የቱንዢያው ህዝባዊ ማእበል ተከትሎ ህውሀትና ተለጣፊዎቹ አስቸኩዋይ ስብሰባ እንዳደረጉ ታወቀ

ከቱኒዚያ በመነሳት ወደ ግብጽ ቀጥሎም ወደ የመን እንደሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ የመጣው ህዝባዊ አመጽ ዘረኛውና አምባገነኑን መለስን ዜናዊንና በዙሪያው የተኮለኮሉትን ሆድ አደሮች ከፍተኛ ውጠረት ውስጥ እንደከተታቸው የግንቦት 7 ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ከላኩት ዘገባ ለማወቅ ተችሎአል። እንደውስጥ አዋቂ ምንጮች ዘገባ በተቃውሞው የተደናገጡት የህውሃት ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት የሌሎች ተለጣፊ ድርጂቶች መሪዎችን በማካተት ውጥረቱን ለማርገብ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመምከር ባለፈው ሰኞ ጥር 23 ቀን ልዩ ሰባስበ አድርገው እንደነበር ታውቁዋል። የወያኔው አገዛዝ በሰሜን አፍሪካ እየተቀጣጠለ በመጣው ጸረ አምባገነን ሰላማዊ ተቃውሞ ከፍተኛ መደናገጥ ውስጥ የገባበት ዋናው ምክንያት በወያኔ መሪዎች አይን ለረጅም ጊዜ ያለተቀናቃኝ በሥልጣን ላይ የቆዩት የሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አምባገነኖቹ ለዘመናት ያደራጁት የደህንነትና የጸጥታ ሃይሎች የተነሳባቸውን የለውጥ ማዕበል መቋቋም ተስኖአቸው ከህዝቡ ጎን በመቆማቸው እንደሆነና ለአመታት ጠንካራ ሸሪኮቻቸው የነበሩት የምዕራብ አገራት መንግሥታት በቅጽበት ተለውጠው ለተቃውሞ ወደ ጎዳናና አደባባይ ከወጣው ህዝብ ጎን እንደሆኑ ያለምንም ማወላወል ተደጋጋሚ መግለጫ በማከታተል በማውጣታቸው ነው ተብሎአል።

አንደ መለስ ዜናዊ በጸረሽብርተኝነቱ ዘመቻ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆርጅ ቡሽ ዋና ሸሪክ የነበሩት እና በ23 አመት የሥልጣን ዘመናቸው በአገራቸው ውስጥ ልማትንና ዕድገትን አስመዝግበዋል ተብለው በምዕራቡ አለም ሲወደሱ የነበሩት የቱንዚያው መሪ ቤነ አሊ፤ ህዝባዊ አመጽ ሲነሳባቸውና የአፈና መዋቅር ሆኖ ሲያገለግላቸው የነበረው ወታደርና ፖሊሲ ፊቱን ሲያዞርባቸው በአውሮፓም ሆነ በአሜሪካ መጠጊያ እንኳን ማግኘት አለመቻላቸው ለመለስ ዜናዊና ጥቂት ግብረአበሮቹ ላይ ሊፈጥር የሚችለው ድንጋጤ መገመት ከባድ እንዳልሆነ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው።

በሰሞኑ የሰሜን አፍሪካ ሁኔታ የተደናገጡት የወያኔ ባለሥልጣኖችና የቅርብ አጋሮቻቸው በአገራችን ሊነሳ ይችላል ብለው የፈሩትን ህዝባዊ ተቃውሞ አስቀድሞ ለመምታት በህዝቡ ላይ የሥነልቦና ዘመቻ መክፈታቸውን ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ በላከው ዜና ገልጾአል። በአድስ አበባ ነዋሪ የሆኑትን እናቶች ስብስቦ ወጣት ልጆቻቸው በጸረ መንግሥት ተቃውሞ አንዳይሳተፉ ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር ከመስጠት ጀምሮ “አገር የከዱ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሃገሪቱዋ እንድትጠፋ ተንኮል እየሸረቡ ነው፣ መንግሥታችን እያከናወነ ያለውን የልማት ስራ ሊያደናቅፉ እና ህዝቡን ለ ዕልቂት እያነሳሱ ነው ፤ ኢሳት የተባለው ተለቪዝን የሚዲያ ጦሪነት ከፍቶብናልና ሰለባ እንዳትሆኑ ወዘተ ” የሚል ፕሮፓጋንዳ በህዝቡ ውስጥ እንዲነገር ትእዛዝ ማስተላለፋቸውን ለማወቅ ተችሎአል። ከዚህም በተጨማሪ የወያኔው አገዛዝ ወታደሮችና ፖሊሶች በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ፣ አድማ በታኝ ፖሊሶች ተጨማሪ ስልጠና እንዲወስዱና የአድማ መበተኛ ተሽከርካሪዎች ውሃ እየሞሉ በተጠንቀቅ ሆነው ት ዕዛዝ እንዲጠባበቁ መመሪያ መተላለፉ ታውቆአል ። በተያያዜ ዜና በዘረኛ የወያኔ መዋቅር ተጠቃሚ ከሆኑት የትግራይ ተወላጆች አንዷ የሆነቺው የቀድሞው የቪ ኦ ኤ ጋዘጠኛ ሚሚ ስብሃት የተባለች ሴት ንብረት የሆነው ዛኑ በመባል የሚታወቀው ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያ “የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት እንዲከሰትና በሃገሪቱም አለመረጋጋት እንዲፈጠር እየሰሩ ናቸውና ተጠንቀቁ” የሚል መለክት በየቀኑ እያስተላለፈ መሆኑ ታውቁአል። ላለፉት 20 አመታት ማን ምን እንደሆነና ለምን ወያኔ ዕድሜ ለማራዘም እንደሚተጋ የተረዳው የኢትዮጵያ ህዝብ ለወያኔ ማስጠንቀቂያና ማስፈራሪያ ቁብ ሳይሰጥ ሁነታውን በቅርበት እየተከታተለ እንደሆነ ከህዝብ የተገኘው አስተያየት ያመለክታል። በተለይ ወጣቱ ትውልድ “እን ነሳ” የሚል የስልክ መል ዕክት ኤ ስ ኤም ኤስ እየተለዋወጠ እንደሆነ ሪፖርተራችን አክሎ ገልጾአል።

