የትግራዩ ገዢ ጉጂሌ የሚያካሂደው ዘረኝነት በትምህርት መስክም ተጠናክሮ መቀጠሉ ታወቀ

ወያኔ ለድል አብቅቶኛል ብሎ የሚመጻደቅበትን የትግራይ ብሄረሰብ ዋና የድጋፍ መሠረቱ አድርጎ ለመቀጠል ባለው ስትራቴጂ ላለፉት 20 አመታት ክልሉን ኢሚዛናዊ የሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪ በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የሚሰጡትን የትምህርት ዕድሎች ላይ በአመዛኙ የትግራይ ተወላጆች ከፍተኛውን የተጠቃሚነት ድርሻ አንዲይዙ እያደረገ መሆኑን ሰሞኑን ከትምህርት ሚንስተር አካባቢ የደረሱን መረጃዎች አጋልጠዋል።

እንደ መረጃ ምንጮቻችን ዘገባ ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ተብሎ በተለያዩ ክልሎች ከተከፈቱት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በውስጣዊ ድርጅታቸውና በሚሰጡት የትምህረት አይነትና ጥራት በእጂጉ እንደሚበልጡ ከሚነገርላቸው በትግራይ ውስጥ እንደ አሸን ከፈሉት የተለያዩ ኮሌጆች በተጨማሪ በአንጋፋነቱና ባሉት የመምህራን ደረጃ ከበረታ አለው በሚባለው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲት የተለያዩ ዲፓርተመንቶች ውስጥ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉት የትግራይ ተማሪዎች ኮታ በማንኛውም የአገሪቱ ክልሎች ከሚኖሩት ብሄረሰቦች ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ አንዳለው ለማወቅ ተችሎአል። በዚህም የተነሳ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴኪኒኦሎጂ ፋካሊት ውስጥ በዘንድሮው የትምህርት አመት ተመዝግበው ከሚገኙት ተማሪዎች ውስጥ 70 ከመቶ ፤ በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በምህንድስና (ኢን ጂነሪንግ) ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙት ተማሪዎች ደግሞ 90 በመቶ የሆኑት ተማሪዎች ትግሪኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች እንደሆኑ ሲታወቅ ይህ ብዛት በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን ሆን ተብሎ በተደራጀና በተቀናበረ የዘረኝነት ፖሊሲ እየተመራ የተደረሰበት የመጠቃቀም ዘመቻው አካል ነው ተብሎአል።

በትምህርቱ ዘርፍ የወያኔው አገዛዝ እየፈጸመ ያለውን ግፍ አስመልክቶ ዘጋቢያችን ያናገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ እንዲህ አይነት አሠራር የወያኔ አገዛዝ የአገሪቱን የሥልጣን ማ ዕከል ከተቆጣጠረ ማግሥት ጀምሮ እየተገበረ ያለ እንደሆነና ተማሪዎቹን ብቻ ሳይሆን ቢሳካላቸውና የተማረ የሰው ሃይል ቢኖራቸው ኖር ትግሪኛ የማንናገረውን የግቢውን ሠራተኛ በሙሉ ጠራርገው በማባረር በራሳቸው ሰዎች ከመተካት የማይመለሱ ነበሩ ብለዋል።

አያይዘውም በትምህርቱ መስክ እየተወሰደ ያለው እንዲህ አይነት በፍጹም ዘረኝነት ላይ የተመሠረተ አሠራር የነገው አገር ተረካቢ የሆነውን ወጣት ትውልድ እድል ከማጨለም አልፎ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚሞከረውንም ቡድን ጥቅም አያስከብርም በማለት በሩዋንዳ በሁቱና ቱቲሲ መካከል የተፈጸመውን ዘግናኝ የብቀላ ጦርነት አስታውሰዋል። ላለፉት በርካታ አመታት ወደ ውጪ አገር ለከፍተኛ ትምህርት እየተላኩ ያሉ ወጣቶች ሆን ተብሎ በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሆነ፤ በአገር ቤት ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች ውስጥ የትግራይ ተወላጆች የዝሆን ድርሻ አንዲኖራቸው እየተመቻቸ መሆኑን፤ ትምህርታቸውንም ሲጨርሱ ሌሎችን በመግፋት በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች ላይ እንዲሰማሩ እየተደረገ እንደሆነ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲገለጽ መቆየቱ አይዘነጋም

በተያያዜ ዜና ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የሁለት አሃዝ እድገት አስመዘገቤያለሁ ፣ የተለያዩ የግምባታ ስራዎችን ከመቼውም ጊዜ በላይ አከናወኛለሁ እያለ ለመኩራራት ቢጥርም እውነታው ግን ዘረኝነትን ማ ዕከል ባደረገ የራሱን ብሄረሰብ የአገሪቱን ከፍተኛ የፖለቲካ ሥልጣንና ሃብት እስከወዲያኛው ለመቆጣጠር እንዲችል የማደረግ ዘመቻ አካል መሆኑን ከተለያዩ ምንጮች እየደረሱን ያሉት ማስረጃዎች ያሳያሉ፣ ፣

የግንቦት ሰባት ዘጋቢ ሰሞኑን በላከልን ዘገባ እንደገለጸው በሃገሪቱ ዋና ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉት ምርጥ ህንጻዎች በአገዛዙ ባለስልጣናትና ከአገዛዙ ጋር ቁርኝት ባላቸው የአገዛዙ ደጋፊዎች ባለቤትነት ይዞታ ሥር የሚገኙ መሆኑን የከተማውን አስተዳደር ምንጮች ዋቢ በማድረግ ገልጾአል፣ ፣ በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ባለፉት 10 አመታት የተገነቡትና በመገንባት ላይ ካሉ ዘመናዊ ህንጻዎች ከ90 በመቶው በላይ ከህወሃት ጋር ቅርበት ያላቸው ትግሪኛ ተናጋሪዎች ሃብት መሆኑን ለዚሁም መረጃ ከአዲስ አበባ ኡራኤል በቴክርስቲያን ጀምሮ አስከ መገናኛ ባለው አንድ መስመር ብቻ ከተገነቡትና በመገንባት ላይ ካሉት 68 ዘመናዊ ህንጻዎች 63ቱ የትግራይ ተወላጆች ንብረት መሆናቸው ታውቋል።

ዘረኛው አገዛዝ በተለይ ከግንባታ ጋር በተያያዘ የህዝብን ንብረት እየዘረፈ ወደ ጥቂቶች እጅ ሲያስተላልፍ እንደቆየ፣ በርካቶች ከአገዛዙ ባለስልጣናት ጋር ያላቸውን ቅርበት ወይም የዘር ትስስራቸውን በመጠቀም ህንጻዎችን በመገንባት ስም፣ የዋጋ ግሽበትን ከግምት ባላስገባ ወለድ ከመንግስት ባንኮች ከሚፈልጉት ገንዘብ በላይ ሲሰጣቸውና ብዙዎቹም ለህንጻው ግንባታ ከሚፈልጉት መጠን የተረፈውን ገንዘብ ወደ ውጭ ሃገራት ሲያሸሹ እንደቆዩ በስፋት ተዘግቡአል።