የአፍሪካ ህብረት ያደረገው የመሪዎች ስብሰባ ጉልህ እርምጃ ሳይወስድ ተጠናቀቀ

ሃሙስ የካቲት 30 ቀን በአዲስ አበባ በተደረገው 265ኛ የአፍሪካ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የተሳተፉት የአፍሪካ መሪዎች በሰሜን አፍሪካይቱ አገር በሊቢያ እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ በጠነከረ ቋንቋ ለማውገዝና ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ለመጠየቅ የሚያስችል ወሳኔ ሳያስተላልፍ መጠናቀቁን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ከላከልን ዜና ለማወቅ ተችሎአል።

ዲሞክራት ነን እያሉ በአያለ የአፍሪካ ቢጤዎቻቸው  ሲሞካሹ የነበሩት የቱንዚያው ቤን አሊንና የግብጹ ሙባረክ በህዝባዊ ተቃውሞ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ከመገደዳቸው በፊት የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቀልበስ ይቆጣጠሩት በነበረው የጸጥታ ሰራተኞች በዜጎቻቸው ህይወት ላይ የመግደል ወንጀል ሲፈጽሙ ምንም አይነት ተቃውሞ ያላሰማው የአፍሪካ ህብረት፤ በሁለቱ አገሮች ውስጥ የተደረገው ለውጥ ወደሌሎች አገሮች እንዳይዛመት ከመስጋት ይመስላል እስከዛሬ ድጋፍም ሆነ የተቃውሞ ድምጽ ሳያሰማ ቆይቶአል። በቅርቡ የአህጉር ድርጅቱ ሊቀመንበር የነበሩት ሞአመድ ጋዳፊ የ42 አመት የአገዛዝ ዘመናቸው እንዲያበቃና በአገራቸው የመንግሥት ለውጥ እንዲኖር የሚጠይቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመደፍጠጥ ከፍተኛ የሆነ የታጠቀ ሃይል በምድርና በሰማይ ያሰማሩ ቢሆንም ይህንን እርምጃ በግልጽ ለማውገዝና እንዲቆም ለማድረግ ምንም አይነት የጸና አቋም አለመውሰዱ የምዕራባዊያን መገናኛ ብዙሃን መዘባበቻ አድርጎታል። በመሪዎቹ ስብሰባ ላይ የጋዳፊን እድሜ ለማራዘም ከፍተኛ ገንዘብ በመቀበል ነፍሰ ገዳይ ወታደሮችን ወደ ሊቢያ የላኩ አገር መሪዎች ጭምር የተገኙ ሲሆን ለሥልጣን ሲሉ የበርካታ ንጹሃን ህይወት በመቅጠፍ የሚታወቁ  እንደ መለስ ዜናዊ አይነቶቹ በዚያ የአህጉር ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ መገኘት የተለሳለሰ አቋም እንዲያዝ ዋና ምክንያት ይሆናል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች አሉ።

ያለ ህዝባቸው ፈቃድና ውሳኔ ለረጅም ጊዜ ስልጣን ማማ ላይ ተቆናጠው የአገራቸውን እና የህዝባቸውን ሃብት በመበዝበር የሚታወቁ ፤ በሙስና የተጨማለቁና የዜጎቻቸውን መብት በመርገጥ የሚታወቁ በርካታ መሪዎችን የተሸከመቺው አህጉራችን አፍሪካ ከ1955 ጀምሮ አንድ የጋራ የሆነ አህጉራዊ ድርጅት ይኑራት እንጂ በዚህ አህጉራዊ ተቋማ አማካይነት እስከ ዛሬ ያስመዘገበቺው እድገት ወይም በአህጉሪቱ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የተወሰደ ተጨባጭ እርምጃ የለም።  ቀደም ሲል የአፍሪካ አንድነት ቆየት ብሎ ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የተባለው ይህ ተቋም በማ ዕቀፉ ውስጥ ያሉ አገሮች መሪዎች የዜጎቻቸውን መብት ሲረግጡ፤ ዜጎቻቸውን ሲገድል፤ ሲያስሩና የተለያየ ዘግናኝ ሰቆቃዎች ሲፈጸሙ  ምንም አይነት ተቃውሞ በማሰማት የማይታወቅ ከመሆኑም በላይ በምርጫ ሽፋን የአገዝዝ ዘመናቸውን ለማራዘም የምርጫ ድራማ የሚያዘጋጁ አገሮችን ላይ በምርጫ ታዛቢነት ሥም እየዞረ የተጭበረበረውና የተዘረፈው  የመራጭ ድምጽ እንዳይታወቅ ከገዥው ወገን ጋር በመወገን ምስክርነት በመስጠት እና ሥልጣን ላይ ያሉት ደግመው ደጋግመው እንዲገዙ ረጅም ዕድሜ በማሰጠት ይታወቃል። በምርጫ 97 በአገራችን ተደርጎ የነበረውን ምርጫ የአውሮጳ ህብረትና የካርተር ማዕከል ከፍተኛ ማጭበርበር የተፈጸመበት መሆኑን ሲያጋልጡ የዚህ ተቋም ታዛቢዎች ግን ለአፍሪካ አረአያነት ያለው ምርጫ ተካሁዶአል በማለት እንዳወደሱት ይታወሳል።