ለነፃ ሚዲያ መኖር የምናደርገው ትግል የነፃነት ትግሉ አካል ነው!!!
አምባገነኖች የሚገዙትን ህዝብ ለመቆጣጠር ከሚወስዷቸው እርምጃዎች ቀዳሚው የመረጃ ፍሰትን መቆጣጠር ነው። እነሱ ከሚሉት ውጭ እንዳይሰማ ለማድረግ ወደ ህዝብ ጆሮ የሚደርሱትን ነገሮች ሁሉ የመቆጣጠር ተግባር ይፈጽማሉ። ከዚህም በተጨማሪ ውሸትን ደጋግሞ በማውራት እውነት ለማስመሰል ይተጋሉ። ይህ የአምባገነን ሥርዓቶች ሁሉ የጋራ ባህርይ ነው።
የትግራዩ ገዥ ጉጅሌ በጉልበት ሚኒሊክ ቤተመንግሥት ከገባበት እለት ጀምሮ እያደረገ ያለው ይህንኑ ነው። ጉጅሌው የመረጃ አውታሮችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ ቀንና ሌሊት ውሸቶችን እውነት ለማስመሰል ይጥራል። ኢትዮጵያ ውስጥ አማራጭ የመረጃ ምንጭ ስለሌለ አንዳንድ ወገኖቻችን ጉጅሌዉ ደጋግሞ የሚናገረዉ ዉሸት እዉነት ቢመስላቸዉ ልንፈርድባቸዉ አይገባም።
“የኢትዮጵያ” የሚል ስም ይዘው ኢትዮጵያን እየገደሉ ያሉ የሬድዮና የቴሌቪዥን ተቋማት እያደረጉት ያለው ምንድነው?
- ኢትዮጵያዊያን በዘረኝነት እጅግ በተማረሩበት፤ አገሪቷ በአገር ውስጥ ቅኝ አገዛዝ ሥር ወድቃለች በሚባልበት በአሁኑ ወቅት ከላይ የተጠቀሱት ሚዲያዎች የሚያወሩት በወሬ ብቻ ስለፈጠሯት በአካል ግን ስለሌለችው ኢትዮጵያ ነው።
- አጠገባቸው ሰቆቃ ሲፈፀም፤ ህፃናት ሲገደሉ፤ እናቶች ሲደፈሩ፤ ተማሪዎች ሲደበደቡ እያዩ “የኢትዮጵያ” ቴሌቪዥንና ራድዮ የሚያወሩት በወያኔ አገዛዝ ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩ ስለመሆናቸው ነው።
- ከአንድ ጎጥ የወጡ ሰዎች ቁልፍ ቦታዎችን ይዘው ሃገሪቷን እየቦጠቦጧት ባሉበት ባሁኑ ወቅት፤ በዘራቸው ከጎጡ አባላት ውጭ የሆኑት አጃቢዎች የምስለኔን ያክል እንኳን ሥልጣን የሌላቸዉ መሆኑ እየታወቀ፤ ዘርና ሃይማኖት መሠረት ያደረጉ ግጭቶች አገሪቷን እያመሷት እና እነዚህን ሁሉ በገዛ ዓይኖቻቸው እያዩ “የኢትዮጵያ” ቴሌቪዥንና ራድዮ የሚያወሩት ፍቅር ሞልቶ ስለመትረፉ እና የብሄር ብሄረሰቦች መብት ስለመከበሩ ነው።
- እነዚህ ሚዲያዎች ወታደሩ፣ ፓሊሱ፣ ደህንነቱ እና ራሳቸው የሚዲያ ተቋማቱ ሁሉም በዘረኝነት የተተበተቡ፤ ከሙያዊ ኃላፊነት ይልቅ ለጆሮ ጠቢነት ይበልጥ ትኩረት የሚሰጡ መሆናቸው እየታወቀ ስለዚህ ጉዳይ ትንፍሽ የማይሉ፤ በግልባጩ “ውጤት-ተኮር”፣ ቢ.ፒ.አር. እያሉ የሚያደናግሩ አደንቋሪዎች ናቸው።
- ፍርድ ቤቶች በፍትህ እያላገጡ ዋሾ ሚዲያዎች ትዕዛዝ የተሰጠባቸውን ዶሴዎች እየቆጠሩ ስለፍርድ ቤቶች “ምርታማነት” መጨመር ያወራሉ።
- የገበሬው ማሳ ተቀምቶ ለባዕዳን በመሰጠቱ ምክንያት የበርካታ ቤተሰቦች ለቅሶ ሰሚ ባጣበት ወቅት እነኚህ የክህደት ሚዲያዎች ሚሊኒየነር ስለሆኑ ገበሬዎች ድራማ ሰርተው ያሳያሉ።
- አገዛዙ ብር እያተመ፤ ድንገተኛ የውጭ ምንዛሪ ምጣኔ ለውጥ እያደረገ አውቆ የፈጠረውን የኑሮ ውድነት በችርቻሮ ነጋዴዎች ላይ እያሳበበ “ስግብግብ ነጋዴዎች” ያመጡት ውድነት ነው እያለ ህዝብን እርስ በርሱ ማባላት ሙያው አድርጎታል።
- “ልማታዊ ጋዜጠኛ” እየተባለ የሚሸነገለው አድርባይ ጋዜጠኛ የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻቸውን በፈረቃ የሚመግቡበት ዘመን መሆኑን እያወቀ፤ ምናልባት በገዛ ራሱ ኑሮም ጭምር ተጨባጭ እውነታውን እያየው መዋሸት ስላለበት ይዋሻል። ጥቂት ዘረኛ የገዢው ጉጅሌ አባላትና ምስለኔዎቻቸው ህይወት የምድር ላይ ገነት መምሰሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ መሻሻል ምልክት ነው እያለ ዓይኑን በጨው አጥቦ ይነግረናል።
