የአራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተቃውሞን ተከትሎ የታሰሩ ተማሪዎች መድረሻቸው አልታወቀም

የአዲስ አበባው አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዚህ ሳምንት ተቃውሞ ማሰማታቸውን እና የዘረኛው አገዛዝ ፌዴራል ፖሊስ ወደ ግቢው መግባቱን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ድርጅት – ኢሳት – ዘግቦ ነበር።

ተቃውሞው የተነሳው የዩኒቨርሲቲው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ተማሪዎች የገናን በዓል በዩኒቨርሲቲው ግቢ ለማክበር ጠይቀው ከተከለከሉ በኋላ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የተማሪዎቹን ተቃውሞ ተከትሎም ባልታወቀ ምክንያት በተለያዩ ብሄር አባላት መካከል ግጭት ተነስቷል። የዩኒቨርሲቲው የሳይንስ ላይብረሪ መስኮቶች፣ እንዲሁም በግቢው ውስጥ ቆመው የነበሩ መኪኖች መሰባበራቸውን ኢሳት ዘግቧል።

ተቃውሞውን ለማስቆም ወደ ግቢው የገቡት የዘረኛው አገዛዝ ፌዴራል ፖሊስ እና የደህንነት ሰዎች አንዳንድ ተማሪዎችን እንዳሰሩ እና የእስረኞቹ እጣ ፈንታም እስካሁን እንደማይታወቅ ምንጮች ገልጸዋል። ፖሊስ በፈጸመው ድብደባ የተጎዱ ተማሪዎች እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።

ተማሪዎቹ በጸጥታ ሃይሎች የተወሰዱ ጓደኞቻቸው እንዲፈቱ ለመጠየቅ የረሃብ አድማ አድርገዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም አራት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ እና አካባቢው ሲቪል እና ዩኒፎርም በለበሱ የዘረኛው አገዛዝ ቅጥረኞች ጥበቃ ስር እንደሚገኙ ምንጮቻችን ገልጸዋል።

ጉዳዩን በሚመለከት ለዝግጅፍ ክፍልችን አስተያየት የሰጡ የፖለቲካ ተንታኝ ተቃውሞው እንደተባለው እውነት ከገና በአል ጋር የተያያዘ ነው ብለው አያምኑም። የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ተስፋ ከምንም ጊዜ በላይ የጨለመበት ጊዜ ላይ ነን ያሉን ግለሰብ፣ ተማሪዎቹ ቤተሰቦቻቸውን የተጋፈጠውን የኑሮ ውድነት እና ረሃብ፤ እንዲሁም እነሱን የሚጠብቃቸውን ስራ አጥነት እያሰቡ ቅሬታቸው እንደተካበ ገልጸዋል። እንደተቀረው ዜጋ ሁሉ የፖለቲካ ተቃውሟቸውን በግልጽ እንዳይገልጹ የታፈኑት ተማሪዎችም፣ የተለያዩ ሰበቦችን በማስታከክ ቅሬታቸውን እንደሚገልጹ አስረድተዋል። ወደፊትም ተመሳሳይ ተቃውሞዎች እንደሚከሰቱ ተንብየዋል