ይህ በዚህ እንዳለ በቱኒዚያ ህዝባዊ አመጽ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በሰሜን አፍሪቃ በርካታ ሃገራት ተመሳሳይ ንቅናቄዎች እየተደረጉ ከመሆኑ አልፎ የመንግሥት ለውጥ ጥያቄው ወደ መካከለኛውና ምስራቅ አፍሪቃም በፍጥነት በመገስገስ ላይ መሆኑን ሮይተርስ የዜና ወኪልን ጨምሮ በርካታ የዜና አውታሮች በመዘገብ ላይ ናቸው። ይህ የተቀጣጠለ የህዝብ አመጽ ባለፈው ማክሰኞ በሱዳንም በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካኝነት የተጀመረ መሆኑ የታወቀ ሲሆን በሰልፉ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሳተፋቸውም ታውቁአል:: በሱዳን የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ለመበተን እጂግ በርካታ ፖሊሶች የተሰማሩ ሲሆን ፖሊሶቹ ከሰልፈኞች ጋር መጋጨታቸውንና በርካታ ተማሪዎችን መታሰራቸው ታውቁአል፡፡ ሮይተርስም ባወጣው ዜናው በፖሊሶች የተደበደበ አንድ ሱዳናዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ህይወቱ ማለፉ ታውቁአል::

ከዚሁ የምስራቅ አፍሪቃ ክልል ሳንወጣ የዩጋንዳ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችም የሃገሪቱ መንግስት የቀረቡለትን ህዝባዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ርምጃ የማይወስድ ከሆኑ በቱኒዚያና በግብጽ የታየው አይነት ህዝባዊ ተቃውሞ እንደሚገጥመው ከወዲሁ እየገለጹ ነው:: እንደ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገባ ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ሙሶቬኒ የህዝብ ጥያቄን መመለስ ከተሳናቸው የሚጠብቃቸው ተቃውሞ ቀላል እንደማይሆነ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቹ አስጠንቅቀዋል::

እንደ ሌሎች የሰሜን አፍሪቃ ሃገራት ሁሉ በመካከለኛው እንዲሁም በምስራቅ የአፍሪቃ ሃገራት ለህዝብ አመጽ መንሴ እነደሆኑ እየተገለጹ ያሉት በየአገሮቹ እየናረ የመጣው የምግብ ዋጋና የባለሥልጣናቱ በሙስና መዘፈቅ መሆኑ ታውቁአል።

በሌላም በኩል ተመሳሳይ የሆነ የህዝብ አመጽ በጋቦን መከሰቱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቡአል:: በጋቦን በተቀሰቅሰ ህዝባዊ አመጽ ሰልፈኞች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው ታውቁአል :: የመንግስት ተቃዋሚ በሆኑ ከአምስት ሺህ በላይ የሆኑ ተቃዋሚዎች በተሳተፉበት ህዝባዊ አመጽ በተነሳው ግጭት ከሃያ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ላይ ጉዳት መድረሱን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቡአል::

ይህ በሰሜን አፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ እንደ ሰደድ እሳት እየተያያዘ ያለው ሕዝባዊ አመፅ ቀጥሎ ወዴት ያመራል የሚለው ጥያቄ በስፋት እየተነሳ ሲሆን በተለይም ኢትዮጵያዊያን በሃገሪቱ እየታየ ካለው እጂግ የከፋና ውስብስብ ችግር አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ህዝባዊ አመጽ ሊነሳ እንደሚችል ምንም ጥርጣሬ እንደሌላቸው እየገለጹ ነው::

የአፍሪካ ህብረትን በንግግር የከፈቱት የፈረንሳዩ ሜሪ ሳርኮዚ አምባገነን የአፍርካ መሪዎች በየአገሮቻቸው ዲሞክራሲያዊ የመንግሥት ለውጥ ካላካሄዱ በቱኒዚያ የተነሳው ህዝባዊ አመጽ በየአገሮቻቸው እንደሚፈነዳና እንደሚበላቸው በግልጽ ተናግረዋል።