሰዎች ይናገራሉ።
ወያኔ ኢሃደግ በቅርቡ አድርጎት በነበረው የማስመሰል ምርጫ 99 6 % የሆነ የህዝብ ድጋፍ አግኝቻለሁ ብሎ በባዶ ሜዳ ይኩራራ የነበረው ዘረኛው መለስ እና ጄሌዎቹ፤ ላለፉት 20 አመታት በተደረገው ተመሳሳይ ምርጫ “የህዝብ ድጋፍና አመኔታ ሳይለየን ኖረናል” ይሉ በነበረው ታሪክ በማፈር የስልጣን ቆይታ ዘመናቸውን ወደ 10 ወራት ለማውረድ መገደዳቸው በሰሜን አፍሪካ ውስጥ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ በስነልቦናቸው ውስጥ ያሳደረው የመረበሽ ምልክት እንደሆነ ያለፈው ቅዳሜ ጋዜጣዊ መግለጫ ፍንትው አድርጎ አጋልጦታል ተብሎአል።
በኢሃደግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የመተካካት ፖሊሲ “ለመጪው 50 |ሃምሳ| አመታት ሥልጣን ይዘን ለመቆየት ምንም የሚያሰጋን የለም” ሲል ባዶ ጉራ በተሄደበት ይነዛ የነበረው የወያኔ ቁንጮ፤ “ህዝቡ የ5 አመት ኮንትራታችንን ከጨረስን ቦኋላ ካልተመቸነው በህገመንግስታችን መሠረት በምርጫ የሰጠንን ድምጹን በመንሳት በዚረራ ሊያባርረን ይችላል” ሲል ተደምጦአል። በምርጫ 97 ወቅት የአድስ አበባ ህዝብ ድምጹን ሙሉ በሙሉ ለቅንጅት በመስጠቱና ወያኔ በዚረራ በመሸነፉ ፤ በመለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ አጋዚ የተባለ ቅልብ ጦር ህፃንና ሽማግሌን ሳይለይ ከ200 በላይ ንፁሃን ዜጎችን በጠራራ ፀሃይ እንደጨፈጨፈ አይዘነጋም። ወያኔ በዝረራ በመሸነፉ ጥርስ የነከሰባቸው በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቃዊሚ ድርጅቶች አሁንም ቢሆን “የወቅቱን የሰሜን አፍሪካን ሁኔታ በመከተል የአደባባይ ነውጥ አያስነሱም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው”ያለው ወንጀለኛው እና ነፍሰ ገዳዩ መለስ ዜናዊ “ይህንን የሚሞክሩ ከሆነ እንደከዚህ በፊቱ እነርሱን እያሰርን መልሰን በይቅርታ መፍታቱ እንደሰለቸን ሊያውቁና ሊታቀቡ አሊያም በህይወታቸው ላይ መወሰናቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል” ሲል የዛቻ መል ዕክት አስተላልፎአል።