መለስ ዜናዊ በሙኒክ ጀርመን ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ገጠመው
እንደፈረንጆች አቆጣጠር ከፈብሪዋሪ 4 እስከ 6 በሙኒክ ከተማ በተደረገው የጸጥታ |ሴኩሪቲ| ስብሰባ ላይ ለመገኘት በጀርመን የልማት ትብብር ሚንስቴር ተጋብዞ የነበረው ዘረኛውና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በጀርመንና አካባቢው በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ እንደገጠመው የግንቦት 7 ድምጽ ተባባሪ ዘጋቢ ከሙኒክ ከተማ በላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎአል። ቁጥራቸው ወደ 3 ሺ የሚገመት ኢትዮጵያዊያን በነቂስ ወጥተው ባሰሙት የተቃውሞ ሠልፍ፤ መለስ ዜናዊ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ መለስ ዜናዊ አምባገነንና በዜጎቹ ላይ ሰቆቃ የሚፈጽም ነው፤ መለስ ዜናዊ ሌባ ነው ፤ በጋምቤላ፤ በኦጋዴን፤ በኦሮሚያና ሌሎች ቦታዎች ለፈጸመው ዘር ማጥፋት ወንጀል ለፍርድ ይቅረብ ወዘተ የሚሉ መፈክሮች ሲስተጋቡ መዋላቸው ተዘግቦአል።
የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥን ኢሳት በኢትዮጵያዊያኑ የተደረገውን ተቃውሞ በቀጥታ ከስፍራው ለኢትዮጵያዊያን አድማጮቹ ያስተላለፈ ሲሆን በየግላቸው ተቃውሞ ሰልፉን አስተባብረው የወጡ የኦጋዴን እና የኦሮሚያ ነጻነት አቀንቃኞች የኢትዮጵያዊያን ወንድሞቻቸውን ሠልፍ በመቀላቀል ጸረ መለስ ዜናዊን መፈክር በጋራ ሲያስተጋቡ እንደዋሉ በምስል የተደገፈ ዘገባ እንዳቀረበ ለማወቅ ተችሎአል።
መለስ ዘናዊ ከድህረ ምርጫ 97 ጀምሮ በየሄደበት ታላላቅ ተቃውሞዎች ሲገጥሙት እንደኖሩና በፈረንጆች አቆጣጠር ዲሰምበር 2006 ዓም በብራስል ከተማ ተዘጋጅቶ በነበረው የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ ከአዳራሹ ዘልቀው የገቡ ኢትዮጵያዊያን መለስ ዜናዊ ለንግግር መድረክ ላይ እንደወጣ የኢራቁ ሳዳም ሁሴንና መለስ ዜናዊ አንድ ናቸው ፍርድ ይገባዋል በማለት መፈክር ማስተጋባት ሲጀምሩ በድንጋጤ ብዛት ለ20 ደቂቃ የተሰጠውን ንግግር ማጠናቀቅ ተስኖት አንዳቋረጠ በመድረክ ላይ ሆኖም እጅና ከንፈሩ ሲንቀጠቀጥ እንደተስተዋለ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።
በተያያዜ ዜና በአምባገነኑና ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ግፍና በደል እናት ሃገራቸውን ለቀው በስደት ኖርዎይ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የኖርዎይ መንግስት የስደተኝነት ጥያቄአችንን በአግባቡ አላስተናገደም በሚል ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ዘጋቢያችን ከኦስሎ ኖርዎይ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ:: ሰልፈኞቹ የወያኔውን አምባገነን አገዛዝ ዘግናኝ ድርጊቶችና ጭፍጨፋዎች የሚገልጹ ፎቶግራፎችን እንዲሁም መፈክሮችንም መያዛቸውም ታውቁአል::
ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በተለይም በኦስሎ ከተማ ባካሄዱት ሰልፍ የአምባገነኑንና ዘረኛውን መለስ ዜናዊ እንዲሁም የበረከት ስም ኦን፣ አዜብ መስፍንና ሌሎችንም የአምባገነኑ ስርአት ቁኝጮዎች ፎቶግራፎቸ ኦስሎ ከሚገኘው የኖርዎይ ፓርላሜንት ጽ ቤት ፊት ለፊ በእሳት ማቃጠላቸው ታውቁአል::
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት ኢትዮጵያዊያኑ በኖርዎይ ያደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ በዋነኛነት በኦስሎ ከተማ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የኖርዎይ ከተሞችም ጭምር መሆኑን ለማወቅ ችለናል:: በኦስሎ ከተማ በተካሄደው ሰልፍ ከአምስት መቶ በላይ የሚሆኑ ሰልፈኞች የተገኙ ሲሆን ሰልፈኞቹ ከፖልኪሶች ጋርም መጋጨታቸው ታውቁአል:: ይሁን እንጂ ከፖሊስ ጋር በተደረገው ግጭት የደረሰው ጉዳት አለመኖሩን ዘጋቢያችን ጨምሮ ገልጹአል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በደረሰን ዘገባ ኢትዮጵያዊያኑ ስደተኞች በኦስሎ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ ካካሄዱ በሁአላ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ በመግባት ከቤተክርስትያኑ አንወጣም ማለታቸውንና የኖርዎይ መንግስት ተገቢዉን መልስ የማይሰጣቸው ከሆነ ጥያቄአቸውን ማቅረብ እንደሚቀጥሉ በመግለጽ የረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ዘጋቢያችን ባስተላለፈልን ሪፖርት አስታውቁአል::
ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ባለው ጥፋት ምክንያት እጂግ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለስደት እንደሚዳረጉ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ በስደተኞች ብዛት የቀዳሚነት ስፍራን እየያዘች መምጣቱአን መዘገባችን ይታወሳል::