- የመለስ ዜናዊ ተንኮለኛ “ብልጣ ብልጥነት” የአመራር ብቃት መመዘኛ አለመሆኑ መላው ዓለም እየተረዳ ባለበት፤ በአፍሪካ የመሪዎች የብቃት ምዘና መለስ 32 ከመቶ አምጥቶ መውደቁን ይፋ በሆነበት በአሁኑ ወቅት “ልማታዊው” ዋሾ ጋዜጠኛና ሚዲያው ስለመለስ የአፍሪካ ግንባር ቀደም መሪነት ይደሰኩራል።
ይህ ዓይነቱ ሚዲያ ነው አሁን የኢትዮጵያን አየር ያጣበበው።
ሰሞኑን ደግሞ በነፃ ሚዲያ ስም ስምንት የውሸት ማሰራጫዎች እንደሚከፈቱ ተነግሯል። የአንደኛው ባለቤት በእርግጠኝነት ይታወቃል የወያኔው ፋና ነው። ፋና ወያኔ ከበረሃ ጀምሮ ይዞት የመጣው ሬድዮ ነው። እስከዛሬ ፋና ሬድዮ በነፃ ሬድዮነት ስም “ከኢትዮጵያ” ሬድዮ በላይ ሲዋሽ ኖሯል። አሁን ደግሞ ፋና ቲቪ ከኢቲቪ በላይ ለመዋሸት አኮብኩቧል። ለጊዜው ስማቸውን ባናነሳም የቀሩት ሰባቱም መሠረታቸው አንድ እንደሆነ እናውቃለን።
ይህ ሁሉ በአንድነት ሲስተዋል የነፃ ሚዲያ አስፈላጊነትን እጅግ አንገብጋቢ ያደርገዋል። ለመሆኑ
- ዘወትር ስለፈጣን ግስጋሴ ቢነገረውም የሚበላውን ያጣውን የኢትዮጵያ ህዝብ፣ የትግራይ ገዢ ጉጅሌ አባላትና ምስለኔዎቻቸው ስለሚያጋብሱት ገንዘብ ማን ሹክ ይለዋል?
- በጋምቤላ ገበሬ ላይ የደረሰው በደል በከፋም፣ በአሶሳም፣ በሲዳማም እየደረሰ መሆኑን እና በደሉ መላው አገሪቷን ያጠቃለለ መሆኑን ለህዝባችን ማን ይነግረዋል?
- በኢኮኖሚ ለማደግ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መጠመቅ የማያስፈልግ መሆኑን የሌሎች አፍሪቃ አገሮች ልምድ እያጣቀሰ ማን መረጃ ይሰጠዋል?
- በአገራችን ያለው ዘረኝነት በቶሎ ካልተገታ ወደ አስከፊ አዘቅት የሚወስደን መሆኑ ከዚሁ መንገድ ተጉዘው መራር ጽዋ ከተጎነጩ አገሮች ልምድ ጋር አስታኮ ማን ይነግረዋል?
- የኢትዮጵያ ህዝብ እውነት መች እና በምን ይሰማል?
እነዚህ ነገሮች ሁላችንንም ሊያስጨንቁን የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው። ስለሆነም ለእውነት የቆመ ነፃ ሚዲያ መወለድና ማበብ መታገል የትግላችን አንዱ አካል ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።
ግንቦት 7 የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የነፃ ሚዲያ ጥቅምን ጠንቅቆ ይገነዘባል። ለእውነት የቆሙ ነፃ ሚዲያዎች መኖር ፍትህ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የምናደርገውን ትግል ያግዛሉ። ራሷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ያለ ነፃ ሚዲያ ማሰብ አይቻልም:: የንቅናቄዓችን አባላትና ደጋፊዎችም ለነፃ ሚዲያ መፈጠርና ማበብ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ለነፃነታችን የምናደርገው ትግል አካል መሆኑን ይገነዘባሉ። መረጃ የተጠማው የኢትዮጵያ ህዝብም ነፃ የሚዲያ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲጠናከሩ የሚደረገውን ትግል እንዲደግፍ ጥሪ እናደርጋለን።